አነስተኛና ጥቃቅን አምራች ኢንዱስትሪዎች ከሽግግር ጋር በተያያዘ የሚገጥሙ ችግሮች ለመፍታት እና ወጥ ድጋፍ እንዲሰጣቸው ይደረጋል የተባለለት የሽግግር ስትራቴጂና መመሪያ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ለአሐዱ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዞች ልማት የሕዝብ ግንኙነት ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ ሮቤል አህመድ፤ የተዘጋጀው የሽግግር ስትራቴጂ ማስፈፀሚያ መመሪያ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጸድቅ ተናግረዋል፡፡
አምራች ኢንተርፕራይዞች ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ መሸጋገር እንዳለባቸው ያነሱት ኃላፊው፤ አምራች ድርጅቶች በአነስተኛና ጥቃቅን ሥራ ሲጀምሩ ጠቅላላ ወጭያቸው ከ600 ሺሕ እስከ 10 ሚሊዮን ብር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“ይህም አዲስ የሽግግር ስትራቴጂ አምራች ድርጅቶች ባሉበት ደረጃ እንዲሸጋገሩ እና የሚደረግላቸው ድጋፍ ያሉበትን የማምረት አቅም የሚመጥንና ወጥ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ ያስችላል” ብለዋል።
እስካሁን የነበረው አሰራር በተበጣጠሰ መልኩ ሲደረግ መቆየቱን የገለጹም ሲሆን፤ አሁን ግን ክልሎች የራሳቸውን የሽግግር አሰራር እንዲኖራቸው እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
በዚህም መሰረት ወጥ በሆነ መልኩ በፌዴራል ደረጃ ለኢንተርፕራይዞች የሚመጥን ድጋፍ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
አክለውም “እስከ አሁን በነበረው አሠራር ኢንተርፕራይዞች በብዛት ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ መሸጋገር አይፈልጉም” ያሉ ሲሆን፤ “ከአንዱ ደረጃ ወደ ሌላ መሸጋገር የማይፈልጉበት ምክንያትም፤ ‘የሚሰጠን ድጋፍ ይቀንሳል’ የሚል እሳቤ በመኖሩ ነው” ብለዋል።
ከደረጃ ወደ ደረጃ ከተሸጋገሩ የሚሰጣቸው ድጋፍ ተመሳሳይ እንደማይሆን የገለጹት ኃላፊው፤ “ገቢያቸውን ያማከለ ድጋፍ እንዲኖራቸው ይደረጋል” ብለዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
ትክክለኛዎቹን የአሐዱ ራዲዮ የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ!
ፌስቡክ: https://www.facebook.com/ahaduradio
ድረ ገጽ፡- https://ahaduradio.com/
ዩትዩብ፦ http://shorturl.at/cknFP
ቲክቶክ ፡- www.tiktok.com/@ahadutv.official
ዋትስአፕ፦ whatsapp.com/channel/0029VajDfVZI1rcb05C5B22b
አስተያየት እና ጥቆማ ለመስጠት በ7545 አጭር የፅሁፍ መልክት ይላኩ
