ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር የተሰጠ መግለጫ
18 ክለቦችን ተሳታፊ የሚያደርገውና 4 ወራጅ ክለቦች የሚኖሩት የዘንድሮ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር መካሄዱን ቀጥሎ የ32ኛ ሳምንት መገባደጃ ላይ ይገኛል።
የሊግ ውድድሩ ጤናማ የስፖርታዊ ፉክክር ይዞ እንዲቀጥል እና ፍትሃዊ እንዲሆን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ያደረጋል። ከነዚም ውስጥ የአመቱ መጨረሻ የክለቦች የአክሲዮን ክፍፍል ክፍያንም ውጤትን መሰረት አድርጎ በየደረጃው የሚሊዮን ብሮች ልዩነት እንዲኖረው ያደረገበት አንዱ ነው።
በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርና ስነ ስርዓት ኮሚቴ እና በቴክኒክ ኮሚቴ ሪፖርት መሰረት በሁለተኛው ዙር ከተደረጉ ጨዋታዎች ውስጥ አስር ጨዋታዎች ከአቅም በታች የመጫወት(የመላቀቅ) ምልክቶች እንደታዩባቸው እና አስፈላጊው ጥንቃቄ እንደደረግና ተጨማሪ ምርመራም እንዲካሄድ ከዳይሬክተሮች ቦርድ ጋር ውይይት ተደርጓል።
ስለሆነም በዚህ ተግባር ውስጥ የተጠረጠሩ አሰልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ ዳኞች፣ የክለብ አመራሮች እና ሌሎች አካላት ላይ ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚደረጉና ቀሪ የሊጉ ጨወታዎችንም የተቋቋመው ኮሚቴ ከሌሎች ተቋማት ጋር በመሆን የተጠናከረ ክትትልና ምርመራ አንደሚያካሂድ እየገለፅን ቀሪ ጨዋታዎችም በጥናቃቄ መደረግ እንዳለባቸው አቅጣጫ ተቀምጧል።
የውድድር ቴክኒክ ኮሚቴው በውድድር ቦታው በመገኘት የጨዋታዎች ግምገማ የሚያደርግ ሲሆን የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ላይም የቪድዮ ትንተና ይሰራል።
በተጨማሪም ከሜዳ ውጪ የሚደረጉ እግር ካሳዊ ያልሆኑ ያልተገቡ የጥቅም ግንኙነቶችም ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ተጨማሪ ምርመራ ይደረግባቸዋል። ስለዚህም በነዚህ ድርጊት እየተሳተፈ የሚገኝ አካል ከድርጊቱ እንዲታቀብ እያሳወቅን በማስረጃ በተረጋገጡት ላይ ተገቢው የእርምት ርምጃ ይወሰዳል።
ክለቦችም ከአቅም በታች በመጫወት ዙሪያ በማስረጃ ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በማህበራዊ ሚድያ በመልቀቅ ደጋፊዎቻች በስሜታዊነት ላላስፈላጊ ረብሻ እንዳይጋለጡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ እያሳወቅን በቀጣይ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የበላይ አመራሮች ጋር በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ቀነ ቀጠሮ መያዙን እንገልፃለን።
ጨዋታዎች የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ማግኘታቸው የውድድሩ ተመልካች ተደራሽነት ከማስፋቱም በላይ ለፉክክሩ የተሻለ ድባብ እንደሚጨምርለት ይታወቃል። በዚህም በውድድር አመቱ የ32 ጨዋታዎች ሽፋን ብቻ የሰጠው ሱፐር ስፖርት የመጨረሻ ቀሪ የአራት ሳምንት(ከ33ኛ እስከ 36ኛ) ጨዋታዎችን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ይሰጣል። ስለዚህም በበቂ ማስረጃ የጨዋታ ግምገማ ስለሚደረግ ሁሉም አካላት ይህን አውቃችሁ በስፓርታዊ ጨዋነት እንድትንቀሳቀሱ እናሳስባለን።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አ.ማ
