የመንግስት መ/ቤቶች በፍርድ ቤት ከሚሰጥ ትዕዛዝ ወይንም በሕግ በግልጽ ከተደነገገው ውጭ ከሰራተኞች ደመወዝ ላይ መቁረጥ የአስተዳደር በደል በመሆኑ ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ ስለ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተገቢው እርምት ሊደረግ ይገባል ሲል የህዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ።
በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የመንግስት ሰራተኞች ለተለያዩ ስራዎች በሚል ደመወዛችን ያለ ፈቃዳችን ይቆረጥብናል የሚል ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸው የኢትዮጵያ እንባ ጠባቂ ተቋም የህዝብ ግንኙነት ስራ አስፈፃሚ አቶ አንለይ ወርቄ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል ።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህም በተለይ በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ በርካታ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎችና ሌሎች ሰራተኞች ፈቃዳቸውን ሳይሰጡ ከደመወዛቸው ላይ እየተቆረጠ ነው።
በዚህም መፍትሄ እንዲሰጣቸው በተለያዩ ጊዜያት ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም አዋሳ ቅርንጫፍ አቅርበዋል።በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ዳውሮ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ መምህራን ተመሳሳይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን ይህም ችግሩ ምን ያህል ሰፊ እንደሆነ ያሳያል።
ለኢትዮጵያ ህዝብ ዕምባ ጠባቂ ተቋም በሕግ ከተሰጡት ስልጣንና ተግባራት መካካል አንዱ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት የሚያወጧቸው አስተዳደራዊ መመሪያዎች፣ የሚሰጧቸው ውሳኔዎችና አሰራሮቻቸው ሕገ መንግስታዊ ድንጋጌዎች እንዲሁም ሌሎች ሕጎችን የማይቃረኑ መሆናቸውን መመርመር፣ መቆጣጠርና ማረጋገጥ መሆኑን ገልፀዋል ።
የፌደራል መንግሥት ሠራተኞች አዋጅ ቁጥር 1353/2017 ዓ/ም በአንቀጽ 11 ንዑስ አንቀጽ (2) ላይ “የማንኛውም የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ አዋጁ ከሚያዘው በስተቀር ሊያዝ ወይም ሊቆረጥ አይችልም።ሠራተኛው ስምምነቱን በጽሑፍ ሲገልጽ፣በፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ ወይም በሕግ በተደነገገው መሠረት፣ ካልሆነ በስተቀር ሊያዝ ወይም ሲቆረጥ አይችልም” ተብሎ መደንገጉን ተናግረዋል ።
በዚሁ ንኡስ አንቀጽ (ስ) ወይም (ሐ) መሠረት ከሠራተኛ ደመወዝ በየወሩ የሚቆረጠው ከደመወዙ አንድ ሦስተኛ እንደማይበልጥ በንኡስ አንቀጽ ላይ በግልፅ ተደንግጓል።በብሄራዊ ክልሎች የመጡ የመንግስት ሰራተኛ ሕጎች በዚህ ረገድ ተመሳሳይ ናቸው።
ሰራተኛው በዕዳ ወይም ሌላ ማናቸውም ምክንያት በፍርድ ቤት ተፈርዶበት ከሚከፈለው ደመወዙ ላይ እንዲቆረጥ ካልታዘዘ ወይም በሕግ በተደነገገ (የገቢ ግብር) መሰረት ካልሆነ በስተቀር ሠራተኛው ስምምነቱን በጽሑፍ ሳይገለጽ ከደመወዙ ሊቆረጥ አይችልም። በመሆኑም ችግሩ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ሁሉ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ተገቢ እርምት ሊደረግ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አሳስቧል።
