Home ልዩ ልዩ ዜና የማኅበራዊ ሚዲያ ጥላቻ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ እየተባባሰ መምጣቱ ተጋለጠ

የማኅበራዊ ሚዲያ ጥላቻ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ እየተባባሰ መምጣቱ ተጋለጠ

የማኅበራዊ ሚዲያ ጥላቻ  ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ እየተባባሰ መምጣቱ ተጋለጠ

በኢትዮጵያ ሴቶችና ልጃገረዶች በማኅበራዊ ሚዲያ በተደጋጋሚ የጥላቻ ንግግርና ማግለል እየደረሰባቸው መሆኑን አዲስ ጥናት አመለከተ።

ሴንተር ፎር ኢንፎርሜሽን ሪዚሊየንስ (ሲ.አይ.አር) የተባለ ተቋም ባካሄደው ጥናት መሰረት፣ ይህ ችግር ሴቶችን ከማኅበራዊ ተሳትፎ ከመግፋት ባለፈ በዲጂታል ዓለም ያላቸውን ደህንነት አደጋ ላይ ጥሏል።

ጥናቱ በፌስቡክ፣ ኤክስ (ትዊተር)፣ ቴሌግራም፣ ዩትዩብ እና ቲክቶክ ላይ የተደረገ ሲሆን፣ በተለይም የተለመደውን የአኗኗር ዘይቤ የሚቃወሙ ወይም በአመራር ቦታና በስፖርት ውስጥ ያሉ ሴቶች ለከፋ ትንኮሳና ንቀት እንደሚጋለጡ አመልክቷል።

ተመራማሪዎቹ ይህ የጥላቻ ንግግር በሴቶች ላይ ከሚያደርሰው የስነ ልቦና ጫና ባሻገር፣ በአጠቃላይ በሀገሪቱ ውስጥ ያላቸውን ሚናና ተሳትፎ እያደከመ መሆኑን አሳስበዋል።

በተጨማሪም ጥናቱ እንዳመለከተው በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በስርዓተ-ፆታ ላይ ባሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችና ማኅበራዊ ሚናዎች የተጠናወተው ነው። የፖለቲካ አለመረጋጋቶችና ግጭቶች ደግሞ የዘርንና የፆታን ጥላቻ የሚያባብሱ ሆነው ተገኝተዋል።

የሲ.አይ.አር የምርምር ኃላፊ ፌልሲቲ ሙልፎርድ “በማኅበራዊ ሚዲያ የሚፈጠረው ጥላቻ በገሃዱ ዓለምም አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ጥናቱ አሁን ያሉት የይዘት ቁጥጥር ስርዓቶች ሴቶችንና ልጃገረዶችን በበቂ ሁኔታ ከመጠበቅ አንፃር ክፍተት እንዳላቸው አሳይቷል። ተቋሙ ይህ ጥናት በኢትዮጵያ የዲጂታል ምህዳር ውስጥ ያለውን አሳሳቢ ሁኔታ ለመጠቆም ያለመ መሆኑን ለካፒታል በላከዉ መግለጫ ገልጿል።

CapitalNews