ዝነኛው ቤተ እሥራኤላዊ ፖለቲከኛ ጋዲ ይባርከን

Date:

ጋዲ ይባርከን በመባል የሚታወቀው ደስታ ይባርከን በእሥራኤል ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ የሥልጣን ቦታን ከያዙት ቀዳሚው ነው፡፡ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር ተነጋግሮ የነበረው ጋዲ፣ በሀገረ እሥራኤል በአጭር ጊዜ ታዋቂ ፖለቲከኛ ለመሆን የቻለ ነው፡፡ ሉኪድ ፓርቲን ወክሎ ክኔሴት የተሰኘው የሀገሪቱ ምክር ቤት ውስጥ የፓርቲው ወኪል የሆነው ይህ ቤተ እሥራኤላዊ ከዚህ ቀደም “ብሉ ኤንድ ዋይት አሊያንስ”ን ወክሎ የምክር ቤቱ አባልም ነበር፡፡ በፈረንጆቹ 1981 ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለደው ጋዲ ይባርከን ከነቤተሰቡ በ1991 “ኦፕሬሽን ሰለሞን” በተባለው ዘመቻ ወደ እሥራኤል ገብቷል፡፡ በመጀመሪያ ቲቢሪያስ ውስጥ ከኖረ በኋላ ቀጥሎ ኪቡትዝ ሁልዳ ውስጥ መኖር ቀጥሏል፡፡ ሚክቫ እሥራኤል የተሰኘ የአዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ ተምሮ ከጨረሰ በኋላ፣ ወታደራዊ ግዳጁን ጊቫቲ ብርጌድ ውስጥ ፈጽሟል፡፡ ከጦር ቤት ከወጣ በኋላም በሕግ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

ጋዲ ይባርከን ለመጀመሪያ ጊዜ ሉኪድ ፓርቲን ወክሎ የተወዳደረው በፈረንጆቹ 2009 ቢሆንም አልተሳካለትም፡፡ በ2013 የምክር ቤት ተወካይ ለመሆን በድጋሚ ቢሞክርም ለ2ኛ ጊዜ ሳይሳካለት ቀርቷል፡፡ በዛው ዓመት በሬሄቮት የከተማ ምርጫ ላይ የኢትዮጵያ ስደተኞች ጥምረት የሆነውን አህዶትን መርቶ ነበር፡፡ በ2016 ቤሪ የተሰኘውን ተቋም መሥርቷል፡፡ በ2019 በተካሄደው ምርጫ ለመሳተፍ ቴሌም የተሰኘ ፓርቲን የተቀላቀለው ጋዲ፣ ፓርቲው የብሉ እና ዋይት አሊያንስን ተቀላቅሎ በመወዳደር ለማሸነፍ በቅቷል፡፡ ጥምረቱ ካሸነፋቸው 35 መቀመጫዎች አንዱን ያገኘው ጋዲ፣ ከወራት በኋላ በተካሄደው የድጋሚ ምርጫም ማሸነፍ ችሏል፡፡ ይህ የኬኔሴቱ ቆይታው ግን አልዘለቀም ነበር፡፡ ለፓርቲው አመራሮች ወደ ሉኪድ ፓርቲ ልቀይር ነው በማለቱ ከ2020ው ምርጫ በፊት ምክር ቤቱን እንዲለቅ ተደርጎ ነበር፡፡ በሉኪድ ፓርቲ ውክልና ሲያገኝ ከምክር ቤቱ በመልቀቅ የሉኪድ ፓርቲ አባል በመሆን በቀጣይ ምርጫ አሸንፎ ወደ ምክር ቤቱ በድጋሚ ሊገባ ችሏል፡፡

ቤተ እሥራኤላዊው ደስታ ይባርከን በአሁን ወቅት የሀገሪቱ የደህንነት ምክትል ሚኒስትርና የቤተ እሥራኤላውያኑን ጉዳይ የሚከታተል ተቋም ዳይሬክተር ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡ ይህን ሥልጣን ከመያዙ በፊት በተለያዩ መስኮች ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቤተእሥራኤላውያንን እና የሀገሪቱን ሌሎች ዜጎች ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ዘረኝነትን ለመዋጋት የተመሠረተን ጥምረት ሲመራ የነበረ ሲሆን፣ በሪ የተሰኘውንና ከውትድርና ግዳጅ በፊት ወጣቶችን የሚያዘጋጅ ተቋም በመመሥረት ሲመራው ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፣ ቄሲም የተባለ የቤተ-እሥራኤላውያኑ መንፈሳዊ መሪነት በእሥራኤል ተቀባይነት እንዲያገኝ ከሚታገሉት መካከል በግንባር ቀደምነት ፍላጎታቸውን ለማሳካት ላለፏት 20 ዓመታት ሲጥር ቆይቷል፡፡ የሀገሪቱ 21ኛ እና 22ኛው የተወካዮች ምክር ቤት ወይም ኬኔሴት አባል በመሆን ለብሉና ዋይት ፓርቲ ከማገልገሉ ባሻገር፣ አሁን የወከለውን የሉኪድ ፓርቲ እጩ በመሆንም 23ኛው ምክር ቤት አባላትን ተቀላቅሏል፡፡

ጋዲ ይቫርከን ወደ ሥልጣን ከመምጣቱ በፊትም ሆነ በኋላ ከሁሉ ሥራዎቹ በይበልጥ የሚታወቀው ዘረኝነትን ለመፋለም ባደረገው አስተዋጽኦ ነው፡፡ በእሥራኤል ሀገር የነጭ የበላይነት በመኖሩ፣ ጥቁሮች መናቃቸውና ተገቢውን ቦታ አለማግኘታቸው የሚያስቆጨው ይህ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ቤተ-እሥራኤላዊ ዝም ብሎ ተቀምጦ መብቱን ለመጠበቅ አልሞከረም፡፡ ጠያቂ ከሌለ ሰጪና ወሳጅ አይኖርም ብሎ በማመኑ፣ ባገኘው አጋጣሚ የዘር መድሎ እንዳይኖር ከሚታገሉ ጋር አብሮ ሰርቷል፡፡ በአሜሪካ የጥቁሮች መብት ጥያቄ በተጋጋለበት ሰሞን ቤተእሥራኤላውያንም መብታችን ይከበር በማለት አደባባይ ወጥተው ነበር፡፡ በሀገሪቱ ያለውን የዘር መድሎ ለመቀነስ በመንግሥት ውስጥ ሆኖም የሚታገለው ጋዲ የተለያዩ ጥሪዎችን በማድረግ ቤተእሥራኤላያኑ እንደዜጋ ተቀላቅለው እንዲኖሩ በመሥራት ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ የተወለዱት ቤተእሥራኤላውያን እድሜያቸው እየገፋ ቢሆንም፣ የነበረውን የዘር መድሎ ታግሰው እዚህ ወቅት ላይ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ የእነሱ ልጆች የሆኑት ወጣት ቤተእሥራኤላውያኑ ግን በወላጆቻቸው ላይ ሲያዩት የነበረው ግፍና መድሎ እንዲቀጥል አይፈልጉም፡፡ ይህንን ዘረኛ አካሄድ በተለያዩ ወቅቶች አደባባይ ወጥተው በይበልጥ የሚቃወሙት እነሱ ሲሆኑ፣ አሁን ጋዲ የገባበት ምክር ቤትም ዘላቂ የሆነ ፀረ-ዘረኞች የሆነ ሕግ እንዲያወጣ ሲወተውቱ ኖረዋል፡፡ ጋዲ ይባርከን ወደ ምክር ቤቱ ከመቀላቀሉ ጀምሮ የባህል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት አካላትን በዘረኝነት ተግባር ሲወቅስና እርምት እንዲያደርጉ ሲወተውት ቆይቷል፡፡ ይህን ተግባሩን የሚደግፏ በርካታ እሥራኤላውያንም አሉ፡፡ አሁን ድረስ እሱ የደረሰበት የስልጣን ማማ ላይ መድረስ የሚችሉ ቤተእሥራኤላውያን ቁጥር በንጽጽር አነስተኛ እንደሆነ ግን ይነገራል፡፡

ቤተ እሥራኤላውያንን ለመደገፍና ከሌላው ለማቀላቀል የሚበጀተው ባጀት አነስተኛ ከመሆኑ ባሻገር፣ ለአመታት የዘለቀው መድሎ ጠንካራ ስለነበር ያላቸወን ልዩነት ለማካካስ ከባድ እንደሆነ ጋዲ ይናገራል፡፡ በዚህ ረገድ የኬኔሴቱ የመጀመሪያ ቤተእሥራኤላዊ አባል የሆነችው ፒኒና ታማኖሻታ ዘረኝነቱን በይፋ ስትዋጋ ቆይታለች፡፡ ከፈረንጆቹ 2013 ጀምሮ ትውልደ ኢትያጵያውያኑ ቤተ እሥራኤሎች በፖሊስ አላግባብ መድሎ ይፈፀምባቸዋል፣ በኢኮኖሚ ረገድም ከፍተኛ ተጽእኖ ስለሚደረግባቸው አብዛኞቹ ከድህነት መውጣት አልቻሉም እያለች ስትከስና ስትሟገት ኖራለች፡፡ ቤተእሥራኤላዊያኑ በከፍተኛ ቁጥር እስርቤት ይገባሉ፡፡ የማደግ ተስፋቸው እንዲመነምን ስለተደረገም ራሳቸውን ለማጥፋት እየተገደዱ እንደሆነ የ19 አመቱ ቤተ እሥራኤላዊ ፖሊስ መንገድ ላይ መገደሉን ተከትሎ በርካቶች ተቃውሟቸውን አደባባይ ወጥተው ሲያሰሙ በነበረበት ወቅት ይፋ አወጥታ ነበር፡፡ ይህ ወቅትም ለቤተእሥራኤላውያኑ የተሻለ ዘመን እንዲመጣ ዕውቅናና ስልጣን ያላቸው ጋዲ ይባርከንን የመሳሰሉ ግለሰቦች ድምፃቸውን ለአለም ያሰሙበት ነው፡፡

ጋዲ ይባርከን በእሥራኤል ያለውን የዘር መድሎ በይፋ ለመናገር አያመነታም፡፡ የሀገሪቱ የመጀመሪያ ቤተ እሥራኤላዊው ሚኒሰቴር በአንድ ወቅት ስለዘር መድሎ ተጠይቆ የእሥራኤል መንግሥት አሁኑኑ ሊነቃና መድሎውን ሊያቆ ይገባዋል ብሏል፡፡ ስርአቱ ኢፍትሀዊ ነው ብሎ የሚያምነው ጋዲ ይባርከን በተለይ በፍትህ ስርዓቱ ውስት በደንብ ይታያል ይላል፡፡ ነጭ እሥራኤላውያን ፖሊስ ሲያዩ ድህንነት የሚሰማቸውን ያህል ጥቁር እሥራኤላውያንን ግን በተቃራኒው ስጋት ውስጥ ይወድቃሉ ብሏል፡፡ ተመሳሳይ ኃይማኖትና አኗኗር እየኖሩ እንኳን በቆዳ ቀለማቸው ብቻ በስራ መስክ ይገለላሉ፡፡ በደልም ይፈፀምባቸዋል እዛው ተወልደው እንደማንኛውም እሥራኤላዊ የእብራይስጥ ቋንቋን አቀላጥፈው ቢናገሩም ከመድሎና መገለል አይድኑም፡፡ በሀገሪቱ በተካሄዱ ጥናቶች መሠረት፣ በእሥራኤል የሚኖሩ ቤተ እሥራኤላውያን ከ140 ሺህ እንደሚበልጡ ይነገራል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 50 ሺህ የሚሆኑት እዛው የተወለዱ እንደሆኑ ተመዝግቧል፡፡ ከእነሱ በተጨማሪ 400 ቤተ እሥራኤላውያንን ከኢትዮጵያ ለማጓጓዝ የሀገሪቱ ምክር ቤት ከዓመት በፊት ውሳኔ አሳልፎ ነበር፡፡ ቤተ እሥራኤላውያኑ ከወታደራዊ ግዳጅ ወቅት ጀምሮ መድሎ ይፈፀምባቸዋል፡፡ እስር ቤት ከሚገቡ ወታደሮች አብዛኞቹ እነሱ ናቸው፡፡ ከእሥራኤል ጦር ሀይል 4 በመቶ የሚሆኑት ጥቁሮቹ ቤተ እሥራኤላውያን ቢሆኑም፣ በእስር ቤት ከሚገኙት ሴቶች 15 በመቶ በላይና ከወንዶቹ ታሳሪዎች ደግሞ 11 በመቶ ገደማን ይይዛሉ፡፡ ይህን መረጃ ያወጣው የሀገሪቱ የቤት እሥራኤላውያኑ ማህበር ሲሆን፣ ይህ አይነት መድሎ በስራ ቅጥርና በሌላውም መስክ የሚታይ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከሀገሪቱ ህዝብ 1.7 በመቶ የሚሆኑት ቤተ እሥራኤላውያኑ ከአጠቃላይ ታሳሪዎች 3.27 በመቶ ይሆናሉ፡፡ ይህን የመሳሰሉ ስር የሰደዱ የዘረኝነት ተግባሮችን የሚታገለው ጋዲ ይባርከን ስልጣኑን ተጠቅሞ ለውጥ እንደሚያመጣ ያምናል፡፡ በደህንነት መስክ ከኢትዮጵያ ጋር በቅርቡ አዲስ አበባ መጥቶ ስምምነት ያደረገው  ቤተ እሥራኤላውዊው  በወጣትነት ዘመኑ ለዚህ ኃላፊነት በመብቃቱ ለወደፊት ብዙ እንደሚሠራ ይጠበቃል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...