ኢትዮጵያ ምጥ ላይ ነች

Date:

ተገኑ ጸጋዬ

በአሁኑ ሰዓት አገራችን ላይ እየተደረገ ያለው ነገር ምንድን ነው? ሀገሪቱ ያለምንም ፋታ በተለያዩ ችግሮች እየታመሰች ነው፡፡ ለችግሩቹ ዋና መንስኤ ደግሞ ቋንቋን መሠረት ያደረገ የፌደራል ስርአት አወቃቀር መተግበሯ መሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ከሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ እንደምንረዳው ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፌዳራሊዝም አወቃቀር በጥንቃቄና በብልሀት ካልተገበረ መድሃኒት ተብሎ የሚታዘዘው እንክብል መርዝ የሚሆንበት እድል ሰፊ ነው፡፡ እንደምሳሌ የቀድሞዋ የሶቭየት ህብረት መፈራረስ በትክክል የሚሳየው ይህንኑ ነው፡፡ ለምን ታዲያ ሀገራችን ላይ ይህንን ጉዳይ መተግባር አስፈለገ? ይህ የፌደራሊዝም አወቃቀር ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅም ብዙ ምሁራን ሲናገሩ ሰሚ አጥተጠው ቀርተዋል፡፡ እንዳውም በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ስለዚህ ጉዳይ እንዲህ ነበር ያሉት “ፌደራላዊውን ስርአት ህጋዊ ያደረገው ህገ መንግስት ከመተባበር ይልቅ መበታተንን ከመቀራረብ መራራቅን ከውህደት ይልቅ መለያየትን ስለሚያበረታታ ህገ መንግስት ሳይሆን ህገ አራዊት ነው” ብለው ነበር፡፡

ይህ የፌደራሊዝም አወቃቀር ብዙ ችግሮች ያሉበት መሆኑን ለማሳያ ያህል የብሄሮች ድንበር አከላለል አዋጅ ቁጥር 1/1985 በፖለቲካ ውሳኔ መደረጉ ግጭቶች ያለማቋረጥ እንዲቀጥሉ ማድረጉን መጥቀስ እንችላለን፡፡ መንግሥት እነዚህን ችግሮች መፍታት ባለመቻሉ ልማት የሚባለውን ከወሬ በዘለለ ሊተገብር አልቻለም፡፡ ሚካኤል ጆንሰን የሚባል ማህበረሰብ አጥኚ አንድ ጽሁፉ ላይ እንዲ ይለናል “ልማት በየትም አለም የተቆጣን ህዝብ ልብ የማለዘብ ልዩ ብርታት እንዳለው ጃፓንን ማስተዋል በቂ ነው”፡፡ እኛ አገር በተቃራኒው በብሔሮች መካከል የድንበር እና የሀብት ሽሚያ በመጧጧፉ ሀገሪቱ በሰላም እጦት ላይ ትገኛለች፡፡ ግጭቱ በዚህ አላቆመም፡፡ አሁን ደግሞ ፊቱን አዙሮ በታላቋ ቤተክርስቲያን ሃይማኖትን በብሔር ለመከፋፈል የታቀደና የተቀናጀ ስራ ተጀምሯል፡፡

ብዙዎች የሚመሰክሩላት ቅድስት ቤተክርስቲያን ከሺህ ዘመን በላይ ያስቆጠረ የራሷ ቀኖናና እና ዶግማ ብቻ ሳይሆን በጣም ጥርት ያለ አስተዳደሪያዊ መርሆች ያሏት በሀገር ጉዳይ የማትደራደር ግጭትን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ለህዝብ ሰላም ለህዝብ ማረፊያ የሆነች ትልቅ ተቋም ነች፡፡ እንግዲህ በቤተክርስቲያን ቀኖና መሰረት ቅዱስ ፓትሪያሪክ በቤተክርስቲያን ከተሾመ በኋላ ሌላ ፓትሪያሪክ የሚሾመው የቀድሞ በሞት ከተለዩ ነው፡፡ የኢህአዲግ መንግስት ይህንን የነበረ ህግ በመሻር የቀድሞ ፓትሪያሪክ እያሉ የራሱን ፓትሪያሪክ በመሾም ቤተክርስቲያንን በብሔር በሟቧደን ሲያተራምሳት ቆይቷል፡፡ የተሾሙትን አዲስ ፓትሪያሪክ ህዝቡ ፖለቲከኛ አድርጎ ስለሚያያቸው ተቀባይነታቸውም አነስተኛ ነበር፡፡ ፓትሪያሪኩ ከሚታሙባቸው ነገሮች መሀከል የካህናት ምድባቸው ላይ የየራሳቸውን ብሔር ላይ ትኩረት ማድረጋቸውና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ተቃውሞ ወቅት ከታጣቂ ለመሸሽ ወደ ቅድስተ ማርያም የተጣሉትን ወጣቶች አሳልፈው መስጠታቸውና ሌሎች የገንዘብ ጉዳዮች ተደምረው ተቀባይነታቸው ላይ ተጽኖ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ በመጨረሻም በሞት ከዚህ አለም ተለይተዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ሌላ ፓትሪያሪክ ለመሾም ከተደረገ የውስጥ ሽኩቻ በኋላ አዲስ ፓትሪያሪክ ተሾመ፡፡ የቀድሞ ፓትሪያሪክ ከስደት መጥተው በሞት እስከተለዩበት ድረስ በመተጋገዝ እያገለገሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ የኢህአዲግ በቤተክርስቲያን ውስጥ በጥብጦት የሄደው የብሔር እርሾ ኩፍ አለና ለመጋገር ዝግጅት ላይ ነው፡፡ አሁን የሚቀረው እሳቱን ማንደድና ምጣዱን ማጋል ብቻ ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ሁሉንም በእኩል አይን የምታይ ሆኖ ሳለ በእኛ ቋንቋ አልተሰበከም ብሎ ተገነጠልኩ የሚል ሲኖዶስ ከዚህ መገንጠል የሚሰጠው ልዩ ጥቅም ምንድን ነው ከማፍረስ በስተቀር በሀቅ ለመናገር የስልጣን ፍላጎት ለማርካት እና የገንዘብ ጥቅም ከማግኘት በስተቀር በመንፈሳዊ እይታ ኪሳራው አመዝኖ ይታያል፡፡

እስቲ ከዚህ በፊት ቤተክርስቲያን ገጥሟት የነበረው ችግር በውይይት ፈታ ሰርጎ ገቦችን በውግዘት እንዴት እንዳሰናበተቻቸው እንመልከት፡፡

ከዚህ በፊት በ34 ዓ.ም ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ በግለሰብ ደረጃ ክርስትናን መቀበሉ ይታወቃል፡፡ በሀገር ደረጃ ክርስትናን የተቀበለችው ግን ታላቁ የነቂያን ጉባኤ በኋላ በ328 ዓ.ም ነው፡፡ በአለም ላይ በመንግስት ደረጃ ክርስትናን ከተቀበሉት ሀገሮች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ነች የተቀሩት ሮማ፣ ግሪክ፣ አርመኒያ ናቸው፡፡ እስከዛሬ በክርስትና ጉዳይ ከተደረጉ ታላላቅ ጉባኤዎች ወስጥ በ325 ዓ.ም የተደረገው የኒቂያ ጉበኤ የሚስተካከለው የለም ይህ 317 ሊቃውንት የተሳተፉበት የኒቃያ ጉባኤ ከፍተኛ ውሳኔ አስተላልፎ ተጠናቋል፡፡

ከኒቂያ ጉባኤ አጀንዳዎች ውስጥ ዋነናው አርዮስ የሚባለው ሊቀ ይዞት የመጣው አዲስ ሀሳብ ነበር እርሱም ኢየሱስ ሰው ነው የአምላክ ክብር አይገባውም የሚል ነበር፡፡ ሊቃውንቶቹ ብዙ ከተመካከሩ በኋላ ግብጽን ወክሎ የመጣው አትናቲሞስ የሚባል ሊቅ አምላክ ሰው ሆነ ሰውም አምላክ ሆነ መንፈስ ቅዱስ ከስጋ ተዋህዶ ኢየሱስ ተወለደ አለምን ሊያድን አንድያ ልጁን ሰጥቶናል ብለው ባቀረቡት ሀሳብ አሪዮስ ተሸንፎ በጉባኤው ተወገዘ፡፡ ውግዘ ከመአሪዮስ የሚባለው ቢዚህ ምክንያት ነው፡፡ እንግዲህ ታሪክ እንደሚነግረን ጉባኤው ተጨማሪ ጉዳዮች ተመልክቶ ተጠናቋል፡፡

እንግዲህ ከዚህ ሀሳብ ስንነሳ አሁን ሀገራችን ላይ ያለው የሀይማኖት ጉዳይ ለምን በሰላም መፍታት አልተቻለም ብለን እንድንጠይቅ ያደርገናል፡፡

መንግስት ሀይማኖት ውስጥ እጄን አላስገባም ቢልም ቀደም ሲል እንደተገለጸው እጁ እንዳለበት ብዙ ማሳያዎች አሉ፡፡ ምክንያቱም አዲስ ነኝ የሚለው ሲኖዶስ በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፌደራሊዝም አወቃቀር ለመተግበር መነሳቱ የፖለቲካ ይዞታ ያለው መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል፡፡ እንግዲህ ይህ መርዝ የሆነው የፌደራሊዝም ስርአት መሻሻል እስካልተደረገለት ድረስ   ከዚህ ችግር ለመውጣት ምፅአት መጠብቅ ሊኖርብ ነው፡፡

በሌሎች ሀገሮች እንደተስተዋለው ታምቀው የነበሩ ቅሬታዎች በማህበራዊ መነቃቃት (Social Empowerment) ምክንያት የመፈንዳት ዝንባሌ ይኖራቸዋል፡፡ በጣም አደገኛ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት የቋንቋ ቡድኖች የራሳቸው አስተዳደር የራሳቸውን መንግስት ተቋማት የራሳቸውን ፖሊሳዊ ሀይልና የሚሊሺያ ሰራዊት ባለቤት ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ተደማምረው ያለፉ ታሪካዊ ቅራኔዎችን ቀስቅሰው ጥያቄ የሚጭሩት ጥያቄው ደግሞ ወደ ግጭት ያመራሉ፡፡ 

ይህ ጉዳይ በዚህ ከቀጠለ ምን አይነት ሀገር ትሆናለች ብለን ስንገምት ደግሞ ሁሉም በረሀብ በድህነት ግፊት ወደ እየራሱ ቀዬ የሚሮጥባት እና የሚቀራመታት ፍርስርሷ የወጣ ሀገር ትሆናች ይህን ግጭት ማስተካከል እና ወደ በጎ መለወጥ የብልህ መሪዎች ተግባር ነው፡፡ ግጭቱን በሳይንሳዊ መንግድ ማብራራት ደግሞ የሙህራን ድርሻ ነበረ እንዳለመታደል ደግሞ የኛዎቹ ምሁራን ብሔራቸውን ውስጥ ተሸጉጠዋል፡፡

ለመሆኑ መንግስት መፍትሔ አጥቶ ነው ወይስ ግጭቱን ይፈልገዋል? ይህ ጉዳይ የአብዛኛው ህዝብ ጥያቄ ነው የአቅም ማጣት እንዳልሆነ ግን መገመት አይከብድም ለምሳሌ ሕገ መንግሥቱ ላይ መጠነኛ መሻሻል ቢያደርግ ሌሎች ሀገሮች እንዳደረጉት ቅራኔውን ዜሮ ባያደርገውም እንደሚቀንስም እሙን ነው፡፡ መንግስት ግን ህገ መንገስቱ ከሚነካ ሞቴን እመርጣለሁ ብሏል፡፡ እስከመቼ?

ከፍ ብለን በጨረፍታ እንዳየነው ኢትዮጵያ አሁንም የምጥ ጣር ላይ ትገኛለች፡፡ እንደሚታወቀው ከወራት በፊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያም ውስጥ የተፈጠው ክፍፍል የእምነት ተከታዮችን ብቻ ሳይሆን ለቤተክርስቲያኗ ክብር ባላቸው ወገኖች ጭምር ቅር ያሰኘ ድርጊት ተፈጽሟል፡፡ ምዕመኑ ያለው ጉልበት ጸሎት ብቻ ስለሆነ ተግቶ እየፀለየ ይገኛል በዚህ ህዝቡን ሰቅዞ በሀዘን ስሜት ውስጥ ባለት ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጣልቃ በመግባት የሚመለከታቸውን አካላት በማነጋገር መፍትሄ ለማምጣት እየሰሩ እንደሆነ ነገሩን ውይይቱ እንደሚቀጥልም ተስፋ ሰጪ እንደሆነ አበሰሩልን፡፡ ልብ አድርጉ ውዝግቡ እንደተጀመረ እነዚህ አካላት ያለምንም ጣልቃ ገብነት ችግሮቻቸውን እራሳቸው እንዲፈቱ ሀሳብ አቅርበው ነበር እውነት ለመነጋገር ይህን ንግግራቸውን በበጎ ያልተመለከቱት ምዕመናን ከፍተኛ ቁጥር ነበራቸው እንደምክንያት የሚያቀርቡት ደግሞ እነዚህ አንገነጠላለን የሚሉ አካላት በመንግስት ታጣቂ ጥበቃ የሚደረግላቸው በሆነ አካል አይዞህ ባይነት የሚንቀሳቀሱ ከመሆናቸው በተጨማሪ የሚጠይቁት ጉዳይ የቤተክርስቲያኗን ቀኖና የሚጥስና ጠቅላላ ትኩረቱ የሀብት ክፍፍል ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ብዙሃን ህዝብ አሳዝኗል በውይይታቸውም ላይ ከተጠየቁት ጥያቄ ውስጥ አቡነ ሳሪዮስ ያቀረቡት ጥያቄ እንዲህ ይላል፡፡

‹‹ቤታችን ታሽጓል፣ ደመወዛችን ታግቷል›› ለዚህ ጥያቄ አቡነ ኤርምያስ ሲመልሱ እናንተንስ ገዝተን የለም እንዴ? ይህን ትንሹን ነገር ታነሱታላችሁ መቼም ተጋጭተናል ደመወዝ ከማገድ ቤት ከማሸግ በበለጠ እናንተን ገዝተን ለይተናል መንፈሳዊ አገልግሎት ጭምር እንዳታገኙ ብለናል እኮ፡፡ እኔም ከቀኖናው ስወጣ ማንም ሳይሆን ቀኖናው ያግደኛል ብለው መልስ ሰጡ፡፡

ከዚህ ቁምነገር የምንረዳው ቤተክርስቲያኗ ለሺ ዘመን ከምትተዳደርበት ህግና ቆኖና ውጭ በማንም ጣልቃ ገብነት የማይፈታ መሆኑን በተለይ ደግሞ መንፈሳዊነት በጎደለው የአመራር ጥበብ ይህን ትልቅ ችግር ለመፍታት መሞከር አደገኝነቱ ያመዝናል እንኳን ወገንተኝነቱ በግልጽ እየታየ ከጥንት ጀምሮ በቤተክርስቲያን ላይ አንዳንድ ችግሮች ቢከሰቱም እንዲህ አይነት ጣልቃ ገብነት ተከስቶ የሚያቅ አይመስለኝም  እንዳውም ታላቁ መጽሀፍ እንደሚለው ማንም በድፍረት በተቀባ ሰው ላይ እጁን አያነሳም፡፡ ለዚህ ነው አቤሶሎም ዳዊትን ሊገድለው ቢፈልግም የተቀባ ስለሆነ ከልብሱ ላይ ጨርቅ ቆርጦ ከመውሰድ ውጪ የተቀባውን ንጉስ መግደል እንደሚያስቀስፈው ያውቅ ነበር በአሁኑ ሰዓት ይህ ከእግዚአብሔር በራቅን ቁጥር የሚመጣውን መንፈሳዊ ድርቀት ቤተክርስቲያኗ ውስጥ ገብቶ እያመሳት ይገኛል፡፡

አሁን ደግሞ እንደጲላጦስ ከደሙ ንጹህ ነኝ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስቴር እንደገና ሁለቱን ቡድኖች ለማስታረቅ በመሀላቸው ተገኝተው የጲላጦስ ድርጊት ተገቢ አይደለም ጲላጦስ ጉዳዩ የሚመለከተው ሆኖ ሳላ እራሱን ነጻ ማድረጉን ኮንነዋል፡፡ እንደውም ስለ እውነት በተነገረው ጉዳይ እውነት ከዚህ የለችም እውነት ከስፍራዋ ነው ያለችው ብለዋል፡፡ የት እንዳለች ግን አልተናገሩም፡፡ አባቶችም አልጠየቁም እኛማ የት አግኝተናቸው  በውይይቱ ላይ ከአንድ አባት የተሰነዘረ ጥያቄ ነበር፡፡ እኛ ቀደም ብለን ደብዳቤ ለእርስዎ አቅርበን ነበር የሚል ጠቅላዩ ሲመለሱ ከባልደረቦቼ ጋር መክረበታለሁ መልሱ ግን ይቆይ የሚል መንፈስ ያለው መልስ ሰጥተዋል፡፡ አጥጋቢ መልስ ያጡት አባት ለጠቅላዩ እኔ በቃኝ ጡረታ ልውጣ ብለው ለጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ ግን በጣም አስደንጋጭና አስገራሚ ነበር ጠቅላይ ሚኒስተሩ እንዲህ ነበር ያሉት ስንት የጠፋ ነብስ እያለ ስንት የጠፉ በጎች እያሉ እንዴት ጡረታ ልውጣ ይላሉ? ቤተክርስቲያን ችግሮቻችን በጋራ እንፍታ ነው ያለችው ወርቃማው ነገር ቤተክርስቲያን በሁሉም ቋንቋ ብታስተምር እናንተም ደስ ይላችኋል ይሉና ይቀጥላሉ የምን ሽሽት ነው አይሽሹ አሏቸውና ሲቀጥሉ እኔ ባለኝ የሩቅ እውቀት እርስዎ ኦረዲ ሞተዋል ተሳሳትኩ ብለው ይቅርታ ጠይቀዋል እኮ ብለዋቸው እርፍ፡፡

“ከፀሀይ በታች ያየሁት ክፉ ነገር አለ እርሱም ከገዢ የሚወጣ ስህተት ነው” (መጽሐፈ መክብብ  10፡5)

በዚህ ሁሉ ውዝግብ መሀል በየቦታው በካሀንነታቸውና በብሔራቸው ምክንያት ቁጥራቸው በርካታ ሰዎች ቤት ያለምንም ማስጠንቀቂያ እየፈረሰ ነው ህዝቡ እንደሆነ ማቄ ክብሬ ፤ሀዘኔ ጉልበቴ ፤እንባዬ ሀይሌ፣ ጾሜ ሰልፍ፣ ጸሎትም ድሌ ነው ብሎ የለተለት ተግባር አድርጎታል፡፡

መንፈሳዊ ድርቀት ያለባቸው ሸምጋዮች ግን ነገሩን ከማባባስ የዘለለ ጠብ የሚያደርጉት ነገር እንደሌለ እያሳዩን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን ለሺ ዘመን ባስቆጠሩ ቀኖናዋ ችግሯን እንድትፈታ የዘወትር ጸሎት ያሻናል፡፡

‹‹ኢየሱስም ወደ ቤተመቅደስ ውስጥ ገባና በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ሁሉ አወጣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የእርግብ ሻጮችንም ወንበሮች ገለበጠና ቤቴ የፀሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፏል እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው›› (ማቴዎስ 21፡12)

ሌላው ሸገር ፕሮጀክት በሚል ሽፋን የቤት ማፍረስ ስራ በዘመቻ የጀመረው መንግስት ለህብረተሰቡ ጊዚያዊ መጠለያ እንኳን ሳያዘጋጅ ህዝቡን ሜዳ ላይ እየበተነ ነው፡፡ በቅርቡ እንኳን ለብዙ ህዝብ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይሰጡ የነበሩ 2 ትልልቅ የህዝብ መዝናኛ ቤቶች በቦሌ አካባቢ ፈርሰዋል፡፡ እነዚህ የህዝብ መገልገያዎች ለህዝቡ ከሚሰጡት መጠነ ሰፊ ጠቀሜታ በተጨማሪ በርካታ ሰራኞች በስሩ የሚተዳደሩበት ትልቅ ድርጅት ነበር፡፡ ባለስልጣናቱ ግን የመሬት መቀራመት አባዜአቸው ስላልለቀቃቸው እያነፈነፉ መሬቱን ወደ ግል ይዞታ ማዞር ሰበብ ድሃውን ህብረተሰብ ለበለጠ ችግር ዳርገውታል፡፡

ሌላው በቦረና ዞን የተከሰተው አሰቃቂ ረሀብ የሀገሪቱ ዋና ችግር ነው፡፡ ይህ ረሀብ በመንግስት ባለስልጣኖች ቸልተኝነት ከፍተኛ ጉዳት ካደረሰ በኋላ በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች በተደረገው የመረጃ ለውውጥና በህብረተሰቡ ቀና ትብብር ጭምር መጠነኛ ድጋፍ ማድረግ ተችሏል፡፡ ከሁሉ በላይ የሚያስገርመው ግን ይህ ከፍተኛ ረሀብ በተከሰተበት ወቅት በሀገር ውስጥ የተመረተውን ስንዴ ለወጪ ገበያ መቅረቡ እውነትም ኢትዮጵያን የሚመሯት ኢትዮጵያውያን እንዳልሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ መንግሥት ያቀረበው ምክንያት ደግሞ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ ነው፡፡ ጎበዝ የሚያስረዳኝ ካለ ለመረዳት ዝግጁ ነኝ ለመሆኑ ከውጭ ምንዛሬ እና ከሰው ህይወት የትኛው ይቀድማል? እዚህ ድረስ ለወገኑ ክብር ለሌለው መንግስት ለህዝቡ ምን እንዲያደርግ ይጠበቃል ? ህዝቡ ካለቀ በኋላስ ማንን ሊመሩ ነው የሚቀመጡት?

እኔ አሁን የሚመስለኝ መሪዎቹ በራሳቸው ሀሳብ በራሳቸው የአስተዳደር እውቀት ሀገሪቷን እንደማያስተዳድሯት ነው ሀገሪቷን የሚስተዳድሯት ከሆነ አካል በሚመጣላቸው ትእዛዝ እና መመሪያ ነው፡፡ እንደማሳያ ባለፉት ጥቂት አመታት በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው የእርስ በእርስ ግጭት ብዙ ህይወት እና ንብረት እንደወደመ የሚታወስ ነው፡፡ ለመሆኑ የዚህ እርስ በእርስ ጦርነት የማን ፍላጎት ነበር ለህዝቡ የሚሰጠው ፋይዳስ ምንድን ነው? ሱዳን ድንበራችን ጥሳ ወራን ሉአላዊነታችን ተደፍሮ መልስ ሳንሰጥ በዜሮ ባጀት እርስ በእርስ በጦርነት የሚያጨርሰን የማንን ፍላጎት ለማሟላት ነው? መንግስትስ በማን አስገዳጅነት ነው በውጭ ምንዛሬ እጥረት የምትናጠው ሀገር ጦርነቱን ያለምንም ማቅማማት የተሳተፈችው? ከጦርነቱ ሁለቱ ተፋላሚዎች ከንብረት እና ከሰው ህይወት መጥፋት በስተቀር ምን ያተርፋሉ? ብለን ስንጠይቅ መልሱ ምንም ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ እልቂት በኋላ አይኗን ከኢትዮጵያ ላይ ነቅላ ማታውቀው አሜሪካ እንደማሀል ዳኛ ፊሽካዋን ነፍታ ተፋላሚዎቹ ደብብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ተገናኝነተው እርቅ እንዲያደርጉ ቀጭን ትእዛዝ አስተላልፋለች፡፡ ወገኖቼ ከዚህ ምን ትረዳላችሁ እውነት የእነዚህ ወገኖች መታረቅ ካሳሰባት ከጦርነቱ በፊት ልታደርገው ትችል ነበር፡፡

አሁን እኮ የኢትዮጵያን ምጥ ያበረታው ሀገር ውስጥ ያለው አጥፊ ሀይል በውጭ ሀይሎች ድጋፍና በሚሰጠው መመሪያ በእቅድ እየፈጸመ መገኘቱ ነው፡፡ እንደምታስታውሱት በቤንሻንጉል የተደረገው ዘግናኝ ጭፍጨፋ በእቅድ የተነደፈ እንደሆነና በዘር ላይ መሰረት ያደረገ እንደነበረ የሰብአዊ መብት ተሟጓች ድርጅቾች በተለያዩ ጊዜ በሰጡት መግለጫ አስተውቀዋል፡፡ አሁን ደግሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡ ምን አይነት መመሪያ ሰጥተው እንደሚመለሱ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ሁኔታው ግን ያው የፈረደበት የኢኮኖሚ ችግራችን አስታኮ እጅ ለመጠምዘዝ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ግን እስከ መቼ ነው ይህን ቁልቁለት መንገድ ላይ ሆነን የምንዘልቀው?

ለመሆኑ ከሌሎች ሀገሮች ምን እንማራለን? ከዓመታት በፊት በኢኮኖሚ አቅሟ ወታደራዊ ጉልበቷ አነስተኛ የነበረችው ደብብ ኮሪያ አሁን የት ላይ ደርሳለች? ታሪክ እንደሚነግረን የኢትዮጵያ መንግስት የዚህ ደካማ ሀገር በወቅቱ የኢኮኖሚ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን ወታደረዊ ድጋፍ አድርጓል፡፡ ባይገርማችሁ በዛን ዘመን የኢትዮጵያ የነብስ ወከፍ ገቢ በወር 280 ዶላር ሲሆን የኮርያ ደግሞ 80 ዶላር አካባቢ ነበር አሁን የእኛ በውል ባይታወቅም የኮርያ የነብስ ወከፍ ገቢ 30,000 ዶላር ደርሷል፡፡ ይህን ትንግር የሚመስል እድገት ከየት መጣ ብለን ስንጠይቅ ከጦርነቱ በኋላ ሙሉ ሀይላቸውን ወደ ልማት ማዞራቸው እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እኛስ መልማት ያቃተን እርግማን ይሆን?

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንግስና ዘመን ብቅ ብሎ የነበረው የኢኮኖሚ እድገት መቀጠል ያቃተው ለምን ይሆን? ወደ ዋናው የኢትዮጵያ ምጥ ስንመለስ ህዝብና መንግስት መግባባት አቅቶት ብቻ ሳይሆን ሆድና ጀርባ ሆነዋል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በየለቱ ህዝቡ ለሚያሰማው እሮሮ መንግስት ጆሮ ዳባ ብሎ ማለፉ ነው፡፡ ጊዜ ጠብቆ የሚደረገው የቤት ፈረሳ ደግሞ ድሮም ኢህአዴግ አሁንም ኢህአዴግ እሳት ካየሁ ምን ለየሁ የሚያስብል ሆኗል፡፡ ሕዝብ የጠበቀውን ለውጥ ማግኘት አልቻለም፡፡ በእርግጥም ከቀድሞ ቡድን አንድ ክፍል ተቀንሶ እንዳለ ነው፡፡ ሪፎርም የሚሉት ማደናገሪያ ተጨመረለት እንጂ አንዳችም ለውጥ የለውም ያኛው ቡድን ካቆመበት ገጽ ይኸኛው ቡድን ቀጥሎበታል ፤ እንዲያውም በተጠናከረ ሁኔታ፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...