Home ምን እንጠይቅልዎት? “የሚቆጨኝ መኪና መንዳት አለመቻሌ ነበር” ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ

“የሚቆጨኝ መኪና መንዳት አለመቻሌ ነበር” ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ

“የሚቆጨኝ መኪና መንዳት አለመቻሌ ነበር” ወ/ሮ የትነበርሽ ንጉሴ

10 አጫጭር ጥያቄዎች

መጠጥ ትወጃለሽ?

– ውሃ ከሆነ አዎ፤ አልኮል አልጠጣም፤

ከሙያሽ የመውጣት ሃሳብ አለሽ?

– ከ45 ዓመቴ በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መምሕር ብሆን ደስ ይለኛል፡፡

ዕለተ ሰንበትን ከማን ጋር ታሳልፊያለሽ?

– ግማሹን ቀን ቤተክርስቲያን፤ ከሰዓት በኋላ ግን አስቸጋሪ ነገር ካልተፈጠረ ከባለቤቴ ጋር፤

የአንድ ቀን ስልጣን ቢኖርሽ?

– መብቱን ያወቀ ሰው ባለስልጣን ነው፤ ሁሌም ባለስልጣን ነኝ፤ የፖለቲካ ስልጣን ከሆነ ግን 24ቱን ሰዓት የተጣሉትን ሰዎች ሁሉ አስታርቃለሁ፡፡

ኮከብሽ?

– አኳሪየስ

ከእግር ኳስ የማን ደጋፊ ነሽ?

– እነርሱ እኔን ጥለው ሄዱ እንጂ አርሴናል ነበርኩ፤

 ከድምፃውያን ማንን ታደንቂያለሽ?

– ቴዲ አፍሮን፤

ተመልሶ በተወለደ የምትይው?

– ተመልሰው እንደማይወለዱ ባውቅም ማዘር ቴሬዛን፤

ከዓለማችን የምታደንቂው አንድ ሰው?

– አሁንም ማዘር ቴሬዛ፤

ከቲያትርና ከፊልም የቱን ትመርጫለሽ?

– ቲያትር፤ (Live) ስለሆነ፤

ሕይወት በአንቺ እንዴት ትገለፃለች?

ሕይወት ይፍሩ ከመሳለሚያ

የትነበርሽ፡- ሕይወት በእኔ ዕይታ ሁለት ዋና ዋና ገጽታዎች አሏት፤ መጥፎና ጥሩ፣  ሞቃትና ቀዝቃዛ ገጽታ አላት፡፡ ሕይወት ለእኔ እንደዚህ ነች፡፡ ስለዚህ ሰው እንደ ምርጫው ይኖራል፡፡  ሕይወት ምርጫ ያለባት መንገድ ናት፡፡ ወደ ሙቅና ቀዝቃዛው ለመሄድ፤ ደግም ክፉም ለመሆን አማራጭ አሏት፡፡

ጎልተሽ መውጣት የጀመርሽው በዩኒቨርሲቲ ቆይታሽ ነው፤ ለመታወቅ ብለሽ ያደረግሽው ይሆን? የዩኒቨርስቲ ቆይታሽን እንዴት ትገልጪዋለሽ?

ዮናስ ተክለማርያም ከጅማ

የትነበርሽ፡- የሰው ትዝታ ነው እንጂ እኔ መገናኛ ብዙኃን ላይ መውጣት የጀመርኩት ከልጅነቴ ጀምሮ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ የነበረኝ የመገናኛ ብዙኃን ቆይታ “ከልጆች ዓለም” በሚል ፕሮግራም ሲሆን፣ ሻሸመኔ የ4ኛ ክፍል ተማሪ ሆኜ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ ያቀረብኩትና ከዚያ ጋር ተያይዞ የተደረገልኝ ቃለ-መጠይቅ ነው፡፡ ከዚያ በኋላም 8ኛ ክፍል ሆኜ የአድዋ 100ኛ ዓመት ሲከበር እንዲሁም በሃይስኩል ቆይታዬ የበርካታ ሚዲያዎችን ትኩረት ስቤ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ግን የዩኒቨርሲቲውን ለየት የሚያደርገው ከስሜ ጋር ተያያዘ፤ ነፍሳቸውን ይማርና ጋሽ ክፍሌ ወዳጆ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ጥያቄ ካቀረብኩ በኋላ  “እውነትም የትነበርሽ” አሉኝ፡፡ በዚሕም ሰው ሕሊና ውስጥ ከነስሜ እንድቀር ሆነ፡፡ ያ አጋጣሚ ነው ወደ እውቅና ማማ ያወጣኝ፡፡ እኔ ለመታወቅ ብዬ ያደረግሁት ነገር አይደለም፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ የምችለውን ነገር ማድረግ እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ የማልችለው ነገር ደግሞ በጣም ውስን እንደሆነ፣ የማልችለውንም ነገር ለመለማመድ እንደምችል አምናለሁ፡፡ …ለምሳሌ ምኒልክ ት/ቤት የተማሪዎች መማክርት ም/ፕ/ት ሆኜ፣ የተለያዩ  ክበባት ሊቀመንበር ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ ያ ዝንባሌዬ ቀጥሎ አ.አ ዩኒቨርስቲ ስገባ የፀረ-ኤድስ ክበብ የተማሪዎች ተወካይ በመሆን፣ የሴት ተማሪዎችን ማህበር በመመስረት፣ በሊቀመንበርነትም በመምራት፣ የአይነ ስውራን ተማሪዎችን ኅብረት በመወከል በርካታ የበጎ ፈቃደኝነት እንቅስቃሴዎችን አደርግ ስለነበር ከነዚህ ማዕቀፎች ነው ልመረጥ የቻልኩት፡፡… አካል ጉዳተኛ ሆነህ እንደዚህ አይነት እንቅስቃሴዎችን ስታደርግ የተለመደ ስላልሆነ በኅብረተሰቡ ዘንድ ትኩረት ይሰጠዋል፡፡

…የአ.አ ዩኒቨርስቲ ቆይታዬ በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ሃይስኩል የነበረኝን የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ ያሳደግሁበት ነው፡፡ እድሜ እየጨመረ በሄደ ቁጥር አንተነትህ ውስጥ ያለው ኳሊቲም እየጨመረ መሄድ አለበት፡፡… እና ዩኒቨርሲቲ ማለት ከሌሎቹ የሕይወት ምዕራፎች መካከል ለትልቅ ኃላፊነት ልትታጭ ወደሚያበቃህ የሕይወት መስመር የምትገባበት ቦታ ነው፡፡ ያንን ስፍራ ሁለት ቦታ ማለትም “ተሰሎንቄ” ወይም “ቆሮንቶስ” አድርጎ መጠቀም ይቻላል፡፡ ቆሮንቶስ ገዳም ነው፤ ተሰሎንቄ ማለት ደግሞ የቀለጠው መንደር ነው፡፡ ምርጫ ነበረኝ፤ እኔ በአግባቡ ተጠቅሜበታለሁ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ከዚያ ማግኘት ያለብኝን እውቀት፣ አመለካከትና መልካም ስብዕና ይዤ ወጥቼበታለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡

ዕንቁ፡- አቶ ክፍሌ ወዳጆ “እውነትም የትነበርሽ” ያሉሽ በምን ምክንያት ነበር?

የትነበርሽ፡- ጥያቄ አቅርቤ ነው፤ የፖሊሲ መድረክ ክርክር ነበር፤ እዚያ ላይ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል፡፡ የሴቶች፣ የወጣቶች፣ የምሁራን፣ የነጋዴዎች ተወካዮች በአጠቃላይ በጣም በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ነበሩ፡፡ በወቅቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አንድ ሰው አንድ ጥያቄ ብቻ ነበር ማቅረብ የሚችለው፡፡ …የጠየቅሁት ጥያቄ በጊዜው የነበረኝን ስሜትና ንዴት ያንፀባረቀ ነበር፡፡ ጥያቄው ትንሽ ከበድ ያለ ነበር፡፡ ከመንግስት አንፃር የሚከተለውን ፖሊሲና አፈፃፀም የሚመለከት ስሜት የሚያንፀባርቅ ነበር፡፡ ቀድሞ መቅረብ የነበረበት ጥያቄ ሊሆን ይችላል፡፡ በርግጥም እውነትም የትነበርሽ የሚያሰኝ ጥያቄ ነው አሉ፡፡ የምክክር መድረኩ የተካሄደው በ1994 ይመስለኛል፡፡ ያኔ አ.አ ዩኒቨርስቲ ፍሬሽ የሕግ ተማሪ ነበርኩ፡፡

የሕግ ትምህርት ካጠናቀቅሽ በኋላ ለማኅበረሰቡ ምን የረባ አገልግሎት አበረከትሽ?

አለሜነህ ይስማሸዋ ከአሰላ – ኢ-ሜል

የትነበርሽ፡- ጠበቃ፣ ዳኛ፣ አቃቤ ሕግ አልሆንኩም፡፡ (ሳቅ) …እንግዲህ ሕግ ማለት ዘርፈ ብዙ ነው፡፡ ሕግ የተማረ ሁሉ ፍርድ ቤት መሄድ አይጠበቅበትም፡፡ ስለ ሰዎች መብት በተለያየ ዘርፍ መስራት ይቻላል፡፡ እኔ ሰዎች በልማት እንቅስቃሴ ውስጥ የመካተት መብት አላቸው፣ በተለይ አካል ጉዳተኞች መብታቸው ተጥሷል ብዬም ስለማምን የመካተት መብታቸውን ለማስከበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎች እያደረግኩ ነው እንጂ በፍርድ ቤት ደረጃ ብዙ አልሠራሁም፡፡ ለሦስት ወር ያህል ለልደታ ማርያም የልጃገረዶች ት/ቤት (በተለምዶ ካቴድራል ለሚባለው) የአሠሪና ሠራተኛ አማካሪ ሆኜ የተወሰነ ጊዜ ሠርቻለሁ፡፡ በተለመደው የሕግ መስክ ውስጥ ግን አልሠራሁም፡፡

ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ለመስጠት እየተንቀሳቀስሽ እንደሆነ በስፋት ይታወቃል፤ ሊጠቀሱ የሚችሉ ጉልህ ተግባራት የምትያቸውን ብትገጪልኝ?

መግደላዊት አየለ – በስልክ

የትነበርሽ፡- ዓላማዬ በተለያዩ የልማት እንቅስቃሴዎች ውስጥ እንዲካተቱ ማድረግ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች ማለትም በጤና፣ በትምህርት፣ በእርሻ፣ በስነ-ተዋልዶ እና በመሳሰሉት እንዲካተቱ ስልጠና መስጠት፣ አዕምሯቸውን መገንባት ላይ ነው እየሠራሁ ያለሁት፡፡ ብዙ የሠራሁትና ያረካኛል ብዬ የማስበው ለአካል ጉዳተኞች መነሻ ካፒታል እየሰጠን ከልመና ወደ ልማት እንዲገቡ ያደረግናቸው በርካታዎች ናቸው፡፡ ብዙ አካል ጉዳተኞች ሕይወታቸው ተቀይሮ አይቻለሁ፤ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ሠርተው የሚያተርፉ፣ ለሌሎች የሚተርፉ ሲሆኑ በማየቴ ይህን አሳክቻለሁ ብዬ አስባለሁ፡፡ በሥራውም በተለያዩ ክልሎች እንዲሁም በአ.አ ለሚገኙ ከ30 በላይ ለሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች ማህበራት በቢሮዬ በኩል የገንዘብ ድጋፍ አድርገናል፡፡ ለእኔ ትልቅ ስኬት ብዬ የምቆጥረው ይህ ነው፡፡ ምክንያቱም አንደኛ ራሳቸውን ችለዋል፤ ሁለተኛ ሰዎች ስለነርሱ ያላቸው አመለካከት በቀጥታ እንዲቀየርና ጥገኛ እንዳልሆኑም አሳይተዋል፤ ሦስተኛ ቤተሰቦቻቸውን ረድተዋል፤ አራተኛ ሃገራቸውን ጠቅመዋል፡፡ ይህ ለእኔ ትልቅ ነገር ነው፡፡

በአምስት ዓመት ዕድሜሽ ዓይነስውር ከመሆንሽ በፊት የነበረውን የልጅነት ጊዜ ትውስታሽን እንዴት ትገልጪዋለሽ?

ናርዶስ አላምረው – ከሰበታ

የትነበርሽ፡- ብዙው የልጅነት ስለሆነ አላስታውሰውም፤ በተለይ ስታድግ ብዙ ነገሮችን የምታስተውል ከሆነ የቀደመውን ነገር አታስታውሰውም፡፡ ገጠር ውስጥ ነው የተወለድኩት፡፡ ሰፊ ሜዳ፣ መስክ፣ እንሰሶች፣ ቅጠላቅጠል፣ በጣም የሚያማምሩ ዛፎች እና በጣም ደስ የሚሉ አበቦችን አስታውሳለሁ፡፡ የሚገርምህ ከ22 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዛሬ ሦስት ዓመት ወደ ትውልድ ስፍራዬ ተመልሼ ሄጄ ነበር፡፡ ፍፁም የተለየ ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ የትውልድ ቦታዬ አማራ ሳይንት ይባላል፤ ደቡብ ወሎ የሚገኝ ቦታ ነው፡፡ ቦታውን የማውቀው በልጅነቴ ነው፡፡ አሁን ስሄድ መስኩን እንዳለ አግኝቼዋለሁ፡፡ ልጆች ሆነን ታጭዶ የተከመረ እህል ላይ የምንጫወተው ጨዋታ፣ እሸት መካከል ሆኖ እየቀጠፉ መብላት፣ ሰዎች ተሸክመው ሲሄዱ… እነዚያ እነዚያ የልጅነት ትዝታዎቼን አስታውሻለሁ፡፡ በዚህ ደስተኛ ነኝ፡፡

በአካል ጉዳተኝነቴ አጥቻቸዋለሁ ብለሽ በቁጭት የምታስቢያቸው ነገሮች ይኖራሉ?

ሃለፎም ወልዱ – ከተክለሃይማኖት

የትነበርሽ፡- ብዙም የለም፤ እንዲያውም በአካል ጉዳተኝነቴ አግኝቼዋለሁ የምለው ነገር ነው የሚበዛው፡፡ የተወለድኩት ገጠር ውስጥ ሲሆን በቅርቡ ተመልሼ ስሄድ ያስተዋልኩት አካል ጉዳተኛ በመሆኔ ብዙ መጠቀሜን ነው፡፡ አሁንም ድረስ እዚያ ያሉ የአካል ጉዳት ያልደረሰባቸው ሴቶች ብዙዎቹ ያለ እድሜያቸው ያገባሉ፡፡ በ12ና በ13 ዓመት ዕድሜ መዳር የተለመደ ነው፡፡ ዓይነ ስውር መሆኔ እዚያ አካባቢ ያሉ ሴቶች ላይ የሚደርስባቸው የባህል ተጽዕኖ እንዳይደርስብኝ አድርጎኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ የሚቆጨኝ መኪና መንዳት አለመቻሌ ነበር፡፡ አሁን እሱን ሳስበው ብዙ አያስጨንቀኝም፡፡ ምክንያቱም መንዳት የማይችሉ ግን የሚያዩ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ደግሞም በኮምፒውተር መኪና መንዳት እንደሚቻል ስላወቅሁ በጣም በሕይወቴ አጥቼዋለሁ የምለው ነገር የለኝም፡፡ ምናልባት ሰዓሊ ልሆን እችል ነበር ወይ ብዬ አስቤም ነበር፡፡ የስዕል ሥራ ከዓይን ጋር ስለሚያያዝ ለሠዓሊነትም ብዙ ፍላጎት የለኝም መሰለኝ፡፡ ስለዚህ ጠቃሚ የሆነ ነገር አጥቻለሁ ብዬ አላስብም፡፡ ያው ከኅብረተሰቡ ጋር የምታደርገው የአመለካከት ግብግብ እንዳለ ሆኖ አካል ጉዳተኛም ባልሆን ሴት በመሆኔ ወይም በሌላ ምክንያት ሊመጣ ይችላል፡፡ ላልፍበት የሚገባ የሕይወት መስመር ነው ብዬ ስለማምን በአካል ጉዳተኝነቴ አጥቼዋለሁ ብዬ የማስበው ጉልህ ነገር የለም፡፡

ከቤት ውጪ ባለው ሕይወትሽ ስኬታማ እንደሆነሽ አስባለሁ፤ ሴትነትን በሚጠይቁ የቤት ውስጥ ጣጣዎችስ እንዴት ነሽ?

ወንደሰን መብራቱ – ከቄራ

የትነበርሽ፡- የቤት ውስጥ ጣጣዎች ሴትነትን ሳይሆን ሰውነትን ነው የሚጠይቁት፡፡ ሽንኩርት መክተፍ፣ እቃ ማጠብ፣ እንጀራ መጋገር… የመሳሰሉት ነገሮች ሴትነትን ብቻ ይጠይቃሉ ብዬ አላምንም፡፡ በአብዛኛው ሰው መሆንን ይፈልጋሉ፡፡ ሰው የሆነ ሁሉ ሊሠራቸው ይገባል፡፡ እኔም እሠራለሁ፡፡ በአብዛኛው የሚያስደስተኝ ግን ሽንኩርት መክተፍ ነው፤ ማብሰል ብዙም አያስደስተኝም፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ…  የዶሮ ሽንኩርት እኔ ካልከተፍኩ ሌላ ሰው ሲከትፍ እናቴ ደስ አይላትም፡፡ ዕቃ ማጠብ ላይ ጎበዝ ነበርኩኝ፤ ምክንያቱም እኔ ስለማላይ ሁሉን ቦታ ተጠንቅቄ ነው የምዳብሰው፤ ሳሙናው ለቋል ወይስ አልለቀቀም እያልኩ ከሚያዩት ይልቅ እኔ በደንብ ነበር የማፀዳው፡፡ አሁን ግን ያለኝን ጊዜ ብዙውን ውጪ ነው የማሳልፈው፡፡ በርግጥ እኔና ባለቤት እቃ እናጥባለን፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቅዳሜና ዕሁድ ሲሆን የየራሳችንን እቃ የማጠብ፣ ልብስ የማጠብ፣ የማስተካከል፣ የፅዳት ሥራ አብሮ የመሥራት ሁኔታ አለ፡፡ ግን ይህም በሴትነቴ ሳይሆን ቤት ውስጥ ስለምኖር አባል ነኝ ይመለከተኛል ከሚል ተነስቼ የምሠራው ነው፡፡

ሴት የሕግ ባለሙያ እንደመሆንሽ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለውን አስከፊና ዘግናኝ ጥቃት እንዴት ትገልጪዋለሽ፤ መንስኤው ምንድነው? መፍትሔውስ?

ፍርቱና አያና – ከወሠርቢ

የትነበርሽ፡- የሚደርሰው ጥቃት የሕግ ባለሙያ ለሆነም ላለሆነም በጣም የሚዘገንን ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በቃ ልንል ይገባል፡፡ እኔ የሕግ ባለሙያ በመሆኔ ብቻ ሳይሆን ሰው ከመሆኔም የሚመነጭ አመለካከት ነው ያለኝ፡፡ ሴቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በማንም ሰው ላይ የሚደርስን ጥቃት እቃወማለሁ፡፡ ወንዶችም ላይ የሚደርስ ጥቃት ያመኛል፤ ምክንያቱም ሰው እግዚአብሔር የፈጠረው፣ ምንም አምሳል፣ ወደር፣ ዋጋም ሊሰጠው የማይቻል በጣም ውድ ፍጡር ነው፡፡ ማንም ሰው በሌላ ሰውነት ላይ ስልጣን አለው ብዬ ስለማላምን ማንም ላይ አደጋ እንዲደርስ አልሻም፡፡ በሴቶች ላይ ሲደርስ ያሳምማል፡፡ ጫና እና ጭቆና ተቋቁመው፣ ለህይወት ዋጋ የከፈሉ፣ ለብዙ ቤተሰብ መሠረት የሆኑ ሴቶች ሲጎዱ እናያለን፤ ሴት ልጅ የሚገባት ይሄ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በተለይ በእኛ ሃገር ተጨባጭ ማህበረሰብ አኗኗር ሴት ልጅ ይሄ አይገባትም፡፡ በዚሕ ልቤ በጣም ይነካል፡፡ ማንም ሰው ራሱ ላይ ሊደረግበት የማይወደውን ነገር ሌላው ላይ ማድረግ የለበትም፡፡ ይሄ ወርቃማው የአውራምባ ማሕበረሰብ ሕግ እኔ በሕይወቴ የምመራበት ሕግ ነው፡፡ እኔ ላይ ሲደረግብኝ የሚያመኝን ነገር ሌላው ላይ ማድረግ አይኖርብኝም፡፡

በልመና የተሰማሩ የአካል ጉዳተኞችን ሕይወት ለመቀየር ተቋምሽ እየሠራ ያለው ነገር ይኖር ይሆን?

ሰዒድ ኑርሃሰን – ከመሳለሚያ

የትነበርሽ፡- በጣም ብዙ ሥራ ሠርተናል፤ “መከታ” የሚባል መካኒሳ አካባቢ ያለ የአካል ጉዳተኞች የህብረት ሥራ ማህበር አለ፤ ትልልቅ አረጋውያንና የትም አይደርሱም የተባሉ ሰዎች ነበሩ፡፡ የመኪና እጥበት ሥራ አስጀመርናቸው፤ ከዚያ ለጃፓን ኤምባሲ ፕሮጀክት ቀረጽንላቸው፡፡ አሁን ሥጋ ቤት ከፍተዋል፤ ዲኤስቲቪ ያሳያሉ፤ ፀጉር ቤት አላቸው፤ ትልቅ ህንፃ ሠርተው የሠርግ መናፈሻ እንዲሠሩ ስፖንሰር አድርገናቸዋል፡፡ አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ መቀሌ፣ አዋሳ፣ ምዕራብ ባኮና በርካታ ቦታዎች ላይ የገንዘብ ድጋፍ እያደረግን አብዛኞቹን ወደ ስኬት እንዲመጡ አድርገናል፡፡ አንድ ሰው አንድ ነገር ጎደለው ማለት ሁሉንም ነገር አጥቷል ማለት አይደለም፡፡ ሁሉም ሰው በውስጡ እምቅ ችሎታ አለው፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች አንድን ሰው ሲያዩት ስለጎደለው ነገር ነው የሚያስቡትና ዋጋ የሚሰጡት፡፡ እኔ ግን ከጎደለው ነገር በስተጀርባ ብዙ ነገሮች አሉት ብዬ ስለማምን ባለው ነገር ላይ ተመስርተን ስኬታማ መሆን እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ዕንቁ፡- እናንተ ሌሎቹን ስፖንሰር ታደርጋላችሁ፤ ድርጅታችሁ በአቅም ራሱን የቻለ ነው ወይስ እናንተንም የሚያግዟችሁ ድርጅቶች አሉ?

የትነበርሽ፡- እኛንም የሚያግዙን በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት አሉ፤ ብዙዎቹ ግን እዚህ ሃገር የተለመዱ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ ራስን የማስቻል ሥራን የምንሠራው ፊንላንድ ውስጥ ከሚገኙ Ablif foundation እና Tresh hold ከሚባሉ ድርጅቶች ጋር ነው፤ ከዩኤስኤአይዲ፣ ከፓካርድ ፋውንዴሽን እና ላይትስ ኦፍ ዘ ወርልድ ከሚባል የኦስትሪያና የሆላንድ ድርጅት ጋር እንሠራለን፡፡ ከበርካታ ድርጅቶች ጋር የሥራ ትስስር አለን፡፡

ብዙ መስማትና ማየት የተሳናቸው አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ አሉ፤ ለነርሱ የሚደረገው እንክብካቤ ምን ይመስላል?

ፋሲል ጠናጋሻው – ከአዳማ

የትነበርሽ፡- መስማትና ማየት የተሳናቸው በርካታ አካል ጉዳተኞችን አውቃለሁ፤ የኢትዮጵያ መስማትና ማየት የተሳናቸው ማኅበርም አለ፡፡ የእኛ ማኅበር ከዚህ ማኅበር ጋር በቅርበት ይሰራል፡፡ ለነርሱ የሚደረገው እንክብካቤም በዓለም አቀፍ ደረጃ Tactile የሚባል በእጅ ምልክት እና እጅ በመነካካት የሚነጋገሩበት የመግባቢያ ቋንቋ አላቸው፤ በእኛ ሀገር ግን እርሱ በልጽጎ አልተጀመረም፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት እየተደረገ ያለው በተለይ በከፊል የመስማት ችሎታ ላላቸው አጠገባቸው ሆኖ ጮህ ብሎ በመንገር ነው ለመግባበት እየተሞከረ ያለው፡፡ ግን ማኅበሩ ከፍተኛ ጥረት ጀምሯል፡፡ በተለይ የፊዚዮቴራፒ አገልግሎት እንዲያገኙ እና እንዲንቀሳቀሱ፤ ይህ ነገር ከነርቭ ጋርም ስለሚያያዝ ነርቮቻቸው እንዲነቃቁ ለማድረግ፣ መስማትና ማየት በማይፈልጉ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ (ለምሳሌ ማሳጅ) ማኅበሩ ስልጠና እየሰጠ ነው ያለው፡፡

ትምሕርት ቤት ከፍተሻል ይባላል፤ ምን አይነት ት/ቤት ነው፤ ምን ላይ ያተኩራል?

ትእግስት አለሙ ከአምቦ-በፌስ ቡክ

የትነበርሽ፡- ያው ማስተማር ላይ ያተኮረ ነው፤ አፀደ ሕፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ነው፡፡ እኔ ራሴ ገጠር ከድሃ ቤተሰብ ነው የተወለድኩት፡፡ በመማሬ ምክንያት በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የነበረኝ የትምሕርት መሠረት ለዛሬ በራስ የመተማመኔና ስኬቴ ምስጢር ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ በአፀደ ሕፃናት እና በመጀመሪያ ደረጃ ላይ ተማሪዎች በቃል ከምናስተምራቸው ከተግባር ጋር ባለ ቁርኝት የበለጠ ሊማሩ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም አካል ጉዳተኞች የሆኑና ያልሆኑ ሕፃናት በጋራ መማር ይችላሉ በሚል ነው ት/ቤቱን የከፈትኩት፡፡ በርካታ የግል ት/ቤቶች የተለየ ነገር እንደሚጠይቅና በጣም ከባድ እንደሆነ ስለሚያስቡ አካል ጉዳተኞችን አይቀበሉም፡፡ ይህንን ለማስወገድ ሁሉም ሰው ተቀላቅሎ የሚማርበትን እንዲሁም አካል ጉዳተኞችን ብቻም ሳይሆን ለተቸገሩና ወላጆቻቸውን በኤችአይቪ ያጡ ልጆችን በማሰብ ነው ት/ቤቱ የተቋቋመው፡፡

ከሰሞኑ “ማየት ለሚባል ተልካሻ ነገር ጊዜ የለኝም” ብለሻል፤ ይህን ማለት ካንቺ ይጠበቃል? የሌለሽን ነገር ማጣጣል አይመስልብሽም ወይ?

ዳናዊት አሸብር – ከደጃች ውቤ

የትነበርሽ፡- ጥሩና ወቅታዊ ጥያቄ ነው፡፡ የሌለን ነገር ማድነቅ ቀቢጸ-ተስፋነት መሆኑን በግሌ አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ የሌላውን ኑሮ ስናደንቅ የራሳችን ያለፈብን ብዙዎች አለን፡፡ ስለዚህ ባለኝ ነገር መኩራት የራሴ ፀባይ ነው፡፡ በጣም የምደሰትበት የስኬቴም ምስጢር ነው፡፡ ይህ አባባሌ የወጣው “አውራምባ ታይምስ” ጋዜጣ ላይ ነው፡፡ ጋዜጣው ከወጣ በኋላ ከጋዜጠኛው ጋር የመነጋገር ዕድል ገጥሞኝ ነበር፡፡ ትልቁ ችግር ይህ ዓረፍተ ነገር ከፊት ገጽ እንደ ርዕስ ሆኖ መቀመጡ ነው፡፡ ምክንያቱም የጽሑፉን ዓላማ ለመረዳት የሚለውን እስከመጨረሻ ማየት ወሳኝ ነው፡፡ በተለምዶ ሰዎች ከፊት ያለውን ብቻ የማየት አዝማሚያ አላቸው፡፡ የተጠየቅኩት “አንድ ቀን የማየት ዕድል ቢሰጥሽ ምን ታደርጊያለሽ?” የሚል ነው፡፡ ለእኔ ማየት ጠቃሚ አይደለም፤ ምክንያቱም ስለማላይ፤ በዚያ ላይ ደግሞ ለአንድ ቀን ተብሎ ማየት እንደ ብርቅ ነገር እንዲሰጠኝ አልፈልግም፡፡ ምክንያቱም ከማየት ውጪ ሆኜ ኖሬያለሁ፡፡ ስኬታማም ሆኛለሁ፡፡ ስለዚህ አንድ ቀን አንድ ደቂቃ… የሚሉ ጥያቄዎችን እኔ አልቀበላቸውም፡፡ አንድ ቀንም ሆነ አንድ ደቂቃ እኔ ዋጋ ለምሰጠው ነገር ነው ቦታ የሚኖረው፡፡ ስለዚህ እኔ በተለይ ለማየት ቦታ አልሰጠውም፡፡ ያ ማለት ግን ሌሎች ቦታ ሊኖራቸው አይገባም የሚል እምነት የለኝም፡፡ እኔ ሰዎች እንዲረዱልኝ የምፈልገው… ከዓይን ውጪ ሌላ ሕይወት እንዳለ የማምን ሰው ስለሆንኩ ከሕዝብ ጋር የሚኖረኝ ቆይታ ከዓይንና ከማየት የራቀ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም እኔን የሚያውቀኝ ማንኛውም ሰው ስለማየቴና ስላለማየቴ ይጨነቃል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በርካታ አድናቂዎቼም የሚጨነቁልኝና የሚመኙልኝ ባለሁበት ሁኔታ ያለሁበትን ተቀብዬ የተሻለ ነገር እንድሠራ ነው፡፡ ባለማየቴ እየተቆጨሁ የምፀፀት ስላልሆነ አሁንም እኔ ማየት ለሚባል ነገር ጊዜ የለኝም፡፡ ማየትም አልፈልግም፡፡ ደግሞም ለአንድ ስኬታማ ሰው የስኬት ምስጢሩ ያለበትን ሁኔታ አምኖ መቀበሉ ነው፡፡ እኔ ስለሌሎች ማየት አስተያየት አልሰጠሁም፡፡ በእኔ ሕይወት ውስጥ ማየት ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ ከዚህ የበለጡ ትልልቅ በርካታ ነገሮችን አሳክቻለሁ፤ ይህ ጥያቄ ስለተነሳ ግን አመሰግናለሁ፡፡ …ብታዪ ምን ታደርጊያለሽ ተብዬ መጠየቅ ያለብኝ ምንም ካልሠራሁ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ባለማየቴ ያልሠራሁት ነገር አለ ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ ሳላይ የሠራሁት ነገር ላይ ወይም መሥራት የምችለው ነገር ላይ ለምን አይተኮርም፡፡ እኔ ባለማየት ውስጥ ስለምኖር… ማየትን ረስቼዋለሁ፡፡ ስለማላውቀው ነገር ነው የተጠየቅኩት፡፡

ከባለቤትሽ ጋር የት ተዋወቃችሁ? ባለቤትሽን ምኑን ወደድሽለት? የትዳር ሕይወትስ ምን ይመስላል?

ምትኩ ተሾመ – ከመገናኛ

የትነበርሽ፡- ከባሌ ጋር እዚሁ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው የተዋወቅነው፡፡ ሁለታችንም የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ነን፡፡ ስለዚህ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ውስጥ ነው የተዋወቅነው፡፡ የፍቅር ሕይወታችን ግን ከዚያ አልጀመረም፡፡ በሂደት ነው የተጀመረው፡፡ እርሱ እዚህ ሀገር አይኖርም ነበር፡፡ ለሥራ ወደ አውሮፓ በሄድኩበት አጋጣሚ ነው ተነጋግረን ወደ ፍቅር ሕይወት ለመምጣት የወሰንነው፡፡ ምኑን ወደድሽለት ለተባለው የምጠላለት ነገር የለኝም፡፡ በአብዛኛው ግን ለሰው ልጅ ያለውን ክብር እወድለታለሁ፡፡ ስብዕና ለሚባለው ነገር ትልቅ ክብር አለው፡፡ የሰው ልጅ በእግዚአብሔር አምሳል እስከተፈጠረ ድረስ ድንቅ ነው፣ ክቡር ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሁልጊዜ ደግሞ ለሰዎች በማድረግ ይረካል፡፡ ስለዚህ እኔ ውስጤን የምገነባው በዚያ ነው፡፡ ለሌሎች ባደረግሁት ቁጥር የእኔን ጎደሎ እሞላለሁ፡፡ እንደዚህ አይነት ጸጋ ያለው ሰው ሳገኝ የጋራ የሆነ ነገር እንዳለ ስለተረዳሁ ለመጋባት ወስነናል፡፡ የትዳር ሕይወታችንም በጣም ጥሩ ነው፡፡ ገና ጀማሪዎች ነን፡፡ አስር ወራችን ነው፡፡ ገና ከሙሽርነት አልወጣንም፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን ባለን ሕይወት ደስተኞች ነን፡፡

ዕንቁ፡- በአሁኑ ወቅት እርሱም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ አብራችሁ መኖር ጀምራችኋል?

የትነበርሽ፡- በትክክል፤ ከኢትዮጵያ ከወጡት አንድ አስመልሻለሁ ማለት ነው፡፡ (ሳቅ)

ለእናትነት ያለሽ የስነ-ልቦና ዝግጅት ምን ይመስላል?

ሰናይ በፍርዱ

የትነበርሽ፡- (ሳቅ)… ብዙ ጊዜ እናትነት የምትሆነው ነው፤ እኔ ለእናትነት ትልቅ ልብ አለኝ፡፡ ከዚህ በኋላ እናት መሆን እንዳለብኝ አምናለሁ፡፡ በኔ ውሳኔ ብቻ የሚመጣ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ ሲታከልበት ነው፡፡ ለእኔ እናትነት ሰው በዚህ ዓለም ላይ በትምህርት ወይም በጥረት ሊያገኘው የማይችለው ከፈጣሪው ብቻ ሊሰጠው የሚችለው ትልቅ ጸጋ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቢረዳኝ በቅርቡ እናት ብሆን እወዳለሁ፡፡

“ፍቅር በዓይን ይገባል” ይባላል፤ የእናንተ ፍቅር ግን “በጆሮ ይገባል” ብዬ አስባለሁ፤ መስማት የማየትን ያህል አስተማማኝ ይሆናል ትያለሽ?

ቻቺ ጌቴ – ከአዲስ አበባ

የትነበርሽ፡- ብዙ አባባሎች አሉ፤ ለምሳሌ “ዓይኔን በዓይኔ አየሁት”፣ “ፍቅር በዓይን ይገባል”ም ይባላል፡፡ በጣም ስለተለመዱም ሰዎች በጣም ይጨነቃሉ፡፡ ልጅ ስትወልዱ እንዴት ዓይነት ስሜት ያድርባችኋል ይላሉ፤ ፍቅር በዓይን ብቻ የሚገባ ከሆነ የምናፈቅራቸው ሰዎች እንዳየናቸው በበቁን ነበር፡፡ በርግጥ መነሻ ሊሆን ይችላል፤ ከማየት ልንነሳ እንችላለን፡፡ ግን በዓይን የሚታየው ነገር በእጅም ሊዳሰስ ይችላል፡፡ ፍቅር መቀራረብ አይደል?! በዚህ ሂደትም ከማየት ባለፈ በመዳበስ ልታውቀው ትችላለህ፡፡ ብዙ ጊዜ ግን ፍቅር የሚሆነው የውስጥ እይታ ነው፡፡ ውስጥን ማየት ሲቻል ነው መሠረታዊም የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም በአይንህ ብቻ የወደድከው ከሆነ አንድ ነገር እኮ ከሆነ ጊዜ በኋላ ይሰለቻል፤ ውስጥህ፣ ልብህ ዘልቆ የገባ ከሆነ ግን ፍቅርንና ትዳርን ከዘላቂነት ጋር ስለምናየው Personal quality የሆኑ መገለጫ ነገሮች አሉ፡፡ ርህሩህርነትን፣ ታማኝነትን፣ በአይን አይቶ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ እንዲያውም የዓይን ዳኝነት እያወዛገበ አሁን ሰው ወደ ሕሊና ዳኝነት እየተሸጋገረ ያለበት ዘመን ነው፡፡ ስለዚህ በመስማት ብቻ ፍቅርን መመስረት ከባድ ነው፡፡ እና ለኔ ፍቅር በሕሊና ይገባል በሚለው ቢስተካከል እመርጣለሁ፡፡

ዕንቁ፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የምትፈልጊው መልዕክት… የትነበርሽ፡- ለኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ እኔ የሚገባኝን ያህል ሠርቻለሁ ብዬ አላምንም፡፡ ይህ ሕዝብ ግን ለሠራኋት ትንሽ ነገር ትልቅ ቦታ ሰጥቶኛልና ባለዕዳነት አለብኝ፡፡ ሌላው አሁን ያለንበት ወቅት በጣም ወሳኝ ወቅት ነው፡፡ የሰው ልጆች እርስ በርስ መተባበርና መደጋገፍ ያለብን ወቅት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የምንለውን ዋጋ ለይተን በተለይ የኛ የሆኑ ነገሮች እንዳይጠፉ ማድረግ አለብን የሚል መልዕክት አለኝ፡፡ አድናቂዎቼም እነዚህን ጥያቄዎች የጠየቁት ስለ እኔ ለማወቅ ካላቸው ጉጉት በመነሳት ነው፡፡ እና ጊዜያቸውን ወስደው ከግምት ወጥተው እርግጠኛ ለመሆን ጥያቄዎቻቸውን በዕንቁ መፅሔት በኩል ስለላኩልኝ በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በመልሴ ካላረካኋቸው ከእኔም ጋር መወያየት ከፈለጉ በአድራሻዬ ሊያገኙኝ ይችላሉ፡፡ ጊዜያቸውን ወስደው ጉዳዬ ብለው ስለጠየቁኝ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ፡፡