ዝክረ

Date:

ማትሪክ፣ አዴይታትና ተጋዳላይ

አቦነህ አሻግሬ ዘኢየሱስ

የማትሪክ ሥነ ሥርዓት

ኢሕአዴግ አገሪቱን በተቆጣጠረ በዓመቱ ማትሪክ ለመፈተን የተላክሁት ትግራይ ነበር፡፡ እንዴት ማትርክ ፈታኝ ልትሆን ቻልክ? የሚል ጥያቄ የሚያነሱ ከሆነ ታሪካዊ ዳራዉን ልንገርዎ፡፡ እግረ መንገዱዎን የፈተናዉ ሥርዓት እንዴት እንደነበረ ለታሪክ ይረዳሉ፡፡ ከአሁኑ ሁኔታ ጋር አመዛዝነዉ ልዩነቱን ይገነዘባሉ፡፡

ብሔራዊ  የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ይዘጋጅ የነበረዉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኃላፊነት ሥር ነበር፡፡ ስድስት ኪሎ ካምፓስ (አሁን የሬጂስትራር ህንጻ ከቆመበት በስተጀርባ ባሉት ጥቂት ክፍሎች ዉስጥ)፡፡ ያን ያክል የገዘፈ ብሔራዊ  ፈተና ከዝግጅቱ አስከ እርምቱ ይከናወን የነበረዉ ከአምስት በማይበልጡ የሰለጠኑ (ካልቸርድ) ሰዎች ብቻ ነበር፡፡ ዲሬክተሩ አቶ ጌታቸዉ ነበሩ፡፡ ጌታቸዉ አዘወትረዉ ካኪ ሱሪና ሸሚዝ ለባሽ ናቸዉ፡፡ በግቢዉ ለመግባት የሚቀድማቸዉ የማለዳ ወፍ ብቻ ነበር፡፡ ከግቢ የሚወጡት ደግሞ እኛ እንቅልፍ በምንለጥጥበት ሰዓት፡፡ ቅዳሜና እሁድ፣ ብሔራዊና ባህላዊ በዓል ለሳቸዉ የእረፍት ቀን አልነበረም፡፡ ኮስታራና ጭምት ሲሆኑ ለሳቸዉ እረፍት የሚባለዉ ከቢሯቸዉ ወጥተዉ ጢስ እንደ ባቡር እያምቦለቦሉ እግራቸዉን ለማፍታታ ሄድ መለስ፣ ሄድ መለስ ማለት ነበር፡፡

ረዳቶቻቸዉ ሁለት ትንታግ ሴቶች ወ/ሮ ትበርህና ወ/ሮ ተዋበች፣ አስተዳዳሪዉ አቶ እሸቱ ነበሩ፡፡ሁሉም ፈገግታና ትህትና በመጎናጸፋቸዉ በስተቀር በሥራ ሥነምግባራቸዉ፣ ታጋሽነታቸዉና ትህትናቸዉ   እንደጌታቸዉ ነበሩ፡፡ ጸሐፊዋም ሆነች ዘበኛዉ ገና ወደ ግቢዉ ሲገቡ የጥርጣሬና የጥበቃ ነርቫቸዉን ያናዝራሉ፡፡ ወደ ተከለሉት ሁለት ክፍሎች ውልፊት የለም፡፡ ያካባቢዉ ብሔራዊ ተግባር በጥቂት ታማኝና ትጉህ ሰዎች ብቻ የመከናወኑ ልማድ ሳሆን አልቀረም፣ ፈተና ተሰረቀ፣ ፈተና ወጣ የሚል ሀሜት ተሰምቶ አይታወቅም ለዓመታት፡፡ ለሀገርና ለሙያ ታማኝ መኾን ያኔ አልረከሰም፡፡

እዚያ ግቢ እየኖርን፣ የዚያ ሁሉ ሕዝብ ትምህርት ፈተና በማንና እንዴት እንደሚዘጋጅ አንኳን ለማወቅ የሚቻል አልነበረም፡፡ ዲሬክተሩ ለፈታና አዉጭነትና ለፈታኝነት የሚሆኑ ታማኝና ኃላፊነት የሚሰማቸዉን ሰዎች በምን ዘዴ እንደሚለዩ እስካሁን ልረዳዉ ያልቻልኩት ነዉ፡፡ ዋናዉ መርሆዋቸዉ ፈተና አዉጪዉ ሆነ ፈታኙ በነጻነት ኃላፊነት እንዲሰማዉ ማድረግ ነዉ፡፡ እንዲያ ሲባል የአምስቱ የንሥር ዓይኖች ለቅጽበት ይከደናሉ ማለት አይደለም፡፡

የፈተና መስጪያ ጊዜዉ ሲቃረብ ማትሪክ ለመፈተን የሚፈልጉ ሰዎች ፎርም እንዲሞሉ ለዩኒቨርሲቲ መምህራን፣ እንዲሁም የትምህርት ሚኒስቴር ተቀጣሪ ለሆኑ የአዲስ አበባ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን፣ ሱፕሪቫይዘሮች፣ ዲሬክተሮች፣ ለአዉራጃ ሥራ አስኪያጆች ቅጽ ይበተናል፡፡ በምን ተአምርና ስልት እንደሆነ በማይታወቅ ሁኔታ በእነኚህ ጥቂት ሰዎች ማጣራት ተደርጎ ብቃት ያለዉ ለፈታኝነት ይመረጣል፡፡ ሳይመረጥ የቀረዉ ለምን እንዳልተመረጠ እራሱን እየጠየቀ ዓመቱን ይዘልቃል፡፡ ለመፈተን የሚፈልግበትን ከተማ አመልክቶ ከማይፈልገዉ ሥፍራ የተደለደለም ይጨነቃል፡፡ ምደባዉ በግል ጥላቻ እንደሆነ የሚጠረጥር አንድም አልነበረም፡፡ ሥፍራዉ ለዚህ ዝግ እንደሆነ ሁሉም ያምናል፡፡ የመሥሪያ ቤቱ ታማኝነት ከቶ ከጥያቄ የሚገባ አልነበረምና፡፡ ይልቅስ “ባለፈዉ ዓመት ምን አጥፍቼ ይሆን ዘንድሮ ያልተመረጥኩት? አፈታተኔ እንዴት ነበር? ለሥራ ማስኬጃ የተረከብኩት ገንዘብ ከሥራ ላይ የዋለበት ሁኔታ ከጥርጣሬ ላይ ጥሎኝ ይሆን? ታማኝነቴና ኃላፊነት የመወጣት አመኔታ ምኑ ላይ ነዉ ጌታቸዉን ከጥያቄ ያስገባብኝ?” ብሎ ራሱን ይመረምራል እንጂ አይፈርድበትም፡፡ በቀጣዩ ዓመት በተራ ኃላፊነት ከጥብቅ የፈተና ጣቢያ አስተባባሪ ሥር ተመድቦ ይፈትናል፡፡ የቀጣዩን ዓመት የፈተና አስተባባሪነትና የፈታኝነት እድሉ በዚህ ይወሰናል፡፡ ይገርማል ከአምስት ባልበለጡ ሰዎች ይህ ሁሉ ያገር ትልቅ ቁብ ነገር በዝርዝር ሲከናወን፡፡

“ለመፈተን ይህን ያህል ምን የሚያሳስብ ጉዳይ ተገኘ?” ልትሉ ትችላላችሁ፡፡ ለዩኒቨርሲቲና ለሁለተኛ ደረጃ መምህር ማትሪክን እንደመፈተን የሚያጓጓ ነገር አልነበረም፤- በሁለት ምክንያት፡፡ አንደኛዉ የተለያዩ የአገሪቷን ክፍል ለማየት፡፡ አስተማሪን ለቱሪስትነት የሚያበቃ ደመወዝ ስለሌለ በዚህ ሰበብ ነዉ አገር የሚያዉ፡፡ ሁለተኛ እንደ መዝናኛ፤- የዉሎ አበሉ ከሌላዉ መሥሪያ ቤት እጥፍ ያህል ነበር፡፡ በቀን እስከ ብር 8 የደረሰ ይመስለኛል፡፡ ታዲያ በዚህ ገንዘብ ሰበር ቸቻ ነዉ፡፡ አብረዉት ከተመደቡት ሁለት፣ ሦስት አሥርም፣ (እንደተመደበበት የትምህርት ቤት ትልቅነት) ሰዎች ጋር ገንዘብ ያጋጭና በቅናሽ ቀላቢ ይኮናተራል፡፡ ሁሌ ባንድነት ለገበታ ይቀርባል፡፡ ከተጋጨዉ ገንዘብ ጥቂቱ ለማታዉ ባህላዊ መጠጥ መስተንግዶ ይሆናል፡፡ ከጠላ አንስቶ እስከ ኬፍከፌና ጠጅ ይደጋገምና በደራ ጨዋታ እርስ በእርስ መግባባት ይዳብራል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተዋወቁ የእድሜ ልክ ጉዋደኞች ሊሆኑ እንደበቁ እመሰክራለሁ፡፡ ይህ አዉዳመታዊ ማህበረሰባዊ ሱስ ይሆናል፡፡ መች ዓመቱ በደረሰ ያሰኛል፡፡

ኃላፊነቱ የዩኒቨርሲቲዉ ስለሆነ በጣቢያ የፈተና ኃላፊነት የሚመደበዉ የዩኒቨርሲቲ መምህር ነዉ፡፡ ኃላፊ መምህሩን የሚያግዙ፣ በእያንዳንዱ ክፍል ዉስጥ የፈተናዉን ሂደት የሚቆጣጠሩ ደግሞ የሚመረጡት የአዲስ አበባ መምህራን ናቸዉ፡፡ በኦሬንቴሽ ቀን እንዲተዋወቁ ይደረጋል፡፡ የጉዞዉ ዕለት የጣቢያ ኃላፊዉ በሁለት ትላልቅ ቁልፎች የታነቁና በጥንቃቁ የታሸጉ የሸራ ጆንያዎችን አረጋግጦ በመፈረም ይረከባል፡፡ አብሮት ከአቶቡስ ይጫንና ጉዞ ወደጣቢያዉ ይሆናል፡፡

ከፈተና ጣቢያዉ እንደተደረሰ ኃላፊዉ ከነፈተናዉ ወደ ፖሊስ ጣቢያዉ ያመራል፡፡ አንድ ክፍል ዉስጥ በአደራ ይቀመጥና አራት ወታደር እማኞች በፈረሙበት ወረቀት መስኮትና በሩ ይታሸጋል፡፡ በየፈተናዉ እለት እማኞች በተገኙበት እሽጉ አለመነካቱ ተፈትሾ ርክክብ ይደረግና በፖሊስ ታጅቦ ፈተናዉ ከሚሰጥበት ትምህርት ቤት ይደረሳል፡፡ ከከተማዋ የትምህርት ኃላፊና ከተማሪዎች ፊት የጆንያዉ መታሸግና የቁልፉ አለመከፈት ተረጋግጦ የፈተናዉ ትልቅ ፖስታ በግልጽ ይከፈታል፡፡ ፈተናዉ እየወጣ በሥነሥርዓት ለተማሪዉ ይከፋፈላል፡፡ ከየትምህርት ቤቱም ኩረጃን የሚጠብቅ ዲሬክተር ወይም መምህር በየክፍሉ ሊመደብ ይችላል፡፡ የኃላፊዉና የአዲስ አበባ ፈታኞች አንዱ ጣጣ ከአካባቢዉ የተመደበዉን ፈታኝ በዓይነ ቁራኛ መጠበቅ ነበር፡፡ አንዳንዱ ለትምህርት ቤቱ ዝና ሲል፣ ወይ የሚያዉቀዉን ተፈታኝ በማስኮረጅ ለመርዳት አዩኝ አላዩኝን ሲጫወት ተደርሶበት ከፈታኝነት ወዲያዉ ይባረራል፡፡ ይህ ለሥነሥርዓት የተገዛና ማንኘዉንም አድልዎ ሊያስወግድ መሰረት ያገኘ አሰራር ነበር፡፡ ይህ አሠራር ነበር፣ ብሔራዊዉን የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ተአማኒነት ለበርካታ ዐሠርት ዓመታት ጠብቆ ያቆየዉ፡፡… እሰከ 1983 ዓ.ም ድረስ፡፡

ጉዞ ወደ ፈተና ጣቢያ

እግዜር ይስጣቸዉ እነ አቶ ጌታቸዉ፣ ልፈትን ከመረጥኩት ትግራይ ክልል ነበር የመደቡኝ፤ ኢሕአዴግ በገባ በዓመቱ፡፡ ከዚህ ቀደም ትግራይን አንዴ በተማሪ ቱሪስትነት ያየሁ ቢሆንም ኢሕአዴግ ከሌሎች ክፍለ ሀገሮች በተለየ በትግራይ ከተማዎች የእህል ዋጋ እንዲረክስ እንዳደረገና ልማትንም በአድሎአዊነት እያሳለጠ እንዳለ በሰፊዉ በመወራቱ ለህሊናዬ ለማረጋጥ ስል ነበር እዚያ ለመሄድ የመረጥኩኝ፡፡

በትግራይ የተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተመደበዉ ሰዉ በሦስት አዉቶቡስ ሞልቶ፣ ፈተናዉ በጥንቃቄ ተጭኖ፣ በፕሮፌሰር አለማዩ ኃይሌ አጠቃላይ መሪነት ጉዞ ወደ አክሱም ኾነ፤ አክሱም ማእከል ሆና ሌሎች ወደየአቅጣጫቸዉ እንዲሰማሩ፡፡ ለሦስት ሰዓት ከተጓዝን በኋላ ከሹፌሩ ጎን ለአመራር እንዲመች የተቀመጡት ፕሮፈሰሩ ተነስተዉ አጨበጨቡና የዐሥራ አምስት ደቂቃ የቁርስ እረፍት አበሰሩ፡፡ ከእረፍት ሰዓት እንዳበቃ የአዉቶቡስ የጥሩምባ ጥሪ ሲደጋገም አብዛኛዉ እየተጣደፈ ቦታ ቦታዉን ሲይዝ ሁለት ሲኒየር ሰዎች ብቅ አልል አሉ፡፡ ገና ብዙ ርቀት ይጠብቀናል፡፡ ቶሎ ለመድረስም ተናፍቆዋል፡፡ ጥሩምባ ቢደጋገም ብቅ የሚል ጠፋ፡፡ ልጅ እግር የሆነዉ ፈታኝ ወርዶ በየቁርስ ቤቱ አሰሳ አደረገ፤ አላገኛቸዉም፡፡ ሁሉም እየተነጫነጨ ሳለ ሁለቱ ጓደኛሞች ከፊት ለፊታችን ካለች፣ ከደጃፍዋ ጣሳ ከተሰቀለባትና የካቲካላ መለኪያ ከተደረደረባት ጎጆ እየተጣደፉ ወጡ፡፡ የተሳፈረዉ ሁሉ በትችት ጮኸባቸዉ፡፡ መልስ አልተነፈሱም፡፡ ከዚያ በኋላ ለምሳ ሲወረድ፣ሁለቱ እንደገና እንዳጠፉ የሚከታተሉ ሰዎች ፕሮፌሰሩ መመደባቸዉን አወጁ፡፡ ደግነቱ ሁለቱ ከፕሮፌሰሩ ጋር ጓደኛሞች ስለነበሩ ይሄ ሁሉ ከቅሬታ ላይ የጣለ አልነበረም፡፡

ከምሳ በኋላ የነበረዉ የአዉቶቡስ ጉዙ በአያሌዉ የሚያስፈራና የሚያስጨንቅ ነበር፡፡ ገደላ ገደል ከሆነ ጠመዝማዛ ረጅም መንገድ ስንደርስ የፕሮፌሰሩ ቁጣ እያየለ ሄደ፡፡ ሼፌሩን ደጋግመዉ ይገስጻሉ፡፡ ሹፌሩ ግን “እሺ እሺ” ከማለት በቀር የሚያሳየዉ መስተካከል የለም፡፡ የችግሩ ዋና መንስኤ የሹፌሩ ዘና ያለ አነዳድ ነበር፡፡ በዚያ ገደል ላይ የመኪናዉን መሪ በሁለት እጁ ማሽከርከር ሲገባዉ፣ አንድ እጁን ከመስኮት ላይ በቄንጥ ደግፎ በአንድ እጁ አራት ጣቶች ብቻ መሪዉን መደባበሱ ነበር፡፡ ደግሞ ኃላፊያችንን የሚያስጮኸዉ እሳቸዉ ከሹፌሩ ጎን ካለዉ መስተዋት ጥግ ስለተቀመጡ፣ በጠባቡ ቁልቁለት ማዞርያ ላይ የመኪናዉ አፍንጫ ከመንገድ ወጥቶ ወደገደል የደረሰ ይመስል ስለነበረ ነዉ፡፡ ጎማዉ አስፋልቱን ባይለቅም አካሉ ከአስፋልት ወጣ ይል ስለነበረ ገደል እንደገባን እየቆጠሩ ነበር የሚቆጡት፡፡ ሁላችንም እየደነገጥን የጮኽነዉ ሹፌሩ “እሺ” ከማለት አልፎ በመደንገጣችን እየተገረመ ሳይሆን አይቀርም እንደመሳቅ እንደመሳቅ ያደርገዉ ስለነበረም ነዉ፡፡ ለሽንት ተወርዶ ትንሽ እፎይታ እንደተገኘ  ከመሀላችን አንዱ በማስፈራራት ሊበቀለን ብሎ ነዉ፡፡ ቅድም ምሳ ስንበላ እሱንም ማብላት ነበረብን” አለ፡፡ በዚህ አይነት ሰቀቀን አክሱም እንደተወረደ የፈታኞች አመጽ መሪያችን ላይ ተመታ፡፡ “እንዲህ ነፍሳችንን ሸጠን እየተሳቀቅን በዚህ አዉቶብስ አንመለስም፡፡ በአውሮፕላን የማንመለስ ካልሆነ አንፈተንም” ተባለ፡፡ አቶ ጌታቸዉ መቼም ብልህ ናቸዉ፤ ለአመቱ ፈታኞችን ሊያጡ አልፈለጉም፡፤ የአይሮፕላን ቲኬት ተቆርጦ ግልግል ሆነ፡፡   

አዴይ አደታት

አክሱም ማዕከል ከሆነችበት ምክንያት አንዱ ሀዉልቱን የመጎብኘት እድል ለተፈታኙም ለማስፋት ነበር፡፡ እና ሁሉም ወደ ሀዉልቶቹ ሮጠ፡፡ ከፊትለፊት መስክ ላይ አረፍ ብሎ የትክላቸዉን ቅርጽና መጠን ማየት ሲጀመር ሺህ ጥያቄዎች አእምሮን ያብሰለስላሉ፡፡ ሁለት ሺህ ዓመታት በምናብ አስጉዘዉ የጥንት ቅመአያቶችንን የሕዝብ ብዛትና መስተጋብር፣ ሥልጣኔንና ኪሂሎትን ይስላሉ (ያኔ ገና ለወላይታዉ ምኑ ነዉ አልተነገረም)፡፡ ከስሜት ያዥነቱ የተነሳ ከሥፍራዉ ለመለየት ቀኑ መምሽት ነበረበት፡፡

ወደ ገበያ በእግር ጉዞ ስጀምር ከየመንገዱ ሙዚቃ ቤቶች በሚሰሙት ዘፈኖች ግራ ተጋባሁ፡፡ ጥላሁን ገሠሠ፣ አስቴር አወቀ በሞንታርቦ መንደሩን ይነቀንቃሉ፡፡ እንዴ! አልኩኝ፡፡ ገበያ ከእህል ነጋዴ ዘንድ ደርሼ ጤፍ ዘግኜ አየሁ፤ጤፍ አዲስ አበባ በስንት እንደሚሸጥ አጣርቻለሁ፡፡

 “አሀደ ኪሎ ክንዴይ አዩ?” አልኩ፡፡

የአዲስ አበባን እጥፍ ሊሆን ምንም አልቀረዉም፡፡

በአዉቶቡስ መናኸሪያዉ ሳልፍ ሕዝብ ቲኬት ለመቁረጥ ይገፋፋል፡፡ ጠየቅሁ፤ ለማግስቱ አይገኝም፣ ለተነገወዲያ አይገኝም፤ ናፍጣ በከተማዉ የለም፡፡ ትግራይ? እንዴ!

ሲመሽ ወደሆቴል ተመልሼ እራት ስበላ፣ ከቀጣዩ ጠረጴዛ ካለዉ ተግባቢ ሰዉ ጋር ንግግር ጀመርን፡፡ ለምን እንደመጣሁ ከጠየቀኝ በኋላ እሱ ከአዲስአባ የመጣዉ ባለቤቱ ታማሚ ስለሆነች የአክሱም ጽዮንን ጠበል እንዲያመጣላት እንደላከችዉና፣ ከተሳካ ደግሞ ትንሽ የእህል ወፍጮ ፋብሪካ ለማቋቋም መሬትና ፈቃድ ለመጠየቅ እንደሆነ ነገረኝ፡፡ የክልሉ ተወላጅ ባይሆንም ገና ጀማሪ ነጋዴ በመሆኑ ከአዲስ አበባ ባለጠጋ ጋር ከመወዳደር፣ ገና ያልለማ ሥፍራ ይሻል ይሆናል በማለት እንደመጣ አጫወተኝ፡፡

ዋናዉ ችግር የጠበል መያዣ ጠርሙስ ከየት ሊያገኝ እንሚችል ነበር፡፡ እንደዛሬ ሳይሆን ያኔ ጠርሙስ በቀላሉ የሚገኝ አልነበረም፡፡ ቡናቤት እየተዝናኑ ሳለ ድንገት ጠረጴዛ ነክተዉ ወይ ከእጅዎ አምልጦ ጠርሙስ ቢሰበር፣ አንድ ቢራ ጠጥተዉ የሦስት ከፍለዉ እንዲወጡ ይገደዳሉ፡፡ ደግም የሚሸጥበት ሥፍራም አልነበረም፡፡

 “አንድ ዘዴ ግን አስቤያለሁ” አለኝ፡፡

“ምን?”

“የጨጓራ በሽታ ማስታገሻ ሺሮፕ ገዝቼ ሺሮፑን አፈስሼ ባዶ አደርገዉና በሱ ይዤላት እሄዳለሁ፡፡”

ስቅጥጥ አለኝ፡፡ “ሺሮፕ አፍስሰህ?”  

እኔ የመድኃኒቱ ተጠቃሚ ስለነበርኩ ምን ያህል ኪስ እንደሚጎዳ አዉቃለሁ፡፡ ብቻ ተያይዘን ወደ ፋርማሲ ገባን፡፡ በሠላሳዎቹ እድሜ ዉስጥ ያሉ ቀይ ዳማ ደመግቡ ሴት የአበሻ ልብስ ለብሰዉ፣ ሽሩባቸዉን በነጠላ ሸፍነዉ ከባንኮኒ ዉስጥ ተቀምጠዋል፡፡

“ከመይ ዉእልኩም” አሉ ልክ እንዳዩን ብድግ ብለዉ፡፡

ዳህን፣ ከመይ ዉእልክን፡፡ አደይ፣ ሽሮፕ አበኒ፡፡ አለኩ፡፡ ሀበኒ የምትለዉን ቃል በልጅነቴ ጓደኞቼ በምሥጢር ከምትጣፍጥ ነገር ጋር አጣምረዉ አስተምረዉኛል፡፡ ቋንቋ ቢሰባበርም ካግባባ በቂ ነዉ፡፡

“ናይ ምንታይ ሽሮፕ?”

የወጣቱ ነጋዴ አይን እንዴት እንደፈጠነ በማይታወቅ ሁኔታ ባንዴ የመድሀኒት መደርደርያዉን ቃኝቶ፤ ከአናቱ ላይ ወደ ተቀመጠዉ የኦሬንጅ/ቢቢታ ጠርሙስ ጠቆመ፡፡

“ያ ጠርሙስ ይሸጣል? በደንብ እከፍላለሁ፡፡”  

      “ንምንታይ ደሊሁሞ? ”  ወደ ጠርሙሱዋ እያዩ፡፡

“ጠበል ይዤበት ለሚስቴ አዲስ አበባ ልወስድበት ነበር፡፡”

ከተቀመጡበት ወንበር ላይ ወጥተዉ ቆሙ፡፡ ተንጠራርተዉ አወረዱ፡፡ ተረስቶ የቆየ ወይ እንደ ቅርስ የተቀመጠ ይመስላል ሲያዩት፡፡ ይዘዉት ከጉዋዳ ገቡ፡፡ የማጠብ ድምጽ ይሰማናል፡፡

“ስንት ትል ይሆን? ሀምሳ ብር? መቶም ብትል እገዛታለሁ፡፡” አለ እያየኝ በማማከር አይነት፡፡

በጨርቅ እየወለወሉ ገቡና ከባንኮኒዉ ላይ ከፊታችን አስቀመጡ፡፡

“አዴይ ክንዴይ እዩ?” አልኩኝ አዲሱ ጉዋደኛዬ እንዳይበላ ልከራከርለት ተዘጋጅቼ፡፡

      “ንጠበልዩ አይበልኩምኒንዶ?”

“እወ፡፡”

“እሞ ንጠበል መተሀዚ ዋጋ የሀፍልን ዲዩ?”

ነገሩ አልገባንም፡፡ ወጣቱ ነጋዴ መቶ ብር መዝዞ ዘረጋላቸዉ፡፡

“ኖኖኖ ኖ” አሉ ኮስተር ብለዉ፡፡

ልብ ይወጋል፡፡ ለማያዉቁት ሰዉ ጠረሙስን የሚያክል ነገር በነጻ? አመስግነን ስለ ትግሬ ደግነት እየተፈላሰፍን ወደ አንድ ሁለት መባባያ አዘገምን፡፡

ነጋ፡፡ የአክሱም ጸዮን እለት፡፡ ጠረሙሳችንን ይዘን ወደ ቤተክርስቲያን ሄድን፡፡ ልዩ በዓል ነዉ፡፡ በቤቱ የቀረ የለም፡፡ ከዐዉደምሕረቱ ላይ አይቼዉ የማላዉቅ መንፈሳዊ ትርኢት ይታያል፡፡ የጦርነት ማግስት ስለነበረ ሴቱ ሁሉ አንድ አይነት ይመስላል፡፡ ድህነት የደቆሰዉ ቀጫጫ አጭር ሰዉነት የተሸፈነበት የአበሻ ቀሚስና ነጠላ ንጣቱን አጥቶዋል፡፡ ብዙ ሽሩባዎች በሽበት ተወረዋል፡፡ የሁሉም ከሲታ ግንባርና ፊት እየተጣጠፈ መስመር በመስመር ሆኖዋል፡፡ የጦርነት አሻራ ሁለመናቸዉ ላይ ታትሞዋል፡፡ ሁሉም በትንሽ መሰከንባይ ወይ በነጠላ ንፍሮ ይዘዋል፡፡ ክብ ሰርተዉ “እግዚኦ ማረነ..” የሚል ቃል ባለበት፣ ማርያም ጽዮንንም በሚጠራ አንጀት በሚበላ አራራይ ዝማሬ ይማለዳሉ፡፡ ልብ የሚነካ የሰዉነት እንቅስቃሴ ያሳያሉ፡፡ አጅግ ከባድ የሆነ ሀዘኔታን የሚጭር ትዉፊት ነበር፡፡ እንዲያ እያሉ ደግሞ ላገኙት ሁሉ፣ ለኛም ጭምር ንፍሮዉን እየዘገኑ ያሲዛሉ፡፡ የቀረቻቸዉን አሙዋጠዉ ሲለግሱ ያማል፡፡ የትኛዉ የጦርነት ክፋት ይሆን እንዲህ ልባቸዉን የሰበረዉ? ማርያም ጽዮን ዳግም ጦርነት እንዳታሳየቸዉ ነዉ መሰል “ሰላም ሰላም” የሚልም ቃል ያወጣሉ፡፡ አወይ ምስኪን እናቶች፡፡

ምሳ በልተን፣ ወጣቱ ነጋዴ ወደ አቤቱታዉ ሄዶ ሁለት ሰዓት ሳይሞላ ተመለሰ፡፡ ከከተማ መሀል ቁልፍ ቦታ መርጠዉ እንደሰጡትና ፈቃዱንም እንዳገኘ፣ ኑሮዉንም እዚያ እንደሚያደርግ በደስታ ነገረኝ፡፡ እንዴ! አይ ዘመን!

በማትሪክ መፈተኛ ጣቢያ

በማግስቱ ጆንያዬን ከትከሻዬ አድርጌ ወደመፈተኛዬ ትንሽ ከተማ ደረስኩ፡፡ በደንቡ መሠረት ወደ ፖሊስ ጣቢያ አመራሁ፡፡ እንደደረስኩ ያጋጠሙኝ ፖሊሶች አልነበሩም፡፡ ጥብቆ ሸሚዝና ቁምጣ የለበሱ፡፡ የእጅ ቦምብ በወገባቸዉ ዙርያ የታጠቁ፣ ሸበጥ የተጫሙ አፍሮዎች ነበር የተቀበሉኝ፡፡ ከክፍለሀገሩ የትምህርት ሥራ አስኪያጅ በስልክ ይሁን በሬዲዮ ቀድሞ ተነግሮዋቸዉ ስለነበረ፣ ጆንያዬን ከትከሻ አዉርደዉልኝ ይዘዉኝ ከኃላፊዉ ቢሮ አሰገቡኝ፡፡ ኃላፊዉ ቆምጨጭና ረጋ ያሉ ናቸዉ፡፡

“ፈተናዉን ፖሊስ ጣቢያ ዉስጥ አሽጌ በአደራ እስከ ጠዋት ለማስቀመጥ ነበር፡፡” አልኳቸዉ፡፡ ብድግ ብለዉ ወደ ዉጭ ወጥተዉ ተመለሱ፡፡ ጆንያዉን ብድግ አድርገዉ እንድከተላቸዉ በትግርኛና በምልክት ነገሩኝ፡፡ እንደደንቡ አሽገን ወደ ቢሮዋቸዉ እንደተመለስን ደብተራቸዉን እያገላበጡ ስለትግሉ ዓላማ መሠረታዊ ትምህርት ሊሰጡኝ ጥረት አደረጉ፡፡ አማርኛ አነጋገራቸዉ እንደትግራይ ከተሜ ልጆች መልእክትን በበቂዉ ሊያስተላለፍ የሚችል አልነበረም፡፡ የተሰጠኝንም ትምህርት ዓመቱን ሙሉ በሬዲዮና በቴቪ የሰማሁት ስለነበረ አዲስ እዉቀት አላገኘሁበትም፡፡

ጥሩ ሆቴል የት እንደሚገኝ ጠየቅኋቸዉ፡፡ ሁለት ተጋዳላይ ጠርተዉ ከተመካከሩ በኋላ ሻንጣየን ተሸክመዉ ከኋላ አጅበዉኝ ካንዱ ወሰዱኝ፡፡ ፊትለፊቱ ሲታይ ፎቅ ያመስላል፡፡ ወደ ዉስጥ ሲገባ አነስ ያለች ቡና ቤት ሆና፣ ወደ ዉስጥ ስንዘልቅ በኤል ሼፕ የተሰሩ ትናንሽ የየጭቃ ምርግ መኝታ ክፍሎች አየሁ፡፡ በመስኮታቸዉ ስቃኛቸዉ አንዱ ከሌላዉ የሚመረጥ ስላልነበረ ወደጥግ ካለዉ ክፍል ሻንጣዬን አስገባሁ፡፡ ተጋዳላይ ከአንድ በአርባዎቹ እድሜ ዉስጥ ካሉ እመቤት ጋር ከበረንዳዉ ላይ አፍ ለአፍ ገጥሞ ይንሾካሾካል፡፡

“አዴይ ኪራዩ ሰንት ነዉ?”  ቀድሞ ይከፈል ይሆናል፡፡

“አርባአተ ቅርሺ፡፡”

አራት ብር ያክል ዉድ ከሆነ የከተማዋ አንደኛ ሆቴል መሆኑዋን አስጠረጠረኝ፡፡ ቆጥሬ ልሰጣቸዉ ስል፤       “የሚያስሾኩል አይደለም፡፡ ገና ይቆዩ የለ እንዴ? አንድ ላይ ይከፍላሉ፡፡” አሉ፡፡

“ለምለማ ቀልጥፊ፣ ብን አቀራርቢ፡፡” ወንበር ከበረንዳዉ አወጡልኝ፡፡ ጥቁር እንግዳ እንደመጣበት ነጠላቸዉን ከወገባቸዉ አስረዉ ጉድ ጉድ ማለት ጀመሩ፡፡ መጥረጊያ ይዘዉ ሻንጣዬ ያለበትን ክፍል እስኪጠራርጉ የቡናዉ ቁሌት አካባቢዉን አወደ፡፡ በመሃል አንዱ ተጋዳላይ ጀሪካን ይዞ ወደሳቸዉ ተጣደፈ፡፡ ያቺ ክፍል በጥቁር የተቃጠለ ጋዝ ከሌሎቹ በልጣ ስትደምቅ ከሩቅ ታየችን፡፡ ሽንብራ አስቆልተዉ ከነማቅረቢያዉ አስቀምጠዉልኝ ከፊትለፊቴ ተቀምጠዉ ጨዋታ ጀመሩ፡፡  ከአዲስ አበባ ከብጻይ መለስ ዜና እንደተላከ የመንግሥት ባለሥልጣን እንጂ እንደተራ ማትሪክ ፈታኝ አልነበረም ሲያወሩኝ፡፡ ከተማዋ በደርግ ጊዜ የወታደር ሰፈር ስለነበረችም በቋንቋም ለመግባባት ሳንካ አላጋጠመንም፡፡ ወዲያዉ ድንገት አንድ ነገር ያስታወሱ በሚመስል ሁኔታ ብድግ ብለዉ፣ተነጥላ ያለችዉን ክፍል ከፍተዉ ገቡ፡፡ እቃ እያወጡ ከባለጋዝዋ ክፍል እየተመላለሱ ያስገባሉ፡፡ በመጨረሻ የገባዉ በትልቅ መስታዋት ያለ ጉርድ ፎቶግራፋቸዉ ነበር፡፡ ብርድልብስ ወደዉጭ አዉጥተዉ በዱላ ከነረቱ በኋላ ተመልሰዉ ወደ ክፍሉዋ እየገቡ፣-፡   

“ቡና እሰኪወርድ ኑ አረፍ በሉ፡፡” በመስኮት ወደ ዉስጥ ሳይ በፋሚሊ አልጋ ያበደ ባለቁምሳጥን ሰፊ መኝታ ቤት ነዉ፡፡

“እንዴ ይሄ መኝታ ቤትዎ አይደለም እንዴ”

“ዋይ አንግዳ አይደሉም! ይምጡ፡፡” ሻኝጣዬን ወደክፍሉዋ አዘዋወሩ፡፡

“አዴይ፣ በፍ . ጹ . ም አይሆንም፡፡ ነዉር ነዉ፡፡”

ከብዙ ቆልፎች መካከል አንዱን ፈልቅቀዉ በግድ አስረከቡኝ፡፡ ቡና በነጻ ጠጥቼ አረፍ አልኩ፡፡ አመሻሹ ላይ እራት ልበላ ከበረንዳዋ ወጣሁ፡፡ በልዩ የተዘጋጀ በያይነቱ እየጎረስኩ እያለሁ አንድ ጋንታ ተጋዳላይ በሙሉ ትጥቅ በሰልፍ ገብቶ በመሰላል ወደ ፎቅብጤዋ አመራ፡፡ በመጀመርያ ደነገጥኩ፡፡ በኋላ ሳስብ ለደህንነቴ ጥበቃ ሊሆን እንደሚችል ገምቼ በምስኪንነታቸዉ ተገረምኩ፡፡

የፈተና እለት

በደንቡ መሰረት እኚያ የጣቢያዉ ኃላፊ እማኝ በሆኑበት የፈተና ወረቀቶችን ከፍቼ ለተማሪዉ አደልኩ፡፡ ወንበር ስበዉ ሲቀመጡ ፈተና ለማስጀመር ታዛቢነት እንጂ የማይፈተን ሰዉ ባካባቢዉ እንዲኖር ሕጉ አንደማይፈቅድ ሥነግራቸዉ ጠመንጃቸዉን አዘቅዝቀዉ ወጡ፡፡

የተፈታኞች ሁኔታ ግን ድሮ ከማዉቀዉ በጣም ተለየ፡፡ በፈተና ጊዜ ለመኮረጅ አንዳንዱ አዩኝ አላዩኝ እያለ ዓይኑን ወርወር፣ ቆርጠጥ ማለቱ አንግዳ ነገር አልነበረም፡፡ የነዚህ ተፈታኞች ግን ግልጽና ዓይናዉጣ ሆነብኝ፡፡ ለመቆጣጠር መቆጣቱ ሆነ ማስፈራራቱ ዉጤት አላስገኝ አለ፡፡ አፍጥጬ እያየኋቸዉ፣ አፍጥጠዉ እየተነጋገሩ ሲኮርጁ የምይዘዉ የምጨብጠዉ ጠፋ፡፡ ከዉጭ የቆሙትን ተጋዳላዮች በእጅ ጠርቼ በቶሎ ዋናዉን እንዲጠሩልኝ አደረግሁ፡፡ ከመቅጽበት ደረሱልኝ፡፡ ችግሩን ካስረዳኋቸዉና ሕጉንም ካብራራሁላቸዉ በኋላ አርፈዉ የማይፈተኑ ከሆነ ዩኒቨርሲቲ ሪፖርት አድርጌ አጠቃላይ ፈተናቸዉ እንደሚሰረዝ ነገርኩዋቸዉ፡፡ እሳቸዉም በትግርኛ ከመከሯቸዉ በኋላ የአይጥና የድመት ጨዋታ እየተጫወትን የጠዋቱ ፈተና በመከራ አለቀ፡፡

ለከሰዓት በኋላ ፈተና በቦታዉ እንደደረስኩ ዋናዉ ተጋዳላይ ወደኔ መጡና ቅሬታ ተናገሩ፡፡ ከመጠን በላይ ቁጥጥር በማድረግ ልጆቹ መልስ ማሰብ እንዳይችሉ እያደረኩ እንደሆነና በዚያ ዐይነት ከቀጠልኩ ተማሪዎች ፈተና መሥራት አንደማይችሉ ኮስተር ብለዉ ነገሩኝ፡፡ መኮራረጅን ለመግታት የሚቻለዉ ሁሉ የግድ መደረግ እንዳለበት፣ ካልተኮራረጁ ቃል እንደማልተነፍስ፣ ክልክል ቢሆንም ከክልፍ ተቀምጠዉ ሁኔታዉን እንዲታዘቡ ነገርኳቸዉ፡፡  

በተስማማነዉ መሰረት ከክፍል እንደገባን ተማሪዎች እየተነሱ ኮነኑኝ፡፡ ጦርነቱ በቅርብ በማለቁ ያልተዘጋጁ እንደሆነና ከምሳ በፊት ወደሌሎች ከተማዎች ደዉለዉ በነጻ ተለቅቀዉ እንደልባቸዉ ሲኮራርጁ እንደነበረ መስማታቸዉን፣ እኔም የአእምሮ መጨነቅ ዉስጥ እንደከተትኩዋቸዉ በስሜት ተናገሩ፡፡ በማባበል መልክ የሞከርኩት ሳይሳካ ሲቀር የክልሉ ትምህርት ሥራ አሰኪያጅ ዘንድ እንዲደወልልኝና እሳቸዉ ጠዋት መጥተዉ ባሉበት የአሁኑ ፈተና ነገ እንደሚሰጥ ሳስረዳቸዉ ዋናዉ ተጋዳላይ ነገሩ አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት ገሰጹዋቸዉ፡፡ ከሞላ ጎደል የእለቱ ፈተና በአንጻራዊ ሰላም ተጠናቀቀ፡፡ ለመቀሌ የቢሮ ኃላፊዉ ችግሩን በስልክ ሥነግራቸዉ አዝነዉ ሁሉም እንደሚስተካከል ቃል ገቡ፡፡ እዉነትም በሌሎች ቀናት ደንቡን አሙዋልቶ ተጠናቀቀና የመልስ ኮሮጆዉ ከፖሊስ ጣቢያ ታሸገ፡፡

ሥራዬ በመጠናቀቁ ከተማዋን ተዙዋዙሬ ለማየት ከበር እንደወጣሁ የተፈተኑት ጎረምሶች በሙሉ ከሆቴልዋ ደጃፍ ተሰብስበዋል፡፡ አመጽ መነሳቱና እኔ ላይ ጥቃት መታሰቡ ተሰማኝና ወደ ሆቴሌ ተመለስኩ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሁለት ጎረምሳዎች ፈገግ እያሉ ወደ እኔ መጡ፡፡

“መምህር የአገራችንን ጠላ ልንጋብዞት ነዉ የመጣነዉ፡፡ ሁሉም ዉጭ እየጠበቀዎት ነዉ፡፡” አሉ በትህትና፡፡ መጠንቀቅ ነበረብኝ፡፡ ፈታኝ ከተማሪ ጋር ግንኙነት እንዲያደርግ እንደማይፈቀድና በዉጤት ለመርዳት እንደማይቻል ሥነግራቸዉ፤-

“ዋይ መምህር፡፡ እንደሱ አይደለም፡፡ ፈተናዉማ አልቆዋል…”

የመጣዉ ይምጣ ብዬ ግብዣዉን ተቀበልኩ፡፡ ያ ሁሉ እንደ አንበሳ ሲያገሳብኝ የነበረ ወጣት በፈገግታና በትህትና በየተራ ጨበጠኝ፡፡ መደብ ላይ ተቀምጠን እኩለሌት ድረስ በፍቅር ስንጨዋወት ቆየን፡፡ አጅበዉኝ ከቤት አደረሱኝ፡፡ ስለፈተና ያነሳ አልነበረም፡፡

ማትሪክ ቦጠለቀ

ከሁለቱ መንግሥታት ዘመን በተለየ ይህ የኢሕአዴግ ዘመን የማትሪክ ፈተና ሁኔታ ያመላከተኝ ነገር ቢኖር አደገኛና አዝቃጅ አካሄድ መጀመሩ ነበር፡፡ የማትሪክ ሕግና ደንብ በጉልበት ተጥሶ በክልላዊ ወገንተኛነት፣ ያጠናም ያላጠናም ተማሪ ዩኒቨርሲቲ እንዲገባ ብሔርተኝነት መሰረት እንደሚሆን አዝማሚያ የታየኝ ያኔ ነበር፡፡ እንደተፈራዉ የፈተና መኮራረጅና መልስ በመምህራን ተሰርቶ ተማሪዉ እንዲገለብጠዉ ማድረግ፤ እንዲሁም የግል ትምህርት ቤቶች ነጻ አዉጪ ዐይነት ሆነዉ፣ ኩረጃና መልስ ማስተካከያ በነጻነት እንዲካሄድ ለንግዳቸዉ ሲሉ ፈታኞችን በረብጣ ብር እንዲገዙ ማድረግ፣ይህ ሁሉ እንዲመቻች የማትሪክ ኃላፊነትን ከዩኒቨርሲቲ ሥር አዉጥቶ የኢሕአዴግ መንግሥት እንደፈለገዉ የሚቆጣጠረዉን የብሔራዊ  ፈተና ድርጅት ማቋቋምና ወደ መሀይምነት የሚያስጉዝ የትምህርት ፖሊሲ መንደፍ፣ የዬኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተናን ሥርዓት የሌብነት፣ የማጭበርበር የዘረኝነት፤ የደንቆሮነት ዐዉድ አደረገዉ፡፡

ባለፉት 27 ዓመታት ዩኒቨርሲቲዎች እንደ አሸን እየፈሉ፣ ሥማቸዉን አጥርተዉ ለመጻፍ እንኳን የማይችሉ የመልስ ሌቦች፣ ትምህርት የመከታተል አቅም ሳይኖራቸዉ በኮሌጆችም ዉስጥ ያለከልካይ እየተሰራረቁ ያለ እዉቀት በገፍ የድንቁርና ዲግሪ ጫኑ፡፡ ትምህርት ጨርሰናል እየተባለልኝ ድል ያለ መመረቂያ ድግስ እየተደገሰ፣ ከጠጡት ጠላ፣ ቢራና ዉስኪ ፊኛቸዉ በሚንዠቀዠቀዉ አሲድ ይህቺን ቅድስት ምድር አነተቧት፡፡ ሌቦቹ በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸዉ፣ ይዘዉ የወጡት እዉቀት ቢኖር፣በቃላት ድምጸት ጎራ የተገነባ ክፋትን፣ ጨካኝነትን፣ ጥላቻ፣ ራስ ወዳድነት፣ ጎጠኝነት፣ ዘረኝነት፣ የበታችነትን፣ ጥብቆነትና እብሪትን ብቻ ሆነ፡፡ አይን የፊቱን ብርሀን ማየት ሲሳነዉ፣ ጀርባ የኋለቱን ጨለማ ለማየት አፈጠጠ፡፡ የሰዉ ልጅ ክቡርነትና የነፍስ እሴት ከአንድ ሊትር ዘይት ዋጋ በታች ሆነ፡፡ ሰዉን ማረድ፣ መበለት፣ መተልተል፣ መቀቀል፣ መብላት፣ መጥላት፣ መበቀል፣ አስገድዶ መድፈር፣ማቃጠል፣ ማሥራብ፣ ማሰደድ፣ መዝረፍ፣ ማታለል፣ ማጭበርበር፣ መዋሸት በኩራት የሚከናወን አዉሬአዊ የእለት ተእለት ተግባር ሆነ፡፡ 

እና ማትርኪዬ እንዲያ ፖለቲከኛ ሆና ሕዝብና መንግሥትን ለማዉደም ወደ ተካነ ጨካኝ የነፍስ ሌባ መፈልፈያ መድረክነት ተቀየረች፡፡ ደርዘ ብዙ መዘዝዋ ለኢትዮጵያ ብዙ ሆነ፡፡ ገና መች ተነካና፡፡ 27 ዓመት የገነገነን አዉዳሚ የአገር ሥርዓተ ትምህርት ለማስተካከል ስንት 27 ዓመታት ይፈጅ ይሆን?

አሎሄ አሎሄ አገሬን ለምን ተዉካት? “ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፡፡ እሱም ይሰማታል” ስትል ትንቢት አሥነግረህ አልነበረምን? ምነዉ በቃሽ ብትላት?

ኤዲያ! እኔንም ዝረፍ ዝረፍ አለኝ — ቅኔ፤

የድሮዉ ሊቅ ገራገር ነዉ፣ ሥም ማዉጣት አይችልበት፣

ሰረቀ- ብርሀን ይለዋል የሰማዩ ዉበት ስቦት፤

ጠላ ጠማቂዉ ዛሬ ዛሬ በሺህ ክንድ ይበልጠዋል፣

ሰረቀ-ማትሪክ ብሎ ጠርቶት ከመሬት ይተክለዋል፡፡

የጥንቱ …. ሩህ አዳሪ፤

ዘመናይ ….ሰዉ መታሪ፡፡

ይበል !ድንቅ በሉኝ እባካችሁ፡፡ሰላም!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...