ትውልደ ኢትዮጵያዊው የጆ ባይደን ሹም

Date:

ዮሐንስ አብርሃም ይባላል፡፡ ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሁን በአሜሪካ ለከፍተኛ ሥልጣን ታጭቶ የጆ ባይደንን መንግሥት ለማገልገል የተመረጠ ሰው ነው፡፡ የትራምፕ አስተዳደር አብቅቶ አዲሱ የዴሞክራቶች ፓርቲ በትረ መንግሥቱን ሲቆጣጠር፣ ይህ ሰው ሹመቱን ተቀብሎ የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት ኃላፊ እና የአስተዳደሩ ዋና ፀሐፊ (chief of staff and executive secretary) ይሆናል፡፡

ዮሐንስ አብርሃም ከዚህ ቀደም በነበረው የኦባማ የሥልጣን ዘመን ሥልጣን ተሰጥቶት እውቅና ያገኘ ቢሆንም፣ በዘረኝነት የሚታወቀው ትራምፕ ወደ ሥልጣን ሲመጣ ተገሎ ቆይቶ የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆኖ ነበር፡፡ አሁን የጆ ባይደንን መመረጥ ተከትሎ በድጋሚ ወደ ሥልጣን ማማው መውጣት የቻለ ሲሆን፣ የአሁኑ ሥልጣኑ በፀጥታ፣ በሰላም፣ በውጭ ግንኙነትና በደህንነት ጉዳዮች የአሜሪካ ፕሬዝዳንትንና ምክትል ፕሬዝዳንቷን ያማክራል፡፡ ከባድ ውሳኔ የሚሠጥበትም ሥልጣን እንደመሆኑ፣ በአሜሪካ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ በበርካቶች ከሚፈለጉ እርከኖች መካከል ቁንጮው መሆኑ ይነገራል፡፡ ዮሐንስ ለሹመቱ የበቃው ባለው የፖለቲካ ብስለት፣ ብቃት፣ ልምድና ዕውቀት በመሆኑ በአዲሱ የጆ ባይደን መንግሥት ምስረታ ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡ የሽግግር ቡድኑ ዋና ዳይሬክተር በመሆን አዲሱን የአሜሪካ መንግሥት ካቢኔን እያዋቀረ እንደሚገኝ ተነግሮለታል፡፡

ዮሐንስ እዚህ ደረጃ ሊደርስ የቻለው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ነው፡፡ በፐብሊክ ፖሊሲ ትምህርት መምህር ኾኖ በሀርቫርድ ኬኔዲ ስኩል እያገለገለ የነበረ ሲሆን፣ ከዛ በፊት በኢንስትቲዩት ኦፍ ፖለቲክስ፣ ሬዚደንሺያል ፌሎው ሆኖ ሲያገለግል ነበር፡፡ ከሀርቫርድ በፊት በኦባማ ፋውንዴሽን ከፍተኛ አማካሪ ሆኖ የሰራው ዮሐንስ፣ አዲሱን ተቋም በመመሥረት በኃላፊነት ደረጃ ሲያገለግልም ቆይቷል፡፡ ከኦባማ ፋውንዴሽን በፊት በነጩ ቤተመንግሥት የብሔራዊ ኢኮኖሚ ካውንስል ከፍተኛ አማካሪ በመሆን፣ እንዲሁም የሀገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት የፕሬዝዳንቱ ምክትል በመሆን ትልልቅ ሥራዎችን ሲያከናውን ነበር፡፡ ከፍተኛ አማካሪ በነበረበት በዚህ ወቅት የማዕከላዊው መንግሥት ከግዛቶች ጋር ያለውን ግንኙነቶች፣ የግሉን ሴክተርና የሰው ኃይልን በተመለከተ፣ እንዲሁም የኦባማ አስተዳደር የሚያወጣቸው ፖሊሲዎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ የተቋቋሙ ቡድኖችን ሥራ ሲከታተል ቆይቷል፡፡ በዚህ የሥልጣን ቆይታው በተለይ በኹለተኛው የኦባማ የሥልጣን ዘመን በነበሩ የሕግ ማውጣት ማረጋገጥና ማስተዋወቅ ላይ በነበሩ ፍልሚያዎች ተሳታፊ ነበር፡፡

ባራክ ኦባማ አስተዳደር ውስጥ ዝናን ያተረፈው አብርሃም ወደ ፖለቲካው ዓለም ሙሉ በሙሉ የተቀላቀለው በፈረንጆቹ 2007 ነበር፡፡ ኦባማ በአዮዋ ግዛት ቅስቀሳ በሚያደርግበት ወቅት ነበር ለመጀመሪያ ጊዜ ስራውን የጀመረው፡፡ በዚህ ሥራው በአጭር ጊዜ ተቀባይነት በማግኘቱ የኦባማ የቨርጂኒያ ፊልድ ዳይሬክተር በመሆን በ2008ቱ የአሜሪካ ምርጫ የወቅቱን ሴናተር ኦባማን ማገዙን ቀጥሏል፡፡ ውድድሩን አሸንፈው ቤተመንግሥት ሲገቡ እሱም ወደ ዋይት ሀውስ በማምራት፣ በሕግ ጉዳዮችና የፖለቲካ ጉዳዮች ዳይሬክተር በመሆን አራቱን ዓመታት በብቃት መወጣቱን የሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ በ2012 ኦባማና ባይደን በድጋሚ ለመመረጥ ያደርጉት በነበረው ቅስቀሳ ወቅት እንዲያግዙ በግንባር ቀደምነትኑ ከተመረጡት መካከል አብርሃም ቀዳሚው ሆኖ ነበር፡፡

በሥራው ታታሪነት ከሥልጣን ወደ ሥልጣን እየተሸጋገረ ከፍተኛ ሹም ለመሆን የበቃው ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ የቨርጂኒያ ስፕሪንግ ፊልድ ነዋሪ ነበር፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪውን ከየል ኮሌጅ ያገኘው አብርሃም፣ ማስተርሱን ከሀርቫርድ ቢዝነስ ስኩል በከፍተኛ ማዕረግ አግኝቶ ኑሮውን በቨርጂኒያ አሌክሳንድሪያ ከተማ በማድረግ የዴሞክራቲክ ኮሚቴ አባል በመሆን ነው የፖለቲካ አለሙን “ሀ” ብሎ የጀመረው፡፡ በኦባማ የሥልጣን ዘመን ብቃቱን ያስመሰከረው አብርሃም፣ የዴሞክራቲክ እጩ ሆነው ውድድሩን ያሸነፏት ጆ ባይደን ጋር ከቅስቀሳ ወቅት ጀምሮ ነበር አብሯቸው ሲሰራ የነበረው፡፡ ምርጫውን ሲያሸንፉ የመንግሥት ሽግግሩ እንዴት መካሄድ እንዳለበት የሚሠራውን ሥራ እንዲቆጣጠር ነበር ኃላፊነት የተሰጠው፡፡ በሥልጣን ሽግግሩ ወቅት የማያስፈልጉ ተግባሮችን አቅዶ ተግባራዊ እንዲደረጉ የሚያስችል ሥራን ሲያከናውንም ቆይቷል፡፡ በጆ ባይደን የተቀጠረው አብርሃም፣ የግብፅን የለት ተዕለት ጉዳይ እንዲከታተልም ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ በጆ ባይደን አስተዳደር ውስጥ ሊካተቱ ስለሚችሉ ሰዎች ምርጫ፣ እንዲሁም አዲሱ ፕሬዝዳንት ወደ ቤተመንግሥቱ ሊገቡ ስለሚችሉበት መንገድ ኃላፊነት የተሰጠው ለአብርሃም ብቻ ባይሆንም፣ ሥራው ብቃትን የሚጠይቅ መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ኃላፊነቱ ያን ያህል ወሳኝ የሚባል አይደለም በማለት ሊያጣጥሉት ቢሞክሩም፣ ከመጋረጃ ጀርባ የሚከናወኑ አስፈላጊ ተግባሮችን የሚያውቁ ብቻ ጠቃሚነቱን እንደሚረዱ ግልፅ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ከተሰደዱ ወላጆች የተገኘው አብርሃም፣ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ ከባዶ ተነስተው ትልቅ ደረጃ ከደረሱ ጉምቱ ፖለቲከኞች ተርታ የሚሰለፍ ነው፡፡ ከቤተሰብ የወረሰው ዝናና ሀብት ሳኖረው በጥረቱ ለትልቅ ኃላፊነት የበቃው ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ፖለቲከኛ፣ ለሌሎች ስደተኞች ጥሩ ምሳሌ ይሆናል ተብሎለታል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን ልጆቻቸውን ለከፍተኛ ትምህርት አብቅተው በትልልቅ መስኮች ተካፋይ እንዲሆኑ የሚያበረታታ ምሳሌ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ አሁን በሚሠራበት ዋሽንግተን ከተማ ከ50 ሺህ በላይ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚገኙ ሲሆን፣ እሱም በቤተመንግሥት በማገልገል ለወደፊት ፍሬ ለሚሆኑት ሕፃናት ጥሩ አርአያ ይሆናል ተብሏል፡፡

በፈረንጆቹ 2016 ከሎስ አንጀለስ ታይምስ ጋር ቃለ መጠይቅ ያደረገው ዮሐንስ፣ “ታማኙ የኦባማ ዴሞክራት” በመባል ይታወቃል፡፡ በቃለ መጠይቁ ወቅት፣ “እኛ ፖለቲከኞች ሳንሆን የኦባማ ሰዎች ነን” ያለው ንግግሩ በሠፊው ናኝቶ ነበር፡፡ ከስራው በተጨማሪ በመሳጭ ንግግሩ የሚታወቀው ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ፣ ባራክ ኦባማ በቆዩባቸው 2 የሥልጣን ዘመናት ከጎናቸው ሆኖ አሜሪካንን ሲያገለግል ኖሯል፡፡ እህቱ ጂቱ አብርሃም በዋሽንግተን በተካሄደ የቁንጅና ውድድር አሸንፋ ሚስ ኢትዮጵያ ተብላ የነበረች ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የታወቀች የሚዲያ ባለሙያ ናት፡፡ ዮሐንስ አብርሃም በዋይት ኀውስ ውስጥ ለከፍተኛ ሥልጣን የበቃ የመጀመሪያው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ አሁን የተሰጠውን ኃላፊነት ከእሱ በላይ ሊወጣው የሚችል እንደሌለ የበላይ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ቫለሪ ጃሬት ከNBC ጋር በነበራቸው ቆይታ ስለሹመቱ ትክክለኛነት ተናግረዋል፡፡ ዮሐንስ በአንድ ወቅት ቃለመጠይቅ ሲደረግለት ለዚህ ያበቁት ስደተኛ ወላጆቹ እንደሆኑ ይናገራል፡፡ “በጠንካራ ሥራ እንዳምን፣ እንዲሁም ሕዝብን እንዳገለግል አድርገው በሚገባ መንገድ አሳድገውኛል፡፡ ለስኬቴም ሞዴል የሆኑኝ እነሱ ናቸው” ብሎ ተናግሯል፡፡ ማንንም የማያውቁበት ሀገር መጥተው በሀገር ጉዳይ ጭምር ተሳታፊ እንድንሆን አድርገው፣ ለራሳቸው ሳይሆን ቅድሚያ ለእኛ በማሰብ ተንከባክበው አሳድገውናል ይላል፡፡ ከሰው በቀላሉ እንድንግባባ ከማድረግ ባሻገር፣ ለሰዎች እንድንታገልም አድርገውናል ብሎ ስለ አስተዳደጋቸው ተናግሯል፡፡ ከሠብዓዊ መብት ጋር በተገናኘ የቀደሙ ተሟጋቾችን ማመስገን እንደሚገባ የሚናገረው ዮሐንስ፣ እነሱ ታግለው ያመጡልንን መብት ላለመጠቀም ምንም ምክንያት የለንም ብሎ ያስባል፡፡ አይመለከተንም ወይም አንችልም ማለት ትተን ተባብረን ለሠው ልጆች ሕይወት መሻሻል መጣር እንደሚገባን ባገኘው አጋጣሚ ይናገራል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...