ሪፊውጂስ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ ኡጋንዳ ከኢትዮጵያ፣ ከሶማሊያ እና ከኤርትራ ለሚመጡ አዲስ ስደተኞች የስደተኛነት መብት መስጠቷን ማቆሟን “አሳሳቢ እርምጃ” ሲል አውግዟል።
ድርጅቱ ከቀናት በፊት ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው፣ በዜግነት ላይ ብቻ ተመስርቶ ጥገኝነትን መከልከል የዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግን የሚጥስ ሲሆን፣ አዲሱ ገደብ እነዚህን ስደተኞች ሕጋዊ አጣብቂኝ ውስጥ በመክተት ለከፋ ብዝበዛና ጥቃት ይዳርጋቸዋል።
ይህ ውሳኔ ኡጋንዳ ቀደም ሲል ስደተኞችን በመቀበል ያላት ኩሩ ልማድ የሚጻረር መሆኑም ተገልጿል።
ሪፊውጂስ ኢንተርናሽናል፣ ኡጋንዳ የደረሰባት ከፍተኛ የእርዳታ ቅነሳ የጥገኝነት ሥርዓቷን ችግር ውስጥ መክተቱን አምኗል።
በተለይም ዩናይትድ ስቴትስ የጥገኝነት ጠያቂዎችን ወደ ኡጋንዳ ለመላክ ስምምነት ብትፈርምም፣ የራሷን እርዳታ መቀነሷ ለችግሩ መባባስ ምክንያት መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፣ ለዓመታት ኡጋንዳን ሲያሞግሱ የቆዩ ለጋሽ መንግሥታት አሁን ቃላቸውን ለስደተኞችም ሆነ ለአስተናጋጅ ማኅበረሰቦች በሚሰጡት ተጨባጭ ድጋፍ በማረጋገጥ፣ ኡጋንዳ የገጠማትን የገንዘብ ችግር እንዲያቀልሉ ጥሪ አቅርቧል።
