የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ስልታዊ አቀማመጥ ያላት እና በማዕድን የበለጸገችው ግሪንላንድ ግዛቲቱን ሀገራቸው በኃይል ልትጠቀልል እንደምትችል ሰሞኑን ፍንጭ ሰጥተዋል።የዴንማርክ፣ ግሪንላንድ እና የአሜሪካ ባለሥልጣናት በጉዳዩ ላይ ውይይት ያደረጉ ቢሆንም ያለ ሥምምነት መበተናቸው ታውቋል።
ይህንን ተከትሎ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ድጋፋቸውን ለማሳየት ወታደሮቻቸውን በአርክቲክ ቀጠና ወደምትገኘው ራስ ገዝ ግዛት እየላኩ ይገኛሉ። ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን እና ኔዘርላንድስ ውስን ቁጥር ያላቸው ወታደሮች ወደግሪንላንድ መላካቸውን አስታውቀዋል።
ርምጃው በአውሮፓ ሀገራት መካከል አንድነት መኖርን ለማሳየት እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የግሪንላንድን ደሕንነት መጠበቅ ስለሚችል አሜሪካ ግዛቲቱን መጠቅለል እንደማያስፈልጋት ለፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ መልዕክት ለማስተላለፍ ያለመ እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።
ነገር ግን የአውሮፓ ሀገራት ርምጃ የአሜሪካ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ደሴቱን ለመጠቅለል ያላቸውን ፍላጎት እንደማይለውጥ አሜሪካ አስታውቃለች።የዋይት ሀውስ የፕሬስ ፀሐፊ ካሮሊን ሊቪት ተልዕኮውን አቅልለውታል። ይህ በትራምፕ ውሳኔ አሰጣጥ ወይም ግሪንላንድን የማግኘት ግብ ላይ ምንም ተጽእኖ እንደማይኖረው ተናግረዋል።ካሮሊን ሊቪት አያይዘውም “ፕሬዝዳንቱ ቅድሚያ የሚሰጡት ነገር ግልፅ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ ግሪንላንድን እንድታስተዳድር ይፈልጋሉ። ይህንን የሚያደርጉት ለብሔራዊ ደህንነታችን በማሰብ ነው።” ብለዋል።
ከ57,000 በታች ህዝብ ያላት ግሪንላንድ በዴንማርክ መንግሥት ውስጥ ከፊል ራስ ገዝ ግዛት ስትሆን ለደሴቲቱ የመከላከያ እና የውጭ ፖሊሲ ዴንማርክ ኃላፊነት ትወስዳለች።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ደሴቲቱ ለዩናይትድ ስቴትስ ጥቅም ወሳኝ ናት የሚል አቋም ቢኖራቸውም፤ ግሪንላንድ እና ዴንማርክ ግን ግዛቲቱ አትሸጥም ሲሉ ተቃውመዋል። ትራምፕ ሩሲያ ወይም ቻይና ግሪንላንድን ለመያዝ ቢፈልጉ ዴንማርክ መከላከል ትችላለች ተብሎ መተማመን እንደማይቻል ከሀገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ከተወያዩ በኋላ ገልጸዋል።
