ትምህርት ላይ የሚፈጸመው ጂኖሳይድ!

Date:

ትምህርት በሀገራችን ሕዝብ ዘንድ ልክ እንደሌላው ዓለም ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የሀብቶች ሁሉ ቁንጮው ሀብት ነው፡፡ በተለይም ቀደም ባለው ጊዜ አውሮፓውያንና ምዕራባውያን በጭለማው ዘመን ሲዋኙ ኢትዮጵያውያን ብራና ፍቀው ቀለም በጥብጠው ልጆቻቸውን ያስተምሩ ነበር፡፡ ድርሳናትን ጽፈው ለትውልድ ከትበው ያስቀሩ ነበር፡፡ የጊዜ ቀመርን ሰፍተውና ለክተው ለትውልዱ ሥነ ከዋክብትና ፍልስፍና ያስተምሩ ነበር፡፡ ቀመራት ቀምረው መድሐኒት ቀምመው ከበሽታና ሕመማቸው ይፈወሱ ነበር፡፡ ይህ የኢትዮጵያ እውነታ ለዛሬዎቹ ጥቂት ዘረኛና ጎጠኛ ትውልዶች አይዋጥላቸው ይኾናል፣ ሀቁን ግን አይቀይረውም፡፡

የኾኖ ኾኖ ለወትሮው የትምህርት ጥራት ይጎለዋል እየተባለ ሲተች የነበረው የትምህርት ፖሊሲና ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ ደግሞ በርካታ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን መጣሉን ተከትሎ በዘውገኝነት ተከሷል፡፡ የቀረበበት ክስ ባለመንታ ሀሳብ ነው፡፡ የመጀመሪያው ፈተናው “ለጥቂቶች ተከፍቶ ለኩረጃ ተጋልጣል” የሚል ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ “ኾን ተብሎ የውጤት ቅነሳ ተደርጎብናል፤ ከዚያም ባለፈ በጦርነት ውስጥ የከረምን በመኾናችን ልዩ ድጋፍ ያስፈልገናል” የሚል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ትምህርት ሚኒስቴር ለቀረበበት ክስ እርስ በእርሱ የሚጋጭና ከአንድ ተቋም የወጡ የማይመስሉ ከሦስት የላቁ ምላሾችን የክሱ ማብረጃ ለማድረግ ሞክሯል፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር በእነዚህ መግለጫዎቹም ከዚህ ቀደም በነበረ ታሪኩ በዚህ ልክ ወርዶና የተቋምነት ሚናውን ዘንግቶ አያውቅም የሚሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ አሁን ላይ ግን በርካታ ተማሪዎች በማንነታቸው ተለይቶ በዚህ ልክ  በገፍ ለመጣል የቆረጠበትን ወኔ ከየት ሊያመጣው እንደቻለ ግራ አጋቢ ይመስላል፡፡ ምክንያቱም እሮሮውም ይሁን የወዳቂው ተማሪ ብዛት ጎልቶ የወጣው ከአንድ ክልል ብቻ በመኾኑ ነው፡፡

አሁን ላይ ተማሪን በማንነቱ ለይቶ በዚህ ልክ እንዲወድቅ ማድረግ በዓለማችን በዘር ማጥፋት ወንጀል ጭምር ሊያስከስስ የሚችል ነው፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን በሰይፍ እና በስለት ከሚጠፋው ትውልድ በላይ በትምህርት ጄኖሳይድ እየተፈጸመበት ያለው ትውልድ ይበልጣል። በትምህርት ላይ የሚፈጸም ጄኖሳይድ ወዲያው አላባው አይታይም፡፡ ቆይቶ ግን ልክ እንደአሁኑ ትውልድ ከሃያ እና ከሠላሳ ዓመታት በኋላ በትውልዱ ድርጊት ይገለጻል፡፡ ትምህትር ሚኒስቴር ያለአግባብ የጣላቸውን ተማሪዎች አስመልክቶ ማብራሪያ ሲጠየቅ ሁለት የተለያዩ ምላሾችን ሰጥቷል፡፡ በመጀመሪያ መግለጫው የፈተናዎች ኤጀንሲ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ም/ዋ/ዳይሬክተር የፈተናው እርማት ከሰው ንክኪ ነፃ ኾኖ የተከናወነ ቢኾንም በሁለተኛው ዙር ፈተና እርማት ላይ የቴክኒክ ችግር ማጋጠሙን እና እርማት መደረጉን ገልፀዋል፡፡

የእርማት ችግሩ የተፈጠረው በ559 ባልበለጡ ተማሪዎች ላይ እንደኾነ እና ዳግም ምልከታ ተደርጎ ማስተካከያ እንደተደረገ በመጠቆም የፈተና እርማት ችግር ማጋጠሙ የተገኘውም የፈተናዎች አገልግሎት ባደረገው ምርመራ እንደኾነም ተናግረዋል፡፡ ቅሬታዎችን በተመለከተም ተማሪዎች ሳይጉላሉ ባሉበት ቦታ ኾነው ቅሬታቸውን ለመፍታት የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቶ መሠራቱን ገልፀዋል፡፡ በሥርዓቱ መሠረትም ከ20ሺህ በላይ ተማሪዎች ቅሬታቸውን አቅርበው ምላሽ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ በዘንድሮው ዓመት የተፈታኝ ተማሪዎች መብዛት እና በአገራችን ውስጥ ካሉት 47 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ አሁን 43ቱ  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ብቻ የሚቀበሉ ስለኾነ ይህም የዩኒቨርስቲ ቅበላ አቅም አነስተኛ እንዲኾን በማድረጉ መግቢያ ነጥቡን ከፍ እንዳደረገውም ጠቁመዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በዘንድሮው ዓመት ፈተናውን ከወሰዱት ውስጥ 25 ፐርሰንት ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርስቲ እንደሚገቡ ተነግሯል፡፡ ተቋሙ በዚህ መግለጫው ከተማሪዎች ቅሬታ ጋር የተጣጣመ መልስ ሰጥተዋል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱ በርካታ ተማሪዎች ወድቀው ባሉበት ሁኔታ በተቋሙ ዘንድ እውቅና ያገኙት 559 ተማሪዎች ብቻ ናቸው፡፡ ያም ኾኖ ዳሬክተሩ ችግሩ የተፈጠረው 559 ተማሪዎች ላይ ነው ቢሉም ከ20ሺ በላይ ተማሪዎች ቅሬታ አስገብተው መስተናገዳቸውን ተናግረዋል፡፡  

ሁለተኛው የተቋሙ መግለጫ የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍል (ዶ/ር) የ12ኛ ክፍል ፈተና በሁለት ዙር እንዲሰጥ መደረጉንና በመጀመሪያው ዙር የሥነ-ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ከፈተናው ቀን ቀድሞ በመውጣቱና የውጤት ግሽበት በመምጣቱ እንዲሰረዝ መደረጉን ተናግረዋል። በመጀመሪያ ዙር ፈተና ከወሰዱት ተማሪዎች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚኾኑት 50 ከመቶና በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው በመጀመሪያው ዙር ፈተና ከወሠዱት 544 ሺሕ 682 ተማሪዎች ውስጥ 44 ከመቶዎቹ 50 ከመቶ እና ከዚያ በላይ ውጤት ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል። በሁለተኛው ዙር ከተፈተኑት 53 ሺሕ 997 ተማሪዎች ውስጥ 28 ከመቶዎቹ እንዲሁም ከመጀመሪያው ዙር 554 ሺሕ 682 ተፈታኞች ውስጥ 25 ከመቶዎቹ ወደ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እንደሚመደቡ ገልጸዋል። የ10ኛ ክፍል የማትሪክ ፈተና በመቅረቱ ምክንያት በጣም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል ፈተናን ወስደዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው አራት ዩኒቨርሲቲዎች መቀበል በማይችሉበት ሁኔታ ከአምናው የተሻለ ቁጥር ያለው ተማሪ ወደ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች እንዲመደቡ መደረጉንም አስረድተዋል። ይህ የሚኒስቴር ዲኤታው ምለሽ ግን ለቀረበው ቅሬታ አንዳች መፍትሔ ተደርጎ የሚታይ አይደለም፡፡

በአንጻሩ የተለያዩ ተቋማት ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴርን አካሄድ አውግዘዋል፡፡ የተማሪዎቹን ውጤት ላይ የተፈጠረው ችግር ዳግም እንዲመረመርና እንዲፈተሸ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ጊዜውም እንዲራዘም ጠይቀዋል፡፡ በዚህም የተማሪዎችን ያልተጠበቀ የውጤት መቀነስ ምክንያት ለማወቅ ኹሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ መኾኑን የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ ገለጿል። የመማክርት ጉባዔው የአማራ ክልል 12ኛ ክፍል ተፈታኝ ተማሪዎች ውጤት ከዚህ ቀደም ይመዘገብ ከነበረው ያነሰ መኾኑን መረጃ ማግኘቱን አስታውቆ ይህንን መሠረት በማድረግም የአማራ ምሁራን መማክርት ጉባዔ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዝቅተኛ ውጤት እንዲመዘገብ ያጋጠሙ ምክንያቶችን ለማጣራት ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ጋር በቅርበት እየሠራ እንደሆነ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ዶክተር ዳዊት መኮንን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ላይ እርማት እንዲደረግ ጠይቋል። የመግቢያ ፈተናውን ውጤት ተከትሎ የሚወጡት መረጃዎች ያልተለመዱና አስደንጋጭ ናቸው ያለው የአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በተወሰኑ ተማሪዎችና ወላጆች ግፊትና ጫና  የተስተካከሉ ውጤቶች ለተፈጠረው ስሕተት ሁነኛ ማሳያዎች ናቸው ብሏል። የአማራ ትምህርት ቢሮ የሁሉንም ትምህርት ቤቶች ውጤት ዝርዝር መረጃ በመሰብሰብ ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሕዝብ ይፋ ማድረግ እንደሚገባው የጠቆመው ፎረሙ ትምህርት ሚኒስቴርና የፈተናዎች ድርጅት ለችግሩ ትኩረት ሰጥተው ለማረም እድል ያገኛሉ ብሎ እንደሚያምን ገልጿል። የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮም በበኩሉ በ2013 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች የዩኒቨርስቲ መግቢያ ጊዜው እንዲራዘም ትምህርት ሚኒስቴርን ጠይቋል። ከዚያም ባለፈ የተፈጠረውን ከፍተኛ ቅሬታ የሚያጣራ ቡድን ወደ አዲስ አበባ መላኩን አስታውቋል፡፡ በመኾኑም ከክልሉ ትምህርት ቢሮ አመራሮቸና ባለሙያዎች፣ ከአማራ ምሁራን መማክርት ጉባኤ፣ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከትምህርት ቤት ርዕሰ መምህራንና መምህራን የተውጣጣ ቡድን ወደ ፈተናወች ኤጀንሲ መላኩን አስታውቋል፡፡ በአጠቃላይ ይህ በውዝግብ የሚላተመው ተቋም ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ እና የትምህርት ሚኒስትር ዲኤታዉ ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ የጅማ ዩኒቨርሲቲን በጎበኙበት ወቅት የትምህርት ሥርዓቱ በኢትዮጵያ ያለበትን ደረጃ ምን እንደሚመስል አብራርተዋል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ ካሉ የ3ኛ ክፍል ተማሪዎች 65 በመቶ ማንበብ እንማይችሉ እና መምህራን ተብለው የሚያስተምሩትን ትምህርት ከተፈተኑት መምህራን መካከል 85 በመቶ የሚኾኑት ብቁ አለመኾናቸውን እንዲሁም ያለፉትን ሰባት ተከታታይ ዓመታት የሀገር አቀፍ ፈተና መሰረቁነው ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም በሀገሪቱ የሚገኙ 99 በመቶ የሚኾኑ ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን መሥፈርት እንደማያሟሉም አመላክተዋል። ከዚህ አኳያ ተቋሙ ምን ያህል ደረጃውን ባልጠበቀ መልኩ እየተጓዘ እንደሚገኝ መገመት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ትምህርት ሚኒስቴር ኾነ የፈተናዎች ኤጀንሲ በደንብ መፈተሽና መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...