ከቀውስ ጠማቂያን ሰላም ይፈልቃልን?

Date:

ቀጸላ ክፍሌ

ኢትዮጵያ በርካታ ጊዜ የእርስ በእርስ ጦርነቶችን አካሂዳለች፡፡ ከዘመነ መሳፍንት በኋላ ያለፈው ስድሳ ዓመት ታሪኳም ያንን የሚጠቁም ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ያሉት ግጭቶች ተደምረው የቅርቡን ጦርነት አያክሉም፡፡ ቁሳዊ ኪሳራም ይሁን ሰብዓዊ ውድመታቸው ፈጽሞ ከቀድሞዎቹ የእርስ በእርስ ግጭቶች ጋር አይገናኝም፡፡ ኢትዮጵያ በታሪኳ ይህን ያህል በልጆቿ ተጎድታ አታውቅም ቢባል ስሕተት አይኾንም፡፡ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን ገንዘብ ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው በሰሜን ኢትዮጵያ አካባቢዎች በተለይም በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመታት በተካሄደውና በሌሎች የተወሰኑ አካባቢዎች በነበረው ጦርነት ኢትዮጵያ ከ1.5 ትሪሊዮን ብር በላይ የሚገመት ጉዳትና ኪሳራ አስተናግዳለች።

ይህን ያህል ገንዘብ ከአንዲት ደሃ ሀገር በጦርነት ሳቢያ መውደሙ እጅግ የሚያሳዝን ነው፡፡ ዋናውና ይበልጥ አሳዛኙ ጉዳይ ግን ከገንዘቡም በላይ ይህን በመሰለው የሰላም እጦት በመቶ ሺህና በሚሊዮን የሚቆጠሩ እልፍ ልጆቿንም የምድር ሲሳይ ኾነው መቅረታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ በተደራራቢ ጦርነቶች ኢኮኖሚዋ የተጎዳ ሕዝቧ የተጎሳቆለባት ሀገር ነች፡፡ በርካታ ሀገራት በዚህ ሂደት ውስጥ አልፈዋል፡፡ ነገር ግን ሁሉም በሚባል ደረጃ በተለይ እንደኢትዮጵያ የሺህ ዓመታት ገናና ታሪክ ኖሯቸው ባሉበት እየተንፏቀቁ አልቀሩም፡፡ ወድቀው ተነስተዋል፡፡ ከስሕተታቸው ተምረዋል፡፡ የውድቀት ታሪካቸውን ትናንት አድርገው ዛሬን በቀድሞ ገናናነታቸው ተክተዋል፡፡ ከመቶ ዓመት በፊት ወደረኛችን የነበረችው ጃፓንና መሰሎቿ ለዚህ ምሳሌ መኾን የሚችሉ ናቸው፡፡ የእኛዋ ኢትዮጵያ ግን ለዚህ አልታደለችም፡፡ አሁንም በትላንቱ አረንቋ ውስጥ ተዘፍቃለች፡፡ ዛሬም ልጆቿ በችጋርና በበሽታ ይረግፋሉ፡፡

ከዚህ አኳያ ሰሞኑን ‹‹ኦክስፋም›› የተባለው ተቋም በትንበያው እንዳስታወቀው ረሃብ በየ28 ሰከንድ አንድ ሰው ሊገድል እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚታየው ግጭት እና የምግብ ዋጋ መናር ከ40 ሚሊየን በላይ የሚኾኑ የቀጠናው ሕዝቦችን ለከፍተኛ ረሃብ እንደሚጋለጥ ተቋሙ አስጠንቅቋል። በረሃብ የሚጠቃው ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጻር የሁለት ሦስተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የጠቆመው ዘገባው 85ሺ የሚኾኑ በደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የሚገኙ ሰዎች ለከፋ ረሃብ ደረጃ ጫፍ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል። ዘገባው ከሶማሊያና ኬንያ ቀጥሎ ኢትዮጵያም የዚህ ችግር ሰለባ መኾኗን አስምሮበታል፡፡ ሀገራችን ከረሀቡ በተጨማሪ ዜጎቿን በመበተን ከዓለም ሀገራት በግንባር ቀደምትነት የምትታወቅ ኾናለች፡፡ ለዚህ መንስዔው ከፍ ሲል እንዳየነው ጦርነትና ጦርነት ወለድ ችግሮች ናቸው፡፡ ጦርነት ከሚወልዳቸው ችግሮች መካከል አንዱ ስደትና መፈናቀል ነው፡፡ አሁን ላይ ስደት በኢትዮጵያ ምድር አይነተኛ የችግር ማምለጫ ዘዴ ተደርጎ የተወሰደ ይመስላል፡፡

ሰሞኑን ቢቢሲ አማርኛ እንደዘገበው በየመን በረሃ ላይ ሞተው በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የአስከሬናቸው ምስሎች ሲሰራጩ የሰነበቱት ፍልሰተኞች ኢትዮጵያውያን እንደኾኑ ተረጋግጧል። ፍልሰተኞቹ ሕይወታቸው ያለፈው በሕገወጥ ሰው አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከየመን ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ በእግር በመጓዝ ላይ ሳሉ መኾኑን የዓይን ምስክር ፍልሰተኞች መናገራቸውን ዘገባው ጠቅሷል። 20 ያህል የሚኾኑት ወንድና ሴት ኢትዮጵያውያን ፍልሰተኞች ሕይወታቸው ያለፈው፣ በድካም፣ ርሃብና ውሃ ጥም መኾኑን የዓይን ምስክሮቹ መናገራቸውን ዜና ምንጩ አመልክቷል። እንደምሳሌ ይህ ተነሳ እንጂ በስደት ምክንያት ከሀገሩ የሚወጣው እንዲሁም ያለመው ሳይሳካ በየሜዳው የሚቀረው ኢትዮጵያዊ ብዛት ቤት ይቁጠረው፡፡

የኾኖ ኾኖ የሰላም ንፋስ ከጠፋ እነዚህ ችግሮች መቼም አይቀረፉም፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላይ ቀስተኛው በማይታወቅበት ሁኔታ ከሁሉም ወገን እየደማች ያለች ሀገር ትመስላለች፡፡ እራሱ መንግሥት፣ ህወሓት፣ ሸኔና መሰል ኃይሎች ሁሉም ለፍላጎታቸው ሲሉ ከየአቅጣጫው እያቆሰሏት ይገኛሉ፡፡ እንኳን ዳግመኛ ቆስላ ይቅርና ሁለት ዓመት የዘለቀው የመንግሥትና የህወሓት ፍልሚያ ጥሎባት የሄደው ጠባሳ በቀላል የሚሽር አይደለም፡፡ ሰሞኑን በፕሪቶሪያ የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተፈፃሚነት የሚቆጣጠርና የሚያረጋግጠው ልኡክ ወይንም (ኤዩ ኤም ቪሲኤም) ለሁለት ቀናት በመቀሌ ያደረገውን ጉብኝት ተከትሎ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በመግለጫው የትግራይን ታጣቂ ኃይል ትጥቅ የማስፈታቱ ሂደት ወሳኝ ደረጃ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡ የአፍሪካ ህብረት ግጭት አስተዳደር ዳይሬክተር አልሀጂ ሳርጆህ ባህ እንደተናገሩት ሁሉም አካላት በበጎ ፈቃደኛነት በመሳተፋቸውና ሰላም ወዳዱ ሕዝብ በመተባበሩ የተነሳ ጥሩ ውጤት ሊገኝ ተችሏል፡፡

እንደእውነታው ግን አሸማጋዩ አካል ይህን ይበል እንጂ ህወሓት አሁንም ከነትጥቁ ተቀምጧል፡፡ በወልቃይት ተከዜ አዋሳኝ ከባድ መሣሪያ (መድፍ ጭምር) አላሰረከበም። ሰሞኑን በወልቃይት በሁለት ግንባር በምርታር እና በዙ-23 የታገዘ ልምምድ እያደረገ ይገኛል። በራያ በኩልም የዚሁ ተመሳሳይ ቀጥሏል፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም በሰልፍ የታገዘ የግዛት ጥያቄ ተነስቷል፡፡ ሰሞኑን በክልሉ በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ‹‹የፕሮቶሪያው ስምንት በአግባቡ ይፈጸም›› ከሚሉ መፈክሮች ጀርባ ከአጎራባች ከልሎች ጋር የሚያጋጩ አጀንዳዎችም ሲራገቡ ነበር፡፡ ይህ የትዕቢት ፖለቲካ ሄዶ ሄዶ እዚያው አረንቋ ላይ እንደሚዘፍቀን ግልጽ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህን ሰልፍ የጠራው ህወሓት ነው። የአፍሪካ ኅብረት አሸማጋዩ ልዑክ ግን ይህን የህወሓት ዳግም ዝግጅት ዘንግቶ ‹‹እስከ ሰማኒያ አምስት ፐርሰንት የሚኾነውን ከባድ መሣሪያ ትጥቅ ማስፈታት ተችሏል›› ይላል፡፡

እንደኅብረቱ ልዑክ ገለጻ ቀጣዩ እርምጃ ቀላል መሳሪያዎችን ማስፈታት፣ የተቀበሩ ፈንጂዎችን ማምከንና የቀድሞ ታጣቂዎችን ከማኅበረሰቡ ጋር መቀላቀል ነው፡፡ የልዑካን ቡድኑ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ስቴፈን ራዲና በመግለጫው “በመቀሌ ከባድ መሣሪያዎና የአየር መቃወሚያዎች ትጥቅ ሲፈታ ለመመልከት ችለናል፤ የሞርታርና ፀረ ታንክ መሣሪያዎች መፍታቱ ሂደት በሚቀጥሉት ሳምንታት ይጠናቀቃል፡፡” ብለዋል፡፡ ነገር ግን ጄኔራል ስቴፈን ያዩት መቀሌን እንጂ ተከዜ ማዶን አይደለም፡፡ ይህ በመኾኑም ኅብረቱ በእጁ ያለው መረጃ የተዛባ መኾኑን ያመለክታል፡፡ በሌላ በኩል ህወሓት እንደፓርቲ ከምርጫ ቦርድና ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመጋጨት ላይ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን ምርጫ ቦርድ የህወሓትን ፖርቲነት ወይም ሕጋዊ ሰውነት እውቅና አለመስጠትን ተከትሎ በህወሓት ቤት ግርግር ተፈጥሯል፡፡ ህወሓት ፓርቲውን ከስረዛ ማውጣት “የፕሪቶሪያውን ስምምነት እውን ማድረግ ነው” ብሎ ሲያምን ምርጫ ቦርድ ደግሞ ይህን ማድረግ የሚያስችለው ሕጋዊ ማዕቀፍ እንደሌለ በግልጽ ቋንቋ ተናግሯል፡፡ ይህ በመኾኑ የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካዔል ድርጅታቸው በድጋሚ ሕጋዊ ፓርቲ ለመኾን የምዝገባ ጥያቄ እንደማያስገባ መናገራቸውን የክልሉ ዜና ምንጮች ዘግበዋል። የፓርቲው ሊቀመንብ “ፓርቲው በሌላ መንገድ ካልፈረሰ በስተቀር ወደፊትም ይቀጥላል” ማለታቸውን ዘገባው ጠቅሷል።

በአጠቃላይ በርዕሱ ላይ እንደተጠቀሰው ቀውስን ጠምቆ ሰላምን መቅዳት አይቻልም፡፡ አሁን ላይ በሀገራችን በሁሉም ዘርፍ ያለው እንቅስቃሴ ቀውስን የሚያባብስ ከፍ ሲልም ቀውስን የሚጠምቅ እንጅ ሰላምን የሚያዋልድ አይደለም፡፡ መንግሥት እንደመንግሥት የዜጎችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ ከፍ ሲልም በሕይወት የመኖር ተፈጥሯዊ ደህንነት ማስጠበቅ አልቻለም፡፡ እንደውም በሁሉም መስክ መንግሥት ቀውሶችን እያባባሰ የሚገኝ ይመስላል፡፡ ፍትሕን ማስፈን ተስኖታል፡፡ ፍትሕ ማስፈን አለመቻል ብቻም ሳይኾን ፍትሕን ሲያዛባም ተስተውሏል፡፡ ከመቶ ሺህ በላይ የሚኾኑ ዜጎችን መኖሪያ ቤት በማፍረስ ቀውስን ወልዶ ፍትሕ አዛብቷል፡፡ ማኅበረሰብን ከማኅበረሰብ በማላተምና ጦርነት በመክፈት አንዴ ካንዱ ሌላ ጊዜ ከሌላው በመወገን ቀውስን ጠምቆ በመቅዳት ለንጹሐን ዜጎች አጠጥቷል፡፡ በሃይማኖት ተቋማት፣ በሲቪል ማኅበራትና በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ሰርጎ በመግባት የቀውስ ምንጭ ኾኗል፡፡ ስለዚህ መንግሥትም ይኹን ማንኛውም የቀውስ መንገድ ጠራጊ የኾነ አካል ወደልቦናው በመመለስ አሁናዊ ሁኔታችንን ማጤን ይኖርበታል፡፡ 

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...