አገር አጥፊ አገር እያጠፋ የሚኖርባት አገር!

Date:

አዳነ ጥላሁን ዳኜ(ወልዲያ)

ከአፄ ኃ/ሥላሴ ዘመነ አገዛዝ ወዲህ ይቺ ሀገር ብልህ መሪ አግኝታ አታውቅም፡፡ ደርግ፣ ኢሕአዴግም ሆነ የብልፅግና መንግሥት በስሜት ተነጂ እንጂ ብልህ አልነበሩም ፤ አይደሉምም፡፡  ደርግም ሆነ ኢሕአዴግ የአመራር ጥበባቸውም ቢሆን የሕዝብን ይሁንታ ያገኘ አልነበረም፡፡    የብልፅግናው መሪ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ያስተዋወቁን የመደመር ዕሳቤም ቢሆን በመሬት ላይ ሲታይ በአንድ ተሰባስበን የተደመርንበት ሳይሆን በስበባሰበብ ተነጣጥለን መቀነስን ጎልተን ያሳየንበት የአንድ ሰሞን ወረት አዘል አስተሳሰብ ሆኖ ተረስቷል፡፡

አጋጣሚውን ባገኙ ቁጥር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ካፋቸው ማር ጠብ በሚል ጣዕመ ንግግርና አገላለፅ የሚያሽሞነሙኑልን መሪያችን ለአንድ ሰሞን ከነፍሳችን አብልጠን በፍቅር ብንከንፍላቸውም አሁን አሁን ቀስ እያሉ ወደዘረኛው ኢሕአዴግ የዘር ፖለቲካ እየተንሸራተቱ በመጓዝ በርካታ አነጋጋሪና ግራ አጋቢ ተግባር እየፈፀሙ በመሆኑ ለእርሳቸው የነበረንን ልባዊ ፍቅርና ከበሬታ እየሸረሸሩት  ስለመሆኑ በግልፅ መናገር ይገባኛል፡፡

በተለይ በዚህ የ2015 ዘመነ ዓመት ሁለመናቸው ተቀይሮ ሳንወድ በግድ ወደማንፈልገው የጎሳ ተኮር ፖለቲካ አፍቃሪነት እየገፉን ነው፡፡ ትናንት ከትናንት በስቲያ ኢትዮጵያዊነትን የሰበከው አንደበታቸው ሙሉ በሙሉ ተቀይሮ ኦሮሞ ጠል ናችሁ የሚል ክስ አይሉት ወቀሳ ያቀረበብን በቅርብ ጊዜ ነው፡፡ አስከትለውም ስሙንና ትርጉሙን የማናውቀውን ሸኔ የሚል ማዕረገ ሹመት ለአማራ ተወላጆች ሲሰጡን ማመን አቅቶን ጆሯችንን ተጠራጠርን እንጂ ስለመሳሳታቸው ድምዳሜ ላይ አልደረስንም፡፡

ለነገሩ የመልካም መሪ ናፍቆት አዕምሯችንን ጋርዶት ነገሯን ሳናብሰለስላት ቀርተን እንጂ እርሳቸውን መጠርጠር የነበረብን ገና በአፍላ የሥልጣን ዘመናቸው ቤተመንግሥቱን ጥሰው የገቡ ወታደሮችን የጂምናስቲከ ቅጣት በቀጡበት ወቅት ለነበረው ሴራ በአለኝታ ጋሻ መከታነት የጠሩት በፍቅር እየከነፈላቸው የነበረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይሆን የቡራዩና አካባቢው ሕዝብ ስለመሆኑ በነገሩን ጊዜ ነበር፡፡

በተጨባጭ እንደሚታየው የብልፅግና መንግሥት ወደሥልጣን ከመጣ ወዲህ ሀገሪቱም እኛም እፎይታ አግኝተን ተረጋግተን ኑሯችንን የመራንበት ወቅት ስለመኖሩ ትዝ አይለኝም፡፡ ያገሪቱ የቀውስ አጀንዳ የተወሳሰበው ደግሞ በየጊዜው አነታራኪ አጀንዳ በማቀበሉ ረገድ ትልቁን ድርሻ የሚይዙት ይመሩናል ብለን የሾምናቸው ያገሪቱ አይነኬ ባለሥልጣናት መሆናቸው ነው፡፡ የትግራይ ክልል ቀውስ አበቃ ብለን ገና ደስታችንን በማጣጣም ላይ እያለን በባንዲራ መስቀልና መዝሙር መዘመር ሰበብ አዲስ አበባ ላይ የነገር ክብሪት የጫሩት አንቱ የተባሉት ባለሥልጣናት ነበሩ፡፡

በተለይ የኦሮሚያ ክልል ባለሥልጣናት የዚህ ዓመት ኩነት ለነጋሪም ለአድማጭም የሚመች አይደለም፡፡ በሁሉም ቦታ ጠብ ያማረው ጎረምሳ ዓይነት ድርጊት እየሆነ ተቸግረናል፡፡ ሕዝብ በአርቆ አስተዋይነት ትንኮሳውን ሁሉ በትዕግሥት ስለያዘው እንጂ የዚህ ክልል መንግሥት ባለሥልጣናት ድርጊት ሲታይ በዘመነ ሥልጣናቸው የሚዋጉት ጦር እንዲልክላቸው መሬትን በየቀኑ አርባ ጅራፍ ያስገርፉ እንደነበር በአፈ ታሪክ ይነገር የነበረው የአፄ ልብነድንግል ታሪክ ነው የሚያስታውሰን፡፡

ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ የአማራ ክልል መንገደኞችን ያለምክንያት በየኬላው እያገቱ ለሁለት ሦስት ቀን ማጉላላት የሚያመለክተው ጦር ናፋቂነትን እንጂ  የሰላም  ሐዋርያነትን አይደለም፡፡ ይኸ ዕብሪት አዘል ተግባር ደግሞ ያለመንግሥት ዕውቅና የተፈፀመ ነው ብሎ ለመናገር አይቻልም፡፡

የሌሎች ታዛቢዎችን ሁኔታ ባላውቅም በበኩሌ አንዳንዴ የእሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በፌደራል መንግሥት ሥር የሚተዳደርና የፌደራል መንግሥቱን መመሪያና ትዕዛዝ አክብሮ የሚፈፅም አልመስልህ እያለኝ ተቸግሬአለሁ፡፡ የዚህ ክልል ሁኔታና ሌሎች ክስተቶችም ተጨማምረው ኑሯችንን የሲዖል ኑሮ አድርገውታል፡፡

በሃይማኖት ሽፋን ሰሞኑን ባገራችን እየተፈፀመ ያለውን አሳዛኝም አስተዛዛቢም ፖለቲካ አዘል ሴራ እንደሰማሁ እኔ በምኖርበት ወልዲያ ከተማ ኗሪ የነበረች አረጋሽ የተባለች እብድ አንድ ቀን መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በሚገኘው የቀብር ቦታ እየተዘዋወረች “እናንተ ሙታን አርፋችሁ ተኙ መድረሻ አጥተን ነው እንጂ እኛም አልተመቸን” ብላ ለሙታን ያስተላለፈችው ከዕብድ የማይጠበቅ ቁም ነገር አዘል ንግግር ነው፡፡ ትዝ ይለኛል አረጋሽ እንዳለችው እዚህም እዚያም ለቅሶ፣ ዋይታ፣ ትርምስ፣ መፈናቀል፣ እስራት፣ ድብደባ፣ ግድያ አለ እና እኛ ቆመን መሄዳችን ካልሆነ በስተቀር ከሙታን በምን እንደምንሻል አልገባህ ብሎኛል፡፡ ወደሰማይ አንወጣ የመወጣጫው ብልሀቱ የለንም፤ መሬት ውስጥ አንገባ በቁሙ በድን የሆነው አካላችን ይንከላወሳል፤ መሬት ላይ አርፈን እንዳንቀመጥ አሳዳጃችን፡፡ በዝቷል የት እንግባ ጎበዝ?

መቸም ያገሪቱ ርግማን ከዓመት ዓመት ከወር ወር እየጨመረ ነውና የሚሄደው አሁን ላይ ደግሞ ርግማኑ ጠንቶባት ከሺህ ዘመን በላይ ዕድሜ ባላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት አካባቢ አነጋጋሪና አነታራኪ የቀውስ አጀንዳ ተከስቶ ኢትዮጵያን እያንቀረቀባት ነው፡፡ በዚች ቤተ ዕምነት ዙሪያ የተነሳውን የነገር ትኩሳት አስደንጋጭም አስፈሪም አደጋ ጋባዥ ያደረገውም የተከሰተውን ችግር ከሃይማኖትና መንፈሳዊነቱ አውጥቶ የፖለቲካ ካባ ለማላበስ በሚደረገው ግብግብ ዙሪያ የመንግሥት አካላት እጅ ያለበት መሆኑ ነው፡፡

ያገራችን ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዚህ ቀውስ ዙሪያ ለሚኒስተሮቻቸው በሰጡት ገለፃ የቤተ ዕምነቷን ትምክህት፣ ሙስና፣ ዘረኝነትና በፖለቲካ መበከል ነካክተውና ስለትግራይ ጳጳሳት በቋንቋ መስፈርት ሹመት አውስተው በኦሮሚያ የሚገኙ የተዋሕዶ ልጆች በቋንቋ ለመጠቀም ያቀረቡትን ጥያቄ መከልከል እንደማይችሉ ተናግረው ያም ሆኖ በሁለቱም ጎራ የተሰለፉት አባቶቻችን ናቸውና ማንም ባለስልጣን በዚህ ቀውስ ውስጥ እጁን እንዳያስገባ አስጠንቅቀው መንግሥት ገለልተኛ ነው ይበሉን እንጂ በግልፅ የታየው ግን የመንግሥትን ገለልተኝነት የሚያጠናክር ድርጊት አልነበረም፡፡

የመንግሥት አፈቀላጤ የሆነው መ/ቤትም ቤተክርስቲያኗ መብቷን ለማስከበር ሕገመንግሥቱን ተንተርሳ የጠራችውን ሰላማዊ ሰልፍ አውግዞ በሕገወጥነት መፈረጁ ሳይበቃው ምኑን ከምን እንዳገናኘው ባላወቅነው ሁኔታ በውጭ ያገር ጠላት ግፊትና እጅ ጥምዘዛ ሕገመንግሥቱን ለመናድ የተሴረ የሽብር ተግባር ነው በሚል ቤተ ዕምነቷን ነው የወነጀለው፡፡ ነገርን ነገር ያነሳዋልና ይኸ ሕገመንግሥት መናድ የሚል ሟርት ከኢህአዴግ አፍላ የወጣትነት ዘመን አንስቶ አሁንም የቀጠለ የተሰለቸ  እድሜ ጠገብ ወንጀል መሆኑ ትዝ ሲለኝ ቀድሞ የሚመጣብኝ የውንጀላው ክብደት ሳይሆን ሳቄ ነው፡፡

ወደዋናው ነጥብ ስመለስ  የብልፅግና መንግሥት ባስተላለፈው በዚህ ከዕውነት ያፈነገጠ ገለፃ እጅግ በርካታ ሕዝብ ማዘኑን ሳልደብቅ እናገራለሁ፡፡ ውሱን ሰዎች ያዘነው ደግሞ በመንግሥት በኩል በተሰጠው ኢተዐማኒ መግለጫ ብቻ ሳይሆን ወደፊት መንግሥታችን ዕውነት ቢናገር ጭምር ለማመን እንደምንቸገረር ስናስበው ነው፡፡

መንግሥት በቤተ እምነቷ ዙሪያ በተነሳው ሃይማኖት ለበስ የፖለቲካ ሴራ ገለልተኛ ነኝ ነው ያለን፡፡ በግልፅ እንደምናየው ግን ሕገወጡ ቡድን እየፈፀመ ባለው የቤተክርስቲያን ወረራና ቁልፍ ሰበራ ሰበብ ከአማኙ ምዕምን እየደረሰበት ያለውን ተቃውሞ ለማክሸፍ ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ያሉት የኦሮሚያ መንግሥት ታጣቂዎች መሆናቸውን ነው፡፡ ይኸን ጣልቃ ገብነት በማየትም የመንግሥት ገለልተኝነት የት ላይ ነው? የሚል ጥያቄ እንድናነሳ አስገድዶናል፡፡

ያቤሎ ከተማ ኗሪና የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ የነበሩትን አባ ገብረሚካኤል ፈንቴን ሽንት ቤት ዘግተው የደበደቧቸውና ሊናገሩት የሚዘገንን ግፍ የፈፀሙባቸውም ሆነ ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ ይጓዙ የነበሩትን የቤተክርስቲያን አገልጋይ ክብር ደፍሮ በጥፊ የመታቸው እንዲሁም ሻሸመኔና ጅማ ብሎም በሌሎች የኦሮሚያ ቀበሌዎች የተዋሕዶን ልጆች የደበደቡ ያሰሩና በግፍ የገደሉ  በኦሮሚያ መንግሥት የሚታዘዙ ወታደሮች እንጂ ከጫካ የወጡ ጃዊሳ ሽፍቶች አልነበሩም፡፡ እነዚህ ደብዳቢ አሳሪና ገዳዮች ደግሞ ይኸን ሊሰሙትም ሆነ ሊናገሩት የሚዘገንን ተግባር የፈፀሙት  ያለባለስልጣናት ይሁንታ በራሳቸው ተነሳሽነት እንደማይፈፅሙት አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡

ለኔ እስከሚገባኝ ድረስም መንግሥት ባለበት ሀገር በቤተዕምነቷና በአማኝ የተዋሕዶ አገልጋይ ካህናትና ምዕምን ላይ ይኸ ሁሉ ግፍ እየተፈፀመ ያለው በምን ምክንያት ነው? የሚል ጥያቄ ቢነሳ  መልሱ አንድም ቤተዕምነቷ በኢትዮጵያ አንድነት ዙሪያ የማያወላውል አቋም ያላት መሆኑና በሌላ በኩልም ሙታን መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ፣ ሕሙማን ከሕመማቸው እንዲፈወሱና ስደተኞችም ወደሀገራቸው በሰላም በጤና እንዲመለሱ ሀገራችንም እንድትረጋጋ የመንግሥት ዙፋኑም እንዳይናጋ መሽቶ በነጋ ቁጥር ዘወትር በምታካሂደው ሥርዓተ ፀሎት ስለሀገር ስለሕዝብ ለፈጣሪዋ መፀለይዋ እንደወንጀል ተቆጥሮባት ይመስለኛል፡፡ (በእንተ ሀገሪትነ ኢትዮጵያ ናስተበቁዕ ከመ እግዚአብሔር ብዙኅ ሰላመ ይጸግዋ ፤ “እግዚአብሔር ሰላምን ለኢትዮጵያ ይሰጣት ዘንድ እንማለዳለን” ነውኮ የምትለው ዘወትር በቅዳሴ ወቅት)፡፡

ማጠቃለያ

ከጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንና በዕምነቷ ተከታይ የተዋሕዶ ልጆች ላይ የዘነበው የጥፋት ዝናብ በዘመነ ዮዲት ጉዲት፣ በግራኝ አሕመድና በአፄ ሱስንዮስ ዘመነ ሥልጣን ከደረሰው አሳር መከራ ባይበልጥም ግን ከነዚያ ዘመናት ጥፋት አያንስም፡፡ ዛሬ ቤተ እምነቷ እየተፈተነች ያለው ከውስጧ በወጡ ጡት ነካሾች ብቻ ሳይሆን በመንግሥት ባለስልጣናት ጭምር ነው፡፡ ቤተ ዕምነቷ ሕገ መንግሥታዊ መብቷን ተጠቅማ ለየካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም የጠራእው ሰላማዊ ሰልፍ መካሄድ እንደሌለበት ገልፆ ብትወጡ ግን ወዮላችሁ በማለት እርምጃ እንደሚወስድ በአደባባይ ፉከራ ያሰማን ሕገመንግሥታዊ መብታችንን ያስከብርልናል ያልነው “ፀሐዩ” መንግሥታችን ነው፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ ትዕዛዝ የነነዌን ፆም ጥቁር ለብሰን ምህላ በማድረግ እንድናሳልፍ በተሰጠው አዋጅ ተጠቃሚ እንዳንሆን በብዙ አካባቢዎች ክልከላ ያደረጉት የመንግሥት ባለሥልጣናት ናቸው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ የሀዘን ወቅት የኛ ሀዘን አስደስቶ ያስፈነደቃቸው ግለሰቦች እንደነበሩም ጠቁሜ ማለፍ ግድ ይለኛል፡፡ የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኙ አቶ በቀለ ገርባም ሆነ የኢትዮጵያ ሚዲያ አገልግሎት (ኢ.ኤም.ኤስ) ባልደረባ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌናና የኦሮሞኛ ሙዚቃ አቀንቃኙ ታደለ ገመቹ ነጭ ልብስ ለብሰው ፈገግታ የተላበሰ ምስላቸውን የለቀቁልን መልካቸውን እያየን ስለውበታቸው እንድናደንቅ ሳይሆን የኛ ምሬትና ለቅሶ ስላስደሰታቸው ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተዕምነት ስለመከፋፈሏ እግዚአብሔር ነግሮኛልና ደስ ይበላችሁ እልል በሉ እያለ ተከታዮቹን እልል ሲያሰኝ የነበረው ነቢይ ነኝ ባዩ የፕሮቴስታንት ሰባኪ ድርጊት ደግሞ የእርሱን የቅጥፈት ጥልቀት የሚያሳይ ትዝብት ላይ የሚጥል ተውኔት ነበር የፈፀመው፡፡   የዚህ ሰባኪ ቅጥፈት መረን የለቀቀና እምነቱን በዘፈቀደ ትርጉም የሚያስኬድና በስሜት ብቻ የሚጓዝ መሆኑን ማወቅ የሚቻለውም በየትኛውም የክርስትና እምነት አስተምህሮ ዙሪያ እግዚአብሔር ሰለሰው ልጅ ደህንነትና ስለፍቅር የሚሰብክ አምላክ እንጂ በምድራውያን በሚከወን ብጥብጥ ሁከት ግድያና ሞት የሚደሰት አምላክ አለመሆኑን ስናስብ ነው፡፡

ወደዋናው ፍሬ ጉዳይ ስመለስ የፌደራሉም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት አካል የሆነው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሊያፈርሱ የሞከሩት ሊፈርስ ቀርቶ ለማፍረስ ማሰቡ በራሱ መቅሰፍት አምጪ የሆነውን ቅዱስ ተቋም ነው፡፡ መገዳደር የፈለጉትም ሊገዳደሩት ከማይገባቸው ቤተ እምነት ጋር   ነው፡፡ የነኩትም የማይነካውን የእግዚአብሔር ክብር ነው፡፡ ሙከራቸውም ግዙፉን ተራራ በመርፌ ቆፍሮ ሜዳ ለማድረግ እንደመሞከር የሚቆጠር ተግባር ነው፡፡

ልብ ያለው ልብ ይበል ጆሮ ያለውም ይስማ፡፡ በእግዚአብሔር ሚዛናዊነትና ፍርድ አስተካካይነት ቅንጣት ጥርጣሬ የለኝም፡፡ የሰሞኑ የአባቶቻችንና አማንያን እንባም ሆነ በግፍ የተገደሉት ሰማዕታት ደም በከንቱ ፈሶ ከዳመና በታች እንደማይቀር ርግጠኛ ነኝ፡፡ እግዚአብሔር ትዕቢትንም ሆነ ትዕቢተኛን አይወድም፡፡ በግልም ሆነ በቡድን የሚፈፀመውን ግፍ ይመዝንና የግፉ ቁና ሲሞላ ፍርድ ይሰጣል፡፡

ዕብሪት መዘዙ ብዙ ነው፡፡ በዕብሪት የተሞላ ግለሰብም ሆነ ቡድን ሲሰናከል እንጂ በስኬት ጎዳና ሲጓዝ አልታየም፡፡ በዕብሪት የተሞላ ሁሉ ዕድሜው ለመቅሰፍት የቀረበ ነው፡፡ የፈጣሪ ቁጣ መንደድ ሲጀምር ሁሉም የፅዋውን ይጎነጫል፡፡ በሰፈረው ቁናም ይሰፈራል፡፡ “እግዚአብሔር ለግፍ መሰፈሪያ ያገለግል ዘንድ ቁና ይሰፋል” የሚለው የአበው አባባል እውነት እንጂ ተረት ነው ብለን አቅልለን የምናልፈው አይደለም፡፡ ያኔ እጃቸው በንፁሀን ደም ለታጠቡ ሁሉ ወዮላቸው፡፡ አቶ መለስ በዕብሪት ተነሳስቶ በስኳር ፋብሪካ ግንባታ ሰበብ የማይነካውንና መነካት ያልነበረበትን የዋልድባ ገዳም መነኮሳት ተንኩሰው የተቀሰፉ መሆናቸውን ማስታወሱ ብልህነት ነው፡፡ ከብረት የጠነከርን ነን ብለው በኃይላቸውም በጉልበታቸውም የተመኩ ሁሉ የፈጣሪ ፍርድ ሲሰማ ኢምንት ሆነው ስለመገኘታቸውም ማስረዳት የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም፡፡

የዘመናችን አምባገነኖች ታሪክን አገላብጠው ወደትቢያነት ከተቀየሩት መሰሎቻቸው ትምህርት አለመቅሰማቸውን ሳስብ ዘወትር ይገርመኛል፡፡ አሁን ላይ የብልፅግና መንግሥት በኦርቶዶክስ ቤተ ዕምነት ዙሪያ የሄደበት አካሄድ ለእምነቱ ተከታዮች ብቻ ሳይሆን ለሀገርም የማይበጅ ፍፁም የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ በኔ በኩል ከዚህ አካሄዱ የተረዳሁት የመሪዎቻችንን ፍፁም መሳሳት ብቻ ሳይሆን መንግሥታችን አርቆ ተመልካች አማካሪዎች ዕጥረት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ ነገረ ነገሩን ይበልጥ ግራ አጋቢ የሚያደርገው ደግሞ በቤተክርስቲያን አስተምህሮ ጥርሳቸውን ነቅለው ያደጉት እነሙሐዘ ጥበባት ዳንኤል ክብረት በቤተመንግሥቱ አካባቢ ባልጠፉበት ሁኔታ መፈፀም ያልነበረበት ይኸ ስህተት መፈፀሙ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሀገርም የዕምነት ተቋማትም ሆኑ አማኙ ሕዝብ ተረጋግቶ ከመንግሥት ጎን በመቆም ሀገር የማዘመን ተግባር ይፈፀም ዘንድ የፌደራልም ሆነ የክልል መንግሥታት አሁን ላይ እየፈፀሙት ያለውን ሀገር አውዳሚ ተግባር በመገምገም እጃቸውን በቤተ እምነቶች ውስጥ ከማሰገባት ሊቆጠቡ ይገባል፡፡ በተለይ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መሪዎችን ከዕብሪት አሰወግዶ ፈጣሪ ወደልቦናቸው ይመልሳቸው ዘንድ አባቶች ሊፀልዩላቸው ይገባል፡፡ ከጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው ቅብዐ ሀይማኖት ፖለቲካ ለማውገዝ በአባቶቻችንና በሀገር ሽማግሌዎች ብልሀት የተሞላበት ብርቱ ጥረት የተነሳ የካቲት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ ተሰርዟል፡፡

መቸም የየካቲትን ወር ስናስብ ወሩ በራሱ ብዙ ደግና መጥፎ ክስተት ያስተናገደ ወር መሆኑን የምንረሳው አይመስለኝም፡፡ የዓድዋ ድል የየካቲት ፍሬ ነው፡፡ በ1928 ዓ.ም በፋሺሽት ኢጣሊያ ጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ገዳይ ቡድኖች ጭፍጨፋ የተነሳ አዲስ አበባ 30 ሺህ ዜጎቿን ለሞት የገበረችው የካቲት 12 ቀን ነው፡፡ አይነቀነቅም ተብሎ ይታሰብ የነበረው የአፄ ኃ/ሥላሴ ዙፉን ላይመለስ መፍረስ የጀመረውም በየካቲት ወር ነው፡፡ መርዛቸውን ሲረጩብን የቆዩት የወያኔ እባቦች መፈልፈል የጀመሩትም በየካቲት ወር ነው፡፡ ከተነሳሁበት ጭብጥ ያወጣኛል እንጂ የኢትዮጵያን ታሪክ እንመርምር ካልን በየካቲት ወር ያልጠቀስኳቸው በርካታ ታሪካዊ ኩነቶች ተመዝግበዋል፡፡

ሰሞኑን በተነሳው የሃይማኖት ቀውስ የተነሳ የካቲት 5 ቀን በሚካሄደው ሰልፍ ሰበብ የየካቲት 12 ዓይነት ጭፍጨፋ እንዳይፈፀም መደረጉ የሚያስመሰግን ተግባር ነው፡፡ ያ ማለት ግን ቸግሩ ሙሉ በሙሉ ተፈትቷል ብለን የምንዘናጋበት ነው ማለት አይደለም፡፡ እንዳውም ከአሁን በኋላ በሁሉም ነገር ጠርጣሪ መሆን ነው ያለብን፡፡ በበኩሌ  የካቲት 6 ቀን 2015 ዓ.ም በቴሌቪዥን የተነገረን የባሌ ስንዴ ምርት ወደውጭ መላክ ዜና በራሱ በመንግሥት ላይ ያለንን ኩርፊያ ማለስለሻ አጀንዳ  ይሆን እንዴ? የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ የኔ ጥርጣሬ ስንዴው ተመርቶ ወደውጭ መላኩ ላይ ሳይሆን ዜናው አሁን ላይ እንዲነገር ለምን አስፈለገ? የሀገር ውስጥ የምርት አቅርቦቱ እጥረት ባለበት ሁኔታ ወደውጭ ተላከ መባሉስ ለምን በሚል አነታራኪ አጀንዳ እንድንዘፈቅ ተፈልጎ ወይም የሰሞኑን የኛን የተከፋ ልብ ለማለስለስ የፖለቲካ ቅመም የተቀመመበት የገፅታ ግንባታ የሚሉ ሀሳቦችን በአዕምሮየ አውጠንጥኛለሁ፡፡

በተረፈ ሰሞኑን ተከስቶ የነበረው ፖለቲካ አዘል የተዋሕዶ ቤተእምነት ችግር ስለመፈታቱ የአባቶችን መግለጫ ሰምተን ብንደሰትም በእብሪት ተነሳስተው ሕዝብ ላይ ተኩሰው የገደሉም ያስገደሉም ያሰሩ ያሳሰሩም የደበደቡ ያስደበደቡም ብቻ ሳይሆን ቀውሱን በመቆጣጠር ሰላም ማስፈን ያልፈለጉትም ሆኑ ሆን ብለው እሳት የለኮሱት ባለስልጣናትና ታዛዥ ወንጀል ፈፃሚ የመንግሥት ታጣቂዎች በሕግ እንዲጠየቁ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡ ያ ካልሆነና ሕግ የሚጥስ ቱባ ባለሥልጣንም ታዛዥ ታጣቂም ሕግ ሲጥሱ ካልተጠየቁ አገሪቱ አገር አጥፊ አገር እያጠፋ ተንደላቆ የሚኖርባት ጉልበተኛ ሁሉ የሚፈነጭባት እንደምትሆን አትጠራጠሩ፡፡

ለማንኛውም አገራችን አገር አጥፊ አገር እያጠፋ ተንደላቆ የሚኖርባት በመሆኑ ሰላማዊ ትግሉ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይሰማኛል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት ይታደጋትም!

ለአሁኑ አበቃሁ፡፡

የሕገ-ወጦች “ሕጋዊ” መንግሥት?

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የክሪፕቶ ሥራ ፈጣሪው የ15 ዓመት እስር ተፈረደበት

የቀድሞው የክሪፕቶከረንሲ ሥራ ፈጣሪ ተሰውሯል ከተባለ 40 ቢሊየን ዶላር...

5ኛው የኢሰመኮ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ፊልም ፌስቲቫል ተካሄደ

በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አዘጋጅነት በየዓመቱ በፈረንጆቹ ታኅሣሥ...

የንግድ ሚኒስቴር 13 ምርቶችን በመነሻ ሀገር የጥራት ማረጋገጫ (PVoC) እንዲያገኙ ወሰነ

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት፣ በሀገር...

ገዳ ባንክ ከ444 ሚሊየን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን ገለፀ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ባንኮች የተከፈለ ካፒታላቸውን በ2018 ዓ.ም...