ዜጎች ስለሚኾነው አብዝቶ መነጋገር የሚገባቸው ጊዜ ነው!

Date:

የሺህ ዓመታቱ ጥንታዊው የኢትዮጵያ ሥነ መንግሥት፣ የሚወቀስባቸው ጎኖችን ባያጣም በትሩፋቶቹ ግን ዓለምን ጭምር ያስደነቁ ወሳኝ መለዮዎች እንደነበሩት አይካድም፡፡ ኾኖም ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ እንደሚለው ብሂል ‹›መደብ›› እና ‹‹ዘውግ››ን ማዕከል ያደረገ ጭቆና ፈጽሟል የሚለው ተረክ ግዘፍ መንሳቱን ተከትሎ እንኩትኩቱ እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ የዘውዱ መንግሥት እና ዐጠቃላይ ሥነ መንግሥታዊ ዕሳቤውም ለመጪዋ ኢትዮጵያ እርሾ መኾን በማይችልበት ጭካኔ ከጥቅም ውጪ እንዲኾን ተደርጓል፡፡ በዚህ መንገድ የኢትዮጵያን አዲስ ምሥል ‹‹እፈጥራለሁ›› ያለው የአስኳላ ሕልመኛም ሀገሪቱን እንግዳ በኾነ የፖለቲካ ባሕል አጠመቃት፡፡

ይኽ ጠበል፣ መንግሥትነት ከሚያጎናጽፈው የነገውንና የተነገወዲያውን ሀገር እና ትውልድ አርቆ ከመመልከት ጸጋ ያጎደለ ሰባራ መድሎት ስለነበር ጎራ ለይቶ መገዳደልን፣ እልም ያለ ዘረኝነትን፣ ሥር የሰደደ ሙሰኝነትን፣ ስግብግብነትን እና ራስወዳድነትን መገለጫው አደረገ፡፡ ጠመንጃ መያዝ ብቻውን ያሻን ለመወሰን፣ የፈለገውንም ለመጫን ኹነኛ መንገድ እንደኾነ ታመነበት፡፡

ታጥቦ አልጠራም ያለው የሽንፍላ ፖለቲካችን አሁናዊ እውነታም ይኼና ይኼ ብቻ ነው፡፡ “ታንኩንም ባንኩንም ይዘናል” የሚል እብሪት ላይ የቆመ ወገን ኹሉ መሻቱን በኃይል ለማስፈጸም ኹለቴ ማሰብ ያላስፈለገውም ለዚህ ይመስላል፡፡ ዛሬ የሚጠመቅ የአምባገነንነት ካቲካላ ነገ ምን ያህል ሕዝብ በ’ሽታ እንደሚያሰክር መረዳቱ የሌለው መንግሥት እንዲህ ባለ ጭካ ማቡካት ውስጥ መዳከሩ የሚጠበቅ የሚኾነውም ለዚህ ነው፡፡ ሀገሩን ጊዜ ጠብቆ ለመበቀል ያደባ ፖለቲከኛ ዙፋን ሲቆናጠጥ የሚያደርገውም ይኼ መኾኑም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ሁሌም አሳዛኙ ትራጀዲ የሚፈጸመው ግን ተስፋን፣ ተድላን እና የሀገር ባለቤትነትን አስቦ በታገለው ሕዝብ ላይ መኾኑ ነው፡፡ አምጦ አምጦ፣ ወልዶ ወልዶ ልጅ እና መንግሥት ያልወጣለት ሕዝብ!

ከሣምንታት በፊት በመዲናችን ዐዲስ አበባ አንዳንድ የመጀመሪያ እና ኹለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች የተፈጸመው ነውር ከፍ ብለን በገለጽነው አግባብ የሚቀመጥ ነው፡፡ የሩብ ምዕተ ዓመቱ የህወሓት አገዛዝ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ቆመውባቸው የነበሩ ካስማዎችን ገዝግዞ ከጣለ በኋላ፣ ለአመል ያህል ‹‹ትንሽዋ ኢትዮጵያ›› በተባለችው ዐዲስ አበባ የቀረውን እንጥፍጣፊ መሠረት በዶማ የመናድ ፈጣን የስግብግቦች አካሔድ እጅግ የሚዘገንን ነው፡፡ በአጭር ቋንቋ ድርጊቱ “ሀገር ጠልነት” ነው፡፡ ይኽ በየትኛውም ለሥነ አመክንዮ ብቁ ባልኾነ መሟገቻ ሊስተባበል የማይችል ኢትዮጵያውያንን እንደ ዜጎች የመናቅ ጥግ ነው፡፡ ጊዜ እና ጉልበትን መከታ አድርጎ የሚፈጸም ሀገርን የማፍረስ መንግሥታዊ ፕሮጀክት ነው፡፡ ‹‹አንድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ›› መፍጠር ዳገት የኾነበት የኢሕአዴግ መንግሥት፣ ፍርስራሹ ተጠርጎ ሳያበቃ ‹‹የአንድ ብሔር የፖለቲካ እና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ መፍጠር›› በሚል ፕሮጀክት መሸጋገሩን ያጤንበት ወለፈንዲ ነው፡፡

ከፍ ብለን እንደጠቀስነው ለኢትዮጵያ ጥንታዊ ሥነ መንግሥት ታሪክም ኾነ ‹‹መንግሥትነት›› ለተባለው ሆደ ሰፊና የአርቆ አሳቢነት ዕሳቤ ባዕድ የኾነው ከተማሪዎች ንቅናቄ የሚነሳው የሀገራችን ትውልድ እንዲህ ባለ የሀገርን ፍርሰት በሚያጣድፍ ተግባር ላይ ተሰማርቶ መመልክት እንግዳ ክስተት መኾኑ ከቀረ ሰንብቷል፡፡ የኢትዮጵያ ነገር አልጋ ሲሉት አመድ ከመኾን አልፎ እኩልነት ኢ ፍትሓዊነት፣ አንድነትም የበላይነት የሚሉ ትርጉሞችን ይዞ የአንድን ክልል ባንዲራ እና መዝሙር በኃይል “እናዘምራለን” ብሎ እስከመፎከር የተደረሰበት ሀፍረተ ቢስነት መጪው ዘመን የትግል እንጂ የተስፋ አለመኾኑን አለት ላይ እንደተቀረጸ ማኅተም አረጋግጦት አልፏል፡፡ በጥቅሉ፣ በመዲናችን አዲስ አበባ መንግሥት መር የኾነው ከፋፋይ፣ ዘረኛ እና አግላይ የእብሪት ፖሊሲ ስለመንግሥት፣ ስለፖለቲካዊ ትግል እና ኢትዮጵያን ዳግም ስለማንበብ የሚሰጠው ትምህርት ቀላል ባለመኾኑ ዜጎች ከኾነው በላይ ስለሚኾነው አብዝቶ መነጋገር የሚገባቸው ጊዜ ነው የሚለው ሳምንታዊ መልዕክታችን ነው፡፡                

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...