በጉዳዩ ዙሪያ ስምምነት ላይ ካልደረሱ የቦምብ ጥቃት እፈጽማለሁ ጥቃቱም ከዚህ በፊት አይተውት የማያውቁት ይሆናል ብለዋል የአሜሪካው ፕሬዝዳንት፡፡
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር መርሃ ግብሯ ላይ ከዋሽንግተን ጋር ለመደራደር ካልተስማማች ታይቶ የማይታወቅ የቦምብ ጥቃት ይደርስባታል ብለዋል፤
ይህም በጥር ወር ስልጣን ከያዙ በኋላ ስለሚወስዱት ወታደራዊ እርምጃ በጣም ግልፅ የሆነ ማስጠንቀቂያ የሰጡበት ነዉ ተብሏል፡፡
ባለፈው እሁድ የኢራኑ ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን ቴህራን በኒውክሌር መርሃ ግብሯ ላይ ከአሜሪካ ጋር የምታደርገውን ቀጥተኛ ድርድር ውድቅ እንዳደረገች በመግለጽ፤ኢራን ቀጥተኛ ምላሽ የሚያስፈልገዉን ከዶናልድ ትራምፕ የመጣ ደብዳቤ ለጠቅላይ መሪ አሊ ካሜኔ መላኳን አስታዉቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ በተዘዋዋሪ ድርድር የማካሄድ እድልን ግን ክፍት አድርገዋል።
ትራምፕ ኢራን በቀጥታ ንግግሮች ላይ እንድትሳተፍ ለወራት በይፋ ግፊት ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም ቴህራን የውሳኔ ሃሳቡን ውድቅ ካደረገች በጣም መጥፎ ምላሽ እንደሚከተላት ፍንጭ ሰጥተዉ ነበር፡፡
በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ፤የአለም ኃያላን እና ኢራን የጋራ አጠቃላይ የድርጊት መርሃ ግብር በመባል ከሚታወቀው የኒውክሌር ስምምነት ራሳቸዉን በማግለል በቴህራን ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ መጣላቸዉ ይታወሳል ሲል አናዶሉ ዘግቧል፡፡
