Home ብዝሃ ሃይማኖት አነጋጋሪው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ!

አነጋጋሪው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ!

አነጋጋሪው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ!

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ አካሒዶት በነበረው ጉባኤ በተደራቢነት በተያዙ፣ ጉልህና አንገብጋቢ ችግር ባለባቸው በኦሮምያ ክልልና በደቡብ ክልል ባሉ አህጉረ ስብከት ላይ 9 ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስመራጭ ኮሚቴ መሰየሙ ይታወሳል፡፡ ይኽን ተከትሎም ምልዓተ ጉባኤው ይህን ጉዳይ በጥናትና በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት የሚለይና የሚያከናውን 7 ሊቃነ ጳጳሳት የተካተቱበት አስመራጭ ኮሚቴ መምረጡም ተገልጾ ነበር። አስመራጭ ኮሚቴውም ላለፈው አንድ ወር እንቅስቃሴውን ሲያከናውን ቆይቷል፡፡ ኾኖም በዚህ መሠረት የዕጩ ኤጲስ ቆጶሳትን ምልመላ ኮሚቴው በምሥጢር ማከናወኑ ከበርካታ የቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራት እና ምዕመናን ጥያቄ ሲቀርብበት ቆይቷል፡፡

በዚህ ረገድ ‹‹ፍኖተ ጽድቅ ወሕይወት ጉባኤ ማኅበራ ለቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ ኅብረት›› እና ‹‹በሰሜን አሜሪካ ማኅበረ ካህናት›› የተሰኙት ማኅበራት ቀዳሚዎቹ ሲኾኑ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ ቀሲስ በላይ መኮንንም በድብቅ እና ሕገ ወጥ አካሔድ የተጠቆሙ ቆሞሳትን በዕጩነት እንዳይቀበል በመጠየቅ ግልጽ ተቃውሞ ለቅዱስ ሲኖዶስ አሰምተዋል፡፡     

ይኽን ተከትሎ ማክሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ለመሰብሰብ ዕቅድ ይዞ የነበረው የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልዓተ ጉባኤ አቅዶት የነበረውን የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ በዕለቱ ማካሔድ ሳይችል ቀርቷል፡፡ በዕለቱ የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ፣ ከውጭ ይልቅ የሀገር ውስጥ አህጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት፣ በአንጻራዊ ብዛት የተገኙበት ሲኾን፣ በቅዱስ ሲኖዶስ የስብሰባ ሥነ ሥርዐት መሠረት፣ ቀኖናዊ ለኾነው የሢመተ ኤጰስ ቆጰሳት አጀንዳ፣ ከጠቅላላ አባላቱ (53+)፣ ቢያንስ 75 በመቶ ማለትም ከ38 ያላነሱ አባላት መገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ኾኖም፣ የተገኙት አባላት ከ30 ያልበለጡ እንደኾኑና ተፈላጊው የምልአተ ጉባኤ ቁጥር ባለመሟላቱ፣ ስብሰባውን ለመቀጠል አዳጋች እንደኾነበት ተነግሯል፡፡

በስብሰባው ካልተገኙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል፣ የኢሉ አባቦራ እና የሚኒሶታ እና አካባቢው አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፀዕ አባ ኤዎስጣቴዎስ እና የጉጂ ሊበን ቦረና ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳሰ ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ፣ ከቁጥር መጉደላቸው፣ የጉባኤውን አባላት በልዩ ትኩረት እንዳነጋገረ ተገልጿል፡፡ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ባለፈው ጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ተፈጽሞ ከነበረው ሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ጋራ፣ ዛሬም እንዳላቸው የሚነገረው “ስሜታዊ ቁርኝት”፣ በዕለቱ ስብስባ አለመገኘታቸው በዋዛ እንዳይታይ አድርጎታል፡፡ አስመራጭ ኮሚቴው፣ ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በሰጠው የጥቆማ ዕድል እንዳልተጠቀሙበትና “እኛ የሾምነውን ሾመናል” በማለት ተዐቅቦ እንዳደረጉም ተሰምቷል፡፡

በመኾኑም፣ ከጉባኤው በአፍኣ ኾነው ውሳኔውን ለማፍረስ ምክንያት እንዳያገኙ፣ ከጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ ማረፊያ በዓታቸው መጥተው በስብሰባው እንዲሳተፉ፣ ሁለት ጊዜ መልእክት እንደላከባቸው ተገልጿል፡፡ ይኹንና ‹‹እመጣለኹ›› ብለው ቃል ቢገቡም ባለመገኘታቸው፣ የቅዱስ ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ፣ ከቀትር በኋላ በነበረው ውሎ፣ ከጥብቅ ማስጠንቀቂያ ጋራ በደብዳቤ ጥሪ እንዲደረግላቸው ትእዛዝ ሰጥቷል፡፡

በትእዛዙ መሠረት፣ ለኹለቱም ብፁዓን አባቶች በየስማቸው ደብዳቤው ተጽፎ እንዲደርሳቸው የተደረገ ሲኾን፣ በመኾኑም የካቲት 8 ቀን 2015 ዓ.ም ለተደረሰው ስምምነት የመፍትሔው አካል ለመኾን እንደተስማሙ አውስቶ፣ በማግሥቱ ረቡዕ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ከጧቱ 2፡30 ላይ በቅዱስ ሲኖዶስ መሰብሰቢያ አዳራሽ እንዲገኙ፣ ምልአተ ጉባኤው አዟቸዋል፡፡ በስብሰባው የማይገኙ ከኾነ ግን፣ ስምምነቱ እንዳይፈጸም ካደረጉት አካላት አንዱ እንደኾኑ ታውቆ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በውሳኔው ላይ ተገቢው ውሳኔ እንደሚሰጠበት አስታውቆ ነበር፡፡

በተያያዘ፣ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ሁለት መነኰሳት በምርጫው እንዲካተቱላቸው የጠቆሙበት ደብዳቤ፣ ለጉባኤው በንባብ ቀርቦ ተሰምቷል፡፡ ይኹንና፣ የዐዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሢመቱ በሁለት ዙር እንዲከናወን፣ በርክበ ካህናቱ ምልአተ ጉባኤ በተወሰነው መሠረት፣ በቅዱስነታቸው የቀረቡት ኹለቱ መነኰሳት ማለትም የልዩ ረዳታቸው መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ኀይለ ገብርኤል ነጋሽ እና ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት አባ አብርሃም ገረመው ዕጩነት፣ በቀጣዩ ዓመት ጥቅምት ምልአተ ጉባኤ ቢታይ የተሻለ ይኾናል በሚል ታልፏል፡፡

የቅድመ ምርጫ ጥያቄዎች እና ውዝግቦች ባልተለዩት በዕለቱ ውሎ፣ በትኩረት ከተደመጡት አስተያየቶች አንዱ፣ የዋግ ኽምራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ በርናባስ፣ “ከሹመት ይልቅ እርቁን እናስቀድም፤” ሲሉ የተናገሩት ነው፡፡ የምንሾምለት ሕዝብ፡- ጥቁር ልበስ ስንለው ጥቁር የለበሰ፣ ሱባኤ ግባ ስንለው ሥራውንና ጥቅሙን ሠውቶ ሱባኤ የገባ፣ ሙት ስንለው የሞተ እንደኾነ ያስታወሱት ብፁዕነታቸው፣ ለሕዝብ በቁዔት የማይኾን ሢመተ ኤጲስ ቆጶስ፣ መልሶ እንዳይጎዳን መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ ከዚኽ አንጻር፣ “ተላላኪዎቻችንን [ዕውቀትም ግብረ ገብነትም የሌላቸው አቡነ ቀሲስ እና የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪጆችን] አምጥተን ጳጳስ ስናደርግ፣ ሰው ምን ይለናል?” ብሎ ማሰብ እንደሚያስፈልግ አዘክረዋል፡፡

ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቡነ አብርሃም በተመሳሳይ፣ ከምርጫውም ከሢመቱም አስቀድሞ፣ የትግራይ አህጉረ ስብከት አራት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋራ፣ በቤተ ክርስቲያን ሰላም እና መዋቅራዊ አንድነት ላይ የታቀደውን ውይይት ማጠናቀቁ ቅድሚያ እንዲሰጠው አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ “ምርጫውን አናድርግ፤ አስመራጭ ኮሚቴው ያቀረባቸው 18ቱም ተጠቋሚ ቆሞሳት ሲሠለጠኑ ይቆዩ፤ የትግራዩን እንጠብቅ፤” ማለታቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም መሠረት በማግሥቱ ረቡዕ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ በአካሔደው ልዩ ስብሰባ፣ በኦሮሚያ እና በደቡብ ክልሎች፣ በተደራቢነት ተይዘው ለቆዩ፣ ክፍት በኾኑና አንገብጋቢ ችግር ባለባቸው ዘጠኝ አህጉረ ስብከት ላይ የሚመደቡ ዘጠኝ ኤጲስ ቆጰሳትን ምርጫ አካሒዷል፡፡

በዚኽም መሠረት፡-

ለኦሮሚያ ክልል ሰባት አህጉረ ስብከት፤

1. አባ ሣህለ ማርያም ቶላ – ምዕራብ አርሲ – ሻሸመኔ ሀገረ ስብከት

2. አባ ወልደ ገብርኤል አበበ – ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት

3. አባ ጥላሁን ወርቁ – ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት

4. አባ ዓምደ ሚካኤል ኀይሌ – ሆሮ ጉድሩ ወለጋ – ሻምቡ ሀገረ ስብከት

5. አባ ኀይለ ማርያም ጌታቸው – ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት

6. አባ ተክለ ሃይማኖት ገብሬ – ምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት

7. አባ እስጢፋኖስ ገብሬ – ቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት

ለደቡብ ኢትዮጵያ ኹለት አህጉረ ስብከት፤

8. አባ ክፍለ ገብርኤል ተክለ ሐዋርያት – ጌድኦ አማሮ እና ቡርጂ ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት

9. አባ ስብሐት ለአብ ወልደ ማርያም – ዳውሮ እና ኮንታ ሀገረ ስብከት ኾነው በምልአተ ጉባኤው አብላጫ ድምፅ ተመርጠዋል፡፡

ተመራጭ አባቶች ከሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ሥልጠና የሚገቡ ሲኾኑ፣ እሑድ ሐምሌ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አንብሮተ እድ ሢመተ ኤጲስ ቆጶስ እንደሚፈጸምላቸውም ተገልጾዋል፡፡