የትግራይ ሕዝብ በየትኛውም ጊዜ የሚፈልገው ለግል ፍላጎት የሚመሰሩቱ የፓርቲ ቁጥር መብዛት ሳይሆን፤ ወጣቱን ትውልድ ለለውጥ የሚያሻግር ፓርቲ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ለአሐዱ ተናግረዋል።
አሐዱም በቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መስራችነት በቀጣይ ይፋ ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው “የትግራይ ሊብራል ዲሞክራሲ ፓርቲ (TLDP)”ን መነሻ በማድረግ፤ “በክልሉ ከፓርቲዎች መብዛት ጋር የትግራይ ሕዝብ ምንድን ነው የሚጠብቀው?” ሲል የክልሉን ነዋሪዎች አነጋግሯል።
“የትግራይ ሕዝብ ለሁለት ዓመታት በግጭት ውስጥ ያሳለፈ ነው” የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ “ነገር ግን አሁን ሕዝቡ የምንፈልገው የፓርቲ ቁጥር መብዛት ሳይሆን ለለውጥ የሚያሻግር አመራርን ነው” ብለዋል።
“አሁንም በእነ አቶ ጌታቸው ረዳ በቀጣይ ይፋ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ፓርቲ፤ ከግል ፍላጎት የፀዳ ሆኖ የትግራይን ሕዝብ የሚያሳምን አጀንዳ ቀርፆ መምጣት መቻል አለበት” ሲሉም ተናግረዋል።
“ከዚህ ቀደም የተመሰረቱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በህወሓት እቅፍ ውስጥ ናቸው” የሚሉት ነዋሪዎቹ፤ “ነገር ግን የይስሙላ የህወሓት ተቃዋሚ መስለው ነው የመጡት” ሲሉ ገልጸዋል።
አሐዱም የነዋሪዎችን አስተያየት መነሻ በማድረግ በቀጣይ ይፋ ይደረጋል ተብሎ ከሚጠበቀው፤ “የትግራይ ሊብራል ዲሞክራሲ ፓርቲ” አንዱ መስራችና የቀድሞው የህወሓት አባል የሆኑትን አቶ ጣዕም አርአዶምን አነጋግሯል።
አቶ ጣዕም በሰጡት ምላሽ የፓርቲው ሥም ሊቀየር እንደሚችል ፍንጭ ሰጥተው፤ “ነገር ግን አላማው የትግራይን ሕዝብን እሴት እና ነባራዊ ሁኔታ ያቀፈ ነው” ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
ለ50 ዓመታት ያህል የትግራይ ሕዝብ ውክልና ሆኖ ረጅም ዓመታትን በፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የቆየው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) ከፓርቲነት መሰረዙን ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሳለፍነው ማክሰኞ ማስታወቁ ይታወሳል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
