“ኮምፒውተር ሲባል ፈንድቶ አገር የሚያጋይ ይመስላቸው ነበር” ኢንጂነር ፍሰሐ አጥላው

Date:

“ታይፕራይተር ማጣቴ የአማርኛ ሶፍትዌር ለመሥራት አነሳሳኝ”

ኢንጂነር ፍሰሐ አጥላው

ግዮን፡- ኢ/ር ፍሰሐ ማነው? ከሚለው ብንጀምር፡-

ኢ/ር ፍሰሐ ፡- ፍሰሐ  አጥላው እባላለሁ፡፡ ተወልጄ ያደግኩት አዲስ አበባ ካሳንቺስ አካባቢ ነው፡፡ የተማርኩት ያኔ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመላላሽ ትምህርት ቤት የሚባለውና አሁን ኮከበ ጽባህ የሚባለው ትምህርት ቤት ነው፡፡ ኮከበ ጽባህ የሚባለው ስም ከድሮውም የነበረ ቢኾንም ዋና ስሙ ግን “ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ተመላላሽ ትምህርት ቤት” ነበር፡፡ የሚያስተምረውም ከ1-12ኛ ክፍል ድረስ ነበር፡፡ በጣም ጥሩ ትምህርት ቤት ነው፡፡ እዚያ ስጨርስ ፊዚካል ሳይንስ የሚባል ዲፓርትመንት ውስጥ ገባሁ፡፡ እዚያ እንደገባሁ የአብዮቱ የለውጥ እንቅስቃሴ በመጀመሩ ትምህርት ተቋረጠ፡፡ እኔ ግን ላይብረሪ እየገባሁ ወደ ተለያየ ዓለም አቀፍ ዩንቨርሲቲዎች እፅፍ ስለነበር አሜሪካን ሀገር ሙሉ ስኮላር ሺፕ አግኝቼ ወጣሁ፡፡

“ገና በ15 ዓመቴ ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ጋር ተፈራረምኩ”

ግዮን፡- አሜሪካ ከመሄድህ በፊት በዐሥራዎቹ የእድሜ ክልል እያለህ ስላዘጋጀኸው ቲያትር ብትነግረን? ቲያትሩን የሠራኸው እንዴት ነው? በዚያ የልጅነት እድሜህ ቲያትር ለመፃፍስ ምን አነሳሳህ?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- ከልጅነቴ ጀምሮ የአማርኛ መጻሕፍት ማንበብ እወዳለሁ፡፡ ቲያትሩን የጻፍኩት በ13 ዓመት ዕድሜዬ ነው፡፡ ቲያትሩ በመጀመሪያ በትምህርት ቤታችን ኮከበ ጽባህ ከታየ በኋላ የተለያዩ ቦታዎች ታየ፡፡ የቲያትሩ ዳይሬክትር እኔ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ የትምህርት ቤታችን ርዕሰ መምህር የነበሩት አቶ አማረ ጉልላት የሚባሉ ነበሩ፤ በእሳቸው አጋዥነት እንደ ተፈሪ መኮንን፣ መድኃኔዓለምና የመሳሰሉት ትምህርት ቤቶች እየዞርን እሁድ እሁድ እናሳይ ነበር፡፡ ቲያትሩ ረጅም ርዕስ ያለው ነው፡፡ “እስከመጨረሻው በጣም የታገለ፤ ከላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ ተቀበለ” የሚል ርዕስ የነበረው ቲያትር ነው፡፡ አጠቃላይ ይዘቱ በቤተሰብ ውስጥ ስለሚከሰት የተለያየ ችግር የሚያወራ ነው፡፡ ስለ ልጅ አስተዳደግና ሂደቱ በደንብ ያሳያል፡፡ ቲያትሩ ከትምህርት ቤቶችም በተጨማሪ በተለያዩ ቲያትር ቤቶችም ታይቷል፡፡ በሎሬት  ጸጋዬ ገ/መድህን  አጋዥነት በሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ታይቶ ነበር፡፡ ገና በ15 ዓመቴ ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ጋር ተፈራርሜ መታየት ጀመረ፡፡ እስከዚያን ጊዜ ድረስ ቤተሰቦቼ ምንም አያውቁም ነበር፡፡ በመጀመሪያ ቀን ሲታይ ጋዜጠኞችን ጨምሮ በጣም ብዙ ሰው መጣ፡፡ ጋዜጠኞችም የኢትዮጵያ ድምፅ በተባለ ጋዜጣ ላይ “የ15 ዓመት ደራሲ” በሚል ርዕስ ከእነ ፎቶግራፌ አወጡት፡፡ በልጅነቴ የነበረው የሥነ ጽሑፍ ፍቅር ኢ/ር ኾኜ ሥራ ከጀመርኩ በኋላም በውስጤ እንደነበር ቀጥሏል፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለሁ ማንበብ በጣም እወድ ነበር፡፡ ከዚያ በፊትም ገና የ6ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ “ወጣት ደራሲያን” የሚል ማኅበር አቋቁሜ ብዙ ተማሪዎች ይሳተፉ ነበር፡፡ በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ጋዜጣ ላይ ኤዲተርም ነበርኩ፡፡ በግቢው ውስጥ የሬድዮ ፕሮግራምም ነበረኝ፡፡ በወቅቱ የዳይሬክተር ቢሮ ውስጥ ይገኝ በነበረ ማይክራፎን የተለያዩ መልዕክቶችን ወደተማሪው አስተላልፍ ነበር፡፡ በተለይ ምሳ ሰዓት ላይ የጥያቄና መልስ ፕሮግራም፣ የሙዚቃ ምርጫና የመሳሰሉት ፕሮግራሞች ነበሩብኝ፡፡ በወቅቱ በዚህ ፕሮግራም ውስጥ ካለፉ ተማሪዎች ውስጥ አሁን ላይ አውስትራሊያ የሚገኝ አንድ የዩንቨርሲቲ መምህር አለ፡፡ ቅርብ ጊዜ ደውሎ በወቅቱ የነበረው የሬዲዮ ፕሮግራማችን ምን እንደሚመስል ሲያስታውሰኝ ነበር፡፡ አንድ ወቅት ደግሞ 9ኛ ክፍል እያለሁ የአሜሪካን ኤግዚቢሽን የሚያሳዩ ሰዎች መጡ፡፡ የእኛ ክፍልና የወ/ሮ ካሕኔ አስፋው ክፍል ተመረጠ፡፡ አሜሪካኖችም የተመረጠውን ክፍል ተማሪ በመኪና ጭነው በመውሰድ ኤግዚቪሽኑን አሳዩን፡፡ ያን ኹነት በወቅቱ የአሜሪካ ጋዜጠኞች መጥተው ፎቶ አንስተው ቪዲዮ ቀርጸው ነበር፡፡ ቪዲዮው አሁን ዩቲዩብ ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ኹነት አሁን ላይ ከቴክኖሎጂ ጋር ያለኝ ቁርኝት የጠበቀ እንዲኾን ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጥሮብኛል፡፡

ግዮን፡- ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድህን ባዩህ ጊዜ ምን አሉህ?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- እውነት ለመናገር በጣም ብዙ ሰው ስለነበር በዚያ ፕሮግራም ላይ ይምጣ አይምጣ አላስታውስም፡፡ ወላጆቼም በግብዣ ነበር የመጡት፡፡ ጋዜጠኞች አባቴን “ይህ ሕፃን ልጅ እንዴት ቲያትር ሊፅፍ ቻለ” ሲሉት ምንም እንደማያውቅ ነግሯቸዋል፡፡ እርሱም በሁኔታው በጣም ተገርሞ ቲያትሩን ሲሠሩ ለነበሩ ጓደኞቼ እንድጋብዛቸው 50 ብር ሰጠኝ፤ የገንዘብ ሥጦታውን በደብዳቤ ስለነበር ያሳወቀኝ እስካሁን ደብዳቤው እጄ ላይ አለ፡፡ በነገራችን ላይ የአባቴን የሕይወት ታሪክ ጽፌዋለሁ፡፡ ይህን ደብዳቤና መሰል ነገሮችንም አንድ ላይ አስቀምጫቸዋለሁ፡፡ በአጠቃላይ ግን ያ ቲያትር በሕዝቡ ዘንድ በጣም ነበር ተቀባይነት ያገኘው፡፡ በተለይ የመጀመሪያው ቀን በሀገር ፍቅር ሲታይ ቲያትሩ ላይ የሚሞተው ተዋናይ ሕዝቡ የእውነት መስሎት በእንባ ነበር የታጠበው፡፡ ይህን የእንባና የመላቀስ ኹነትም በወቅቱ ጋዜጦች አውጥተውታል፡፡ ከዚያ በፊት ያን የመሰለ ነገር ሲሠራ በሕዝብ ዘንድ ስላልታየ የተዋናዩ ሞት የምር መስሏቸው ነበር፡፡

ግዮን፡- ዩንቨርሲቲ እያለህ የተማሪ እንቅስቃሴው ውስጥ ነበርክበት?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- አልነበርኩበትም፡፡ ንቅናቄው የተጧጧፈው እኔ አሜሪካ ከገባሁ በኋላ ነው፡፡ እዚህ ከመጣው በኋላ ብዙ ጓደኞቼ ተገድለዋል፡፡ እኔ ጊቢ እያለሁ ያኔ አሜሪካ ላይብረሪ የሚባል ነበር፡፡ እዚያ እየገባሁ ወደተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ስኮላር ሺፕ እጻጻፍ ነበር፡፡ ነጥቤም ጥሩ ስለነበር አውስትራሊያን ጨምሮ ወደ በርካታ ሀገራት ጽፌያለሁ፡፡

ግዮን፡- ኦክላሆማ የተማርከው ምንድነው?

ኢ/ር ፍሰሐ ፡- ኦክላሆማ የተማርኩት ቴሌኮምኒኬሽን እና ማቲማቲክስ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ኾኖ የሄድኩበት ትምህርት ቤት ኢንጂነሪግ አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህ ሦስት ዓመት ማቲማቲክስና ቴሌኮምኒኬሽን ተምሬ ከጨረስኩ በኋላ ወደ ነብራስካ ለማስተርስ ፎሎ ሺፕ ባዮ ሜዲካል ኮምኒኬሽን ዲፓርትመንት አቀናሁ፡፡ ዩንቨርሰቲው “ዩንቨርሲቲ አፍ ነብራስካ ሜዲካል ስኩል” ይባላል፡፡ በዚህ ዩንቨርሲቲ ሁለት ማስተርስ አገኘሁ፡፡ አንደኛው በሲስተምስ ኢንጂነሪግ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ አፕላይድ ማቲማቲክስ ነው፡፡ ይህን ካገኘው በኋላ  በተማሪ ቪዛ ስለነበር ከሀገር የወጣሁት ቪዛ ማግኘት ነበረብኝ፡፡ አሜሪካን ሀገር በትምህርት የቆየሁት አምስት ዓመት ነው፡፡ ትምህርቱን እንደጨረስኩ ፕራክቲካል ትሬኒንግ ወጣሁ፡፡ በአሜሪካ ሕግ በዚያን ወቅት ማንም የውጪ ሰው እንደልቡ እና እንደሀገሬው ዜጋ ተቀጥሮ መሥራት አይችልም ነበር፡፡  

በናርስቲኩም 18 ወር ልዩ ቪዛ ተሰጥቶኝ ነው መሥራት የጀመርኩት፡፡ በዚህ ቪዛ የመኪና ፓርት የሚሠራ ካምፓኒ ውስጥ ማኑፋክቸሪግ ኢንጂነር ኾኜ መሥራት ጀመርኩ፡፡ በመቀጠል ካሊፎርኒያ ሌላ ሥራ አገኘሁና ሄድሁ፡፡ ቪዛዬን እንደሚያስቀይሩልኝና ስፖንሰር እንደሚያደርጉኝ ነገሩኝ፡፡ በዚህም እቃየን ሁሉ ጭነው ካሊፎርኒያ ወሰዱኝ፡፡ ካሊፎርኒያ ስመጣ የሠራተኛ ሚኒስተር ለሚባለው ተቋም የሠራተኛ ቪዛ እንዲሰጡኝ አመለከትኩ፡፡ የሥራ ሚኒስቴር ደግሞ “ምን ያህል ሰው ፈልጋችሁ አጣችሁ? እንዴት አሜሪካ ውስጥ በእርሱ ፊልድ ሰው አጣችሁ?” የሚል ጥያቄ አቅርበውባቸው ድርጅቱ ዋሽንግተን ዲሲ፡ ሎሳንጀለስ፤ ቴክሳስ ማስታወቂያ አውጥቶ “ይህን ያህል ሰው አፕላይ አድርጎ፣ በሱ ፊልድ ግን ሰው አላገኘም” ብሎ መለሰ፡፡ በዚህ ምክንያትም የአሜሪካ የነዋሪነት ቪዛ ተሰጠኝ፡፡ ከዚያም ኑሜሪካል ኮንትሮል የሚባሉ ሮቦቶች ፕሮግራመር ኾንኩ፡፡ ያኔ ኮምፒውተር ይሠራ የነበረው በወረቀት ካርድ ነበር፡፡ እኔም የእሱ ኑሜሪካል ኮንትሮል ፕሮግራመር ነበርኩ፡፡

ግዮን፡- የኢትዮጵያ ፊደል በሶፍትዌር እንዲኖር ለማድረግ ያነሳሳህ የኑሜሪካል ኮንትሮል ፕሮግራመር መኾንህ ነው?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- የመጀመሪያው የአማርኛ ሶፍትዌር መሥራቴ ከፕሮግራመርነቴ ጋር አይገናኝም፡፡ ምክንያቱም እኔ ስሠራበት የነበረው ካምፓኒ ማሽነሮችን ነበር ፕሮግራም የማደርገው፡፡ ሀርድ ዌር የኾኑ ነገሮችን ነበር ፕሮግራም የማደርገው፡፡ ስለዚህ አማርኛ ሶፍትዌር መሥራቴ ከዚህ ጋር አይገናኝም፡፡ ከዚህ ካምፓኒ ከወጣሁ በኋላ አካሪ የሚባል የመጀመሪያ የኮምፒተር ጌም ዲዛይን ድርጅት ገባሁ፡፡ ፋውንድ የሚባለውንም የመጀመሪያ ጌም የሠራነውም በዚያ ኩባንያ ነው፡፡ በመቀጠልም ወደ “ሀይውሊት ፓከርድ ኤች ፒ ዲቨሎፕመንት ኢ/ር” የሚባል ተቋም ገባሁ፡፡ ይኼ ካምፓኒ በወቅቱ በጣም ትልቅ ድርጅት ነበር፡፡

በመኾኑም እዚህ ድርጅት ውስጥ ለመግባት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ኢንተርቪው ራሱ ሙሉቀን ይጨርስ ነበር፡፡ ምክንያቱም ተቋሙ ሰው ከቆጠረ በኋላ ያለማባረር ፖሊሲ ነበረው፡፡ ይህ በመኾኑም የሚቀጥሩትን ሰው በጣም በጥንቃቄ ነው የሚቀበሉት፡፡ በመኾኑም ብዙ ሰዎች ሞክረው ሳይሳካላቸው እኔ በመግባቴ እድለኛ ነኝ፡፡ ምክንያቱም እዛ ለመቀጠር 10 ዓመት ጠብቀናል የሚሉ ሰዎች በመኖራቸው ነው፡፡ በዚያን ወቅት እኔ የምሠራበት አካባቢ ኢትዮጵያዊ አልነበረም፡፡ ኤች ፒ ውስጥ በየዓመቱ የሚዘጋጅ ዲዛይን ላይ ሊቀመንበር ኾኜ የምሠራው እኔ ነበርኩ፡፡ በፕሮግራሙ ላይ ከ30-40 የሚኾኑ የኤች ፒ አከፋፋዮች ይመጡ ነበር፡፡ በተቋሙ ውስጥ ጥሩ እድል ተሰጥቶኝ ነበር፡፡ አፍሪካዊ ቀርቶ ጥቁር አሜሪካዊ በዙሪያዬ አልነበረም፡፡ ተቋሙ በሚልከኝ ቦታ ሁሉ ማለትም እንደ ጃፓን፤ ጀርመን፣ ቤልጂየምና የመሳሳሉት ሀገሮች እየሄድኩ እሠራ ነበር፡፡ ከአቅራቢዎች ጋር የምደራደረውና ስምምነት የማደርገውና ሥልጠና የምሰጠው እኔ ነበርኩኝ፡፡ ይህን እየሠራሁ “ኢ/ር ዲዛይን ሳይንቲስ” የሚባለውን ሥያሜ ሰጡን፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ ሁለት የተለያዩ የድሮ አናሎግ ወደ ዲጂታል የተለወጡበትን አሳትሜያለሁ፡፡ አንድ ዓለም አቀፍ ሲንፖዚየም እንድናዘጋጅና እኔ እንድመራው ተደርጎም ነበር፡፡ በ1994 በፈረንጆቹ አቆጣጠር ላይ ፓወር ኮኔክሽን፤ ኢንተለጀንስ ሞንሽን የሚባል ሰርተን ነበር፡፡ በወቅቱ ጋዜጣ ላይ ወጥቷል፡፡ በጥቅሉ በዚህ ካምፓኒ ውስጥ ከአለቆቼም ይሁን ከሠራተኛው ጋር ብዙ ግንኙነት ነበረኝ፡፡

ግዮን፡- በዚህ ሂደት ላይ እያለህ ነው አማርኛ ሶፍትዌር የሠራኸው?

ኢ/ር ፍሰሐ ፡- ተቋሙ ውስጥ እያለሁም ሥነ ጽሑፍ እወድ ስለነበር እጄ ላይ የተለያዩ የአማርኛ ግጥሞች እና ጽሑፎች ነበሩኝ፡፡ በወቅቱ የአማርኛ ታይፕራይተር ነበር፡፡ እሱን ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ ለማስመጣት ጥረት አደረግሁኝ፡፡ በወቅቱ በኢትዮጵያ ማንኛውም የአማርኛ ጽሑፍ ሥራ ይከናወን የነበረው በዚህ መሣሪያ ነበር፡፡ እነ ኢሕአፓ፤ መኢሶንና የመሳሰሉት ፓርቲዎችም የተለያዩ በራሪ ወረቀቶችንና ጽሑፎችን ያዘጋጁ የነበረው በዚህ መሣሪያ ነው፡፡ ስለዚህ ታይፕራይተሩን ከኢትዮጵያ ለማውጣት በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ በሕግ ደረጃም መሣሪያውን ከሀገር ይዞ የሚወጣ ግለሰብ ከተገኘ እስከሞት ድረስ ሊቀጣ ይችላል፡፡

ግዮን፡- ታይፕራይተሩ አሜሪካ አልነበረም?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- አዎ አልነበረም፡፡ የአማርኛ ታይፕረይተር ስለኾነ እዚያ አልነበረም፡፡ መሣሪያውን የሚሠራው ግን አሊቬቲ የሚባል አንድ የጣሊያን ኩባንያ ነበር፡፡ ስለዚህ በሕጉ መሠረት ከኢትዮጵያ ማውጣት እንደማይቻል ሲነግሩኝ ጣሊያን ሀገር ታይፕራይተሩን ለሚሠራው ኢሊቬቲ ለተባለው ኩባንያ ፃፍኩለት፡፡ ኩባንያውም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውል እዳለውና ሊሸጥልኝ እንደማይችል ነገረኝ፡፡ ከዚያ በእንግሊዘኛ የምሠራበትን ኮምፒውተር መመርመር ጀመርኩ፡፡ ታይፕራይተር ማጣቴ የአማርኛ ሶፍትዌር ለመሥራት አነሳሳኝ፡፡ ይህ ወቅት በፈረንጆቹ 1982 አካባቢ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ኮምፒውተሮቹ  ስታንዳርዳይዝ አልነበሩም፡፡ በአንዱ ሶፍትዌር ላይ ከእነ ሀርድዌሩ ይሸጣል እንጂ አንዱ ለሌላው አይሠራም ነበር፡፡ ማይክሮ ሶፍት ዊንዶው የሚባለው ሲስተምም አልነበረም ነበር፡፡ ስለዚህ የምንጠቀመው በዶት እና በላይን ነበር፡፡ ስለዚህ በኤች ፒ ላድርገው ወይስ በኮሞደር አልያም በአፕል የሚለው ግራ አጋብቶኝ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ትንሽ ወደ ስታንዳርድ የመጣው የአይዲየም ኮምፒውተር ነበር፡፡ ከማይክሮሶፍት ጋር ንግግር ጀመሮም ስለነበር በሱ ላይ መሥራት እንዳለብኝ አሰብኩ፡፡ ነገር ግን ኮምፒውተሩን ለማግኘት ቀላል አልነበረም፡፡ እኔ ቢሮ ያለው ኮምፒውተር “ኤች ፒ ዋን ፊፍቲ” የሚባል ነው፡፡ ምንም ስታንዳርዳይዝ የኾነ አልነበረም፡፡

ስለዚህ ለምፈልገው ዓላማ የምጠቀምበት ኮምፒውተር ስለማይኾን ያኛውን ኮምፒውተር ከእነ ፕሪነተሩ በወር ወደ 1500 ዶላር እየከፈልኩ ተከራየሁ፡፡ እሱ ላይ ኤክስፐርመንት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ ፊደሎቹን ፎንት ለመስጠት ሞከርኩ፡፡ አሁን እንዳለው በቀላሉ መሥራት አይቻልም ነበር፡፡ እያንዳንዱ ፊደል መቀረጽ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ሰባቱ የ”ጨ” ዘር ፊደላት በጣም አስቸጋሪ ነበሩ፡፡ በዚያን ወቅት የአማርኛ ቋንቋ ብቻ ሳይኾን የዐረበኛ፣ የጃፓንና የሌሎች ሀገሮች ቋንቋዎችም አልነበሩም፡፡ በዚያን ወቅት ከፍ ሲል እንዳልኩት ዊንዶ አልነበረም፤ ማውዝ የለ ምንም አልነበረም፡፡ ስለዚህ ለመሥራት ከባድ ነው፡፡ ከሠራሁት በኋላ ግን ወሬው ወዲያው ተሰራጨና ብዙ ሰዎች እነርሱም መሥራት እንደሚፈልጉ ነገሩኝ፡፡ ያን ጊዜ ሲስተሙ አስኪ የሚባል ነበር፡፡ ኮምፒውተሩም የነበረው ቦታ ጥቂት ነበር፡፡ በኋላ ግን ዩኒ ኮድ የሚባል መጣና የትኛውን ፊደል የዐረበኛውንም የቻይንኛውንም ሁሉንም መቀበል የሚችል ሲስተም መጣ፡፡ ዩኒ ኮድ ማለት ዩኒቨርሳል ኮድ ማለት ነው፡፡

ግዮን፡- የኢትዮጵያን ፊደሎች ወደ ሶፍትዌር ለማስገበት ምን ያህል ጊዜ ፈጀብህ?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- ሥራዉን የጀመርኩት ከፍ ሲል እንዳልኩት በፈረንጆች በ1982 አካባቢ ነው፡፡ ጊዜው በጣም አስቸጋሪና ሰካነር ያልነበረበት ዘመን ስለነበር ብዙ ቆይቷል፡፡ በተለይም በኢትዮጵያ ረሃብ ሲከሰት በሳንፍራንሴስኮ፤ ኦስላንና ሳንሆዜ ያለን ኢትዮጵያውያን ተሰባስበን ወገን ለመርዳት ሞከርን፡፡ 3 የሚኾኑ ተቋማት ነበሩ፡፡ አንድ ላይ ተጣምረው ሊቀመንበር አድርገው ሾሙኝ፡፡ በዚህም የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ላይ የውሃ ጉድጓድ ለማስቆፈር እና ልዩ ልዩ እርዳታዎችን ለማድረግ ሞከርን፡፡ እዚህ ከሚገኙ የቴሌቭዝን ጣቢያዎችና ወርልድ ቪዥን ጋር በመነጋገር የተለያዩ ሥራዎችን ሠራን፡፡ እንግዲህ ይህን የመሳሰሉትን ሥራ ሳከናውን ለተወሰነ ጊዜ የአማርኛ ሶፍትዌር ሥራውን አቆምኩት፡፡ ኋላ ላይ ግን በነጮች 1985 ላይ እንደገና ጀመርኩት፡፡

ግዮን፡- ከየክፍለ ግዛቱ ተሰባስባችሁ ለእርዳታ የተንቀሳቀሳችሁበት ሂደት ውጤታማ ነበር?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- አዎ ብዙ ድጋፍ ማድረግ ችለናል፡፡ በየጋዜጣውና በየመጽሔቱ ላይም ወጥቷል፡፡ ከወርልድ ቪዥኖች ጋር በመፈራረም ብዙ ሥራ ሠርተናል፡፡ እኛ ገንዘብ አሰባስበን ስንሰጣቸው እነርሱ የውሃ ጉድጓድ እየቆፈሩ ዝርዝሩን ይሰጡን ነበር፡፡ በወቅቱ ለዚህ ዓላማ ያዋልነው ገንዘብ ይሰላ ቢባል በዚያን ጊዜ ወደ 40ሺህ ዶላር ይጠጋል፡፡ ይሄ ገንዘብ ያኔ ትልቅ ገንዘብ ነው፡፡ ገንዘቡ የተሰበሰበው በአንድ ስቴት ውስጥ ካሉ ሦስት ከተማዎች ነው፡፡ እያንዳንዱ ሰው እስከ 100 ዶላር ነው ያዋጣው፡፡ ገንዘቡ የተወራረደበት ሙሉ መረጃውም እስካሁን በሰነድ አለ፡፡

ግዮን፡- ይህ ሁኔታ ለጊዜው ተሰብስባችሁ የተበተናችሁበት ነው ወይስ በማኅበር መልኩ እስካሁን ቀጥሎል?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- ያን ጊዜ ለአንድ ዓመት ከግማሽ ከተሠራ በኋላ እኔ ኃላፊነቴን ተውኩትና ወደ ሥራዬ ተመለስኩ፡፡ የእኔን ኃላፊነት ወርቁ ነጋሽ ተረከበኝ፡፡ እኔ ከሄድኩ በኋላ ኅብረቱ ለሁለት ያህል ዓመታት ቆይቶ ረሃቡ ስላበቃ ቆመ፡፡ እኔም በፈረንጆች ከ1985 በኋላ ጀምሬው የነበረውን የሶፍትዌር ሥራ ቀጠልኩ፡፡ በወቅቱ ዶ/ር መለሰ ወጉ ብዙ ትራኮችን ያትም ስለነበር ለእርሱ ላኩለት፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ መሥራት ለሚያስቡ ለሌሎች ሰዎችም ላክሁ፡፡ በየቦታው በዚህ ዙሪያ ከሚሠሩት ጋር ሐሳብ እንለዋወጥ ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሶፍትዌሩ ዜና ተስፋፋ፡፡ የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮም በ1987 አካባቢ ደውለውልኝ ቃለመጠይቅ አድርገውልኝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያም ተጠራሁ፡፡ በአጠቃላይ ሶፍትዌሩ አገልግሎት ላይ የዋለው በፈረንጆቹ 1986 ላይ ነው፡፡ እኔ ከዚያ በፊት በግሌ ብጠቀምበትም በሌላው ሰውና በሕዝቡ ዘንድ የደረሰው ግን በጠቀስኩት ዓመት ነው፡፡

ግዮን፡- ምንም እንኳን ፊደሉ የኢትዮጵያ ቢኾንም፣ የሶፍትዌሩ ፈጠራ የአንተ ከመኾኑ አንፃር የባለቤትነት መብት (ፓተንት) አልተሰጠህም?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- ሶፍትዌሩ ኮፒይ ራይት ነው የሚኾነው እንጂ ፓተንት የለውም፡፡ ለምሳሌ ታይፕ አደራረጉ “ሀ” ን መፃፍ የፈለገ ሰው “H”ን ይመታል፡፡ ስለዚህ ኪይ ወርዱ ኮፒ ራይት ስለኾነ ፓተንት የለውም፡፡ እኔም በባለቤትነት ዙሪያ አልሄድኩበትም፡፡ ምክንያቱም ዋናው የእኔ ዓላማ አገልግሎቱ ለሰው እንዲደርስ ነው እንጂ ፓተንት አግኝቶ ባለቤት መኾን አደለም፡፡ የኢትዮጵያ ፊደል ፓተንተብል አይደለም፡፡ ምክንያቱም ፊደሉ በመጀመሪያ ፒምኮድ ኮምፒውተር ውስጥ ገብቷል፡፡ ከዚህ ቁጥር እስከዚህ ቁጥር ተብሎ ቦታ ተይዞለታል፡፡ ፓተንትም የለውም፡፡ አንዳንድ ሰዎች “ፓተንት ያለው የአማርኛ ሶፍትዌር እንሸጣለን” ይላሉ፣ ይኼ ግን ውሸት ነው፡፡ አሁን እንደውም ምንም ታይፕ ቀርቶ ድምፅን ታይፕ ማድረግ የሚችል መተግበሪያ መጥቷል፡፡ በሌላ በኩል “ኢትዮፒክ” የሚለውንም ሥም የሰጠውት እኔ ነኝ፡፡ በዚህ ዙሪያ እንደውም ብዙ ክርክር ነበር፡፡ አንዳንዶች “አማርኛ በሉት” ሲሉን ነበር፡፡ እኔ “ኢትዮፒክ ቢባል ዘላቂነት አለው” ብዬ ለሊቀመንበሩ ዶ/ር ጆይ ቤከር በመንገሬ ነው ሥያሜውን ያገኘው፡፡

ግዮን፡- “ኢትዮፒክ” የሚለውን ስያሜ ለምን መረጥህ?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- ኢትዮፒክ የሚለው ስም አዲስ አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ ፊደል እስከ 16ኛው ክፍለ ዘምን ድረስ “ኢትዮፒክ” በሚል ስም ነበር የሚታወቀው፡፡ አንዳንዶች ሳባ ቢሉትም ወይም ግዕዝ የሚለው ስም ቢገልፀውም “ኢትዮፒክ” የሚለው ስም ግን ይበልጥ የተሻለ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ኢትዮፒክ የሚለው ስም እንዲኾን የታገልኩት ኢትዮጵያ ከሚለው የሀገራችን ስም ጋር እንዲያያዝ ነው፡፡ በተጨማሪም ፊደሉ የአማርኛ ብቻ አይደለም፡፡ ፊደሉ የግዕዝ፣ የትግርኛ፣ የጉራጊኛና አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሴሜቲክ ቋንቋዎች መጠቀሚያ ነው፡፡ ለምሳሌ የመጀመሪያ የአማርኛ ታይፕራይተርን የሠሩት አያና ብሩ የሚባሉ የወለጋ ሰው አፋን ኦሮሞ ተናጋሪ ናቸው፡፡ ይኼ ታይፕራይተር የአማርኛ ታፕይፕራይተር ቢባልም የኢትዮጵያ ታይፕርይተር ነው፡፡ ሁሉንም በዩኒ ኮድ በኩል ለማመቻመች ተሠርቷል፡፡ ለምሳሌ የኦሮምኛ ተናጋሪዎች ይሄኛው ሶፍት ዌር ከቀለላቸው ይጠቀሙበታል፡፡ እንደውም “ኢትዮፒኬኛ” በሚል ጠርተውት ለመጠቀም የሚደረግ ንቅናቄ አለ፡፡ ከዚህ አንፃር በአሁን አገላለፅ ፊደሉ የአንድ ብሔር ብቻ አይደለም፡፡

ግዮን፡- በኢትዮጵያ ውስጥ የራሳቸውን ፊደል ትተው በላቲን ፊደል የሚጠቀሙ ቋንቋዎችን ጉዳይ እንዴት ታየዋለህ?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- እኔ ሶፍትዌሩን በሠራሁበት ጊዜ የኢትዮጵያ ፊደል በጣም ከባድ ነበር፡፡ ሦስት መቶ ምናምን ፊደል ወደ ኮምፒውተር ማስገባት ፈታኝ ነበር፡፡ በመኾኑም በጊዜው “እራሱ አማርኛ ለምንድነው በላቲን የማይፃፈው” የሚሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ ምክንያቱም ኮምፒውተሩ መያዝ የሚችለው 26 የእንግሊዘኛ ፊደል ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በጊዜው ከሦስት መቶ በላይ የሚኾኑ የአማርኛ ፊደላትን ወደ ኮምፒውተር ማስገባት ትልቅ ችግር ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ እኔ ደግሞ ማድረግ እንደሚቻል አምን ነበር፡፡ ወደ ዩኒ ኮድ ስንገባ ደግሞ ያንን አራዘመው፡፡ የአማርኛ ፊደላት ብቻ ሳይኾኑ የኦሮምኛ ፊደላትም በ“ሺፍት” የሚፃፉ እንዲጻፉ ተመቻቸላቸው፡፡ ለምሳሌ እንደ “በዳኔ” (በዻኔ) ያሉት ቃላት በእነዚህ ፊደላት የሚፃፉ ናቸው፡፡ ለትግርኛውም፣ ለዲቃላ ፊደላትም ዩኒ ኮድ ተፈጥሮላችዋል፡፡ ለጋሞ፤ ለከፋ ሕዝብ ለሌሎችም ዩኒ ኮድ ላይ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ሚሲዮናውያን በየቦታው መግባት ያለበትን ድምጽና ፊደል ስለሚነግሩንና ስለሚልኩልን በርካታ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ዩኒ ኮድ ላይ ቦታ አላቸው፡፡ በጥቅሉ ከጥያቄህ አንፃር እኔ መናገር የምፈልገው በላቲን ፊደል ለሚጠቀሙ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ኢትዮፒክ ፊደልን ቢጠቀሙ መልካም ነው ሚለውን ነው፡፡

በእርግጥ አንዳንድ የኦሮሞ ምሁራን ቁቤን ለማዘመን አዲስ “ኢትዮፒከኛ” የሚባል ሶፍትዌር እየሠሩ እንደኾነ አውቃለው፡፡ ይኼን አበረታታለሁ፡፡ ሕዝቡ ግን የፈለገውን እንዲመርጥ ቢደረግ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን ሕዝቡ ለቋንቋውና ለባህሉ እድገት የሚኾነው ኢትዮፒክ ፊደል ነው፡፡ እንኳን የእኛ የኤርትራ እንኳን አትዮፒክ ተብሎ ነው የሚሠራው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን ይህን ተጠቀም ይህን የሚለው ላይ ግፊት ማድረግ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡ እኔ ግን ኢትዮፒክን ጥናት ሳደርግ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ቋንቋ እንዲያሳትፍ አድርጌ ነው፡፡ በእርግጥ ይሄን እኔ ብቻ ክሬዴት መውሰድ አይገባኝም፡፡ ዩኒ ኮድ የሚባል ዓለም አቀፍ ኮሚቴ አለ፡፡ እኔ የዚህ ኮሚቴ አባል ነኝ፤ አፍሪካዊ እኔ ብቻ በመኾኔ ከየቦታው የሚመጣው ጥያቄ ከምሁራን ጋር በመነጋገር ነው የምሠራው፡፡ አንድ ፀሐዬ ተፈራ የሚባል የሥነ ልሣን ባለሙያ ስላለ ከእሱ ጋር ተነጋግረን ነው ብዙዎቹን የሠራሁት፡፡ ኢትዮፒክ የሚለውን ስምም ከእርሱ ጋር ተነጋግረንበት ጥናት ተሠርቶበት ነው ወደ ስያሜ ያመጣነው፡፡ እና በሁሉም ዘርፍ ብቻዬን ሳይኾን ከኮሚቴው ጋር ነው ሥራውን የማከናውነው፡፡ ስለዚህ ከ400 በላይ ቋንቋዎች ኢትዮፒክ በሚለው ስም ውስጥ ተካተዋል፡፡

ግዮን፡- በፊደል አጠቃቀም ዙሪያ የኢትዮጵያ ፊደል መለያችን ከመኾኑ አንፃር ከመንግሥት እና ከምሁራን ምን ይጠበቃል ትላለህ?

ኢ/ር ፍሰሐ፡-  እኔ ለመንግሥትም ይሁን ለምሁራን የምለው ሕዝቡ ይምረጥና የወደደውን ፊደል ይጠቀም ነው፡፡ ይኽን መጠቀም አለበችሁ ብሎ ማስገደድ ቴክኒካል ምክንያት የለውም፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ለምሳሌ አማርኛ ለመጠቀም ቴክኒካል ችግር እንዳለ ተናግሮ ነበር፡፡ ነገር ግን እንደዚያ ብሎ ነገር የለም፡፡ በኦሮምኛ ማጥበቅና ማላላት ማንኛውም በቋንቋው ውስጥ ያለው ሁሉ ተሠርቶለታል፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮፒከኛ በሚል አብሬያቸው የምሠራቸው ልጆች ኦሮምኛ ለመጻፍ የሚጥሩት፡፡ ስለዚህ የእኔ ጥሪ በተቻለ መጠን ከፉክክር በመውጣት በሚጠቅመን እንሥራ የሚል ነው፡፡ ምሁራኖቹ በደንብ ቢያስቡበት መልካም ነው፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገውን ስለሚያውቅ በሕዝቡ ፍላጎት ቢመሩ መልካም ነው፡፡ በእኔ እምነት ግን ኦሮምኛን ከላቲን የተሻለ በኢትዮጵያ ፊደል መፃፍ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ ከሶፍት ዌሩ ጋር በተያያዘ አዲስ የሚፈጠር ነገር የለም፡፡

ግዮን፡- ሶፍትዌሩን ከጨረስህ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተህ ነበር፤ ስትመጣ የጠበቀህ ነገር ምን ይመስል ነበር?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- እዚህ ሀገር ከሥራ ውጪ ባለው ጊዜዬ የተለያዩ ቦታዎች እየተገኘው ስለ ሶፍትዌሩ ገለፃ አደርጋለሁ፡፡ አንድ ወቅት ስታንፎርድ ዩንቨርሲቲ ውስጥ ቴክኒካል ነገሮች እሠራ ነበር፡፡ የኤች ፒው መሥሪያ ቤቴ እዚያ አካባቢ ስለነበር ብዙ ጊዜየን በዩንቨርሲቲው አሳልፍ ነበር፡፡ በአጋጣሚ ታዲያ በአምባሳደር ካሣ ከበደ የሚመራ ሕዝብ ለሕዝብ የሚባል ቡድን ስታንፎርድ ዩንቨርሲቲ መጣ፡፡ በአጋጣሚው የሠራሁትን ሶፍትዌር ሳሳያቸው በጣም ደነቃቸው፡፡ በዚህም አምባሳደር ካሣ ኢትዮጵያ እንድትመጣ አደርጋለሁ አለኝ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለስኩም ከሳይንስ ቴክኖሎጂ ኮሚሽን አበበ ሙሉነህ ከሚባል ሰው የግብዣ ደብዳቤ ደረሰኝ፡፡ በዚህም በፈረንጆቹ 1988 ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ፡፡ ኢትዮጵያ ከገባሁ በኋላ በኢትዮጵያ ሬዲዮም፤ በቴሌቨዥንም ቃለ መጠይቅ ተደረገልኝ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱም እየዞርኩኝ ስለሶፍትዌሩ ገለጻ እና ማብራሪያ እሰጥ ነበር፡፡ በዚህም ጡረታ ሚኒስቴር፤ ገንዘብ ሚኒስቴር እና ሌሎች ትልልቅ ተቋማት ውስጥ ማብራሪያ ሰጠሁ፡፡ በወቅቱ እንደ ሀገር ትልቅ ዜና ኾነ፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ ስዞር ቤተሰቦቼ በአግባቡ ሳልጠይቃቸው ነው ጊዜው ያለቀው፡፡ በዜናው በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጣም ነበር ደስተኛ የኾነው፡፡ አንዴ በሂልተን ሆቴል ሴሚናር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ሴሚናር ላይ ብዙ የውጭ ሀገር ሰዎች ነበሩ፡፡ ቻይናዎች አፍሪካውያኖች እና ሌሎችም ነበሩ፡፡  በወቅቱ በኮምፒውተር ላይ አማርኛ ጽሑፍ ማየት ብርቅ ነበር፡፡

የሂልተን ሴሚናር ላይ ወታደሮች ጥግ ጥግ ይዘው በመቆም ሕዝቡን አስወጡ እና አምባሳደር ካሣ መጣ፡፡ አንድ የሚመጣ ሰው እንዳለም ነገረኝ፡፡ ይህንን ስሰማ እኔ የተለየ ጥርጣሬ አደረብኝ፡፡  በተለይ የተማሪ ንቅናቄ ውስጥ ኾኜ በኢትዮጵያ የነበረውን ግድያና ጭፍጨፋ የምቃወም ሰው ስለነበርኩ መንግሥት ይፈልገኛል የሚል ሥጋት አደረብኝ፡፡ ምክንያቱም በተማሪው እንቅስቃሴ ውስጥ ብዙ ጓደኞቼ ስለተገደሉብኝ የመንግሥት ቀንደኛ ተቃዋሚ ነበርኩኝ፡፡ በተለይ ደግሞ የደህንነት ሚኒስትሩ ኮ/ል ተስፋዬ ወልደሥላሴም ቀጥረውኝ ስለነበር ፈራሁ፡፡ በጥቅሉ ወታደሮች እና እኔ ቀርተን አዳራሹ ባዶ ኾነ፡፡ ኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም 15 በሚኾኑ ወታደሮች ታጅቦ መጣ፡፡ ኮምፒውተሩ ላይ “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!” የሚል በትልቁ ጽፌ ስለነበር መጀመሪያ ያየው ያን ጹሑፍ ነው፡፡ ጽሑፉን ሲያየው ፈገግ አለ፡፡ ከዚያ በሶፍትዌሩ በጣም መገረሙን ነገረን፡፡ “እንግሊዘኛ እንኳን በደንብ ሳናውቅ አማርኛ እንዴት ተሠራ? ማነው የሚረዳህ?” የሚሉና መሠል ብዙ ነገሮች ጠየቀኝና በተቻለ መጠን አስረዳሁት፡፡ ጽሑፉና ፕሪንት አድርጌ ሳሳየው የፕሪንተሩን ካምፓኒ ማንነት ጠይቆኝ ማየት ጀመረ፡፡ እኔም የጽሑፉ ምንጭ ሀርድዌሩ ሳይኾን ሶፍትዌሩ መኾኑን ነገርኩት፡፡

ምን ማለት እንደኾነ ጠየቀኝ፡፡ እኔም ለምሳሌ የእርሶ ንግግር ተቀድቶ በካሴት ሬዲዮ ውስጥ ቢያስገቡት እንደሚናገረው ሁሉ ይኼም በሀርድ ዌር መጫወቻ እየታተመ የሚነበብ ቅንብር ነው አልኩት፡፡ ከዚያ ታይፕ እንዲደረግለት ጠይቆኝ ታይፕ ሳደርግ እንዴት ሊኾን ቻለ ብሎ ተገረመ፡፡ ከዚያም የሚያስፈልገኝን ነገር ጠየቀኝ፡፡ እኔም ከብዙ መሥሪያ ቤቶች ትዕዛዝ ተቀብዬ ስለነበር የሚያስፈልጋቸው የውጭ ምንዛሬ እንዲፈቀድላቸው ጠየቅኩት፡፡ ጥያቄዬን ቢቀበለውም ከዚያ በኋላ ምንም ያደረገልኝ ነገር የለም፡፡ የደህንነት ሚኒስትሩም ባስጠሩኝ መሠረት ላገኛቸው ሄድኩ፡፡ ስለ ኮምፒውተሩ አንዳንድ ነገር ጠይቀውኝ በተለይ ለስላላ ሥራ ያግዝ እንደኾን ጠየቁኝ፡፡ እኔም ከስለላ ሥራ ጋር የተገናኘ አገልግሎት እንደማይሰጥ ነገርኳቸው፡፡ ምክንያቱም ያኔ ኮምፒውተሩ የነበረው ወርድ ፕሮሰስ ብቻ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንንም ቢኾን ለተቋሙ የቴክኒካል ሰዎች እንዳስረዳ ጠየቁኝ፡፡ እኔንም በአጋጣሚው በደንብ ፈተሹኝ፤ ገመገሙኝ፡፡ ከጥቂት ቀናት በኋላም አምባሳደር ካሣ የጉብኝት ጊዜዬን መጨረሴን ነግረኝና ወደ አሜሪካ ተመለስኩ፡፡

ግዮን፡- አንተ ከተቃዋሚው ጎራ ከመኾንህ አንፃር እንደሰጋኸው ሁሉ የመንግሥት ሰዎችም ባንተ ላይ መተናኮል አላሳዩም?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- አዎ በመጠኑ ነበር፡፡ ለምሳሌ የደህንነት ሚኒስትሩ ጠርተው ያናገሩኝ “ይኼ ሰውዬ ምንድነው?” የሚለውንም በማየት ነው፡፡ ምክንያቱም ያ ጊዜ ሌላው ቀርቶ ኮምፒውተር ሲባል ፈንድቶ አገር የሚያጋይ ይመስላቸው ነበር፡፡ በሌላ በኩል እኔ በውጪ ሚዲያዎችና ፕሬሶች በኩል የመንግሥትን ፋሽስትነትና ጨፍጫፊነት እጽፍ ነበር፡፡ ምንም የፖለቲካ ሰው ባልኾንም ሰዎች ሲገደሉ ዝም ማለት ስለማልችል እናገራለሁ፡፡ አምባሳደር ካሣ ባይጋበዘኝ ኖሮ አልመጣም ነበር፡፡ ድፍረቱን የሰጠኝ እርሱ ነው፡፡

ግዮን፡- ካነሳኸው አይቀር ከአምባሳደር ካሣ ጋር ቅርበት ነበራችሁ ማለት ነው?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- አምባሳደር ካሣን ብዙም አላውቀውም፡፡ ነገር ግን በጣም ያበረታታኝ ነበር፡፡ አልፎ አልፎም ይጽፍልኝ ነበር፡፡ ኾኖም ግን ያን ያህል የምንቀራረብ ሰዎች አልነበርንም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ጋብዞኝ ከመጣን በኋላ ለኮ/ል መንግሥቱ ስለእኔ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥቶ ነው ያስተዋውቀኝ፡፡ በጥቅሉ ግን በማለፉ አዝኛለሁ፤ ለቤተሰቦቹም መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

ግዮን፡- ዳሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ መቼ ተቋቋመ? ዳሽንስ ለምን ተባለ?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- ዳሽን ኢንጂነሪንግ ስም እንዲኾን የተፈለገው የኢትዮጵያ ትልቁ ተራራ ራስ ዳሽን በመኾኑ እርሱን ለመግለፅ ነው፡፡ ዳሽን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ የተመሠረተው በፈረንጆቹ 1983 ነው፡፡ መጀመሪያ በግሌ ነበር የምሠራው፤ በኋላ ላይ ግን ብዙ ሰዎች ኮምፒውተር እያዘዙ ሲመጡ ዳሽን ኮምፒውተር የሚል መጠሪያ ያለው ኮምፒውተር ከወንድሜ ጋር እያመረትን ማቅረብ ጀመርን፡፡ ኮምፒውተሩ ላይ የአማርኛ ሶፍትዌር በመጫን ነው የምንሸጠው፡፡ በዚህም ትልልቅ ተቋማት ከየሀገሩ እየመጡ ይወስዱ ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ዳሽን ኮምፒውተር የለም፡፡ ብዙ ነገር ስለተቀየረና ሥራው በሌሎች እየተሠራ ስለኾነ እኛ ከእሱ ወጥተናል፡፡ ነገር ግን አንዲት ልጅ ስለ ዳሽን ኮምፒውተር እየፃፈች እንደኾነ ነግራኛለች፡፡ ስለለዚህ ዳሽን ኢንጂነሪግ ወደ ታሪክነት ተላልፏል፡፡

ግዮን፡- በኢትዮፒክ ሶፍትዌሩ ዙሪያ በግለሰብ ደረጃ አስተያየት የሰጡ ሰዎች እነማን ናቸው? ምንስ አሉ?

ኢ/ር ፍሰሐ፡- ፕ/ር አየለ በክሪ የሚባል የኢትዮጵያ ታሪክ ተመራማሪ እና ደራሲ (ያኔ የአፍሪካ ዲፓርትመንት ኃላፊ) የነበረ ሰው ድንቅ አስተያየት ሰጥቶኛል፡፡ እርሱ ኦሮምኛ ተናጋሪ ነው፡፡ “የኢትዮጵያ ፊደል የሁላችንም ነው” በሚል ሰፋ ያለ ደብዳቤ ጽፎ ልኮልኛል፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የዋሺንግተን ዲሲ ሃገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በነበሩበት በዚያን ወቅት በጣም የሚያበረታታ ደብዳቤ ጽፈውልኛል፡፡ በተለይ ሞክሼ ፊደላት ሳይጎድሉ የሶፍትዌሩ አካል ኾነው መቀጠላቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው ጽፈውልኛል፡፡ ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌም በብዙ መልኩ ሲረዱኝና ሲያግዙኝ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የሶፍትዌር ተጠቃሚም እሳቸው ነበሩ፡፡ የቋንቋ ምሁርም ስለነበሩ መስተካከልና መግባት ያለበትን ይነግሩኝና ያማክሩኝ የነበሩ ሰው ናቸው፡፡

ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም እናመሠግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሕዳሴው ግድብ እስካሁን 23 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መሠረተ ድንጋይ ከተጣለ 14 ዓመትን...

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሁለቱ ውሳኔዎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት በቨርቹዋል ባካሄደው 45ኛ መደበኛ...

በ6 የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት እና የጤና ሠራተኞች ገቢ እስከ 50 በመቶ መቀነሱ ተነገረ

በ6 የአፍሪካ ሀገራት የትምህርት እና ጤና ሠራተኞች ገቢ...