“ኢትዮጵያዊነት በቅድመ ሁኔታዎች የሚገኝ አይደለም”

Date:

ኦባንግ ሜቶ(የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

አቶ ኦባንግ ሜቶ በሰብዓዊ መብት ተሟጋችነታቸው በስፋት የሚታወቁ ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ በዛሬው የ”ኢትዮጵያዊነት” ዓምዳችን ዐሥር ጥያቄዎች ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አኳያ ለሰነዘርንላቸው አንኳር ጥያቄዎችም የሚከተሉትን ምላሾች ሰጥተውናል፡፡  

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊነት በእርሶ እይታ እንዴት ይገለጻል?

ኦባንግ፡- ኢትዮጵያዊነት የመኖራችንና የሉዓላዊነታችን መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት አማራጭ የምናስቀምጥለትና ለድርድር የምናቀርበው አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ የሚለው ቃል እንደ ሀገር የምንጠራበት ስያሜያችን ነው፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ ያለ ማንኛውም አካል ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ከመቶ ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያለባትና ተራሮችና በርካታ ነገሮችን የሚያካትት ሰፊ ግዛትን የሚሸፍን የመሬት አካል ነው፡፡ በዚህ የመሬት አካል ውስጥ የሚገኝ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡

ኢትዮጵያዊነት ማለት የእኛ የማንነታችን መገለጫ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ካርታ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም አካል ተወደደም ተጠላ ኢትዮጵያዊነትን ይጋራል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በቅድመ ሁኔታዎች የሚገኝ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያዊነት የማንደራደርበት ማንነታችን ነው፡፡ ስለዚህ በጥቅሉ ኢትዮጵያ ወይም ኢትዮጵያዊነት ማለት እኛ አብረን የምንኖርበት የራሱ ካርታ ያለው የመሬት አካል ማለት ሲኾን የማንነታችን መገለጫም ነው፡፡

ማንኛውም አካል ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው ስለተገዳደሉ፣ ጭቆና ስለነበረና ሰዎች ስለተበደሉ ወዘተ በሚሉ ምክንያቶች ኢትዮጵያዊነት ላይ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ የለበትም የሚል እምነት አለኝ፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከውበት፣ ከሀብት፣ ከምቾት ወይም ከመከራ ጋር የሚያያዝ መገለጫ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በተሰኘው ካርታ ውስጥ ሰው ኾነን በመፈጠራችን የምናገኘው ማንነታችን ነው፡፡ ለኔ ኢትዮጵያዊነት ማለት የሁላችንና የሉዓላዊነት መገለጫችን ማለት ነው፡፡

ግዮን፡- እሴቶቻችን ምን ምን ናቸው?

ኦባንግ፡- አዎ በርካታ እሴቶች አሉት፡፡ ኢትዮጵያ በርካታ ብሔረሰቦች የሚኖሩባት ሀገር ነች፡፡ በዚህም እያንዳንዱ ብሔረሰብ የራሱ እሴት አለው፡፡ የሁሉም ብሔረሰብ ጥቅል እሴት ደግሞ የሀገሪቱ እሴት ኾኖ የሚገለፅ ነው፡፡ ለምሳሌ እንደ እንጀራ፣ ቡና፣ ሻይ ወዘተ ያሉት ነገሮች የኢትዮጵያውያን የጋራ መገለጫ እሴቶቻችን ናቸው፡፡ ምግብ ስንበላ ከብበን ነው የምንበላው፣ ቡና ስንጠጣ ከጎረቤት ጋር ተጠራርተን ከብበን ነው የምንጠጣው፣ ይኽም የእኛ እሴታችን ነው፡፡ በርካታ በክልል ያልተለያዩ በአንድነት የምንገለፅባቸው እሴቶች አሉን፡፡

ለምሳሌ ቡናን ዛሬ በቢሊዮን የሚቆጠሩ የዓለም ሕዝቦች ይጠጡታል፡፡ ነገር ግን መገኛው የት ነው ከተባለ ኢትዮጵያ መኾኑ ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ያ ለኢትዮጵያውያን እሴታችን ነው፡፡ በሌላ በኩል የለቅሶ፣ የጋብቻ፣ የሠርግ ወዘተ… የመሣሠሉት ሁሉ ከአካባቢ አካባቢ ቢለያዩም በድምሩ የኹሉም ኢትዮጵያውያን እሴቶቻችን ናቸው፡፡

ግዮን፡- ይኽ ትውልድና ኢትዮጵያዊነት ተራርቀዋል?

ኦባንግ፡- አዎ ይኽ ትውልድና ኢትዮጵያዊነት ተራርቀዋል፤ እውነት ነው፡፡ የተራራቁበት ምክንያት ደግሞ ኾን ተብሎ ፖሊሲ ተቀርፆለት በተሠራበት ሥራ ምክንያት ነው፡፡ ከዓመታት በፊት ጭቆና ደርሶብናል ብለው በነፃ አውጭነት ራሳቸውን አደራጅተው የታገሉ ኃይሎች የፈጠሩት የተዛባ አሠራር ነው፡፡ እነዚህ ኃይሎች ናቸው የእነርሱን አስተሳሰብ በትውልዱ ላይ የጫኑት፡፡ የዘረኝነት፣ የኋላቀርነት፣ የበታችነትና የድንቁርና አስተሳሰባቸውን በትውልዱ ላይ ያጋቡበት፡፡ ስለዚህ ትውልዱ በጽንፈኞች የአገዛዝ ሥር ኾኖ ስላደገ ተበላሽቷል፡፡ ለምሳሌ አሁን ላይ ስለዓድዋ ድል የምናስበው በየብሔራችን ተለያይተን ነው፡፡ ያ ግን መኾን አልነበረበትም፡፡ ድሉ የተገኘው በጋራ ውጤት ነው፡፡ ገዥዎች ብሔር ብሔረሰቦች የሚል ትርክትን በመጫናቸው ትውልድ የተለያየ ማንነትን እንዲያነግብ ተደርጓል፡፡ ጠላቶቻችንም አንድነት ምን እንደኾነ ስለማያውቁት ለክፍፍላችን ሠርተዋል፡፡

ግዮን፡- በዚህ ትውልድ ውስጥ የኢትዮጵያዊነት ተግዳሮቶቹ ምን ምን ናቸው?

ኦባንግ፡- ይኽ ትውልድ በኢትዮጵያዊነቱ ላይ የተጋረጠበት ተግዳሮት ቀደም ሲል ከተሠራበት ትክክል ያልኾነ ትርክት የመጣ ነው፡፡ ለምሳሌ ይኽ ዓይነቱ የፌደራልና ክልል አወቃቀር ባይኖር ኖሮ ይኽን እሳቤ ያነገበ ትውልድ አይመጣም ነበር፡፡ ወጣቱ ትውልድ አረንጓዴ፣ ቢጫና፣ ቀይ ሰንደቅ ዓላማውን እንዳያይ ለብሔር የተሰጠ ተቀያሪ ባንዲራን አስተዋወቁት፡፡ ማንነቱንም ብሔር እንዲያደርግ አደረጉት፡፡ ይኽ ደግሞ ዛሬ ላይ ትልቅ ተግዳሮት ኾኗል፡፡ በጥቅሉ የትውልዱ ተግዳሮት የኾነው አሁን ያለው የብሔር መዋቅር ነው፡፡ ትውልዱ እሴቱን ጠብቆ መጓዝ ከቻለ ግን ተግዳሮቶቹን መሻገር ይችላል፡፡

ግዮን፡- ይኽ ትውልድ ከብሔርተኝነት መንፈስ ተላቅቆ ኢትዮጵያዊነትን መቀበል ይችላል?

ኦባንግ፡- ከብሔርተኝነት መንፈስ ለመላቀቅ የሚያስፈልገው መማርና ሰፋ አድርጎ ማሰብ ነው፡፡ ትውልዱ ከታሪክ መማር አለበት፡፡ ልጆች መደበኛ ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት ስለ ሰብዓዊነትና ኢትዮጵያዊነት መማር አለባቸው፡፡ ማንነታቸውን ማወቅ አለባቸው፡፡ “ኢትዮጵያ የምትባል ትልቅ እናት አለቻችሁ” እያልን ልጆቻችንን ማስተማር አለብን፡፡ ከዚያ ከፍ ሲልም ሰው ማለት ፍቅር፣ ኃይል፣ ሕሊና፣ ሕግ እንደኾነ ማስተማር ይጠበቅብናል፡፡ ሰው ማለት ሀገር መውደድ ማለት መኾኑን ትውልዱ እንዲረዳ ማድረግ ይኖርብናል፡፡ የኢትዮጵያን ትርጉም በትክክል ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ እንኳን ሀገር ቀርቶ ቤተሠብን በተንኮል ማስተዳደር በማይቻልበት ሁኔታ ላይ ልጆቻችንን ተንኮል ማስተማር የለብንም፡፡ ይኽን ማድረግ ካልቻልን እርስ በእርስ እየተባላን ለማኝ ኾነን መኖራችን ነው፡፡

ግዮን፡- ኢትዮጵያዊነት ስሜት ነው ወይስ ግብር?

ኦባንግ፡- ለእኔ ኢትዮጵያዊነት ስሜት ብቻ ሳይኾን ከዚያም በላይ ነው፡፡ ስሜት እኮ አንድ ቀን መጥቶ የሚጠፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከስሜት የተሻገረ የማንነት መገለጫ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ማለት ለእኔ ሕሊና ማለት ነው፡፡ “እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ በመወለዴ እዳ አለብኝ፡፡ በዚህች ሀገር ላይ ያለውን ቆሻሻ አስተሳሰብ ማፅዳት አለብኝ፡፡ ይኽችን ሀገር ከቆሰለችበት ችግር ማውጣት አለብኝ” የሚለው ስሜት በሁላችንም ውስጥ ሊፈጠር ይገባል፡፡ ሀገሪቱ ኋላቀር እንዳትኾን፣ የጨቋኖች ሀገር እንዳትኾን ለትውልዱ የማስተካከል እዳ አለብን ብዬ አስባለሁ፡፡

ግዮን፡- ማኅበራዊ ድረ ገጾች ለኢትዮጵያዊነት ያላቸው ሚና ምንድነው?

ኦባንግ፡- ቴክኖሎጂዎችን ለመልካም ነገር እየተጠቀምንባቸው አይደለም፡፡ ለምሳሌ ማኅበራዊ ሚዲያ በእኛ ሀገር ካለማው ይልቅ ያጠፋው ይበዛል፡፡ የጥላቻ ምንጭና ማዛመቻ ኾኖ እያገለገለ ነው፡፡ ዓለም በሠለጠነ መልኩ እየተጠቀመበት ሲገኝ እኛ ለ21ኛው ክፍለ ዘመን በማይመጥኑ ንትርኮች ጥላቻን ስንዘራበት እንውላለን፡፡ መሬታችንን በበሬ እያረስን፣ እቃዎችን በአህያ እያጓጓዝን፣ በፌስቡክ ጥላቻ እየነዛን ጎረቤቶቻችንን መግደል ለእኛ ስለማይመጥነን ነቅተን ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለመልካም ተግባር መጠቀም ይኖርብናል፡፡

ግዮን፡- ወጣቱ ትውልድ ኢትዮጵያዊነትን ይዞ እንዲቀጥል ምን መልዕክት ያስተላልፋሉ?

ኦባንግ፡- ወጣቶቹ የአባቶቻቸው ውጤት ስለኾኑ የኋላ ታሪካቸውን ፈትሸው አንድነቷ ለተጠበቀች ኢትዮጵያ መሥራት አለባቸው፡፡ ዘረኝነትንና ጽንፈኝነትን አስወግደው ስለኢትዮጵያዊነት ማሰብ አለባቸው፡፡ በጥቅሉ ለዚህ ትውልድ ማስተላለፍ የምፈልገው “አሁን የሚታየውን ችግር ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ የለባችሁም፡፡ ችግራችሁን ዛሬ ላይ ተነጋግራችሁ ፈታችሁ የኢትዮጵያን ቀጣይነት ማረጋገጥ አለባችሁ” የሚል ነው፡፡ ራሳቸውን ከሌላው ዓለም የሚያወዳድሩበት ነገር ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ በ21ኛው ክፍለ ዘመን እያንዳንዱ ዜጋ “ዜጋ” እንጂ ብሔር እንዳይኾን መሥራት አለባቸው፡፡ ሀገራቸውን በ21ኛው ክፍለ ዘመን በብሔር ከምትተዳደርበት የውርደት አረንቋ ማውጣት ስላለባቸው ለዚያ የሚመጥን አስተሳሰብ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህ ዘመን በብሔርተኝነት መደራጀት ድንቁርና ስለኾነ ትውልዱ ከዚህ ነፃ ሊኾን ይገባል እላለሁ፡፡

ግዮን፡- የኢትዮጵያን ታሪካዊ ቅርሶች በዓለም ለማስተዋወቅና ክብራቸውን ለመጠበቅ ምን ይደረግ ይላሉ? ሓላፊነቱንስ የማን ነው?

ኦባንግ፡- ከመቶ ሃያ ዓመታት በፊት በምኒልክ ዘመን የነበረው ትውልድ የሀገርን ምንነት ስለተረዳ ዓድዋ ላይ ዘምቶ ነፃነቱን አስከብሯል፡፡ የአሁኑ ትውልድም የሀገርን ትርጉም በቅጡ ሊረዳው ይገባል፡፡ ትውልዱ ከማንም ምንም ሳይጠብቅ ሀገሩን እራሱ መለወጥ ይኖርበታል፡፡ መንግሥትም ሀገሪቱ ያሏትን ቅርሶች መጠበቅ አለበት፡፡ ቅርሶችና እሴቶችን መጠበቅ የሁሉም ዜጋ ሥራ ነው፡፡

ግዮን፡- አባቶቻችን ለዚህ ሀገር በክብር መቆየት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው ለተከታዩ ትውልድ አስተላልፈዋል፡፡ ይሄ ትውልድስ ለቀጣዩ ለማስተላለፍ ምን ይጠበቅበታል? ምን ያድርግ? ኦባንግ፡- ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ሁሉ ነገሯን መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ አባቶቻችን ሀገር ሠርተው ለዚህ ትውልድ አስረክበዋል፡፡ ይኽ ትውልድ ደግሞ አባቶቹ ተሠውተው ያቆዩዋትን ሀገር በአግባቡ ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማቆየት አለበት፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...