ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፓኪስታን ጥያቄ መሠረት ከኢራን ጋር የገቡትንየተኩስ አቁም ማራዘማቸውን አስታወቁ። ትራምፕ የኢራን ወደቦች ላይ የተጣለው እገዳ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ትራምፕ የተኩስ አቁሙን መራዘም ያስታወቁት ከመጠናቀቁ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።
የትራምፕ ውሳኔ ጦርነቱ ዳግም ይቀጥላል የሚለውን ፍራቻ ያስወገደ ሲሆን የሁለተኛው ዙር ድርድርም ቴህራን አቋሟን እስክታሳውቅ ድረስ ተራዝሟል።
ዶናልድ ትራምፕ የተኩስ አቁሙን ማራዘማቸውን ተከትሎ ምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ወደ ኢዝላማባድ የሚያደርጉት ጉዞ መሰረዙን የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
ኢራን ለትራምፕ ውሳኔ በይፋ መግለጫ ባትሰጥም ሁለቱም አገራት ያለ ስምምነት ጦረነቱን ለመቀጠል አንዳቸው ሌላኛቸው ላይ ሲዝቱ ነበር።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት መሠረት በፓኪስታን ጦር አዛዥ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ጥያቄ መሠረት እንዲሁም “የኢራን መንግሥት በከፍተኛ ሁኔታ በመፍረክረኩ” የተኩስ አቁሙ የኢራን መሪዎች እና ተወካዮች “የተቀናጀ ምክረ ሃሳብ ይዘው እስኪመጡ ድረስ” እንዲቀጥል መወሰናቸውን ተናግረዋል።
ትራም ፕበዚሁ መልዕክታቸው ላይ የአሜሪካ ባሕር ኃይል በኢራን ወደቦች ላይ “እገዳውን እንዲቀጥል” አዝዘዋል።የተኩስ አቁሙ ኢራን ምክረ ሃሳቧን እስክታቀርብ እና ውይይቶቹ የሚያመጡት ውጤት ምንም ይሁን ምን እስኪጠናቀቅ ድረስ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ትራምፕ ከዚህ በፊት የተኩስ አቁሙን ለማራዘም ሃሳብ እንደሌላቸው ገልጸው ነበር። ምንም እንኳ ትራምፕ የኢራን ወደቦች ላይ የጣሉት እገዳ እንደሚቀጥል ቢናገሩም ከዚህ ቀደም የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ይህ “ከጦርነት ተግባር” አይተናነስም ሲሉ ኮንነውት ነበር።
በተባበሩት መንግሥታት የኢራን ልዑክ አሜሪካ በሆርሙዝ ወሽመጥ ላይ የጣለችው እገዳ የምታነሳ ከሆነ ንግግሩ ይቀጥላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
BBC
