የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ኅዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በምርጫ ለመወዳደር የሚቀርቡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚያስገድደው የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ-ምግባር አዋጅ ድንጋጌ ለ7ኛው ዙር ሀገራዊ ምርጫ ተፈጻሚ እንዳይሆን ማገዱን በበጎ እንደሚመለከተው አስታወቀ።
ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የድጋፍ ፊርማ ለማሰባሰብ አስቻይ ሁኔታ አለመኖሩን በመጥቀስ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲዎች የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች መነሻ በማድረግ ከዚህ ግዴታ ተፈጻሚነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ መቆየታቸውን ባደረክኩት ክትትሎች ተገንዝቢያለሁ ብሏል።
በዚሁ መሠረት ምክር ቤቱ ኅዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎች የድጋፍ ፊርማ እንዲያሰባስቡ የሚያስገድደው ድንጋጌ ተፈጻሚነት ለ7ኛው ሀገር አቀፍ ምርጫ እንዲታገድ በመወሰን፣ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ-ምግባር ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ማጽደቁን ጠቁሟል።
ኮሚሽኑ፣ የምክር ቤቱ እርምጃ ተጨባጭ ሁኔታዎችን ያገናዘበ፣ በምርጫ የሚወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ የሰጠ እንዲሁም ምርጫው አካታችና አሳታፊ እንዲሆን ከማድረግ አንጻር አስቻይ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የምርጫ እና በሕዝብ አስተዳደር ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብቶችን ለማጠናከር አዎንታዊ አስተዋጽዖ የሚያደርግ ነው ሲል ውሳኔውን ደግፏል።
እርምጃውን በበጎ መልኩ የሚመለከተው መሆኑን የገለጸው ኢሰመኮ፣ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ግልጽ፣ ተአማኒነት ያለውና ሰብአዊ መብቶች በተሟላ ሁኔታ የተከበሩበት እንዲሆን ለማድረግ የሚረዱ አስቻይ ሁኔታዎችን የመፍጠርና የማጠናከር ጥረቶች እንዲቀጥሉ መንግሥትን ጨምሮ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪው አቅርቧል።
በህዳር 25 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው በስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሦስተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ደቀው አዋጅ ቁጥር 1397/2018፣ ቀደም ሲል የጸደቀውን አዋጅ ቁጥር 1162/2014 አንቀጽ 32(2) እና አዲስ የተጨመረውን ንዑስ አንቀጽ 8 ከሥራ ውጪ ያደርጋል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ፣ የድጋፍ ፊርማው ግዴታ ከዚህ ቀደም ለስድስተኛው ሃገራዊ ምርጫ በአዋጅ ቁጥር 1235/2014 መሠረት በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ገደቦች ምክንያት መነሳቱን አውስተዋል።
ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አማካኝነት፣ ጊዜው ውስን መሆኑና ቀጣይነት ያለው የምርጫ ዝግጅት የፊርማ አሰባሰቡን አዳጋች እንዳደረገው በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን ሲገልጹ መቆየታቸውን አስረድተዋል።
አፈ-ጉባዔው አክለውም “የድጋፍ ፊርማ ሕጉን አሁን ማስፈጸም ፓርቲዎች በምርጫው ተወዳድረው የመሳተፍ ብቃታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ስለሚፈጥር ይህንን ማስቀረት የግድ አስፈላጊ ነው”ብለዋል።
የምክር ቤት አባላትም የማሻሻያ አዋጁን ደግፈው አንደኛው አባል ማሻሻያው “ሀገሪቱን ተጠቃሚ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ” በመሆኑ “ተገቢ እና ትክክለኛ ነው” ብለዋል።
ሌላኛው ደግሞ የፊርማ አሰባሰብ “ጊዜን፣ ጉልበትን እና ከፍተኛ ትግልን የሚጠይቅ” መሆኑን አጉልቶ በማሳየት፣ ግዴታውን ማንሳቱ “ለምርጫው ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር፣ ዴሞክራሲያዊነትን የሚያሰፋ እና ለመወዳደር አቅም ለሌላቸው ፓርቲዎች ዕድል የሚሰጥ ነው” ብለዋል። አስ
