የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከደቡብ ኮሪያ ወደ ዋሽንግተን በሚላኩ ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ማድረጋቸውን አስታውቀው ፤ የምስራቅ እስያዊቷ አጋር ከአሜሪካ ጋር የገባችዉን የንግድ ስምምነት በበቂ ፍጥነት ማፅደቅ አልቻለችም ሲሉ ከሰዋል።
ባለፈው አመት በዋሽንግተን እና በሴኡል መካከል የተካሄደውን የንግድ ስምምነት ለማፅደቅ የደቡብ ኮሪያ ህግ አውጭ አካል ባለመቻሉ ትራምፕ ከ15 በመቶ ወደ 25 በመቶ ታሪዱን ከፍ ማድረጋቸዉን የግል ንብረታቸዉ በሆነዉ ትሩዝ ሶሻል ላይ ያጋሩት መግለጫ አመላክቷል፡፡
ትራምፕ ከፍተኛው የታሪፍ ተመን በመኪናዎች ፣በእንጨት እና በመድኃኒት ምርቶች ላይ እንዲሁም በተገላቢጦሽ ታሪፍ ስር ባሉ ዕቃዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል ።”የደቡብ ኮሪያ ህግ አውጭ አካል ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያለውን ስምምነት እየጠበቀ አይደለም” ሲሉ ትራምፕ አክለዋል።
የደቡብ ኮሪያ ፕሬዚዳንታዊ ጽህፈት ቤት ቼንግ ዋ ዴ በሰጠው መግለጫ ሴኡል ስለ ታሪፍ ከአሜሪካ ወገን ምንም አይነት ቅድመ ማሳወቂያ እንዳልደረሳት ተናግሯል።የብሔራዊ ፖሊሲ ዳይሬክተር ኪም ዮንግ-ቢም በትራምፕ ማስታወቂያ ላይ ለመወያየት ስብሰባ እንደሚጠሩ ተናግረዋል ።
በአሁኑ ወቅት በካናዳ የሚገኙት የደቡብ ኮሪያ የንግድ ሚኒስትር ኪም ጁንግ-ኳን ወደ አሜሪካም በመጓዝ ከአሜሪካ የንግድ ሚኒስትር ሃዋርድ ሉትኒክ ጋር እንደሚነጋገሩ ጽህፈት ቤቱ አስታውቋል።ዩናይትድ ስቴትስ እና ደቡብ ኮሪያ በሐምሌ ወር ላይ የንግድ ማዕቀፍ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ።
በዚህ መሠረት ትራምፕ በደቡብ ኮሪያ ምርቶች ላይ የጣሉትን የተገላቢጦሽ ታሪፍ ከ25 በመቶ ወደ 15 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተስማምተዉ እንደነበር ይታወሳል።በስምምነቱ መሰረት ሴኡል ሴሚኮንዳክተሮች እና የመርከብ ግንባታን ጨምሮ ቁልፍ በሆኑ የአሜሪካ ኢንዱስትሪዎች ላይ የ350 ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ተስማምታለች።
