በክቡር ገና
እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ፤ መልካም በዓል!
የኢትዮጵያ መንግሥት የክልል ልዩ ኃይሎችን ትጥቅ ለማስፈታት ወይም በእነሱ አገላለጽ መልሶ በማደራጀት ወደ አንድ ብሔራዊ ኃይል ለማካተት ወስኗል።
ይኽንን ውሣኔ አስመልክቶ የአማራ ኃይሎች በመንግሥት የተላለፈው ውሣኔ ሽፋኑ መልሶ ማደራጀት የሚል ይኹን እንጂ እኩይ ዓላማን በውስጡ ያመቀ ነው ብለው ያምናሉ። ስለምን አሁን ይኽን ማድረግ ተፈለገ? ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ከጫፍ እስከ ጫፍ የሕልውና ስጋት እየገጠመው ካለው የአማራ ሕዝብ መጀመርስ ለምን አስፈለገ ሲሉ ደግመው ይጠይቃሉ። መንግሥት ልክ እንዳለፉት ጊዜያት በውስጡ ሌላ ፍላጎት አምቆ ይኽን ማድረግ እንደፈለገ በመግለጽ፣ የኋላ ኋላ የተናገረው ውሸት መኾኑ ቢታወቅ እንኳን አንዴ ነገሩ ከተበላሸ ምንም ማድረግ አለመቻሉን በሥጋትነት ያነሳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ትጥቅ የማስፈታት ወይም የመልሶ ማደራጀት ዕቅዱ አጠቃላይ ዓላማ ተዓማኒነት ሊያጣ ችሏል፡፡
በወጉ የዳበረ ሥርዓተ መንግሥት ያለበት ሀገር… መንግሥት አንድ ትልቅ ፖሊሲ ከማውጣቱ በፊት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ፖሊሲውን ለማስፈጸም አንድ ገጽ ላይ መቆማቸውን ያረጋግጣል። አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ‹የታጠቁ ኃይሎችን መልሶ ማደራጀት› ምን ማለት እንደኾነ፣ እንዴትስ ተግባራዊ እንደሚደረግ ሙሉ በሙሉ ተረድተው ሊኾን ይችላል፡፡ ኾኖም የቧንቧ ሰራተኛው፣ ቲማቲም ነጋዴዋ እና የአውቶብስ ተቆጣጣሪውስ እሳቸው የተናገሩትን ለማመን ቀርቶ ምን ማለት እንደኾነ ይረዱታል? ማንኛዉንም እርምጃ ወደ መሬት ከማውረድ በፊት በጥንቃቄ ማሰብ፣ መመርመር እና ክርክር መደረግ ያለበትም ለዚህ ነው።
እናም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ነገሩን በሌላ መንገድ ይሞክሩት። ሁኔታዎች እንዳይባባሱ ጉዳዩን ወደ አማካሪዎችዎ በመውሰድ የተሻለ አማራጭ መንገድ እንዲገኝ ማድረግ ይበጃል፡፡
መንግሥት ጥያቄውን በኃይል ለመፍታት ማሰቡ ከአራት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ሌላ አስከፊ ወታደራዊ ውሣኔ ላይ መድረሱን ያሳያል፡፡ እንዲህ ያለው ወታደራዊ እርምጃ በአማራ ላይ ምን ያህል ተፈጻሚ መኾን ይችላል የሚለውን ደግሞ ማሰብ ያስፈልጋል። አሁን ባለንበት ሁኔታ የፌደራል መንግሥት የቱንም ያህል ትንሽ በሚባል ኃይል አማራን ትጥቅ ማስፈታት ቢችል እንኳን ወደሌላ ቀውስ መሸጋገሪያ በር ከመኾን አይመለስም። ይኽ ደግሞ “ጦርነትን ስትችል ልትጀምረው ትችላለህ፣ ፈልገህ ግን አታቆመውም” የሚለውን አባባል ያስታውሳል፡፡
መንግሥት ወታደራዊ መንገድን ምርጫው እንደማያደርግ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይኽ ምርጫ ውጥረቱን ወደ ሌላ አስፈሪ ምዕራፍ ሊያመራው ይችላል፡፡ ከዛ ይልቅ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝብ ተቋማት፣ በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ በመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በፍርድ ቤቶች፣ በባንኮች፣ በማኅበራት፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ በመገናኛ ብዙኃን እና በዩኒቨርሲቲዎች ላይ የተፈጠረውን የሕዝብ አመኔታ ማሽቆልቆል ለማስተካከል መጣር አለበት። ባለፉት አራት ዓመታት በእነኚህ ተቋማት ላይ ሕዝቡ ያለው አመኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ በመምጣቱ በፖለቲካችን፣ በኢኮኖሚያዊ እና የሕግ ሥርዓታችን ላይ ዕምነት እንዳይኖረው አድርጎታል።
እርግጥ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ከታጣቂ ኃይሎች ትጥቅ ማስፈታት ወይም መልሶ ማደራጀት (የትኛውም ሥም ይሰጠው) ጋር ተያይዞ የገጠመን ቀውስ የአጭር ጊዜ አይደለም ፤ ደግሞም ጥልቅ ነው። በአንጻሩ ግን አራት ኪሎ የተቀመጠው መንግሥት ተጠያቂነት የጎደለው፣ ውሸት እና ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም፣ የግልፅነት እጦት እና የሥነምግባር ጉድለቶች እጅጉን የተንሠራፉበት ነው። እንዲህ ያለው ውድቀት ከመሠረቱ መስተካከል ያልቻለው ደግሞ ከመንግሥት አቅም በላይ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር በመኖሩ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ችላ ተብለናል፣ ተገፍተናል፣ ችግራችንን የሚፈታልን መንግሥታዊ አካል የለም በማለት ቅሬታቸውን ከማሰማት ተሻግረው፣ በእነኚህ ተደጋጋሚ ችግሮች ሳቢያ በገዛ አገራቸው ራሳቸውን እንደ ሁለተኛ ዜጋ እንደሚቆጠሩ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል።
በሁሉም የሀገራችን ክፍል ለእድገት የሚኾኑ ዕድሎችን እና ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ይልቅ፣ ልጓም በሌለው የጎሰኝነት ዕሣቤ እርስ በርሳችን ጦርነት ውስጥ ገብተን ለሀገሪቱ እድገትና ብልፅግናን መትጋት የሚያስችለንን ዕድል እንድናጣ እየኾንን ነው።
ይህ ክፉ አዙሪት ነው። በኢኮኖሚ ወደ ኋላ በቀረን ቁጥር ብዙ ሰዎች ለችግራቸው ምላሽ በሚሰጣቸው ሳይኾን አይመለከተኝም ብሎ ፊቱን ባዞረባቸው የመንግሥት ሥርዓት እንደሚተዳደሩ እንዲሰማቸው ምክንያት ይኾናል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን የተከሰቱት የፖለቲካ ውድቀቶች ሀገራችን ፈጣን ለኾነው የዓለም ለውጥ ፤ ለዲጂታል እና አረንጓዴ አብዮት ፤ ለአየር ንብረት ለውጥ ምላሽ፣ ለአቅርቦት ሰንሰለት እጥረት እና ለሥራ አጥነት ችግሮች ራሷን በወጉ አዘጋጅታ ፈተናዎቹን መጋፈጥ እንዳትችል አድርጓታል፡፡ በርግጥም ከእነኚህ የዓለም ተለዋዋጭ ሁኔታዎች እና ችግሮች ጋር ራስን አስማምቶ ለመጓዝ የተለያዩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን ከጎሳ ፖለቲካ በራቀ መንገድ አስተባብሮ መምራትን ይሻል፡፡ በእኔ አተያይ የኢትዮጵያ ችግር ከጎሰኝነት ይልቅ ከፋፋይነት (ትልቁን ሃገራዊ ምስል ከማየት ይልቅ በትናንሽ ቡድን ላይ ማተኮርን ማስቀደም)፣ ስግብግብነት፣ ሌብነት፣ መምራት አለመቻል፣ የመድረሻን አቅጣጫ አለማወቅ እና ደካማ የኃይል አጠቃቀም በመኾኑ ተፈላጊውን ለውጥ እውን ማድረግ ዳገት ከሆነብን በላይ ሕልውናችን አስጊ ኾኗል!!
