Home ክለሣ ድርሳን የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ትግል የሚያስቃኘውና የታሪክ ጉድለታችንን የሚሞላው መፅሐፍ

የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ትግል የሚያስቃኘውና የታሪክ ጉድለታችንን የሚሞላው መፅሐፍ

ሠሎሞን ለማ ገመቹ.

‹‹በመለዮ ለባሹ ግንባር ቀደምትነትና በጭቁኑ ሰፊው ሕዝብ ተባባሪነት የተገኘው ለውጥ ካስገኛቸው ጥቅሞች አንዱ ድርብ ጭቁን የሆነውን ሰፊው ኢትዮጵያዊው እስላም በገዛ ሃገሩ እንደባይተዋር ተቆጥሮ ተነፍጎት የነበረውን የኃይማኖት ነፃነት ማግኘቱ ነው፡፡… የተገኘው የኃይማኖት ነፃነት የአብዮቱ ፍሬ ሲሆን አብዮቱ ፈሩን ሳይለቅ እንዲራመድ ሕዝበ-እስላሙ በበኩሉ ከብሔራዊ ዴሞክራሲያው አብዮት ጋር ተቀናጅቶ መደራጀትና መንቃት ይኖርበታል›› /የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባዔ መልዕክት 1968 ዓ.ም/

ከፍ ሲል በጥቅስ የተቀመጠው አንድ ንዑስ አንቀጽ የተወሰደው ‹‹ለሙስሊሙ መብት አለመጠበቅና አለመጠናከር ጠላቱ ራሱ ሙስሊሙ እንደሆነ…›› (ገጽ 264.) አስረጅ የሚሆኑ ሰነዶችን አያይዞ በማቅረብ ጭምር በቅርቡ ለንባብ ከበቃው ‹‹ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና የመጅሊስ ፈተና›› የተሰኘ ታሪካዊ መፅሐፍ ገጽ 257. ነው፡፡   

ፀሐፊው አቶ (ሐጂ) ሰዒድ መሐመድ አወል፡- ‹‹መፅሐፉን ለመፃፍ ያሰብኩት የአሥራ ሁለት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር፡፡ በሐሣቤ መሠረት በውስጤ እንደ ሽል ሲገላበጥ የኖረውን ታሪክ ለመክተብ በ1984 ዓ.ም ተነሳሳሁ፡፡ ከሦስት ዓመታት በኋላም በ1987 ዓ.ም ለመፅሐፉ ግብዓት የሚሆኑ ቀዳማይ፣ ጠቃሚና አስተማማኝ መረጃዎችን በማግኘቴ ያገኘኋቸውን ሰነዶች በታሪካዊው መፅሐፍ ውስጥ ሊኖራቸው የሚገባውን ሥፍራ እየለየሁ የፅሑፉን ሥራ ወደማደራጀቱ ተግባር አለፍኩ፡፡ ግን የማደራጀቱ ተግባር በ1987 ዓ.ም ባጋጠመኝ የመታሰር ክፉ ዕጣ-ፈንታ ምክንያት ተጓተተ፡፡ ሰባት ዓመታትን በእሥራት አሳልፌ ከወህኒ በወጣሁ ማግስትም ሥራው እንደ አዲስ በልዩ ትጋትና እልህ ቀጠለ፡፡ እነሆ የኅትመት ብርሃን እስኪያገኝ በጥቅሉ ከሃያ ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ‹ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና የመጅሊስ ፈተና› የተሰኘው መፅሐፌ፤ ሐምሌ 24 ቀን በዕለተ ቅዳሜ ከጠዋቱ ሦስት እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ባለው ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ኪነ-ጥበባዊ አዳራሽ ለመመረቅ በቃ›› ይለናል፡፡

ዳጎስ ጠብሰቅ ያለውን፣ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ ቁም-ነገር ያቋተውን፣ በርካታ ሠነዶች ያጨቀውንና በአሁኑ ሰዓት በጃአፋር የመፅሐፎች መደብር በኩል ገበያ ላይ የዋለውን ተመራቂ መፅሐፍ አንደኛው አስተያየት ሰንዛሪና የዩንቨርስቲ መምህር የሆነው ዶክተር እንድሪስ፡- ‹‹በእኛ ደረጃ የምናበረክታቸው ሥራዎች ከዚህኛው ሥራ ጋር ሲነፃፀሩ፤ ይህ ሥራ ለእኔ ያለ ምንም ማጋነን ለፒ.ኤች.ዲ ማሟያ ወይም ‹ዲዘርቴሽን› በቂ የሚሆን አገልግሎት ሊሰጥ የሚችልና የመፅሐፉንም ፀሐፊ ለዶክትሬት ዲግሪ የሚያበቃው ግብዓት መሆኑን ግልጽ ለማድረግ እውዳለሁ›› በማለት ሞቅ ያለ ሞገስ ሰጥቶታል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ደረጀ ገብሬ፣ የጅማው ንጉሥ አባጅፋር የልጅ ልጅ የሆኑት አባቢያ አባጆቢርና ሌሎችም ታላላቅ ዕንግዶች የታደሙበትን የምረቃ ሥነ-ሥርዓት መድረክ ‹‹ከየትኛው ትውልድ ውስጥ እንደሆነ ለማወቅ የሚያዳግተው፣ ግን ደግሞ ሁሉንም ትውልድ የማገናኘት ክህሎትን ከተፈጥሮ የተቸረ የሚመስለው…›› ፣ የመፅሐፉን ሥነ-ፅሑፋዊ ይዘትና ቅርፅ መልክ በማስያዝ ረገድ ‹‹ሙያዊ  ድርሻውን በብቃት ተወጥቷል›› የተባለለት ሑሴን ከድር መርቶታል፡፡ ጋዜጠኛ፣ ተርጓሚና ሃገራዊ ጉዳዮችን ተንታኝ የሆነው አቡበከር ዐለሙ፣ ዶክተር መሐመድ ዓሊ፣ ደራሲ አቶ ተሾመ ብርሃኑ፣ ዶክተር እንድሪስ መሐመድ፣ የታሪክ መምህር ኢብራሂም ሙሉሸዋ መፅሐፉን በተመለከተ አጠር፣ መጠን፣ ዕምር፣ ቅንብብ ያለ ሐሣብ፣ አስተያየትና ምልከታዊ የዳሰሳ ቃሎችን አቅርበውበታል፡፡ 

መፅሐፉ በዚህ የመረጃ ዘመን ከሕዝብ ኑሮ፣ ከድርጅት ታሪክ ወዘተ. አኳያ ፀሐፊው ሰይድ መሐመድ አዲስ ነገር ያሳየበት ስለመሆኑ ስለ ዕውቀት ዕውቀቱ ባላቸው ምሁራን በመድረክ ተመስክሮለታል፡፡ ፀሐፊው ‹‹የኅብረተሰብን ታሪክ በመተረኩ ረገድ አዲስና የራሱ የሆነውን ድርሻ ያበረከተበትም ነው›› ተብሏል፡፡ ‹‹የመፅሐፉ አካል እንዲሆኑ የተደረጉት ሰነዶች እያንዳንዳቸው በፊደል ተለቅመው፣  እንደገና በአግባቡ ተፅፈው መቅረብ ሲኖርባቸው እንዳሉ እንዲቀመጡ መደረጋቸው የሚደገፍና የሚበረታታ ታሪክን  ለባለታሪኩ የማድረስ አሠራር ባይሆንም፤ ለልዩ ልዩ ሥራ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉና በጣም ሊገኙ የማይችሉ ሰነዶች በመፅሐፉ ውስጥ መገኘታቸው የፀሐፊውን ታላቅ አስተዋፅዖ በግልጽ የሚያመለክት ነው›› የሚለው አስተያየት የተሰነዘረበት መፅሐፍ፤ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ የኢትዮጵያ ሥነ-ፅሑፍ አካል ሆኖ የተገኘ መፅሐፍም ነው፡፡

መፅሐፉ ‹‹የአስረጂነትና የነበይነቱ ሚና የጎላ ነው›› የተባለለትም ሲሆን ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች የሕይወት ውጣ-ውረድ አኳያ የነበሩትን፣ የሆኑትን፣ መሆን ‹‹ይገባቸዋል›› የተባሉትን ጉዳዮች ቁልጭ አርጎ እንደሚያሳይም በገምጋሚዎች አንደበት ተመስርክሎለታል፡፡  እንደዚሁም ‹‹ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችና የመጂሊስ ፈተና›› የተሰኘው መፅሐፍ ጥቅል ይዘት፤ ታሪኩ የተነገረለት ኢትዮጵያዊ ወገን ‹‹ወደፊት መሥራት ያለብኝ ምንድን ነው?›› ብሎ ራሱን እንዲጠይቅ የማድረግ አቅም እንዳለውም በምርቃት ሥነ-ሥርዓቱ መድረክ ተነግሮለታል፡፡

በቀደምት የኢትዮጵያ ደራሲዎች ማኅበር ዋና ፀሐፊ ሆነው ያገለገሉት፣ በኩራዝና በበስተኋላው ‹‹ሜጋ›› አሳታሚ ድርጅት ለኅትመት የሚቀርቡ መፅሐፎች ገምጋሚ የነበሩና በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የሥነ-ፅሑፍና የፎክሎር ትምህርት መምህር የሆኑት ዶክተር መሐመድ ዓሊ፤  መፅሐፉ ከ370 በላይ ሰነዶችን ማካተቱን፣ የተካተቱንት ሰነዶች ማሰባሰብ በራሱ በጣም ከባድ ነገር እንደሆነ፣ በርካታዎቹን ሰነዶች ማሰባሰብ ብቻ ሳይሆን አንብቦ፣ ተረድቶ ሲያበቁ ወደ ፅሑፍ የመቀየሩ ሂደት ትልቅ ሥራ እንደሆነ በመጠቆም ስለ መፅሐፉ ታሪካዊና ሥነ-ፅሑፋዊ ፋይዳና ፀሐፊውን ለማድነቅ የተገደዱበትን አሳማኝ ምክንያት ግልጽ አድርገዋል፡፡ ለቀዳሚ ቃሎቻቸው ማጠናከሪያ ይሆን ዘንድ ‹‹ለምን?›› የሚለውን ጥያቄ በማስቀድም፤ ሰነድ ማሰባሰብ፣ የተሰባሰበውን ሰነድ አንብቦ መረዳትና በዚያውም መጠን ወደ መፅሐፍ ፅሑፍነት መቀየር የፀሐፊውን ‹‹ፅናት፣ ጥንካሬ አስገራሚ ያደርገዋል፡፡ ካለምንም ማብራሪያ በመፅሐፉ ውስጥ የተሰደሩት ሰነዶች ብቻቸውን አንድን ትልቅ ‹ኢንሳይክልኦፒዲያ› የሚወክሉ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ››ም ብለዋል ዶክተሩ፡፡ መፅሐፉ ‹‹አለው›› ስላሉት ሦስት ዐብይት ክፍሎችም፡-

1ኛ፡- የተለያዩ ፀሐፊዎች ከፃፏቸው ፅሑፎች ቅኝትና ዳሰሳዊ ጥናት በመነሳት የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ከጥንት ጀምሮ መፅሐፉ እስከተፃፈበት ዘመን ዋዜማ ድረስ ምን ዓይነት ኑሮ እንደኖሩና እንዴትስ ያለ ጫና ይደርስባቸው እንደነበረ ለማሳየት ሰፊ ጥናት ያደረገበት መሆኑን የሚያሳየው ክፍል (‹‹ምንም ዕንኳ ብዙዉን ጊዜ ‹ኢትዮጵያ እስልምናን በመቀበል ባለውለታ ተደርጋ ትቆጠራለች› የሚለውንና በመፅሐፉም ላይ መንፈሱ የሚገኘውን ሐሣብ ወይም ቃል የማልስማማበት ቢሆንም፡፡ ለምን? እኔ መመረጧን ዕድለኛ ናት ያሰኛታል እንጂ ‹ባለውለታ ነች› መባሉን መቀበል ስለማልፈልግ፡፡ እንደገና ለምን? እስልምናን መጠበቅ የአላህ ብቸኛ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ ፈጣሪ መርጧታል፡፡ በመመረጧም ዕድለኛ ናት ብዬ ስለማስብ…›› በማለት ግለ-አስተያየታቸውን  በማክል፡፡) አንደኛው ክፍል መሆኑን፣ 

2ኛ፡- የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት ጉባዔ እስከሚፈጠር ድረስ ዘጠኝ ያህል የሚሆኑ የተለያዩ አደረጃጀቶች የነበሩ መሆናቸውን የሚጠቁመው፣ የድርጅት ጥያቄ የተነሳበትና ‹‹ከሚገርመው አደረጃጀት መሀል ‹የወጣት ሙስሊሞች መንፈሳዊ ክብብ› የሚባለው ነው›› በማለት መፅሐፉ ስላወሳቸው ታሪካዊ ቁም-ነገሮች ‹‹አንደኛው››ንና ‹‹አሁን ሲሆን ያልታየና ያልተሞከረ›› ያሉትን ተግባር… በዋቢነት የሚጠቅሱበት፣ ያም ተጠቃሽ የእስላማዊ ወጣቶች ክበብ ‹ሳምንታዊ የሥነ-ፅሐፍ፣ የቲያትር፣ የመዝሙር፣ የስፖርት፣ የታሪክ አጥኚና መዝናኛ አቀፍ ጉብኝት፣ ለመኃይማን ትምህርትን የሚያዳርስና የበጎ አድራጎት ተግባራት የሚያከናውኑ ንዑሳን ኮሚቴዎች› የነበሩት መሆኑ በተመራቂው መፅሐፍ ገጾች ውስጥ መወሳቱ ልዩ የሆነ አነቃቂ ስሜትን የሚያጭር›› ስለመሆኑ የተዳሰሰበት ወይም የተወሳበት ክፍል ሁለተኛው ክፍል እንደሆነ፣

3ኛ፡- የእስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ም/ቤት ከተቋቋመ በኋላ ስለ ነበሩት ትግሎች፣ በሙስሊሙ ማኅበረሰብ አለመግባባት ምክንያት ስላጋጠሙ ውድቀቶች፣ እሥራቶች በተለይም በ1987/88 ዓ.ም ስለተፈጠረው ክስተት፣ በችሎት ይስተዋል የነበረውን የዳኝነትና የፍርድ ሂደት በዝርዝር የሚያሳይ፣ ወደፊት የሕግ ባለሙያዎች አስተያየት ሊሰጡበት የሚችሉበትን መነሻ ሐሣቦች ያቀፈ፣ የመረጃና የታሪካዊ ሁነቶች ምንነትና እንዴትነት ጥንቅሮች ተቆራኝተው የቀረቡበትና በመፅሐፉ የመጨረሻ ገጾች ላይ የሠፈሩት አጠቃላይ ጉዳዮች የመፅሐፉ ሦስተኛ ክፍል አካል እንደሆኑ በማብራራት፤ ዶክተር መሐመድ ዓሊ  ስለ መፅሐፉ ታሪክን መሠረት ያደረገ ገንቢ የሆነ ጠቀሜታ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ 

ደራሲ አቶ ተሾመ ብርሃኑ  በበኩላቸው፤ መፅሐፉ በ10 የፊደል ቅርፅ  መጠን (ፎንት ሳይዝ) 657 ገጾች፣ 130 ሺህ ወይም ከዚያ በለጥ የሚሉ ቃሎች፣ 24 ምዕራፎች ታሪኩ ተተርኮ የተቀነበበ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በመፅሐፉ ውስጥ ከተሰደሩት በርካታ ደብዳቤዎች መሀል አንደኛው ብቻውን ‹‹አሥር መፅሐፍ ሊወጣው የሚችል ዓይነት ነው›› በማለትም ግለ-አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ የፀሐፊውን ንፉግ አለመሆንም ጠቆም ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ አክለውም ‹‹ደብዳቤዎቹ ተንሰላስለው በመፅሐፉ ውስጥ ቀርበዋል፡፡ አንባቢ በታሪክ ትረካ ውስጥ ለሚያቀርባቸው ህሊናዊ ጥያቄዎች ደብዳቤዎቹ መልስ ሰጪ ሆነው ተሰድረዋል፡፡ በአጭሩ መፅሐፉን አሥርና ከዚያም በላይ ትውልድ ሊጠቀምበት የሚችል ነው…›› በማለትም አድናቆታዊ ቃላቸውን አስደምጠዋል፡፡  

በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የፎክሎር መምህር የሆኑት ዶክተር እንድሪስ ‹‹መፅሐፉ ፀሐፊው የመጅሊስ ታሪክ ውብት እንዲኖረው በመፈለጉ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ጋር አስተሳስሮ ያቀረበበት ነው›› በማለት በቀዳሚ ቃላቸው ገልጸውታል፡፡ በመቀጠልም ስለዛሬ ስናወራ ስለትላንትም ማውሳት፣ ከትላንት በፊት ስለነበረውም ማንሳት ያለብን ስለመሆኑ፣ ያለፉትን ስኬቶችና ውደቀቶች መርምረን እኛ ወዴት መሄድ መቻል ይኖርብናል? የሚለውንም ለማጤን ለምረቃ እንደበቃው የሰዒድ መሐመድ ዓይነት መፅሐፎች ጠቀሜታ እንዳላቸው አሳስበዋል፡፡ መፅሐፉ ለኢትዮጵያዊው ሙስሊም ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ከገባበት የፖለቲካ አዙሪት መውጫ የሚሆነውን መንገድ ጠቋሚ ሊሆኑ የሚችሉ ሐሣቦች፣ እንደዚሁም ፀሐፊው ዋጋ የከፈለባቸው የረቀቁ መረጃዎች ተደራጅተው የቀረቡበት እንደሆነም አመላክተዋል፡፡

ይኸው ለምረቃ የበቃ መፅሐፍ ስለ መጅሊስ ብቻ ሳይሆን ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክና ትውፊት ምንነት በአንባቢያን ዘንድ የተለየ ግንዛቤን የሚያስጨብጥ  እንደሆነ ለማስረዳት የሞከሩት ዶክተር እንድሪስ፤ ያለፉትን የሃገርና የወገን ታሪኮች የምናይባቸው መነፅሮች አንድ ገጽታ ላይ ብቻ ያተኮሩ የመሆናቸው ጉዳይ አሁንም በችግርነት መቀጠሉ እንደሚያሳስባቸው ግልጽ አድርገዋል፡፡ ‹‹ያለፈ ታሪካችን ሁሌ የጭቆና ታሪክ ብቻ አይደለም፡፡ ሁሌም የድክመት ታሪክ አልነበረም›› በማለት ያለ መጨቆን፣ የአስተማሪ ትግል፣ የጥንካሬ ሂደት ጭምር እንደነበር ከቅርብ ጊዜው ‹‹የ1968 ዓ.ም የመጂሊስ ታሪክ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ሙስሊም ለ1400 ዓመታት በኢትዮጵያ ኖሯል›› በማለት  አስቀድሞ የሆነውንና የሙስሊም ባለ ብዙ ሙያና ዕውቀት ጠቢቦችን ታሪክ መረዳት፣ አንዳንዴ በንዑሱ ታሪክ ላይ ብቻ ከማትኮር ትልቁንና አንኳሩን የታሪክ ጉዳይ መጠየቅ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቆም አድርገዋል፡፡     

ሌላው የመፅሐፍ አስተያየት ሰጪ የሆነው የታሪክ መምህሩ ኢብራሂም ሙሉሸዋ በቅድሚያ፡- ‹‹በእኔ ዕምነት መፅሐፉ ከኢትዮጵያ ሙስሊሞች የትግል ታሪክ ረገድ ወደፊት ለሚሠሩ ሥራዎች ትልቅ አስተዋጽዖ የሚያበረክት ነው›› በማለት የመፅሐፉን ጥቅል ይዘት፣ የጥንቅሩን ሁኔታ፣ የጠቀሜታውን ጉዳይ፣ የደራሲውን ጥረትና ድካም ግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ሐሣቡን አቅርቧል፡፡ በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ ‹‹ብዙዎቻችን የምናውቀው መጅሊስ  ለፖሊስ ደብዳቤ ሲፅፍ ቢሆንም ይህ መፅሐፍ ግን በቀደሙት ጊዜያት መጅሊስ ብዙ ታሪክ ያሳለፈ መሆኑን አሳይቶናል››ም ብሏል፡፡

ኢብራሂም ሙሉሸዋ፤ የሐጂ ወይም የአቶ ሰዒድ መሐመድ መፅሐፍ ‹‹ከ1920ዎቹ ቀዳማይ ዓመታት ጀምሮ መጅሊስን ስለማቋቋም የተደረገውን ያላሰለሰ ጥረትና ትግል መልክና ቅርፅ የሚያመለክት እንደመሆኑ የመጅሊሱ ታሪክ በራሱ የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ አንድ አካል›› እንደሆነም ጠቁሟል፡፡ ‹‹እጅግ ታላቅና ጠንካራ ጎኑም የሰነዶች ክምችት የሚገኝበት፣ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ሥርዓትና የሕብረተሰባዊነት ርዕዮት አራማጅ በነበረው የወታደራዊው መንግሥት ጊዜ እንዴት ያለ ሕይወት አሳልፎ እንደነበር በቃላዊ ሥዕሎች አማካይነት የሚነግር ብቻ ሳይሆን የሚያሳይ የታሪካዊ ምስክርነት ጥንቅር ሆኖ መቅረቡ ነው›› የሚለውን አስተያየትም ሰንዝሯል፡፡ የታሪክ መምህሩ ኢብራሂም አስተያየቱን ሲያብራራም፤ መፅሐፉ የኢትዮጵያ ሕዝብና የኢትዮጵያ ታሪክ ወይም የተኖረ እውነት ነፀብራቅ፣ እየተኖረ ላለው ኑሮና ሂደቱ ምሣሌ፣ በመቀጠል ላይ ለሚገኘው መልከ-ብዙ ትግል የነበሩትን መሠረቶች የሚያስቃኝ፣ የሚያስዳስስ፣ ለማፍታታት የሚሞክር የተደከመበት ሥራ የመሆኑን ጉዳይ ነጥብ በነጥብ አንስቷል፡፡ ጠቅለል ሲል የሰይድ መሐመድ አወል ዳጎስ ያለ መፅሐፍ የሃገራችንን የታሪክ ጉድለት ለመሙላት ዋንኛ ግብዓት ሊሆን የመቻሉን ያህል ታሪካዊም ይሁን ፖለቲካዊ ሥህተቶቻችንን አርመን፤ በመቻቻል ሳይሆን ከልብ በመከባበር መንፈስ ለመቀጠል የሚያስችል ዕውቀት የሚገበይበት ነው፡፡