‹‹አስብ የነበረው የሀገርን ችግር ማስተካከል የሚችል ድርጅት እየገነባሁ እንደነበር ነው›› ኢ/ር ፀደቀ ይሁኔ

Date:

‹‹ሀገራዊ ዓላማ ያላቸው ሰዎችና ንግድ አብሮ አይሄድም››

‹‹ተላላ በበዛበት ማኅበረሰብ ውስጥ አታላይ ይበዛል››

የዛሬው የመጽሔታችን እንግዳ በሪልስቴት እና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ከተሰማሩ ሥም ካላቸው ኢትዮጵያውያን አንዱ ናቸው፡፡ ኢንጂነር ፀደቀ ይሁኔ ይባላሉ፡፡ የፍሊንትስቶን ሆምስ መሥራች እና ዋና ሥራ አስፈጻሚም ናቸው፡፡ ላለፉት ሠላሳ ዓመታት በቤቶች ግንባታ ዘርፍ ብዙዎችን የቤት ባለቤት ከማድረግ አንስቶ ትልልቅ ውጤቶችን ያስመዘገበው ድርጅታቸው፣ አሁን ላይ አክሲዮኑን ለብዙኃን ለመሸጥ ተዘጋጅቷል፡፡ ‹‹ጥቂት ሰዎች የሚመሩት ተቋምም ሄዶ ሄዶ ወዳቂ ነው›› የሚሉት ኢንጂነር ፀደቀ፣ አክሲዮኑን ለሽያጭ ያቀረቡበትን ከነጋዴነት ዕሣቤ የተሻገረ ፍልስፍናዊ አመክንዮን ያስረዳሉ፡፡ የመጽሔታችን ባልደረባ የኾነው ፍቃዱ ማኅተመወርቅም፣ ሰፋ ባለ መልኩ ይኽን የመሰለውን የሪልስቴት ዘርፍ ሕይወታቸውን፣ አልፎ አልፎም ግለሰባዊ ጉዳያቸውን እያነሳ የሚከተለውን ቆይታ ከእርሳቸው ጋር አድርጓል፡፡ እነኾ!       

ግዮን፡- በመጀመሪያ እንግዳችን በመኾንዎ እያመሰገንን ድርጅታችሁ ፍሊንትስቶን ሆምስ መቼ ተመሠረተ?

ፀደቀ፡- በደርግ ጊዜ አንድ ጥሩ ሕግ ነበር፡፡ ፈቃድ ሳያወጡ ሥራ መጀመር ይቻል ነበር፡፡ ለአንድ ስድስት ወር ሥራው ከታየ በኋላ ነበር ፈቃድ ማውጣት የሚቻለው፡፡ የፈቃድ ቅጹ ላይ እራሱ መቼ ሥራው እንደተጀመረ ይጠየቅ ነበር፡፡ እኔ ሥራ የጀመርኩት ኢሕአዴግ ከመግባቱ በፊት ነው፡፡ ፈቃድ ግን አላወጣሁም ነበር፡፡ ፈቃድ ያወጣሁት በ1984 ዓ.ም ኢሕአዴግ ገብቶ ጥቅምት ወር ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ድርጅቱ ከተመሠረተ 32 ዓመት ኾኖታል ማለት ነው፡፡

ግየን፡- ድርጅቱ ለምን ‹‹ፍሊንትስቶን›› ተባለ?

ፀደቀ፡- ለድርጅቱ ይህ ሥም የተሰጠው በሁለት ምክንያት ነው፡፡ ፍሊንት ስቶን ማለት የባልጩት ዐይነት ድንጋይ ማለት ነው፡፡ ይህ ድንጋይ እሳት የሚጭር ድንጋይ ነው ፤ እሳት መጫር የሰው ልጆች ለመጀመሪያ ጊዜ ጨለማን ያሸነፉበት ፤ ምግብ ያበሰሉበት ፈጠራቸው ነው፡፡ በእርግጥ ይሄ የኔ ግምት ነው፡፡ ስለዚህ እውቀት የማንም ሳይኾን የሁሉም ነው በሚል ነው የድርጅቴን ሥያሜ ያደረኩት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በ1984 ዓ.ም እንደ አሁኑ የከረረ ብሔርተኝነት ነበር፡፡ በሰዓቱ የአማራ ብሔርና ሌሎች የሚናቆሩበት ጊዜ ስለነበር የትኛውም ሥም በድርጅት ስም መግለፅ አንድ ብሔራዊ ማንነት ይገልፃል በሚል ይህን ሥም የድርጅቱ መጠሪያ ላላደርገው ችያለሁ፡፡ ነጋዴ ብሔር የለውም፡፡ ስለኾነም ከአማርኛ ወይም ከሌላ ሀገረኛ ሥም ይህ የእንግሊዘኛ ሥም እንዲወጣ ወቅቱ አስገድዶኛል ማለት ይቻላል፡፡ መጀመሪያ ላይ በአባቴ በኩል ያለውን የመጨረሻ ስም ሠርፀድንግል ብዬ ጀምሬው ነበር፡፡ ንግድ ፍቃድ እስካወጣ ‹‹ፀደቀ ይሁኔ ሕንፃ ተቋራጭ›› ተብሎ ነበር የሚጠራው፡፡ ኋላ ላይ ግን ነገሮችን ራቅ አድርጌ ሳስባቸው ነጋዴነት አመዘነብኝ፡፡

ግዮን፡- ፍሊንትስቶን በምን ያህል ካፒታልና በስንት ሠራተኞች ሥራ ጀመረ? አሁንስ የካፒታል መጠኑ ምን ያህል ነው?

ፀደቀ፡- መጀመሪያ ፍቃድ ሳወጣ ደረጃ ስምንት በሚል ነው፡፡ ደረጃ ሰባት ለማድረግ መኪናና ሚክሰር ያስፈልግ ነበር፡፡ እኔም በወቅቱ መኪናውን ገዝቼ ሚክሰር አጣሁ፡፡ ቫይብሬተር እና መሰሎቹን ከጓደኞቼ ጋር ባገኝም ሚክሰር ግን ማግኘት አልቻልኩም፡፡ በወቅቱ ፈቃድ ሰጭ የነበረችው ሴት ካሰች የምትባል ስትኾን፣ ሚክሰር ስለሌለኝ ደረጃ ስምንት እንዳወጣ ነገረችኝ፡፡ እኔም ምክሯን ተቀብዬ ደረጃ ስምንት አወጣሁ፡፡ ሥራ ስጀምር በአጠቃላይ ከእናቴ የወሰድኩት ዕዳ ስድስት ሺህ ብር ነበር፡፡

ግዮን፡- አሁን ምን ያህል ካፒታል ደረሰ?

ፀደቀ፡- በየጊዜው የሚለዋወጥ ቢኾንም አሁን ላይ ከ300-400 የሚደርሱ ቋሚ ሠራተኞች አሉን፡፡ በካፒታል ደረጃ 3.5 ቢሊዮን ካፒታል አለው፡፡

ግዮን፡- የድርጅታችሁ 30 ዓመታት የስኬት መንገድ ምን ይመስላል?

ፀደቀ፡- ስኬት መገለጫው ብዙ ነው፡፡ እኔ ስኬቱ ይኼ ነው ብዬ መግለፅ ይከብደኛል፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜ ጉጉት የሚባል ነገር አለ፡፡ በዚያ ላይ በርካታ ውጣ ውረዶች አሉ፡፡ ሰው እንደተስተካከለለት የሚታወቀው በሕይወት እያለ ሳይኾን ካለፈ በኋላ ይመስለኛል፡፡ መውደቅ መነሳት ስላለና በየትኛው ሁኔታ ከዚህ ዓለም መለየት እንደሚመጣ ስለሚታወቅ ስኬትን ይኼ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ ‹‹ያንተ ስኬት ምንድ ነው?›› ከተባለ ግን ሥራው የሚፈልገውን እንጂ እኔ የምፈልገውን ባለመከተል ላለንበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ ሥራ ብዙ ነገር ሲፈልግ እያደረግኩ ሲያተርፍ ደግሞ መልሼ ሥራውን እያሰፋሁ ቀጥያለሁ፡፡ ቁጠባና ጠንካራ የሥራ ባሕልንም ተምሬበታለሁ፡፤ በእነዚህ ሁለት ነገሮች እራሴን አሻሽያለሁ፡፡ ቁጠባና ጠንካራ የሥራ ባሕሌ እዚህ ደረጃ ለመድረሴ አግዘውኛል ብዬ አምናለሁ፡፡

ግዮን፡-  ከድርጅታችሁ ግብ አንፃር ዓላማችሁን አሳክታችኋል?

ፀደቀ፡- አዎ ግባችንን እውን አድርገናል፡፡ ለምሳሌ አሁን የምኖርበት ቤት ሥራው የተጀመረው በ1958 ዓ.ም ነው፡፡ ያለቀው ደግሞ በ1959 ዓ.ም ነው፡፡ ቤቱ ተሠርቶ ያለቀው በአንድ ዓመት ውስጥ ነው፡፡ ከተሠራ አሁን ወደ ስድሳ ዓመት እየኾነው ነው፡፡ እዚህ ቤት ስንገባ እኔ ሦስት ዓመቴ ነበር፡፡ ከዛሬ ስድሳ ዓመት በፊት ይሄ ሠፈር አሁን ካለው ጥቂት ብቻ ነው የሚለየው፡፡ በጣት የሚቆጠሩ ሕንፃዎች ብቻ ናቸው የተሠሩት፡፡ የዛሬ 50 ዓመት የተመሳቀለ ሕይወት ይኖሩ የነበሩ የሰፈራችን ሰዎች አሁንም አሉ፡፡ ይሄ በአንድ መደብ ውስጥ ታንቆ የመኖር አባዜ የመኖር ጉጉትን ይጋርዳል፡፡ ባሳለፍናቸው ሦስት መንግሥታት ውስጥ የማኅበረሰቡን ኑሮ ያው ነው፡፡ እኔ ይህን ማስተካከል የሚቻል ይመስለኝ ነበር፡ አሁን ሳየው ግን እንዲህ ዓይነት ነገር እንኳን በግለሰብ በመንግሥት ደረጃም የሚቻል አይደለም፡፡ እኔ እንኳን አይደለም ሥራ ስጀምር ይቅርና ከ10 ዓመት በፊትም አስብ የነበረው የሀገርን ችግር ማስተካከል የሚችል ድርጅት እየገነባሁ እንደነበር ነው፡፡ ያለፉት ስድስት ሰባት ዓመታት ግን እንኳን የሀገርን ችግር የራሱን የድርጅቱን ችግር መፍታት ይችላል ወይ እስክል ነው ያታገለኝ፡፡

ሀገር በፖለቲካና ኢኮኖሚ ሳይረጋጋ ሲቀር ቤተሰብ ይጎዳል፡፡ በዚያው ልክ ትልልቅ ድርጅቶች በሀገር ልክ ባይኾንም ከፍተኛ ጉዳትን ያስተናግዳሉ፡፡ ያ ማለት ሠራተኛ ይቀንሳሉ፤ ያሉትን ሠራተኞች መብትም አያስከብሩም፡፡ ደንበኞችን ይጎዳሉ፡፡ የደንበኞችን ገንዘብ ያባክናሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ በውል ላይ የተቀመጡ ነገሮችን መፈፀም ያቅትና ያልታሰበ አተካራ ይገጥማቸዋል፡፡ ባለፉት ዓመታት እነዚህ ነገሮች ተከስተውብኛል፡፡ ይኼን ስኬት ልለው አልችልም፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮችን እንደተሸከመች ሁሉ እኔም የሀገሬ አካል እንደመኾኔ መጠን በርካታ ችግሮችን ተሸክሜያለሁ፡፡ ምክንያቱም ካሉ ችግሮች አንፃር ለግል ኑሮዬ መደላደል ስል ንብረቴን ሸጬ አለመሰደዴ በራሱ ለእኔ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በዚህ ድርጅቱንም ከነሠራተኞቻችን ተስፋ እንዲኖረን አድርገናል፡፡

ግዮን፡- አንዳንዶች ስለእርስዎ ሲናገሩ ‹‹ከነጋዴነት ይልቅ ፖለቲከኛ ቢኾን›› ይላሉ፡፡ ምን ይላሉ?

ፀደቀ፡- ሀገራዊ ዓላማ ያላቸው ሰዎችና ንግድ አብሮ አይሄድም፡፡ የግል ጥቅምን ለማስጠበቅ ሲጣር ሀገራዊ ጥቅም ገደል ይገባል፡፡ ሀገራዊ ጥቅም ትልቅ መሥዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡ ነገር ግን እኔ ካደግሁበት ሰፈር አንፃር በወላጆቼና በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ ያለውን የኑሮ ልዩነት ስፋት እያየሁ ለውጥን እሻ ነበር፡፡ ለውጡ ሲመጣ ከማጣት በመጣ ክፋት መነሻነት ጓደኞቼን፣ ወንድሜንና መሰል ሰዎችን አጥቻለሁ፡፡ አምናለሁ፤ በነገራችን ላይ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል ሀገራዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ያለኝ ስሜት ከፍ ያለ የኾነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የተማርኩት ሲቪል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ሥራ የሠራሁትም የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፤ የደርግ ሶሻሊስት መንግሥት በመሐንዲስነት አስተምሮኝ ከዚያም በዚያው መንግሥት ውስጥ ሠራተኛ ኾኜ ማገልገሌ በራሱ አመለካከቴን ሕዝባዊ ያደርገዋል፡፡ እኔ ሁልግዜም ‹‹ምን አለ እስካሁን መንግሥት መሥሪያ ቤት እየሠራሁ ብቆይ›› እያልኩ አስባለሁ፡፡

ምክንያቱም ንግድ ወደራስ ለማድላት የሚያስገድድ የሥራ ክፍል ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ተቋራጭ ሃሳቦች በውስጤ በመኖራቸው ብዙ ጊዜ መንግሥትን እያገለገልኩ ብኖር እያልሁ አስባለሁ፡፡ ብዙ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውጤታማ የኾኑ ወዳጆችም አሉኝ፡፡ እንደእነሱ እኾን ነበር ብዬ  እፀፀታለሁ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥት መሥሪያ ቤት ተደማጭነት አጥተው የሚሰቃዩ ሰዎችን አያለሁ፤ በፖለቲካ ተልዕኮ በመታዘዝ የራሳቸውን ሚና መወጣት የተሳናቸው ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ የተተበተበባቸው ነገር አለ፤ ይህን ሳይ ደግሞ ‹‹እንኳንም ነጋዴ ኾንሁ›› እላለሁ፡፡ ስለዚህ እኔ ሳልኾን ልጆቼ ናቸው መንግሥት መሥሪያ ቤት ብቀር ወይም ነጋዴ ብኾን የሚያውቁት፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በራሴ ላይ መገመትና መፍረድ አልችልም፡፡ የሕዝባዊነት ፍላጎት ግን ሁሌም በውስጤ ይኖራል፡፡

ግዮን፡- ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ሄደው ነበር፤ ምን ተምረው መጡ? ደርሰው ሲመለሱ ድርጅትዎን እንደጠበቁት አገኙት?

ፀደቀ፡- በፈረንጆቹ አቆጣጠር በ2006 ነበር ወደውጭ የሄድኩት፡፡ ከ1997 ምርጫ ቀጥሎ ሀገሪቱ ላይ ጥሩ ነገር አልነበረም፡፡ እኔም በራሴ ጥፋት በቤተሰብ ደረጃ ጥሩ ሁኔታ አልነበረም፡፡ ስለኾነም በሰዓቱ ዞር ማለት ነበረብኝ፡፡ እራሴንና ባሕሪዬን ለማስተካከልና ለማሻሻል እንዲሁም ድርጅቴ ያለ እኔ መኖር ይችላል ወይ የሚለውን ነገር ለማየት ዞር አልኩ፡፡ በዚህም ባሕሪዬ ተሻሻለ፡፡ ስለ ኢንጂነሪንግ ያለኝ ሙያዊ እውቀትም ጎለበተ፡፡ በዚያን ጊዜ ስማር ኢትዮጵያ ሀገሬ ያለኝን ሀብት ከምንም ባለመቁጠር በአውቶቢስ እየተጓጓዝኩ አንድ ዓመት ከምናምን ቆይቼ ማስተርሴን ተምሬ ወደሀገሬ መጣሁ፡፡ እዚህ ስመጣ ድርጅቱ በሚገርም ሁኔታ ውጤታማ ኾኖ አገኘሁት፡፡ የድርጅቱ መሪዎች የሰጠኋቸውን አደራ ከምጠብቀው በላይ አሻሽለውት አገኘኋቸው፡፡ በዚህም በጣም ተደሰትኩ፡፡

ግዮን፡- አሁን ላይ ድርጅታችሁን ወደ አክሲዮን ለማዞር አስባችኋል፤ ይህ ውሣኔ ከ30 ዓመታት በኋላ እንዴት ሊታሰብ ቻለ?

ፀደቀ፡- ውሳኔው ከንግድ ጋር የተገናኘ ትርጉም ያለው ከመኾኑም በላይ ፍልስፍናዊ ምክንያት አለው፡፡ ከንግድ ጋር የተገናኘው ምክንያት የገንዘብ ችግር ነው፡፡ ባንኮችና ትልልቅ ድርጅቶች ገንዘብ ይቸገራሉ፤ በዚህ ጊዜ ገንዘብ የሚኖረው መካከለኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ነው፡፡ የተጠቀመውን ተጠቅሞ ቀሪውን ይቆጥባል፡፡ የእሱን ቁጠባ ደግሞ ትልልቅ ድርጅቶች ከባንክ ይበደሩታል፡፡ ስለዚህ ይሄ መሐል ላይ የተቀመጠ ገንዘብ ለአስቀማጭ ማኅበረሰብም ይሁን ለድርጅታችን ‹‹የተሻለ ጥቅም ማስገኘት ይችላል›› በሚል ነው ወደ አክሲዮን ሽያጭ የገባሁት፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በጥቂት ግለሰቦች የሚመሩ ድርጅት የመውደቅ እድላቸው ሰፊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ይዘገያል እንጂ ‹‹አህያ የጅብ ነች›› እንዲሉ ጥቂት ሰዎች የሚመሩት ተቋምም ሄዶ ሄዶ ወዳቂ ነው፡፡ ብዙ ሰው ያለበት ድርጅት ግን ተጠያቂነትና ሕግ የሚባል ነገር ስላለበት ከሞላጎደል ውድቀት አይከሰትም፡፡ የአክሲዮን ሕጉ የአክሲዮን ኩባንያዎችን የሚቆጣጠርበት ዘዴ ድርጅቶች ግልጽነትና ሕጋዊነት እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ የተሻለ የኮርፖሬት አስተዳዳር ነው ብየ ስለምገምት ነው ወደ አክሲዮን ለሞዞር የወሰንኩት፡፡ በፍልስፍና ደረጃ ግን እኔም ሕዝባዊ አመላከከት ስላለኝ አንድ ሰው ከበላ ከጠጣ እና ዘና ካለ ያለው ሀብት ሁሉ የሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ ተቋምን ሕዝባዊ አደረጃጀት ማድረግ ጠቃሚ ነው፡፡ በመኾኑም እውቀትም ኾነ ሀብት በብዙኃን እጅ ሲኾን የተሻለ ይኾናል የሚል እምነት ስላለኝ ነው ወደ አክሲዮን ያዞርኩት፡፡

ግዮን፡- እንዲህ ካሉ ታዲያ 30 ዓመታት የቆየ ተቋም ሕዝባዊ ለመኾን አልዘገየም?

ፀደቀ፡- ሁሉም ነገር የሚታሰበው ነገሮች ከባድ ሲኾኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የካፒታል ገበያ ባለቤት የአክስዮን ገበያ ማለት ነው፡፡ አክሲዮን ገንዘብም ሰውም ያመጣል፡፡ ባለአክሲዮኖች አክሲዮን መሸጥ ሲፈልጉ የሚሸጡበት ገበያ ከሌለ ባለአክሲዮኖች ታስረው ይቀራሉ፡፡ አሁን የወጣው ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን አዋጅ አክስዮኖች በኋላ የሚሸጡበትን የገበያ ማዕከል ስለሚያዘጋጁ የበለጠ ለአክሲዮን ገበያ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፊት የነበረን ፍላጎት እንዳለ ኾኖ አሁን የበለጠ የሚያጓጓ ነገር ከፊታችን አለ፡፡ ገበያ ላይ ከገባን የአክሲዮን ገበያው ሰፊ ነገር ከፊታችን አቅርቦልናል፡፡

ግዮን፡- ድርጅቱን ወደ አክስዮን ለመቀየር የወሰናችሁት መሬት በተፈለገው መንገድ ማግኘት ባለመቻላችሁ ነው ይባላል?

ፀደቀ፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት ችግር አለ ብዬ አላምንም፡፡ የገንዘብ ችግር እንጂ የመሬት ችግር የለም፡፡ በርካታ መሬት ያላቸው ሰዎች እኛ ጋር ይመጣሉ፡፡ ወደ 200 የሚጠጉ ባለመሬቶች መጥተዋል፡፡ እኛ ግን 20 የሚኾኑትን ነው የተጠቀምነው፡፡ ገንዘብ ቢኖር እነዚህ ወደኛ የመጡ መሬቶችን መጠቀም ይቻል ነበር፤ ስለዚህ አቅም ነው እንጂ የመሬት ችግር የለም፡፡ 200 መሬት ማለት በቢሊየን የሚቆጠር ማለት ነው፡፡ ነገር ግን እኛ አቅም የለንም፡፡ ብረት የለም ፤ ቀለም የለም ፤ መስታወት የለም፡፡ ገንዘብ አሰባስቦ መሬት ላይ ከማዋል ግብዓቱ ላይ ማዋል ያዋጣል፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ መግባት ይሻላል፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ የሚገባውን የሰው ቁጥር በማብዛት ቢዝነስን ማስፋት ተገቢ ነው፡፡ ቤት የሚሠራው ማኑፋክቸሪንግ በተሠራበት ውጤት ልክ ነው፡፡

ግዮን፡- ፍሊንትስቶን በምን በምን የሥራ ዘርፎች ላይ ነው እየሠራ ያለው?

ፀደቀ፡- ስንጀምር ኮንስትራክሽን ነበር የምንሠራው፡፡ ከዚያ ወደ ሪልስቴት ገባን፡፡ አንዳንድ ሪልስቴቶችን ካለማን በኋላ በእጃችን የሚቀሩ ነገሮች አሉ፡፡ ደብረብርሃን አካባቢ ደግሞ የጤፍ ወፍጮ አለን፡፡ አርባምንጭ ሆቴል አለን፡፡ የተለያዩ የገበያ ማዕከላት አሉን፡፡ ይኼ ከሪልስቴት ጋር የተገናኛ በመኾኑ ብቻ ያፈራነው ሀብት አስገድዶን የገባንባቸው ቢዝነሶች ናቸው፡፡ ዋናው ግን አሁን የበለጠ ለሪልስቴት ግብዓት የሚኾኑ በተለይ ብረትና ሲሚንቶ ሌሎች የኮንስትራክሽን ግብአት እቃዎች የማምረቻ ፋብሪካዎች ለመሥራት አቅደናል፡፡ ለምሳሌ ቱለፋ የሚባል ቦታ የብረት ፋብሪካ አለን፡፡ ከአዲስ አበባ 65 ኪ.ሎ ሜትር ርቀት አማራ ክልል የምትገኝ ቦታ ነች፡፡ ደብረብርሃንም አንድ ሌላ ፋብሪካ እየጀመርን ነው፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ የተለያዩ ቦታዎች ላይ አነስተኛ የብረት፣ የበርና መስኮት የቀለም ፋብሪካዎች እንጀምራለን፡፡

ግዮን፡-  ፍሊንትስቶን ምን ያህል ካፒታል መጠን ነው ለአክሲዮን መሸጥ የፈለገው?

ፀደቀ፡- ሙሉ ለሙሉ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የፍሊንስቶን ሀብት በሙሉ ለአክሲዮን ሽያጭ ቀርቧል፡፡ የተለየ ነገር የለም፤ በእርግጥ በግል ያፈራናቸው ፍሊንትስቶን ውስጥ የማይካተቱ በቤተሰብ ያፈራኋቸው ሀብቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ ሀብቶች ውጪ ያሉት በሙሉ ለሽያጭ ይቀርባሉ፡፡ እስካሁን የተከፈለው ካፒታል 400 ሚሊዮን ነው፡፡ ይህ እኔና ባልደረቦቼ የምንመራው ነው፡፡ እኔ ሰማንያ በመቶውን ስመራ 20 በመቶም ደግሞ ስድስት ባልደረቦቼ ይመሩበታል፡፡ ከዚህ ውጭ ወደ ሦስት ቢሊዮን አካባቢ የሚኾን የድርጅቱ እሴት ለገበያ ሲቀርብ 10 ሚሊዮን ሼሮች ይኖሩታል፡፡ እያንዳንዱ 500 ብር የሚያወጣ 10 ሚሊዮን ሼሮች ይኖሩታል፡፡ እነዚያ ዐሥር ሚሊዮን ሼሮች በሙሉ ቢሸጡ እኛ ያለን አክሲዮን 10 በመቶ ይኖሩታል፡፡ 90 በመቶ የሚኾነው የሕዝብ ይኾናል፡፡ ነገር ግን በአንድ ጊዜ የሚኾን አይደለም፡፡

ግዮን፡- አከፋፈሉ እንዴት ነው?

ፀደቀ፡- ትንሹ ሼር 20 ሺህ ብር ነው መግዛት የሚቻለው፤ ትልቁ ደግሞ 2 ሚሊዮን ነው፡፡ እያንዳንዱ ሼር ሲገዛ ቀድሞ የፈራው ሀብት 2.5 ሚሊዮን ስለተገመተ ቀድሞ ለፈራው 250 ብር ይከፈላል፡፡ 500 ብሩ የድርጅቱ ባለቤትነት የሚገኝበት ነው፡፡ ስለዚህ ከፍተኛው 2 ሚሊዮን ትንሹ ደግሞ 20 ሺህ ነው፡፡ እነዚህ ነገሮች ተደምረው በሚቀጥሉት ከ3-5 ያሉ ዓመታት ውስጥ 5 ቢሊዮን ይኾናሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከሕዝብ 5 ቢሊዮን፣ እራሳችን አንድ ቢሊዮን በስድስት ቢሊዮን የ60 ሚሊዮን ሥራ ሰርተን ትልቅ የገበያ ውጤት እናመጣለን ብለን እናምናለን፡፡

ግዮን፡- የእናንተ አክሲዮን ከሌላው በምን ይለያል?

ፀደቀ፡- አክሲዮን ኩባንያዎቹ ሁለት ዐይነት ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሒሳብ ይዞ በመቅረብ መሥራቾቹ ከሕዝብ ገንዘብ ሰብስቦ መነሳት ነው፡፡ ይሄ ብዙ ጊዜ ገንዘቡ እስኪሰበሰብ የሚቀየር ይኾናል፡፡ ወይ ሌላ ገንዘብ ያለው ሰው ቀድሞ ይገባና ገበያውን ይወስደዋል፡፡ አለያም ሐሳቡን ያመነጩ ሰዎች ይከፋፈሉና አንዱ ተገንጥሎ ይሄዳል፤ ወይም ደግሞ ገንዘቡ አልሞላ ይላል፡፡ ገንዘቡ አልሞላ ሲል ሐሳቡን ቀንሶ ከመጀመር ይልቅ ገንዘቡም ሐሳቡም ባክኖ ይቀራል፡፡ የተጀመረ ሥራ ሲኾን ግን ይኼ አይከሰትም፡፡ ለምሳሌ ፍሊንትስቶን ሪል ስቴት ፕሮጀክቶች ብቻ ከ14 በላይ ኾነው ‹‹የሠሪ ያለህ›› እያሉ አፋቸውን ከፍተው እየጠበቁ ይገኛሉ፡፡ የመንግሥት ድርጅቶችም እንደዚሁ በቢሊዮን የሚቆጠሩ አሉ፡፡ መንግሥት አሁን ችግር ላይ ስላለ ገብቶ ለሚሠራ ጥሩ ገንዘብ የሚያወጡ ብዙ ጅምር ሥራዎች አሉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ በመንግሥት እራሱ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር በፐብሊክ ፕራይቬት ፓርትነር ሺፕ ወይም 5 ሺህ ቤቶችን ልንሠራ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመናል፡፡ ሁለት ሺውን አሁን ሊሰጡን እየተዘጋጁ ነው፡፡ አሁን ልገልጸው የማልችል ሌላ የመንግሥት ተቋምም ይኸንኑ ያህል መጠን መሬት አቅርቦ ቤት ልንሠራለት ተዘጋጅተናል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ በመቶ የሚቆጠሩ ባለመሬቶች እየመጡ ይጠይቁናል፡፡ በዚህ ጊዜ በሳምንት ሁለት ሰው እናስተናግዳለን፡፡ መሬት ይዞ መጠቶ ገምቱልን የሚለው ብዙ ነው፡፡ ከሌሎች ጋር እንኳን ለመደራደር መጀመሪያ የእኛን አይተው ነው የሚሄዱት፤ ስለዚህ ስማችን የታወቀ ስለኾነ ገንዘብ ከመጣ በቀጥታ ወደ ሥራ ነው የሚውለው፡፡ የሚቸግረው ግብዓት አለመኖሩ ነው፡፡ የሲሚንቶና የብረት እጥረት አለ፡፡ እጥረቱን ለማጥፋት የመጀመሪያው ገንዘብ የሚውለው የግብዓት ማምረቻ ላይ ነው፡፡ ይሄ ትልቁ ጥቅም ነው፡፡ ገንዘቡ በዚህ ካልዋለ የሕዝቡ ገንዘብ ስለሚባክን ትልቅ ሥጋት ነው፡፡ ሥራ ላይ ከዋለ ግን ትልቅ ትርፍ ያመጣል፡፡

ግዮን፡- አክሲዮን ማቋቋምና መክሰም ለጥቂቶች አንድ ሰሞን የተለመደ ቢዝነስ መስሎ ነበርና ምን ይላሉ?

ፀደቀ፡- አክሲዮን ማቋቋምና መክሰር ወይም መበተን የትም ዓለም ላይ ያለ ነው፡፡ አክሲዮን ተላላና አታላይ ሰው አንድ ላይ ኾነው የሚሠሩት ነገር ነው፡፡ ተላላ በበዛበት ማኅበረሰብ ውስጥ አታላይ ይበዛል፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በመጀመሪያ አታላዮች አታለው መሄጃ የላቸውም፤ ተታላዮች ደግሞ ዋናው የሚታለሉበት ነገር በመጀመሪያ ደረጃ መረጃ አለመኖሩ ነው፡፡ አክሲዮን መግዛት የሚፈልግ ሰው አክሲዮን ከገዛ ሰው ላይ ሳይኾን መረጃ ማግኘትና ማየት አለበት፡፡ የንግድ ሕጉንም ማየት ይኖርባቸዋል፡፡ የንግድ ሕጉ አንድ አክሲዮን አደራጅ ‹‹ምን ምን ነገሮችን በሳቢ መግለጫው ውስጥ ያሰፍራል›› የሚለውን ያስቀምጣል፡፡ ስለዚህ አክሲዮን መግዛት የፈለገ ሰው በእነዚህ ነጥቦች መሠረት መገምገም ይኖርበታል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ አንድ ባለአክሲዮን አክሲዮን የሚገዛበት ገንዘብ ከዕለት ኑሮው የተረፈ ሊኾን ይገባል፡፡ ብዙ ሰው ችግር ውስጥ የሚገባው በአክሲዮን አደራጆች በመጓጓት ያለውን በሙሉ ተበድሮም ጭምር ለዚህ ዓላማ በማዋሉ ነው፡፡ ስለዚህ አክሲዮን ሥጋት ያለው ኢንቨስትመንት በመኾኑ ሕይወትን በማያናጋ ገንዘብ መሠራት ይኖርበታል፡፡ በተረፈ ገንዘብ ነው ኢንቨስት መደረግ ያለበት፡፡

ግዮን፡- ከበጎ አድራጎት ሥራ አንጻር ከዚህ ቀደም አዳሪ ት/ቤት በደሴ አካባቢ ከፍታችኋል፡፡ አዳሪ ት/ቤት ለመክፈት እንዴት አሰባችሁ?

ፀደቀ፡- ይኼ በእኔ ሐሳብ የመነጨ አይደለም፤ በሰዓቱ የቦርድ ኃላፊ የነበረው የአልማው ሕላዌ ዮሴፍ ነበር፡፡ ሕላዌ ዮሴፍ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቱን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ታግሎበታል፡፡ የታሰበው ደሴ ላይ ነበር፡፡ በአልማ 2002 ፕሮግራም ላይ እኔ መንገድ ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ውስጥ ነበርኩ፡፡ ማኅበሩ በማነቃቃት ፕሮግራሙ ላይ ይህን ትምህርት ቤት ከዝርዝሩ ውስጥ ሳየው ‹‹ለምን ተሰባስበን አንሠራም?›› ብየ ብዙ ኮንትራክተሮችን ጠየቅሁ፡፡ በዚህም በማኅበር ‹‹እንዴት ለአንድ ብሔር ትምህርት ቤት እንሠራለን?›› የሚለው ሐሳብ አሳመነኝ፡፡ ስለዚህ ሐሳቡን ከቤተሰቦቼ ጋር ኾኜ መሥራት እንዳለብን በመወሰን ትምህርት ቤቱን ሠራነው፡፡ በወቅቱ ይህን ሳደርግ ብዙ ባይሰማኝም በሂደት ግን ከፍተኛ እርካታ ሰጥቶኛል፡፡ ተግባሩ እንዲሁ ደስ ይለኛል፡፡ ሌሎችም የእኛን ዲዛይን ወስደው ሠርተውበታል፤ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ያን ጊዜ የኦልማ ኃላፊ ነበረች፡፡ በሰዓቱ እኛ ገና እየሠራን ዲዛይኑን ወስዳ አራት ቦታ አሠርታዋለች፡፡ ስለዚህ በሁሉም ክልሎች የሚዘምኑ በጎ ሐሳብ ስለኾኑ የምኮራበት ነገር ነው፡፡

ከዚያን በበለጠ ግን በአንድ ግለሰብ ወይም መኖሪያ ቤት ደረጃ ይህን የሚያክል ነገር ማድረግ መቻሉ ብዙዎች ቢተባበሩ ምን ያህል ሊሠራ ይችላል የሚለውን ነገር ሳሰላው ያስደነግጠኛል፡፡ በነገራችን ላይ በዚያን ወቅት ብዙ ትምህርት ቤቶች በተቋራጭ ማኅበራት ተሰርተዋል፡፡ የኾነ ኾኖ ይህ ትምህርት ቤት ባለፈው ዓመት በፈተና አንደኛ ወጥቷል ፤ ከፍተኛ ውጤት ያመጣው ተማሪም ከዚያው በመኾኑ በጣም ነው ደስ ያለኝ፡፡ ምን ዐይነት እድለኛ ሰው ነኝ ብያለሁ፡፡ ትምህርት ቤቱ የሚጠራው በአባቴ ስም ነው፡፡ ‹‹ይሁኔ ወልዱ ትምህርት ቤት›› ነው የሚባለው፡፡ እናቴ በሕይወት እያለች ይህን በማየቷ በጣም ነው ደስ ያላት፡፡ አንደኛ የወጣውም ልጅ እዚህ መጥቶ ነበር ፤ ከእናቴም ጋር አንድ ላይ ፎቶ አንስቻቸዋለሁ፡፡

ግዮን፡- በቅርቡ የወጣውን የንብረት ታክስ እንዴት አየኸው? ከሥራችሁ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ስለኾነ?

ፀደቀ፡- የሀገሪቱ  ኢኮኖሚ ችግር አንዱ ምንጭ በቂ ታክስ አለመሰብሰብ ነው፡፡ ስለዚህ የኢኮኖሚ ችግር ታክስ ባለመሰብሰብ አይስተካከልም፡፡ ታክስ መሰብሰብ አንዱ የጥሩ ኢኮኖሚ መግለጫ ነው፡፡ የንብረት ታክስ መሰብሰብ የተሻሉ ሀገሮች መግለጫ ነው፡፡ ጥያቄው የተሰበሰበው የንብረት ታክስ ‹‹ለማን ይውላል?›› የሚለው ነው፡፡ የንብረት ታክስ ‹‹ፌደራል ወይስ ክልል ይሰብስብ?›› የሚለው ሲያሟግታቸው ነበር፡፡ ይሄ ያሳፍራል፡፡ የንብረት ታክስ መዋል ያለበት ለሰፈር ነው፡፡ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ነው የሚውለው፡፡ ኅብረተሰቡ በዚህ ዙሪያ ቅሬታ ካለው የሚመነጨው  የንብረት ታክሱ ለራሱ እንደሚያውሉት ስለሚጠራጠር ነው፡፡

ለምሳሌ ከኮንዶሚኒየም የሚሰበሰብ ንብረት ኮንዶሚኒየም አካባቢ ለሚኖር ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ይውላል ቢባል በአንዴ ኪራዩ ይጨምራል፡፡ በበዛ ቁጥር ጥቅሙም በጣም ይጨምራል፡፡ ስለዚህ  የንብረት ታክስ አሁን እየተከፈለ ያለው በጣም በጥቂት ነው፡፡ ገንዘብን ለማስቀመጥ ወይም በበጎ ነገር ላይ ለማዋል ወቅት መዋጀት አያስፈልግም፡፡ ሰፈር ካልጸዳ፣ ፀጥታው ካልተከበረ፣  መብራት መንገድ እና መሰል የጋራ መጠቀሚያ ከሌለው ለነገ የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ አሁን ኅብረተሰቡ መታገል ያለበት ገንዘቡ እንዳይወሰድበት ነው፡፡ ላለመክፈል ሳይኾን ገንዘቡ የሚውልበትን ማወቅ ነው የሚያስፈልገው፡፡ እንደውም ይህ ገንዘብ በእድሮች ነበር መሰብሰብ ያለበት፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ 3600 ብሎኮች አሉ፡፡ ግብሩ በብሎኩም ይህም በቀጠና ተሰብስቦ ለኅብረተሰቡ ጥቅም ላይ መዋል ይኖርበታል፡፡ ከዛ ባለፈ ገንዘቡ ሌላ ጋር ከሄደ ግን ከባድ ነው የሚኾነው፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ትግል ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰቡ ገንዘቡ ለራሱ ማዋሉን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ያ ሲኾን አሁን የተተመነውን ብቻ ሳይኾን ከዚያ በላይም ለመክፈል ፈቃደኛ ይኾናል፡፡

ግዮን፡- በመጨረሻ ስለአክሲዮኑ ሽያጭ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?

ፀደቀ፡- እኔ ከማውቃቸው አክሲዮኖች ጋር አወዳድሬው የፍሊንትስቶን አክሲዮን ከባንኮች አክሲዮን ባልተናነሰ ደረጃ ላይ የሚገኝ ነው፡፡ የባንኮች አክሲዮን ትልቁ ተመራጭነት ሥራው አትራፊ መኾኑ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ የብሔራዊ ባንክ ከፍተኛ ቁጥጥር ስላለ ባንኮች እንዳይወድቁ ሲባል የሚያደርገው ቁጥጥር ባንኮችን አትራፊ አድርጓቸዋል፡ ከአትራፊነቱም በላይ ንብረታቸውን ማስጠበቅ ይችላሉ፡፡ የእኛ ተቋምም በእነዚህ ባንኮች ደረጃ እራሱን የሚቆጣጠር አክሲዮን ነው የሚኾነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ባለአክሲዮኖች ቤት መግዛት የሚፈልጉ ከኾነ ቤት መግዛት ይችላሉ፡፡ ለአክሲዮኑ ያዋሉትን ገንዘብ በየትኛውም ጊዜ ከፍሊንትስቶን ቤት መግዛት ቢፈልጉ በከፈሉት ልክ ታስቦ ወደ ቤት ቦታ ይቀየርላቸዋል፡፡ ይሄ በመተዳደሪያ ደንባችን ላይም የሰፈረ ነው፡፡ ስለዚህ አክሲዮኑን ቢገዙ በብዙ መልኩ እንደሚያዋጣቸው ነው በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ የምፈልገው፡፡    

ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በሱዳን ብሉ ናይል ግዛት ብቻ ከ12ሺ በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሉ

በሱዳን የሚገኘው የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው መረጃ...

ትራምፕ አሜሪካ እና ኢራን “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት ውስጥ” ሊወያዩ እንደሚችሉ ተናገሩ

ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል “በሚቀጥሉት ሁለት ቀናት...

የኢራን ጦርነት የሚቀጥል ከሆነ የዓለም ምጣኔ ኃብት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ አይኤምኤፍ አስጠነቀቀ

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) በመካከለኛው ምሥራቅ የሚካሄደው የኢራን...

የመምህር ዘላለም ወንድሙ (ወልደ ሰማዕት) የ፵ ቀን መታሰቢያ ጥሪ

​"የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው!" (ምሳሌ ፲፥፯)​በሕይወትና በቃል ትምህርታቸው ብዙዎችን...