በኢትዮጵያ የዛሬ ሁለንተና ውስጥ የ‹‹ሰላም እና ደህንነት›› ጉዳይ ዐቢይ እና አንገብጋቢ አጀንዳ ኾኖ መቀጠሉ እጅግ ያሳዛናል፡፡ እውነታው ግን ከዚህ አንዲት ጋት እንኳን ፈቅ ሊል አልቻለም፡፡ የአንድ የምርጫ ዘመን ዕድሜን በሥልጣን ያሳለፈው የዐቢይ አሕመድ መንግሥትም በሀገር እና በዜጎች አማን ውሎ ማደር ‹‹ምንግዴ›› መኾኑን አሁንም እያሳየ ነው፡፡ ከሕዝቦች የመኖር ኅላዌ የሚልቅ እንዴት ያለ ጉዳይ ጠምዶት እንደኾነ ባይታወቅም፣ ከርዕሰ መዲናችን አዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ሳይቀር ከዝንጋኤው ለአፍታ እንኳን ሊያናጥቡት አለመሞከራቸው የሚያደንቅ ነው፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ዕለት ዕለት እየተባባሰ የመጣው የንጹሐን ዜጎች መፈናቀል፣ እገታ፣ አፈና እና ግድያ ክልሉን ‹‹እመራለሁ›› የሚለው አካልም ኾነ ማዕከላዊ መንግሥቱ ዶሮ የጮኸ ያህል እንኳን ደንገጥ ብለው ሕግ እንዲያስከብሩም ኾነ መግለጫ እንዲሰጡ የሚነቀንቃቸው አለመኾኑ፣ ‹‹ሀገሩ ምን እንዲኾን ነው የፈለጉት?›› የሚል መራራም ተላላም ጥያቄ ከመጠየቅ ያለፈ ሌላ ምርምር ውስጥ ይከታል፡፡
አሁን ባለው ተጨባጭ እውነታ በወለጋ ሁለት ዞኖች፣ በምዕራብ፣ ምሥራቅ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ በሱሉልታ ወረዳ ቦቁ ጎልባ፤ ኤካ ጋጆና፤ ቦቁ ሁሩታ እና ሞዬ ጋጆ በሚባሉ ቀበሌዎች፤ በዝዋይ፣ መቂ፣ ሰዴን ሶዶ ወረዳ፣ የአዳ ባርጋ ወረዳ፣ ኩዩ ወረዳ፣ ገርበ ጉራቻ፣ ዋጫሌ ወረዳ፣ በአዳማ፣ በመተሀራ፣ በምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ በአርሲ ዞን፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኙ ቦታዎች ንጹሐን ዜጎች እየታገቱ እና እየተገደሉ፣ የትራንስፖርት እና እቃ ማጓጓዣ መኪና ሹፌሮች እየታፈኑ እና በርካታ የጸጥታ ሥጋት የሆኑ ተግባራት እየተፈጸሙ፣ የዜጎች ሕልውና ፈተና ላይ ወድቋል ፤ ሀገሪቷም የምድር ሲኦል ወደመኾን እየተንደረደረች ነው፡፡ ይኽ ኹሉ አደጋ በሕዝቦች ሕልውና ላይ ቢከሰትም የፌደራል መንግሥቱ ግን ከባባድ የጦር መሣሪያዎቹን እና ኅልቆ መሣፍርት ወታደሮቹን ሌላ ሥፍራ ካሰማራ ወራት እየተቆጠሩ ነው፡፡
በተደጋጋሚ እንደሚገለጸው፣ የመንግሥት በጣም ትንሽ የሚባለው ኃላፊነት የሀገርን ሰላም እና ደኅንነት ማስጠበቅ ቢኾንም፣ አገዛዙ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጊዜ ጊዜ፣ ከዓመት ዓመት በሁሉም ሥፍራ በሰላም ወጥቶ የመግባት፣ ተንቀሳቅሶ የመሥራት፣ ያለሰቀቀን የመኖር እና የደኅንነቱ የመጠበቅ መብቱ በዜሮ እየተባዛ በገዛ ሀገሩ ባይተዋር ኾኖ እንዲኖር ከመፍረድ ውጪ ‹‹መንግሥት›› ሊኾነው አልወደደም፡፡ ይኽ የሚያሳየው፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከአንድ ሳምንት በፊት በመግለጫው እንዳስታወቀው፣ መንግሥት ‹‹መንግሥታዊ ግዴታውን ለመወጣት አቅም ማጣቱን›› አልያም ‹‹ግዴለሽነት›› መኾኑን ነው፡፡ በርግጥም ኢዜማ እንዳለው፣ የመንግሥት ችግር የአቅም ማጣት ቢኾን ያለበትን ሁኔታ በግልጽ አሳውቆ፤ ሕዝብን በማስተባበር በዘመቻ እንዲህ ያለ ተግባር የሚፈጽሙ የሽብር ቡድኖችን መደምሰስ በቻለ ነበር፡፡ ኾኖም መንግሥት ይኽን ከማድረግ ይልቅ በየጊዜው አምታች መግለጫዎችን በመሥጠት እና ከእውነታው ጋር ሕብረት የሌላቸው ምናባዊ ልፈፋዎችን በመደስኮር የግፉ ተባባሪ መኾንን መርጧል፡፡
ኢትዮጵያ ዛሬ ላይ ከአዲስ አበባ አዳማ ደርሶ መመለስ የመከራ አዙሪት እንደመርገጥ ኾኖ የዕለት ጉርሳቸውን ሥዕል ሥለው የሚደፍኑት እንደ ሙሉጌታ ገብረኪዳን ያሉ ምሥኪኖች ሳይቀር ወጥተው የሚቀሩባት የጨካኞች ሀገር ኾናለች፡፡ ይኽ ግን ‹‹እንዴት›› የሚያስብለው አንድም የመንግሥት ባለሥልጣንም ኾነ ‹‹የሕዝብ ተወካይ ነኝ›› የሚል ግለሰብ የለም፡፡ አልፎ አልፎ እንደሚሰማውም የመከራው ገፈት ትልልቆቹን ባለሥልጣናት ሳይቀር ሲጎበኝ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብን ከፍሎ ‹‹ነጻ መውጣት››ን ኹነኛ መንገድ አድርገው የወሰዱበት ሀገር ኾኖም ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ግን ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያውያን ዕለት ዕለት ገሐነም የመኾኗ እውነት ለጥቂት ተምኔታውያን የብልጽግና መንግሥት ሸሪኮች ‹‹ገነት›› ኾና እንደማትሰነብት ለመናገር ሶሻሊሰቱን ጠንቋይ መኾን አይጠይቅም የሚለው ሳምንታዊ መልዕክታችን ነው፡፡
