በከተማዋ በተለያዩ ጊዜያት በተለይም በበዓላት ሰሞን ምርቶቻቸውን የሚያሸሹና አለአግባብ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን ሕገ-ወጥ ተግባር ከ95 በመቶ በላይ መቆጣጠር መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ አስታውቋል።
ይህንን መሰሉ ድርጊት በበዓላት ወቅት እንደሚባባስ ያስታወሱት የቢሮው ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ፤ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎ የተጋነነ ዋጋ ጭማሪ፣ ምርት ማሸሽና መሰል ተግባራት ይስተዋሉ እንደነበር አንስተው አሁን ላይ በተደረገ ክትትል ችግሩን ማስቀረት እንደተቻለ ተናግረዋል።
“የሕገ-ወጦች እንቅስቃሴ የቀነሰው በአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እና በሸገር ከተማ ደግሞ ምክትል ከንቲባ በበላይነት በሚመራው ሕገ-ወጥነትን ለመከላከል በጥምረት በተቋቋመ ግብረ-ኃይል የተጠናክረ ሥራ ነው” ብለዋል።
በሕገ-ወጡ ተግባር ላይ የተሰማሩት ነጋዴዎች ምርቶችን ከአዲስ አበባ በማውጣት የሸገር ከተሞች ላይ ያከማቹ እንደነበር የገለጹት ኃላፊዋ፤ አሁን ላይ በጋራ ግብረ-ኃይሉ አማካኝነት በሁለቱም ከተሞች ውስጥ የሚገኙ መጋዝኖች ስለሚፈተሹ ምርት የማሸሽ ተግባራት ከ95 በመቶ ያክል መቆጣጠር ስለመቻሉ ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የምርት አቅርቦት ችግርና ምርትን የማሸሽ ሂደት አለማጋጠሙን በማንሳት፤ የዋጋ ጭማሪን በሚመለከትም በግብርና ምርቶችና አታክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የቁም እንስሳት ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ እንደሌለ ገልጸዋል።
ከዚህ በተለየ መልኩ ግን ከውጪ የሚመጡ የኢንዱስትሪ ምርቶች ላይ በየጊዜው የዋጋ ጭማሪ እንደሚስተዋል የጠቀሱት ኃላፊዋ፤ ይህንንም ከጉምሩክ ኮሚሽን በኩል በሚወሰድ መረጃ በምን ያክል መጠን ጭማሪ እንዳሳየ የሚከታተሉበት አግባብ ስለመኖሩ ተናግረዋል።
አክለውም ነፃ ገበያ በመሆኑ በየሳምንቱ ዋጋ ከሚወጣላቸው የገበያ ማዕከላትን ጨምሮ ከቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ውጪ የምርቶችን ዋጋ መተመን እንደማይችሉ የገለጹ ሲሆን፤ ሆኖም ግን አሰራሩ ላይ በተቀመጠው አግባብ መሠረት የቁጥጥር ስርዓቱ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በመሆኑም በዓላትን መሠረት አድርጎ የሚሰሩ ሕገ-ወጥ ድርጊቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ ምርትን የማሸሽና የማስወደድ ሂደት እየቀነሰ መምጣቱን በመግለጽ፤ ሥራው አሁንም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የቢሮው ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ ተናግረዋል።
@አሐዱ
