አቶ መሠረት መኮንን ይባላሉ፡፡ የኤን.ኤም ሲ ሪል ስቴት መሥራች እና ባለቤት ሲሆኑ በቅርቡ በ8ነጥብ 5 ቢልዮን 600 በላይ ቤቶችን ለመገንባት ግንባታ ጀምረዋል፡፡ አቶ መሠረት በተጨማሪም የቢዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴል ባለቤት የሆኑት አቶ መሠረት በቱሪዝም ፤ በትራንስፖርት እና በአስመጪ እና ላኪነት ሥራም ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡ በበጎ አደርጎት እና በልማት ሥራዎች ላይ ቀንደኛ ተሳታፊ የሆኑት እኒህ ሥራ ፈጠሪ ባለትዳርና የ6 ልጆች አባትም ናቸው፡፡ ለመኾኑ የኤን.ኤም.ሲ ሪል ስቴት መሥራች ማናቸው? መነሻቸው ምንድን ነው? በምን አይነት ፈተናዎች አለፉ? ለሚለው ይህ ከዚህ በታች የሚቀርበው የህይወት ታሪካቸው መልስ የሚሰጥ ይሆናል፡፡
ልጅነትና የቢዝነስ ዝንባሌ
አቶ መሠረት መኮንን ትውልዱ ደቡብ ጎንደር ነው፡፡ በቤት ውስጥ ሃላፊነትን መቀበል ሲጀምር እድሜው 10 አመት አልሞላም ነበር፡፡ እናቱን መርዳት ከምንም በላይ ደስታን ይሰጠው ነበር፡፡ ገና በታዳጊነቱ ተግባቢ የነበረው መሠረት ለሁሉ የሚታዘዝ ታታሪ ልጅ ነበር፡፡ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ በደቡብ ጎንደር መካነኢየሱስ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት የተማረው መሠረት አንድ ቀን ትልቅ ቦታ እንደሚደርስ ያልም ነበር፡፡ በ1980 የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በሀገሪቱ ጦርነት የተከሰተ በመሆኑ ሌላ አማራጭ ባለመኖሩ ትምህርቱን ገታ በማድረግ ፊቱን ወደ ንግድ አዞረ፡፡ የ19 አመቱን ባከበረ ማግስት ወደ ንግድ አለም የመግባት ፍላጎቱ አየለ፡፡ በመሆኑም በ500 ብር ካፒታል የቢዝነሱን አለም ተቀላቀለ፡፡
ወጣቱ መሠረት ባገኘው ገንዘብ ጥራጥሬ ወደ ሱዳን እየወሰዱ መሸጡን ተያያዘው፡፡ ከሱዳን ደግሞ ጨው በማምጣት ጎንደርና ባህርዳር አካባቢ መሸጥ ጀመረ፡፡ ይህን አይነቱን ንግድ ለ3 አመታት ከሰራበት በኋላ ጥሪት ማጠራቀም ችሎ ነበር፡፡ ከዚያም ጦርነቱ ጋብ ሲል በ1983 ወደ መዲናይቱ አዲስ አበባ መምጣት ነበረበት፡፡ ከዚያም ወደ ቶጎ ውጫሌ፤ ኬንያ ፤ ሞያሌ ፤ ጅቡቲ በመጓዝ እቃዎችን እያመጣ የመሸጡን ሥራ ጀመረ፡፡
የራስን ድርጅት መክፈት
አቶ መሠረት እንደሚናገረው ይህን ሁሉ ሲሰራ ነገሮች አልጋ በአልጋ አልነበሩም፡፡ በርካታ ፈተናዎችን ተጋፍጦ ነው ለስኬት የበቃው፡፡ በረሀ ለበረሀ ከመንከራተቱ ሌላ ሙቀቱ ፈትኖታል፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ ተቋቁሞ አንድ ቀን ትልቅ ቦታ ሊደርስ እንደሚችል በልቡ ያምን ነበር፡፡ ከ1983-1994 ለ 11 አመታት እንዲሁ የራሱን ኩባንያ ሳይከፍት ሲጥር ከቆየ በኋላ በ1994 ቤዝ ኢትዮጵያ ድርጅቱን በይፋ መመስረት ችሏል፡፡ በአሁኑ ሰአት ቤዝ ኢትዮጵያ 21 አመት ያለፈው ድርጅት ሲሆን ለበርካታ ዜጎችም የሥራ እድል የፈጠረ ተቋም ነው፡፡ አቶ መሠረት በ1990ዎቹ ቤዝ ኢትዮጵያ የተሰኘ ሱፐርማርኬት ነበረው፡፡ ከዚህ ሱፐር ማርኬት ስም በመነሳት ነበር ለድርጅቱ ስም ያወጣው ፡፡ አቶ መሠረት በጊዜው የመኪና ማከራየት ሥራዎችንም ይሰራ ነበር፡፡
የሳኡዲው ኤግዚቢሽን
አቶ መሠረት ከዛሬ 23 አመት በፊት ካከናወናቸው ታላላቅ ተግባራት አንዱ በሳኡዲ አረቢያ ያዘጋጀው ኤግዚቢሽን ይጠቀሳል፡፡ የሀሳቡ ፍሬ ነገርም የንግድ ተቋማት ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበት እድልን ማመቻቸት ነበር፡፡ በዚህ ኤግዚቢሽን በአቶ መሠረት አስተባባሪነት ከተሳተፉት ድርጅቶች ውስጥ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ፤ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግ ፤ አያት መኖሪያ ቤቶች ይገኙበታል፡፡ አቶ መሠረት እንደሚያስታውሰው እነዚህ ድርጅቶች ከኤግዚቢሽኑ ብዙ ጥቅም አግኝተዋል፡፡ ታዲያ አቶ መሠረት ይህን ጥረት በማድረጉና ጥረቱም ፍሬ በማግኘቱ በሳኡዲ አረቢያ ልዩ ተሸላሚ ለመሆን ችሎ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ አቶ መሠረት በዚህ ሥራ ላይ ትልቅ ኪሳራ ገጥሞት ነበር፡፡ ይልቁንም በዚህ ሥራ መልካም ስም ማግኘት ችሏል፡፡
ጠንክሮ መቀጠል
የሥራ ፈጣሪው አቶ መሠረት በመቀጠል ከሌሎች ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት ጥራጥሬ ፣ የቅባት እህሎች፣የስጋ ውጤቶችና ቅመማ ቅመም ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ቀጥለውም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ፤ በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በሪል ስቴት ፕሮጀከት ፣ በመኪና ኪራይ በህንጻ ሽያጭና ኪራይ በአስመጪነትና ላኪነት የተሰማሩ ሀገር በቀል ድርጅት ባለቤት ለመሆን በቅተዋል፡፡ አቶ መሠረት በኦሮሚያ ክልል ሰበታ ከተማ በ130 ሚልዮን ብር ካፒታል የታይልስ ፋብሪካ ያቋቋመ ሲሆን ይህም ፋብሪካ ለ230 ሰዎች የሥራ እድል መፍጠር የቻለ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት አቶ መሠረት 15 የትራንስፖርት ተሸከርካሪዎች ፤ በአዲስ አበባም በኩባንያው ስር የተመዘገቡ የ3 ህንጻዎች ባለቤትም ለመሆን የቻለ ነው፡፡ በ500 ብር የተጀመረው የአቶ መሠረት ቢዝነስ በአሁኑ ሰአት 10 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መድረስ ችሏል፡፡
ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴል
አቶ መሠረት በልማት ሥራዎች ላይ በንቃት በመሳተፍ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሽልማት በልዩ ልዩ ጊዜያት ተበርክቶለታል፡፡ አቶ መሠረት ከ 2 አመት በፊት በ2013 ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ሆቴልን ለመጀመር ሀሳብ ያደረገበት ቀዳሚው ምክንያት በቱር ኤንድ ትራቭል የሚመጡ የቤዝ ኢትዮጵያ እንግዶችን በወጉ ለማስተናገድ እንዲያመቸው ነበር፡፡ የራስን እንግዳ ራስህ በሰራኸው ሆቴል ማስተናገድ አስፈላጊ ስለሆነ ሆቴሉን ጀምረናል ይላል አቶ መሠረት፡፡
በጎ አድራጎት እና ልማታዊ ሥራዎች
አቶ መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባቀረበለት ጥሪ መሠረት ለአቅመ-ደካሞችና ለድሀ ድሀ ነዋሪዎች የሚያገለግሉ ቤቶች ሰርቶው አስረክቧል፡፡ በተጨማሪም በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ የባለሀብቶች ኮሚቴ በመሆን 180 ቤቶችን ለመገንባት ችሏል፡፡ ለድሀ ድሀ 4 የዳቦ ፋብሪካዎችን በ87 ሚሊዮን ብር አቋቁሟል፡፡
ከሸገር ዳቦ ፋብሪካ ጋር በመዋዋልም በቀን 30ሺህ ዜጎች ዳቦ እንዲያገኙ በማድረግ የአቶ መሠረት አስተዋጽኦ ትልቅ ነበር፡፡ከዚህም ባሻገር የሸገር ዳቦ ሱቆችን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ-ከተማ በሚገኙ 13ቱም ወረዳዎች እንዲገነባ አድርጓል፡፡ በተጨማሪም በ90 ቀን ሰው ተኮር ፕሮጀክት ባለሀብቶችን በማስተባበር አቶ መሠረት ለሀገር የሚጠቅም በጎ ተግባር ማከናወን ችሏል፡፡
አቶ መሠረት ከሰራቸው በጎ ልማታዊ ሥራዎች አንዱ የቱሉ ዲምቱን አደባባይ በ10ሚልዮን ብር ማስገንባቱ ነው፡፡
የሥራ ፈጣሪው እና ለምንም አይነት ፈተና የማይበገረው አቶ መሠረት ከዘመናዊ አፓርታማዎች ባሻገር ከ 5 እስከ 10 አመታት ለሚሆን ጊዜ ከመንግስት ጋር በመሆን አንድ ሚሊዮን አነስተኛ እና ወጪ ቆጣቢ ቤቶችን ለመገንባት ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ አቶ መሠረት እንደሚናገረው ይህን ግንባታ ለማከናወን የሚያስችሉ ሁሉንም ግብአቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት እንደሚቻል ይናገራል፡፡ ቤዝ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል በ10 የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች እያንዳንዳቸው ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የቱሪስት የመዝናኛ ማእከላት የመገንባት ራእይ አለው፡፡
ቤተሰብ
አቶ መሠረት በ1988 ጋብቻ የመሰረተ ሲሆን ባለቤቱም ወይዘሮ ገነት ተፈራ ትባላለች፡፡ ወይዘሮ ገነት ተፈራ የምታበረታታ እና ከጎን የምትቆም ሚስት እንደሆነች አቶ መሠረት ይናገራል፡፡ እርሱ እንደሚለው ለእኔ ስኬት ቀዳሚዋ ተጠቃሽ ባለቤቴ ናት ይላል፡፡ አቶ መሠረት ልጆቹን ጥሩ አድርጎ አስተምሯል፡፡ የመጀመሪያ ልጁ ሊዲያ መሠረት 2 ዲግሪ ያላት ሲሆን የቤዝ ኢንተርናሽናል ሆቴል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናት፡፡ ሁለተኛ ልጁ የሊዲያ ተከታይም ጺዮንም በሆቴል ውስጥ በከፍተኛ የማኔጅመንት ቦታ ትሰራለች፡፡ አቶ መሠረት ልጆቹ ለቁምነገር በቅተው በዚህ መልኩ ሲያገለግሉ ሲመለከት ርካታው ይጨምራል፡፡ በልጆች በመባረኬ ደስ ይለኛል ሲልም ልጆቹን ያመሰግናል፡፡ የጥሩ ስነ-ምግባር ባለቤት የሆኑት ልጆቹ ሀገራቸውን በመልካም ጎን እንደሚያስጠሩም ሙሉ ለሙሉ ይተማመንባቸዋል፡፡
ምንጭ፡- ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን
