‹‹የራስ መኮንንን ሐውልት አፍርሶ የጀነራል ሰዓረን መሥራት ትርጉሙ ምንድነው?›› አለባቸው ደሳለኝ ሐበሻ

Date:

‹‹የተዛባ ትርክት ብሔራዊ ኩራታችንን አጥፍቶታል››

‹‹ቅርስ ሦስተኛና አራተኛ የዓለም ጦርነት የሚያስነሳ ጉዳይ ነው››

የዛሬው የመጽሔታችን እንግዳ አለባቸው ደሳለኝ ሐበሻ ይባላል፡፡ ከሀገሩ ተሰድዶ ኑሮውን በሀገረ እንግሊዝ ካደረገ ሩብ ምዕተ ዓመት አልፎታል፡፡ አለባቸው በቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት ውስጥ ከራዲዮ ኦፕሬተር እስከ ጋዜጠኝነት ሰርቷል፡፡ የህወሓት/ኢሕአዴግ መንግሥት ኢትዮጵያን መምራት በጀመረ ብዙም ባልቆዩ ዓመታት ከሀገሩ የተሰደደው አለባቸው፣ በአውሮፓ ምድር የተዋጣለት ፎቶግራፈር ለመኾን በቅቷል፡፡ ለሀገሩ ኢትዮጵያ ያለውን ልዩ ፍቅር ገልጾ የማይጠግበው፣ ይኽም ስሜቱ ማይጨው ድረስ ዘምተው ከተሰውት አያቱ ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ እንደኾነ በአስረጂነት የሚያቀርበው የዛሬው እንግዳችን፣ በስደት በኖረባቸው ዓመታት በተለያየ መንገድ ከሀገር እንዲሸሹ የተደረጉ የኢትዮጵያን ቅርሶች በማሰባሰብ ሥራው ደግሞ በስፋት ይታወቃል፡፡ ለመኾኑ የቅርስ ባለውለታው አለባቸው ደሳለኝ ሐበሻ ማነው? ሕይወቱስ ምን ይመስላል ሲል የግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅ የሚከተለውን ሰፋ ያለ ቆይታ አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ!

ግዮን፡-  በቅድሚያ ራስዎን ለአንባቢያን ቢያስተዋውቁልን?

አለባቸው፡- አለባቸው ደሳለኝ አበሻ እባላለሁ፡፡ የተወለድኩት በቀድሞ ወሎ ክፍለሃገር በየጁ አውራጃ በወልዲያ ከተማ ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን በመልካም ቆሌ፣ መለስተኛ ደረጃ ትምህርቴን በእቴጌ ጣይቱ ብጡልና መድኃኔዓለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ነው የተማርኩት፡፡ እኔ 11ኛ ክፍል እያለሁ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥትም የልዩ ኃይል (ስፔሻል ፎርስ) ምልመላ ያደርግ ነበር፡፡ እኔም አጋጣሚውን በመጠቀም ገና በ16 ዓመቴ ልዩ ኃይሉን ተቀላቀልኩ፡፡ ሥልጠናውንም በቀድሞ ሲዳሞ ክፍለሃገር ቀጠልን፡፡   በወቅቱ ሲዳሞ ክፍለሃገር የሚባለው በጣም ሰፊ ነው፡፡ ቦታው ለሥልጠና ፈታኝና እጅግ ምቹ ነበር፡፡ ምቹ ነበር ማለት ሠራዊቱን በብቃት ለማነጽ እንጂ ከፈታኝነት አንጻር አይደለም፡፡ የስፔሻል ፎርስ ሥልጠናው በጣም ከባድና የተለየም ነበር፡፡ ስልጠንው እያገባደድን እያለን ‹‹ምጽዋ በሻዕቢያ እጅ ልትወድቅ ነው›› በሚል ምክንያት ወታደርዊ ግዳጅ ተቀብለን ወደምጽዋ ዘመተን፡፡ ምጽዋ እንደሄድን ሻዕቢያና ወያኔ አየር ማረፊያውን ለመያዝ እየተረባረቡ ነበር፡፡

እኛም ኤርፖርት እንደደረስን ከአውሮፕላን ወርደን በቀጥታ ወደ ውጊያው ነበር የገባነው፡፡ የእኛ ሥልጠና በአብዛኛው በከተማ ውጊያ ላይ መሠረት ያደረገ የእጅ በእጅ ውጊያ ነበር፡፡ ይኼኛው ደግሞ የእግረኛ ውጊያ ነው፡፡ በዚያ ላይ የተግባር ውጊያ ለእኛ የመጀመሪያችን ነው፡፡ የሻዕቢያና ወያኔ ደግሞ አካባቢውን በደንብ  የሚያውቁ ከአየሩ ጋር የተላመዱ በውጊያው ዘርፍም ብዙ ልምድ ያካበቱ ናቸው፡፡ በዚህ ተልዕኳችን ውስጥ የእኔ ሚና የሬዲዮ ኦፕሬተርነት መገናኛ ነበር፡፡

በዚያ በቀለጠ ውጊያ ውስጥ የእኛ ኃይል ከባድ መሳሪያ ሽፋን እየሰጠን ወታደራዊ ሥልት ተጠቅመን ወደ ጠላት ቀጠና ገባን፡፡ የሬዲዮ ኦፕሬተሮቹ ከእኔ ጋር አራት ነበርን፡፡ በመሐል ግን አንድ ባልደረባችን በጥይት ተመታና ሕይወቱ አለፊ፡፡ በዚህ መሐል የከባድ መሣሪያና የአየር ድብደባ ያለ ማቋረጥ ተካሄደ፡፡   አብዛኛው የኛ ኃይልም ከጠላት ጋር አንገት ለአንገት ተናንቆ ሊላቀቅ ባለመቻሉ አብሮ ተመታ፡፡ ከዚያ የተረፍነው በቀጠለው ውጊያ ውስጥ ግጥሚያችን በሳንጃና በቦንብ ብቻ ኾነ፡፡ ይህን ትግል የምናደርገው ምጽዋን እንዳይዙና በተለይም ዋናው የኢትዮጵያን በባሕር ኃይል ቤዝ እንዳይቆጣጠሩና ወደቡ እንዳይዘጋ  ለማድረግ ነው፡፡

በመኾኑም ውጊያው እየበረታ ሲመጣ ረዳት ጦር ሊደርስልን አልቻለም፡፡ በዚህ ምክንያት ሥልታዊ ማፈግፈግ አድርግን የምጽዋ ወደብንና የባሕር ኃይሉን የጦር ካምፕ አናስደፍርም በማለት ዐሥር ወር ሙሉ በምሽግ ውስጥ በጨው ባሕር ውስጥ ተከበን ነበር ያሳለፍነው፡፡ ለአንድ ቀን እንኳን ያልተቋረጠ ውጊያ ሳናደርግ፡፡ አንድ ኮድ ውሃ ለ48 ሰዓት እየተሰጠን ኮቾሮና ደረቅ ምግብ ብቻ እየተመገብን ዐሥር ወር ሙሉ ጭው ያለ ሜዳ ላይ መሽገናል፡፡ ከ10 ወር በኋላ 29ኛ ሜካንይዝድ ብርጌድን ይዘው እነ ጀኔራል ካሳዬ ጨመዳ በመርከብ ደረሱልን፡፡ ድንገተኛ ማጥቃት ከፍተን የሻዕቢያንና የወያኔን ሰራዊት በጨበጣ ውጊያ በሳንጃና በቦንብ ገጥመን የዐሥር ወር ከበባውን ምሽግ ሰብረን ወጣን፡፡

ግዮን፡- እንደምትነግረኝ ውጊያው እጅግ ከባድ ነበር ማለት ነው?

አለባቸው፡- እውነት ነው፡፡ እልህ አስጨረሽ በነበረው የምጽዋ ጦርነት የከፈልነው መስዋእትነት በደም ቀለም የተፃፈ ስለሆነ ወደፊት ትውልድና ታሪክ ይመረምሩትል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡ በዚያ የበርሃ ንዳድ የስፔሻል ፎርስ ጓደኞቼ በደም የተጨማለቀ አካላቸውን፣ በከባድ መሣሪያ ባሩድ የተቦደሰ ሰውነታቸው፣ ሐሩር የለበለበው ፊታቸውን፣ በረሀብ የተጣበቀ አንጀታቸውን፣ በውርጭና በሀሩር የተቃጠለ መላ አካላቸውን፣ አሁን ድረስ ሳስታውስው ከአዕምሮዬ ሊጥፋ አይችልም፡፡ ምናልባት. ዛሬ በሕይወት ተርፈው ይህንን ታሪክ ለማንበብ እድሉ የገጠማቸው የስፔሻል ፎርስ ጓደኞቼ ሕያው ምሥክሮች ናቸው፡፡

ግዮን፡- ምጽዋን ከጠላት ካስለቀቃችሁ በኋላ ቀጣዩ ግዳጃችሁ የት ነበር? ብዙ ሰው ተጎዳባችሁ?

አለባቸው፡- ምጽዋን ብቻ ሳይኾን አሥመራ መንገድንም ከሻዕቢያ ማስለቀቅ ነበረብን፡፡ አምስት መቶ ኾነን ከዘመትነው የስፔሻል ፎርስ አባላት ውስጥ የተረፍነው በመቶወች ቁጥር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ የቀረነው ከ33ኛ እግረኛ ብርጌድ ጋር ተደርበን የአሥመራ ምጽዋ መንገድ ከጠላት ነፃ አድርገን ከፈተነው፡፡ ቀጣዩ ግዳጃችን ደግሞ አሥመራ ውስጥ በጥበቃ ላይ የነበረውን የአየር ወለድ ግዳጅን ተረክበን በተንቀሳቃሽ ወታደራዊ ጂፕ መኪኖች ላይ በመሆን የከተማዋን አጠቃላይ ደህንነት መጠበቅ ነው፡፡ በተጨማሪም አሥመራ ውስጥ የሚገኙትን ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖችን የማጀብ ኃላፊነትም የእኛ ነበር፡፡

ግዮን፡- የአንተ የሥራ ድርሻ በወቅቱ ምን ነበረ?

አለባቸው፡- እንደነገርኩህ የኔ የሥራ ድርሻ ሬዲዮ መገናኛ በመሆኔ ከከፍተኛ የጦር አዛዦቹ የሚሰጡኝን ወታደራዊ ግዳጅ ለሚመለከታቸው አዛዦች ጠላት እንዳይሰማ በመመስጠር ማስተላለፍ ነው፡፡ ነገር ግን የቀይ ኮከብ ዘመቻ ሲጀመር የተለያየ ችሎታ ያለንን እየመረጡ አዲስ ምደባና ግዳጅ ተሰጠን፡፡

ግዮን፡- አንተ የት ተመደብክ?

አለባቸው፡- እኔ መጀመሪያ የሰሜን እዝ ሙዚቀኛ በሚባል ክፍል ውስጥ ተመደብኩ፡፡ ለተወሰነ ዓመት ከሰራሁ በኋላ የሁለተኛ አብዮታዊ ሠራዊት የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ክፍል ውስጥ ተመድበኩ፡፡

ግዮን፡- ከዚያስ የአንተ የሥራ ድርሻ ምን ነበር?

አለባቸው፡- ‹‹የጀግናው ገድል›› በሚል ርዕስ የሚታወቀውን የሰራዊቱን ገድል በሚዘግብ መጽሔትና ጋዜጣ ታላላቅ ፀሐፊዎች ከነበሩት ከነ ሻለቃ ክፍሌ አቦቸር፣ ሻለቃ ዓባይነህ አበራ፣ ከነገበየሁ ዋለልኝ (አሁን ሻለቃ) ከነሱ ጋር ተመደብኩ፡፡ ሰራዊቱ በሚገኝባቸው ሁሉም ቦታዎች ከማዘዣ ጣቢያ እስከ መጨረሻው ምሽግ ድረስ እየዞርን የጀግኖችን ተጋድሎ በጽሑፍ እናዘጋጅ ነበር፡፡ ለአደርኩትም ብቃት ያለው ወታደራዊ ግዳጅ ለበታች ሹሞች የሚሰጠውን ማዕርግ እስከ ሀምሳ አለቃ የማዕረግ እድገት ተሰጥቶኛል፡፡

ከቀይ ኮኮብ ዘመቻም በኋላ የሐረር ጦር ትምህርት ቤት ከ11ኛ ክፍል በላይ ያሉትን አባላትን ፈተና ይፈትን ነበር፡፡ እኔም ተፈትኜ በማለፍ አብሮኝ ይሰራ ከነበረው ጓደኛዬ ከገበየሁ ዋለልኝ ጋር ወደ ሐረር ጦር ትምህርት ቤት ሄድኩ፡፡ የእጩ መኮንነት ጊዜዬን ያሳለፍኩት ሐረር ነው፡፡ የሥልጠናው ጊዜም በጣም ከባድ ነበር፡፡ አንድ መኮንን እንዴት አድርጎ ወታደራዊ ግዳጅን መወጣት እንዳለበትና በሥሩ የሚገኙትን ወታደሮቹን ለግዳጅ ማዘጋጀት እንደሚገባው የውግያ ግዳጅ አፈፃፀም ነበር ትምህርቱ፡፡ እንደነገርኩህ ሥልጠናው ከባድ ሲሆን የምትመራቸው ወታደሮች ሕይወት በአንተ የአመራር ብቃት ነው የሚወሰነው ፤ ስለዚህ  ኃላፊነቱ ቀላል አይደለም፡፡

ግዮን፡- በወታደራዊ ማዕረግ ምን ደረጃ ድረስ ደርሰሃል?

አለባቸው፡- በማዕረግ ደረጃ ሻምበል ልኾን የተወሰኑ ጊዚያቶች  ሲቀረኝ ነበር ወያኔዎች አዲስ አበባ የገቡት፡፡

ግዮን፡-  የሥነ ጽሑፍ ፍላጎት ነበረህ?

አለባቸው፡- አዎ፣ በተማሪነቴ ዘመኔ የትምህርት ቤቱ ጋዜጠኛም ነበርኩ፡፡ በትምህርት ቤት ውስጥ የተለያዩ መድረኮች ሲዘጋጁ የተለያዩ. ፅሁፎችንና ቲይትሮችን  አቀርብ ነበር፡፡ በትምህርት ቤታችን ውስጥ የሥነ ጽሑፍ ውድድር እና ቲአትር ክበብ ነበረን፡፡ ቦይ እስካውትም ነበርኩ፡፡ እንደውም የቡድኑ መሪ እኔ ነኝ፡፡ በትምህርት ቤታችን የተለያዩ ዝግጅቶች ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነኝ፡፡ በሚደረግት የስፖርት ውድድሮች  ላይ ዜና እሰራለሁ፡፡ በየሳምንቱ ሰኞ ሰኞ ሰልፍ ላይ እየወጣሁ የስፖርት ዜና አነባለሁ፡፡ ትምህርት ቤት ሲዘጋ በወላጆች ቀን ድንቅ ከሚባሉት ቲያትር ተጫዋቾች አንዱ ነበርኩ፡፡ እንግዲህ በልጅነቴ የጀመርኩት የጋዜጠኝነት ሙያ ጦር ሜዳ ውስጥ አድጎ መኮንን ከኾንኩ በኋላም ጋዜጠኛ ሆንኩ፡፡ አሁንም ዓለም አቀፍ ፎቶግራፈር ጋዜጠኛ ሆኜ በሞያው ቀጥየበታለሁ፡፡

ግዮን፡- በመኮንንነት ዘመን የነበረህ ቆይታ ምን ይመስል ነበር?

አለባቸው፡- በመከላከያ ኮንስትራክሽን ሰርቻለሁ፡፡ የጦር ኃይሎች ራዲዮ ፕሮግራም ጋዜጠኝም ሆኜ አገልግያለሁ፡፡ እንደውም የመጨረሻ ሥራዬ የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች ጋዜጠኛ እንደነበርኩ ነው ግዳጄን የጨረስኩት፡፡ አብዛኛው የምጽፋቸው የጋዜጣ ሥራዎች ነበሩ፡፡ ወደ ሬዲዮ ስመጣ ደግሞ የሬዲዮ ሥራዎች ውበታቸውም ይሁን አገላለፃቸው የተለየ ነው፡፡ ለሬዲዮ ተብለው የሚዘጋጁ ናቸው፡፡ በተለይ ‹‹ትንሣኤ ኢትዮጵያዎች›› የሚል የጀግኖች ታሪክ ረቡዕ ምሽትና እሁድ ፕሮግራም እየተዘጋጀ ለአድማጭ የሚደርሰውን ፕሮግራም የምፅፈው እኔ ነበርኩ፡፡ አብዛኛው የጋዜጠኝነት ሥራዬን የጀመርኩት አሥመራ ነው፡፡ በጀግኖች የሕይወት ታሪክ ዙሪያ ነው የምፅፍው፡፡ በነገራችን ላይ አባቴ አቶ ደሳለኝ አበሻ ነው የሚባሉት፡፡ አያታችን አበሻ አግደው በማይጨው ጦርነት ጦር መርተው የሄዱና ለሐገራቸው ጦር ሜዳ ላይ ተሰዉተዋል፡፡ አባቴም በማይጨው ጦርነት ገና በዐሥራ ሦስት ዓመቱ ከአባቱ ጋር አብሮ ነው የዘመተው፡፡ አባቱ ጦር ሜዳ ላይ ሲሞቱበት የአበሻ አግደው ልጅ ነው ተብሎ በጣሊያኖች ታስሮ አዚናራ ጣሊያን ሐገር  ለአምስት ዓመት ከታሰሩት ከ270 በላይ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያኖች ውስጥ አንዱ የኔ አባት ነው፡፡ ከኢጣሊያ የመጣው ከነጻነት መልስ ነው፡፡ የአባቴ እህቶችም አርበኞች ነበሩ፡፡ አባቴ ዐሥራ አንድ እህቶች ነበሩት፡፡ እኔም አምስት እህቶች ነበሩኝ፡፡ ለእናቴ አንድ ወንድ የስለት ልጅ እኔ ብቻ ነበርኩ፡፡ በእርግጥ ከሌላ የተወለደ አንድ ትላቅ ወንድም ነበረኝ በሕይወት ግን የለም፡፡

የአባቴ እህቶችም ጀግና አርበኞች ነበሩ፡፡ ብሬ አበሻ፣ ሁሉአገር አበሻ እና ዘውዲቱ አበሻ ይባላሉ፡፡ እነዚህ እህቶቹ ከአርበኞች ጋር ተቀላቅለው ከጠላት ሠራዊት ጋር ተፋልመዋል፡፡ በአካባቢው የታወቁ ስለነበሩ በሞታቸውም ጊዜም የተለያዩ ግጥሞች የተገጠመላቸው ናቸው፡፡

‹‹አየ ሰው አየ ሰው፣ አየ ሰው በከንቱ፣

ብሬ አበሻም ሞተች ሴቲቱ ወንዲቱ›› ሲባልላት ለአባቴ ደግሞ፣

‹‹ወንዱ የወንዱ ልጅ ደሳለኝ አበሻ፣

እራስ ተረግጦ ይመታል ትካሻ፣

የጣሊያንን ባንዳ አሳጥው መድረሻ›› ይባልልቸው ነበር፡፡

በነገራችን ላይ የጀግና ግጥም ለእነርሱ ብቻ ሳይኾን ለአበሻ አግደውም እጅግ በርካታ ግጥሞች ተገጥመውላችዋል፡፡

ግዮን፡- በምህበራዊ ሚድያም ሆነ በጋዜጦች ላይ ስትፅፍ ‹‹አለባቸው ደሳለኝ አበሻ›› ትላለህ፡፡ ብዙ ሰው  ‹‹አበሻ›› የሚለው ቅጽል ሥምህ ይመስላቸው ነበር፡፡ ትክክለኛ የአያትህ ሥም ነው ማለት ነው?

አለባቸው፡- ትክክል ነው፡፡ አበሻ አግደው የሚባሉት የማይጨው ዘማች አያቴ ናቸው፡፡ እንደነገርኩህ ማይጨው ዘምተው አልተመለሱም፡፡ እዚያው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ሲያስከብሩ ሞተዋል፡፡ አባቴም ለኢትዮጵያ ልዩ ፍቅር የነበራቸውና እስከሚሞቱ ድረስ ጠንካራ አቋም ነበራቸው፡፡ መኖሪያ ቤታቸው የኢትዮጵያ ጀግኖችን አልለባሳቶች፣ ጎራዴዎች፣ ጋሻዎች፣ ጦሮችና ሰይፎች ነበሯቸው፡፡ ሳሎን ግርግዳቸው ላይ ነበር የሚሰቅሏቸው፡፡ ጠንካራ የኦርቶዶክስ ሃይማኖተኛም ነበሩ፡፡ በምንኖርበት ግቢያችን ውስጥ ስለማርያም የምትባል ቤተክርስቲያን ነበረቻቸው፡፡ የአባቴ ነፍስ አባትና ቄሶች እየመጡ እሁድ እሁድ ይፀልዩባት ነበር፡፡ ብዙ የቤት ሠራተኞችም ነበሩት፡፡ ሁሉንም ግን ከእኛ አይለያቸውም፤ ልጆቼ ነበር የሚላቸው፡፡ ድሀ ሲበደል አይወድም፡፡ ወደ ከተማ ሲወጣ መሣሪያ በታጠቁ የግል ጠባቂዎቹ ታጅቦ ነው፡፡ ይህም በወቅቱ ከጃንሆይ ጋር ቅሬታ ውስጥ አስገብቷቸው ነበር፡፡ ለመንግሥት ያስጋሉ ተብለው ልዩ  ክትትልም ይደረግበቸው ነበር፡፡

አባቴ ግን በነገሩ ሁል ጊዜ ይገረሙ ስለ ነበረ ‹‹ኢትዮጵያ አፍ የለሽ አትናገሪ›› ይሉ ስለነበረ ከሞቱም በኋላ እስከ ዛሬ ድረስ የሚያውቋቸው ትልልቅ ሰዎች ‹‹ኢትዮጵያ አፍ የለሽ አትናገሪ አሉ ደሳለኝ አበሻ›› እየተባለ ማስታወሻቸው ሆኗል፡፡ በተለይ ድምጻዊ አያሌው መስፍን ስለአባቴ ሲነግረኝ አፌን ያስከፍትኛል፡፡ በደንብ ነው የሚያውቃቸው፡፡ በጥቅሉ አባቴ ለሀገራቸው ብዙ የሠሩና ብዙ ነገር የሰሩ ስለነበሩ፣ እስከ አሁን ድረስ በተወለድንበት አካባቢ ያሉት ትልልቅ ሰዎች በክብር ያስታውሷቸዋል፡፡ ለእኔም ለእህቶቼም በሕዝቡ ሥም ደብዳቤ ይልክልናል፡፡ የአባቴን ግቢ በሙሉ ለቤተክርስቲያን መሥሪያ እንድንሰጣችው ጠይቀውን በሥጦታ አበርክተንላቸዋል፡፡ ቤተክርስቲያኑንም እንዲያሰሩበት ገንዘብ አሰባስበን ልከንላቸው ሰርትው ጨርሰው እየተገለገሉበት ነው፡፡

ግዮን፡-  አባትህ በስንት ዓመታቸው አረፉ?

አለባቸው፡-  አባቴ ሲያርፉ እኔ ልጅ ነኝ፡፡ ወደ ስድሳ ዓመት ይሆናቸዋል፡፡ ነገር ግን በልጅነት አዕምሮ የተቀረፀ በመሆኑ ሁሉንም አስታውሰዋለሁ፡፡ በትክክል የሞቱበትን ቀንና ዓመት ምሕረቱን እህቴ መዝግባ አስቀምጣዋለች፡፡

ግዮን፡- የህወሓት መንግሥት ሀገሪቱን ሲቆጠር ምን ስሜት ተፈጠረብህ? በወቅቱ  የት ነበርክ?

አለባቸው፡- ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ወያኔ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር በወቅቱ የጦር ኃይሉ ሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው አቶ ሲሳይ ታደሰ ጋር በመሆን ለፕሮግራም ሥራዎች ክፍለ ሐገር ሔደን አሰብ ነበርኩ፡፡ ምጽዋ በሻዕቢያ መያዟን የሰማሁትም እዚያው ሆኜ ነው፡፡ እጅግ በጣም ያዘንኩበት ቀን ነበረ፡፡ የአገሪቱም ሕልውና ከፍተኛ አደጋ ላይ መሆኑንንም የተረዳሁት ከዚያ በኋላ ነው፡፡ በ1970 ምጽዋን ላለማስደፈር እኔና ጓደኞቼ የከፈለነውን መስዋዕትነት እያሰብኩ አልቅሻለሁ፡፡ ስሜቱን እንደዚህ በጽሑፍ እንድምትተርክው ቀላል አይደለም፡፡ ከሕዝብ አካል ተከፍለህ ሕይወትህን ኖረህ፣ ለአገርህ ክብር ሰጥተህ፣ ጠላትህን እግርህ ሥር አንበርክከህ በክብር ሞትህን መርጠህ አገርና ሕዝብህን መታደግ አንዱ ወታደራዊ ግዳጃችንና ተልዕኳችን  ነበር፡፡

ይህንን መርህ ተቀብለን ሰንደቅ ዓላማችንን ክንዳቸን ላይ ጠቀልለን፡፡ ለኢትዮጵያ አንድነት ክብር ስንል ምጽዋ ላይ በተደረገው ጦርንት አገራችንን እና ወገናችንን አኩርተንም ነበር፡፡ በተለይ ከሥልጠና እስከ ጦር ግንባር አብሬያቸው ዘምቼ በኤርትራ በርሃዎች በምጽዋ ጦር ግንባር ታሪክ ሰርተው የወደቁትን የልዩ ወታደራዊ ክፍል ‹‹ስፔሻል ፎርስ›› አባሎች ያሳለፍነው ተጋድሎ ሳስብ ሆድ ባሰኝ፡፡ ይኽን ሁሉ የሰው ኃይል ጨርሰን ምጽዋን ላለመስያዝ የከፈልነውን መስዋዕትነት ከንቱ ሆኖ መቅረቱን ስገነዘብ ልቤ በአንድ የደነዘ ስለት የተወጋ ያህል ነው የተስማኝ፡፡ በዚያ የበርሀ ንዳድ ‹‹ስፔሻል ፎርስ›› ጓደኞቼ በደም የተጨማለቀ አካላቸውን በከባድ መሣሪያ ባሩድ የተቦደሰ ሰውነታቸው በርሃ የለበለበው ፊታቸውን በርሀብ የተጣበቀ አንጀታቸውን በውርጭና በሀሩር የተቃጠለ መላ አካላቸውን በሐሳቤ እየመጣ ሀዘን ገባኝ፡፡ የኢትዮጵያ ‹‹ስፔሻል ፎርስ›› ወታደሮች የከፈሉትን መስዋዕትነት ለመረዳት በውስጡ ካላለፍክ በስተቀር በቃል ለማስረዳት ከባድ ነው፡፡

በጥይት እርሳስ እየተቆላን፣ በቦንብ ውርጅብኝ መላ አካላችን እየነደደ፣ ላንቃቸው እሳት በሚተፉ ከባድና ቀላል መሣሪያዎች በግንባርና በደረታችን፣ በእግርና በእጃችን በመላ አካላታችን ላይ ጥይቶች እያራገፉብን  ደማችንን አፍስሰን ውድ ሕይወታችንን፣ ለቀይ ባሕር ምጽዋ ላይ በአጥንትና በደማችን ታሪክ ሰርተን ነበር ግዳጃችንን የተወጣነው፡፡ ወገን ብቻ ሳይሆን የጀግነታችንን ልክ የቱ ድረስ እንደነበረ ምጽዋ ሕያው ምስክር ናት፡፡

‹‹ቢሻው በጨበጣ ጥሎ በኮማንዶ፣

ለዐሥር አንድ ይበቃል እስፔሻል ኮማንዶ›› እየተባለ ይገጠምላቸው ነበር፡፡ ምን ዋጋ አለው?!

ግዮን፡- ይቅርታ ወደ ረጅም ትዝታ አስገባሁህ፡፡ አሰብ ከሔዳችሁ በኋላ መጨረሻ እንዴት ሆናችሁ?

አለባችው፡- በወቅቱ ሥራችንንም ሳናጠናቅቅ ከአሰብ እንድንመለስ መታዘዛችንን የፕሮግራሙ አዘጋጅ አቶ ሲሳይ ታደሰ ነገረኝ፡፡ የሚገርምህ አዲስ አበባ ኤርፖርት ከገባን በኋላ በማግሥቱ የአውሮፕላን በረራ በአገሪቱ ተከለከለ፡፡ አንድ ቀን ብንቆይ አዲስ አበባ አንመለስም ነበር፡፡ ወያኔም አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ ሰራዊቱን በትነው ጎዳና ላይ ለማኝ አደረጉት፡፡ ይኼ ክፋት በጣም ልብ ይሰብር ነበር፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ታሪክ እዚህ ላይ ያበቃ ነበር የሚመስለው፡፡ ኾኖም ውሎ አድሮ የዘሩትን መልሰው አጭደውታል፡፡

ግዮን፡- ህወሓት አዲስ አበባ ከገባ በኋላ ለምን ያህል ጊዜ ቆየህ?

አለባቸው፡- የጦር መኮንኖችን ወያኔዎች ወደ ሆለታ ወስደው ጦር ካምፕ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ አስቀመጡን፡፡ ቆይተው ወደ ጦላይ ወሰዱን፡፡ እዚያም ተሓድሶ ብለው አሰሩን፡፡ ጦላይ ሁሉ ነገሩ በአውሬና በወያኔ ጦር የታጠረ ነው፡፡ እዚያ እያለን አንድ ቀን አብሮኝ የነበረውን የቀድሞ አለቃዬን ሻለቃ ክፍሌ አቦቸርን ከእሥር እናምልጥ ብየ አማከርኩት፡፡ እሱም ለግዜው እንዳልተዘጋጀበትና ልጆች ስላሉትም በአንድ ጊዜ ለመወሰን ተቸገረ፡፡ እኔ ደግሞ በሥልጠና ወቅት የተማርኳትን ማምለጥና መሰወር ለዚህ ጊዜ ማገልግል ነበረባት፡፡ እንዴት ከዚህ እሥር ቤት ማምለጥ እንዳለብኝ ከራሴ ጋር ተማከርኩ፡፡ እሥረኞችን ለመጠየቅ በየቀኑ የሚመላለሱትን አሽከርካሪዎች ጋር ስለ ጉዟቸው ጥያቄዎችን በማቅረብ የተለያዩ መረጃዎችን ለማግኘት ቻልኩ፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ጦላይ ድረስ ያለው ፍተሻ ምን እንደሚመስልና የት የት እንዳለ እንዲሁም መንገደኞች ለማለፍ የሚጠበቅባቸው ግዴታዎችን መረጃ ሰበሰብኩ፡፡ ስለዚህ ፈታሾች አንድን ተጓዥ ፍተሻውን ለማሳለፍ ከሾፌርና ከረዳቱ በቀር በዋናነት መታወቂያ እንደሚያስፈልገው ገባኝ፡፡

እኔ ለዚህ ስልት ነደፍኩ፡፡ ሹፌሩን አግኝቼ መታወቂያ አሰርቶ እንዲያመጣልኝ ስጠይቀው ከባድ መኾኑንና እንደማይችል ነገረኝ፡፡ ነገር ግን ሌላ መንገድ መቀየስ ስለነበረብኝ ከረዳቱና ሹፌሩ ጋር በመመነጋገር እኔ እንደረዳት፣ ረዳቱ ደግሞ መታወቂያውን ይዞ እንደተሳፋሪ ኾነን ለመጓዝ ተስማማን፡፡ በነገራችን ላይ ሹፌሩ ከሰራዊቱ በቦርድ የተሰናበተ በመሆኑ ደፋር ነው፡፡ ድፍረቱም ለኔ ሐሳብ አግዞኛል፡፡ በዚያ መሠረት እኔ ረዳት፣ እርሱ ተሳፋሪ ኾነን ፍተሻዎችን ሁሉ አለፍን፡፡ በዚህ መልኩ በሎንችና ተስፍሬ አዲስ አበባ ገባሁ፡፡ ለዚህ ውለታችንም አንድ ሺህ ብር ከፍያለሁ፡፡ ያረፍኩትም አሥመራ መንገድ አንዲት ዘመዴ ቤት ነበር፡፡ በወቅቱ ጓደኞቼ የሐገር ፍቅር አርቲስቶች እነተፈሪ ዓለሙ፣ አብራር አብዶ፣ አበበ ተምትም፣ ኪሮስ፣ ዮሐንስ ብርሀኑ፣ ከሌሎቹም ቲያትር ቤቶች በሥም ጠቅሼ የማልጨርሳቸው በጣም ብዙ ጓደኞች ነበሩኝ፡፡ እኔ ታስሬ በነበረበት ወቅት የአንድ ወር ደሞዜን የሀገር ፍቅር አርቲስቶች አዋጥተው በተፈሪ ዓለሙና በአብራር አብዶ በኩል ሆለታ ድረስ ልከውልኛል፡፡ ጓደኛዬ ተፈሪ ዓለሙም ግቢው ውስጥ ጠያቂ ሆኖ ገብቶ ስንጫወት ውለን ሊወጣ ሲል ግቢው ተዘግቶበት እኛው ጋር አብሮ እድሮ ጧት ሲነጋ ወጥቶ ሔዷል፡፡ በዚያን ግዜ የነበረን ፍቅርና መተባበር ይህን ይመስል ነበረ፡፡

በነገራችን ላይ አብዛኞቹ የአዲስ አበባ ልጆች ጓደኞቼ ወታደራዊ መኮነን መኾኔን አያውቁም፤ ሲቪል ልብስ ስለሆነ የምለብሰው የሀገር ፍቅር ሰራተኛ ነበር የምመስላቸው፡፡ እኔም ስለማልናገር ጋዜጠኛ መኾኔን ነው የሚያውቁት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከሀገር ፍቅር ልጆች ጋር የነበረኝ ትስስር ቲያትርና ሥነ ጽሑፍ አፍቃሪ በመሆኔ ብቻ የመጣ ነው፡፡ ከሀገር ፍቅር ጋር የቅርብ ቁርኝነት ሊኖረኝ የቻለበት ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም በጣም ተግባቢና ተጫዋች አዛኝም በመሆኔ በችግሬ እንደ ደረሱልኝ በደስትም ሆነ በክፉ ጊዜም እስክ አሁን ድረስ አልተለያየንም፡፡ እውነቱን ለመናገር በጣም ያከብሩኛል በጣም ይወዱኛል፡፡ እኔም ለነሱ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር አለኝ፡፡ አንዱ ጓደኛችን የሆነ ነገር እንኳን ከገጠመው ተፈሪ ደውሎ ይነግረኛል፡፡

ግዮን፡- በምን አጋጣሚ ከሀገር ወጣህ? ከመውጣትህ በፊት ትዳር አልመሠረትክም ነበር?

አለባቸው፡- አልመሰረትኩም፡፡ ግን አንድ የሆነ ታሪክ ላጫውትህ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከሥራ መልስ የምናመሽበት ቡና ቤት ነበረ፡፡ ከሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት ዝቅ ብሎ፡፡ የሆቴሉ ባላቤት አንድ ቆንጆ ሴት ልጅ ነበራቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቿን ለማገዝ ትመጣ ስለነበር ከኔ ጋር ተዋቀን፡፡ ቤተሰቦቿ ሳያውቁ በሚስጥር ጓደኝነት ጀመረን፡፡ ብዙ ሰዎች ስለሚያስቸግሯት እኔ ጋር ካልተጋባን እያለች አስቸገረችኝ፡፡ በዚያን ወቅት ገና አብደን ያልጨረስን ጎረምሶች ነን፡፡ አንድ ቀን አርብ ምሽት ወጋየሁ ንጋቱ፣ አብራር አብዶ፣ ተፈሪ ዓለሙና እኔ ተሰባስበን ቢራ እየጠጣን ሞቅ ብሎን እንጫወት ነበር፡፡ ልጅቱ በድንገት መጣች፡፡ አባቷ የሉም፤ ጨዋታ ተጀመረ፡፡ ሚስጥሩ ሁሉ ተዘርግፎ ሁሉም ሰሙት፡፡ የጋብቻውም ጉዳይ ተነስቶ ለሰርጉ ዝግጅት እንዲጀመር ፕላን ማውጣት ጀመርን፡፡

ወጋየሁ ንጋቱ፣ አብራር አብዶ እና ተፈሪ ዓለሙ እሁድ ጧት ሽማግሌዎች ሆነው አባቷ ቤት እንዲሔዱ አርብ ማታ ተወሰነ፡፡ እሷም ለእናቷ እሁድ ሽማግሌዎች ስለሚመጡ ዝግጅት እንዲያደርጉ እንድትናገር ሓላፊነት ተሰጣት፡፡ ተፈሪ ደግሞ ‹‹እኔ ሚዜ ነው እንጂ ሽማግሌ አልሆንም›› ብሎ አስቸገረ፡፡ በዚያ ምሽት ሌላ ሰው ለማግኝት ስለሚያስቸግር ወጋየሁ ንጋቱና አብራር አብዶ ብቻ እንዲሔዱ ተወሰነ፡፡ ውሳኔ ላይ በጣም ቆራጥ ነኝ፡፡ በነገራችን ላይ ሀገር ፍቅር ቲያትር ቤት በሥሜ አይጠሩኝም፡፡ ‹‹መይሳው›› በሚል ቅፅል ሥም ነው የሚጠሩኝ፡፡ ሥሙን ያወጣልኝ ነፍሱን ይማረውና ፍቃዱ ተክለማርያም ነው፡፡ አንድ ምሽት አብረን ድራፍት እየተጎነጨን ስንጫወት ፍቃዱ የሠራውን ‹‹ቴዎድሮስ›› ቲያትርን ከዐሥራ ሁለት ጊዜ በላይ አይቸው ስለነበር ቲያትሩን በቃሌ አውቀዋለሁ፡፡ በአጋጣሚ  የቴዎድሮስ ቲያትር ጉዳይ ተነሳ፡፡ ከመጀመሪያው እስከመጨረሻው ድረስ ፍቃዱ ተክለማሪያም የሠራውን ቴዎድሮስ ምንም ሳልሳሳት እንደሱ ሆኜ ተረኩለት፡፡ ፍቃዱም ተገረመ፡፡ ደስ አለው፡፡ ከዚያ በኋላ መይሳው ያንተ ስም ነው ብሎ ሰየመኝ፡፡

ከዚያ በኋላ ነፍሱን ይማረውና ዮሐንስ ብርሃኑ ወሬውን አሰራጭቶት ጓደኞቼ ሁሉም ሰሙት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሥሜን ትተው መይሳው እያሉ መጥራት ጀመሩ፡፡ እኔም አቤት ማለት ጀመርኩ፡፡ እስካሁንም ድረስ ሥሙ ፀድቆ ስንገናኝ ‹‹መይሳው›› ብለው ነው የሚጠሩኝ፡፡ ወደጀመርኩት የሽምግልና ታሪክ ልመለስህ፡፡ ለትዳር የመረጥኳት ልጅ ለአባትና እናቷ ተናግራ ሽማግሌዎቹ ተልከው ጋብቻው ተፈቀደልኝ፡፡ ወደ ትዳሩ ልንገባ፣ እኔም ቤተሰቦቼን አስተዋውቄ ሽር ጉድ ተጀመረ፡፡ ነገር ግን ከልጅቱ ጋር መስማማት አቃተን፡፡ ከጓደኞቼ ጋር ለመገናኘት እሷን ማስፈቀድ ግድ ሆነብኝ፡፡ እኔ ገና ዘልዬ ያልጠገብኩ ጎረምሳ ነኝ፡፡ እንዴት ብየ ነው የምሔድበት ቦታ ሁሉ እየነገርኩ አስፈቅጄ የምዘልቀው፡፡ በእውነት ልለምደው አልቻልኩም፡፡ በዚህ ምክንያት ነፃነቴ ናፈቀኝ፡፡ ሳንጋባ ሽምግልናው ሳይፀና ቀረ፡፡ ከሷም ጋር አልቀጠልንም፡፡

ግዮን፡- ከኪነጥበቡ ጋር ያለህ ተዛምዶ ምንድነው?

አለባቸው፡- ኪነጥበብ በጣም እወዳለሁ፡፡ ከኪነጥበብ ውጪ ጤናማ ሕይወት ያለ አይመስለኝም፡፡ ሀገር ፍቅር ገብቼ የቆየሁትም ለዚህ ነው፡፡ ሀገር ፍቅር ደሞዝ ባይከፍለኝም ከሠራተኞቹ እኩል ነበር የምታየው፡፡ ከጦላይ እንደመጣሁ አሥመራ መንገድ የነበሩት ዘመዴ ቤት ተቀምጨ ፊልም መፃፍ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ፀፀት›› የሚለውን ፊልም ፅፌ ስፖንሰር ፈልጌ ወ/ሮ ሩቅያ አሕመድን በወንድማቸው በአቶ ገረመው በኩል አገኘሁ፡፡ አርቲስቶችን አሰባስቤ ፕሮፌሽናል የሆኑ የፊልም ኮርፕሬሽን ሙያተኞች ጋር ነው የሰራሁት፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ፊልም መሳካት ከጎኔ ሳይለኝ የረዳኝን የረዥም ጊዜ ጓደኛዬን ተስፋዬ ሲማን ሳላመሰግነው አላልፍም፡፡ እንደነገርኩህ ፊልሙን ቀርፀን ከጨረስን በኋላ የእህቴ ባል አስመጪና ላኪ ስለነበር ፓስፖርት  አውጥቶልኝ ስኮላርሽፕ ሆላንድ ላከኝ፡፡ የጀርመን፣ የእንግሊዝና የሆላንድ ቪዛ ስለነበረኝ ሆላንድ መሔዴን ሰርዤ ቤተሰብቼ ጋር እንግሊዝ አገር ለንደን ቀረሁ፡፡

ለንደን የስደተኝነት መብት ተሰጥቶኝ ላለፉት 30 ዓመታት ተቀመጥኩ፡፡ ለክብሯ፣ ለዳር ድንበሯ መከበር የልጅነት ወዜን ሳልሰስት ለ13 ዓመት ያገለገልኳት፣ ደሜን ያፈሰስኩላት፣ የሐገሬ ሰዎች ውለታ ቢስ አድርገው በየትኛውም መንግሥታዊ መሥሪያ ቤት እንዳልቀጠር ሜዳ ላይ ሲጥሉኝ፣ ከፍቶኝ ሐገሬን ትቼ ስሰደድ ተቀብለው ያስተናገዱኝ እንግሊዞች ነበሩ፡፡ እናም እንግሊዝን እንደ ሁለተኛ ሀገሬ አድርጌ ሁለት ወንድ ልጆችን ወልጄ ላለፉት 30 ዓመታት የስደት መጠለያ ቤቴ አድርጌ እየኖርኩባት ነው፡፡ ኮሌጅ በመግባት የፎቶግራፍ ጋዜጠኝነትን ሙያ ተምሬ ጨረስኩ፡፡ ከዚያም በዓለም አቀፍ የፎቶግራፍ ጋዜጠኛነት ሙያ በለንደን ማራቶን በዩኬ አትሌቲክስ በሌሎች በርካታ ዝግጅቶች ላይ እየተገኘሁ በመሥራት መኖርን ሕይወቴ አደረኩት፡፡

ግዮን፡- ስለ ፀፀት ፊልም ትንሽ ብታብራራልኝ?

አለባቸው፡- ፀፀት ፊልም ሠርተን ጨረስን፡፡ ኤዲቲንግ ሲጀመር እኔ ከሀገር መጣሁ፤ ከዚያ በኋላ የማናቸውም ስልክ ስላልነበረኝ ማንንም ማግኘት አልቻልኩም፡፡  ክግዜ በኋላ ግን ሒልተን ሆቴል ተመርቆ አዲስ ዘመን ጋዜጣና ኢትዮጵያን ሄራልድ አውጥተውት አየሁ፡፡ ከዛ በኋላ ፊልሙን ስፖንሰር ያደረገችውን ወ/ሮ ሩቅያ አሕመድ ጋር በብዙ ጥረት ተገናኘን፡፡ ወደ ለንደን ይዛው እንድትመጣ ግብዣ ልከንላት የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ይዛው መጥታ ለሁለት ቀን ለንደን ከታየ በኋላ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ አድርገናል፡፡

ግዮን፡-  ‹‹ፀፀት›› ፊልም በምን ላይ ነበር የሚያተኩረው?

አለባቸው፡- የፍቅር ፊልም ነው፡፡ የትናየት ደሳለኝ የምትባል ታላቅ እህት ነበረችኝ በሕይወት የለችም፡፡ በጣም ቆንጆ ነበረች፡፡ ለእርሷ ማስታወሻ ስል ‹‹የትናየት›› በማለት ፊልሙን ፃፍኩት፡፡  በኋላ ግን ‹‹ፀፀት›› የሚል ሥም ተሰጠው፡፡ ፊልሙ በጥበቡ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ሁሉ ያሳተፈ ነበር፡፡ ተወዛዋዦች ዘፋኞች ሳይቀሩ በፊልሙ ላይ ተውነውበታል፡፡ ከ150 በላይ የሚደርሱ ሰዎች በፊልሙ ተሳትፈዋል፡፡ እነጀምበሬ በላይ፣ ፍቃዱ ተ/ማርያም፣ ተስፋዬ ሲማ፣ አምሀ ተወዳጅ፣ ኪሮስ ኃይለሥላሴ፣ አበበ ተምትም፣ በላይነሽ አመዴ፣ አስናቀች ወርቁ፣ ሙናዬ መንበሩ፣ ኩሪባቸው ወ/ማሪያም፣ ቻቺ ታደሰ፣ መልካሙ ተበጀ፣ ጌታቸው የሻው፣ የሺ ተክለወልድ እና ሌሎችም ዛሬ ላይ በሕይወት የሌሉ የሀገራችን አንጋፋንና እውቅ አርቲስቶች የተሳተፉበት ፊልም ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ28 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤትና በአምባሳደር ፊልም ቤት ለሕዝብ ቀርቦ ተወዳጅነትን አትርፏል፡፡

ከዚያ በኋላ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ተቋረጠ፡፡ ነገር ግን ፊልሙ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን በቅርስነት እንዲቀመጥ ኮፒው ተሰጥቷል፡፡ የኢትዮጵያ የፊልም እድገት የዔሊ ጉዞ ነው፡፡ ማንም ባለሀብት ገንዘቡን ለፊልም አያወጣም ነበር፡፡ ወ/ሮ ሩቅያ ብቻ ነች ለመጀመሪያ ጊዜ አግባብቼ ለምኜ እንድትሠራ ያደረኳት፡፡ ፀፀት በመንግሥት ሳይኾን በግል የተሠራ እና ለኢትዮጵያ የፊም እድገት እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ትልቅ ድርሻ ያለው ነው፡፡ ፀፀት የብዙዎችን ዓይን የገለጠ ፊልም ነው ማለት ይቻላል፡፡ የፊልም ጥበብ ኢትዮጵያ ውስጥ ለደረሰበትና አሁን ላለበት እድገት በትንሹም ቢሆን ፀፀት የራሱ የሆነ ድርሻ አለው፡፡ ከፀፀት ፊልም በፊት የተሠሩ ፊልሞች ከጥቁርና ነጩ ምስል ቀጥሎ በባለቀለም የመጀመሪያው በመንግሥት የተሠራው ፊልም አስቴር ነው፡፡ ፀፀት የአስቴር ፊልም በተሠራ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው የተሠራው፡፡

ግዮን፡- በፎቶግራፍ ጋዜጠኝነት ሙያ እንድትዘልቅ ያደረገህ ምክንያት ምንድነው?

አለባቸው፡- ከሀገር የወጣሁትና ለመማር የሄድኩት የፎቶግራፍ ጋዜጠኛ ለመሆን አልነበረም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ያገኘሁት ክፍት ኮርስ እርሱን ብቻ ነበር፡፡ እኔ ከሀገር ስወጣ ብዙ ኮርሶች ተጀምረው ነው የጠበቁኝ፡፡ ማጥናት የምፈልገው ኮምፒውተር ሳይንስ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉንም ኮርሶች ከመጀመራቸውም በፊት እኔ የመረጥኩት ኮርስ ዲፓርትመት አልነበረም፡፡ ስለዚህ የትምህርት ዘመኑ እንዳያልፈኝ በጓደኛዬ ምክር መማር ጀመርኩ፡፡ ትምህርቱን ስጀምረው እየወድድኩት መጣሁ፡፡ አራት ዓመት ተምሬ በማጠናቀቅ ወደ ሥራው ገባሁ፡፡ የጋዜጠኛነት ፎቶግራፈር ዋናው ሥራው ሪፖርት ነው፡፡ ‹‹አንድ ፎቶ ዐሥር ሺህ ቃላት ይናገራል›› እንደሚባል ሁሉ የኔ ሙያ ፎቶግራፎችን አንስቶ ለኤጀንሲዎች መሥጠት ነው፡፡  በነገራችን ላይ ተማሪ ኾኜ አንድ ገጠመኝ አለኝ፡፡ ኃይሌ ገ/ሥላሴ የሚሮጥበት ቀን ነበር፡፡  በወቅቱ ያሸነፈበትን ቲሸርት ፈርሞ ሰጥቶኝ አሁንም አለኝ፡፡ ትምህርት ቤታችን ለስፖርት ጋዜጠኛነት በየቦታው ይልከናል፡፡ እኔ የያዝኳት ካሜራ አንድ ሌንስ መቀየሪያ ያላት. የትምህርት ቤቱ ካሜራ ነች፡፡  ቦታው ተሯሩጦ የሚነሳበት አይደለም፡፡ ጥግህን ይዘህ እየከነፈ የሚመጣውን አትሌት በፈጣን ስፒድ ካሜራ ክንድ ክንድ በሚያካክሉ የዙም ሌንሶች መልቀም ነው፡፡ የፎቶግራፍ ጥበብ አሁን የረቀቀ ሳይንስ ሆኗል፡፡ በምን ያህል ርቀት የምትፈልገውን ዉጤት እንደምታመጣ የምትመርጣቸው አንግሎችና ሳብጄክቶች የአንድ ፎቶግራፍ ባለሙያ ወሳኝ ሥራዎች ናችው፡፡ ፎቶግራፈር ጋዝጠኝነት እራሱ የቻለም ዲስፕሊን አለው፡፡ ፎቶግራፈር ስለሆንክ ብቻ ከታዋቂ ሰዎች ጋር ተለጥፈህ ፎቶግራፍ መነሳት እንኳን አይችልም፡፡ የተከለከለ ነው፡፡

በአንድ ወቅት ሞፋራህ ከእኔ ጋር የተነሳው ፎቶ ነበር፡፡ እሱ ኢትዮጵያዊ እንደሆንኩ አውቆኛል፡፡ ከሌሎቹ ፎቶግራፈሮች ለየት ያለ ክብር ይሰጠኛል፡፡ አብረን የተነሳነው ፎቶ አንድ ቦታ ላይ ተለቀቀ፡፡ ወዲያው ፎቶግራፉን አንሳ የሚል መልዕክት ደረሰኝ፡፡ እኔ ደግሞ በፍፁም እንደማላነሳው ተናገርኩ፡፡ የነገሩ መነሻ ከኃይሌ ገብረሥላሴ የበርኒገሀም የሩጫ ጊዜ ይጀምራል፡፡ ኃይሌ ሲያሸንፍ ፎቶግራፍ ማንሳቴን ትቼ እንደሕዝቡ እጨፍር እጮህ ጀመር፡፡ የካሜራ ሌንሱን ጥዬ ስጨፍር ኃይሌ ‹‹እረ ሌንሱን ጥለኸዋል›› አለኝ፡፡ እኔም የጣልኩትን ሌንስ አነሳሁ፡፡ በወቅቱ ደስታዬ ወደር ስላልነበረው ለንደን ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ያየሁትን ስለኃይሌ ነገርኳቸው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ኃይሌ ገ/ሥላሴ ፋን ክለብ በሚል ሥያሜ አቋቁመን ኢትዮጵያ ኮምኒቲ ጋር በመተባበር ለመጀመሪያ ጊዜ ለንደን ውስጥ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሄዱበት ቦታ ሁሉ መሄድ ሥራችን ኾነ፡፡ ማይክል ጃክሰንም እንዲሁ ለንደን መጥቶ ነበር፡፡  የሚሠራው ሐመር ስሚዝ የሚባል ቦታ ነበር፡፡ ኤጀንሲው የላከኝ እዚያ እንድንሠራ ነው፡፡ እኛ ልንገባ ስንል አስቆሙን፡፡ የምንገባበት በር ሌላ ነበር፡፡ ጓደኞች ትተውኝ በሌላ በር ገብተዋል፡፡ እኔ ብቻየን ቀረሁ፡፡  አድናቂዎቹ ደግሞ ማይክል ጃክሰን መስለው መምጣት ጀመሩ፡፡ እኔ በቃ መግባት ስላልቻልኩ የሚገባውን ሕዝብ ፎቶ ማንሳት ጀመርኩ፡፡ ውስጥ ሳልገባ ሕዝቡን ሳነሳ ቆይቼ ሲያልቅ ተመለስኩ፡፡ የፎቶግራፍ ጋዜጠኛ መኾን ራሱን የቻለ አድካሚ ነው፡፡ የሥነምግባር ደንቦችም አሉት፡፡ በጣም የሚያስከብር ሙያም ነው፡፡ ያለፍቃድ መሥራት ደግሞ አይቻልም፡፡

ግዮን፡- ቅርሶችን ለማሰባሰብ ያነሳሳህ ምንድነው?

አለባቸው፡- ቅርስ በዓለማችን ሦስተኛውና አራተኛው የዓለም ጦርነት የሚያስነሳ ነው፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያ ቅድመ ታሪክ ቅርስ ይባላል፡፡ ቅርሶች በሁሉም ቦታ ተፈላጊ መኾናቸውን በማመናቸው ሰብስበው እንግሊዝ ሀገር አስቀምጠውታል፡፡ እንግሊዝ ሀገር የማይሸጥ የማይለወጥ ቅርስ የለም፡፡ በአንድ አጋጣሚ ፓርቶ ቤሎ ማርኬት ሄድኩኝ፡፡ እዚህ የገበያ ማዕከል ውስጥ የተለያዩ ነገሮች ይሸጣሉ፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ጥሎ አይጥላትም፡፡ አንዳንዱን ሰብዓዊ መብት ተሟጋች ያደርጋል፡፡ ሌላውን የቅርስ ተሟጋቸች ያደርጋል፡፡ ሌላውን ደግሞ የሕፃናት ጠበቃ ያደርጋል፡፡ ፈጣሪ ኃላፊነት የሚሰጣቸው ሠዎች አሉ፡፡ እንደኔ ዐይነት በስደት የሚንከራተት ሰው ለዚያች ሀገር ከፍተኛ ዋጋ ከፍሎ ሀገሩ ውለታውን ሳትከፍል አይታ እንዳላየ ጥላው አቧራዋን ለብሶ ቆስሎ ደምቶ ያሳለፈ አንድ ወታደራዊ መኮንን በስደት ሀገር ኾኖ ለዚያች ሀገር ድጋሜ ለመቆርቆር የሚያስችል ወኔ ለማግኘት ጊዜ አላስፍለገኝም ፡እዚያ ገበያ ውስጥ አንድ የኮሪያና አንድ የኮንጎ ሜዳሊያ የኾነ ሰው ሲሸጥ አየሁ፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ያለበት የኢትዮጵያ ባለድልነት የሚሳይ ነገር ይዟል፡፡ ሄጄ የሚሸጠውን ግለሰብ ስጠይቀው ለሦስቱ ወደ ስልሳ ብር አካባቢ ጠየቀኝ፡፡ ይህ ገንዘብ በወቅቱ በጣም ውድ ነው፡፡ እኔም ገንዘብ አልነበረኝም፡፡ በሚቀጥለው ቀን 60 ብሩን ይዤ ስሄድ ሰውየው የለም፡፡ ለካስ እቃው የሚሸጠው በየሳምንቱ ሰኞ ብቻ ኖሯል፡፡ ሌላ ቀን ሰኞ ስሄድ ዋጋውን ድጋሜ ስጠይቀው ቀንሶ ሸጠልኝ፡፡ እነርሱን አስቀመጥኩ፡፡ ሜዳሊያዎቹን ማውቃቸው በምጽፈው ጽሑፍ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የጀግኖች ታሪክ በምሠራበት ወቅት እነዚያ የኮሪያ የኮንጎ ዘማቾች የዓድዋ እና የማይጨው ዘማቾች ድል አድርገው ሲመጡ ለነፃነታቸው የከፈሉትን ዋጋ ለጀግነነታቸውም ምስክር ማረጋገጫ ደረታቸው ላይ እየተንቦገቦገ የምናየውን ሜዳሊያ በእጄ መንካት ትልቅ ክብር መስሎኝ እርሱን ይዤ ወደ ኮሚኒቲው በመሄድ ለእርዳታ የሚኾን ቲያትር ጠይቀውኝ ‹‹ባሻ አሸብር በአሜሪካ›› የሚለውን የመንግሥቱ ለማን ሥሰራ በወታደራዊ ልብሱ ላይ እነዚያን ሜዳሊያዎች አድርጌ ሠራሁ፡፡ ይህን ሲያይ ሰው ሁሉ በጣም ተደነቀ፡፡ ለንደን ደግሞ የነገሥታት አንድናቂዎችና ቤተሰቦቻችው ስለሚበዛ አንዳንዶቹ እየመጡ ሜዳሊያውን ይስሙት ጀመር፡፡ እኔ ደግሞ ይህን ሳይ በጣም ተደመምኩ፡፡ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የመቶ ዓመታት ታሪክ ነው ያላት ሲል እኔ ደግሞ የለም ብዬ በልቤ ሞገትኩ፡፡ ብዙ መጻሕፍቶችንም አነበብኩ፡፡ በዚህ መሐል ከፕሮፍሰር. ራቻርድ ፓንክረስት ጋር ተገናኘን፡፡ እርሱ የመቅደላ ቅርስ  አስመላሽ ኮሚቴ ያቋቋመብት ወቅት ነበር፡፡ ስንገናኝ ቅርስ መሰብሰቤን ነግሬው ከባለቤቱ ከሪታ ፓንክረስት ጋር መኖርያ ቤቴ ወስጄ ሳሳየው እጅግ ደስ አለው፡፡ በማበርታት የጻፋቸውን መጻሕፍቶች በሙሉ ፈርሞ በታክሲ ላከልኝ፡፡ እኔም በጣም ደስ አለኝ፡፡

የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመለስ በሚደረገው ጥረት ውስጥ ከሱ ጋር ተሳትፎ አደርግ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ቅርሶች ያሉበት ቦታ ሁሉ በየቤተመጻሕፍትና መሸጫ መደብር እየዞርኩኝ መመዝገብ ጀመርኩ፡፡ የተቆርቋሪነት ስሜት እያደረብኝ መጣ፡፡ በጀርመን ድምጽ እየቀረብኩ የኢትዮጵያ ቅርሶች ተዘርፈው ሲወጡ መረጃ ሳገኝ ቃለምልልስ እሰጣለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ቅርስ ተዘርፎ ወጣ ከተባለ ጀርመንም ሬዲዮም ቪአኤ ጋዜጠኞቹ  እኔ ጋር ነው የሚደውሉት፡፡ እኔም ያገኝኋቸውን መረጃዎች እየሰጠሁ ቅርስ የሚሸጡ ግለሰቦችንም ሆነ ባለስልጣኖች ማጋለጥ ጀመርኩ፡፡ በገንዘቤ እየገዝሁ ብዙ ቅርሶችን መሰብሰብ ጀመርኩ፡፡ በብሪትሽ ላይብረሪና በሙዚየሞች ያሉትን ቅርሶች ማስመለስ እንደማልችል ገባኝ፡፡ በነጋዴዎች እጅ ያለውን ቅርስ እንዴት ማስመለስ ይቻላል የሚለውን ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ምክንያቱም ታሪክና ቅርስ የሌለው ሰው ከወደቀበት መነሳት ስለማይችል ነው፡፡ ብዙዎቻችን አሁን ድረስ የቅርስን አስፈላጊነት በትክክል የተረዳን አልመሰለኝም፡፡ ዛሬ በዓለም ላይ የሚካሔደው አብዛኛው የጦርነት ስትራቴጂ የሚቀረፀው የሐገሮችን ጥሬ ሐብትና ቅርስ ዝርፊያ ነው፡፡ ቅርስ የሌለው ሕዝብ ታሪክ አልባ ስለሚሆን የሥነ ልቦና ጦርነት ከፍተው አንገት የሚያስደፉበት ሥልት ነው፡፡

ስለዚህ ቅርስ ማለት በዘመን ርዝማኔ ብዛት የማይንሸዋረር ቅሪት ሲሆን እራስህን ውስጥ ማንነትህን ስትፈልገው ማንነትህን የሚነግርህ፣ የአባት የእናት አያት የቅድመ አያት ውርስህም ታሪክህም በመሆኑ አንተ ውስጥ የምታገኘው፤ የተሠራህበት ውሑድ፤ የተቀረጽክበት የኢትዮጵያዊነት ቀለም ነው፡፡ በወቅቱ ኢትዮጵያ ለማጥፋት ጫካ የገቡ ታጣቂዎች ሁሉም በቅድሚያ የጦርነቱ አንዱ የዘመቻው አካል ያደረጉት የኢትዮጵያን  ታሪኳንና ቅርሷቿን በመዝረፍና በማቃጣል ማውደም ነው፡፡ ይህንን በቅርቡ ወያኔ ደሴ የሚገኘውን ሙዚየም እንዴት እንዳወደሙትና ዘርፈውት እንደሔዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ስለዚህ ላለፉት 40 ዓመታት የኢትዮጵያን ቅርሷን ሲሰርቁና ሲዘርፉ ያልቻሉትንም በማውደም የዚችን ታላቅ ሐገር ክብር ማዋረድ አንዱ የጦርነቱ አካል እንደነበረ መንግሥትም ሕዝብም የታሪክ ምሥክሮች ናቸው፡፡ እኔም ላለፉት 28 ዓመታት ያለ አግባብ ተዘርፈው የወጡትን የኢትዮጵያን ቅርሶች ለማስመለስ አልፎ ተርፎም ከሽያጭ እንዲታገዱ ለማድረግ ለሐገሬ የቅርሶች ተሟጋች የሆንክበት ምስጥር ይኼው ነው፡፡

ግዮን፡- ለመሆን ይህንን ቅርስ ስትሰበስብ በእንግሊዝ መንግሥት በኩል የሚያሳስብህ ጉዳይ የለም?

አለባቸው፡- ለምን አይኖርም ይኖራል እንጂ፡፡ በእንግሊዝ ሐገር ‹‹የኢትዮጵያ ቅርስ ማበልፀጊያ ማኅበር›› በሚል ሥያሜ ሕጋዊ ማኅበር አድርጌ ከዛሬ 26 ዓመት በፊት በቻሪቲ ኮሚሽን እንዲመዘገብ አደረኩት፡፡ ላለፉት 28 ዓመታት ለመላው የሐገሬ ሕዝብ ስጮህና ድምፄን ሳሰማ ቆይቻለሁ፡፡ አሁንም ያለአግባብ ተዘርፈው ለባዕዳን የሚሸጡትን ቅርሶቻችን ቢቻል ለማስመለስ ካልተቻለም በግል ገንዘቤ እየገዛሁ ሰብስቢያቸዋለሁ፡፡

ግዮን፡- ለነዚህ ቅርሶች መባከን መሠረታዊ ችግሩ ምን ይመስልሀል?

አለባቸው፡- እጅግ ብዙ ናቸው፡፡ ከሁሉም የጎዳን ግን ምናልባትም ከውጭ ወራሪዎች ይበልጥ የጎዱን በሐገሪቱ ላይ በየወቅቱ ሥልጣን የሚቀማሙት ባለሥልጣኖችና ዘረኛና ፅንፈኛ የብሔር ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ እነሱ ከሚያራምዱት ያልሰለጠነ ፖለቲካ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ታሪክና ቅርስ በተገቢ ቦታ ተቀምጦ ለሳይንሳዊ ምርምርና ጥናት እንዳይዘጋጅ፣ ቅርሶቹን ሥም እየሰጡ የተለያየ ትርክት በማስወራት የገዝ ታሪኩ ጠላት አድርገውት እንዲጠብቃቸውና እንዲንከባከባቸው ሳይሆን እንዲያወድማቸው ነው የሚዘጋጁት፡፡ ይህ ደግሞ ታሪክ ይቅር የማይለው ትልቅ የሐገር ክሕደት ነው፡፡ አብዛኛወቹም ፖለቲከኞች በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ከጥላቻ የዘለለ እውቀት የላቸውም፡፡ አንዳንዶቹም ታሪክን ጠንቅቀው ከማወቅ ይልቅ የብሽሽቅ ፖለቲካ ያራምዳሉ፡፡ ቅርሶች ደግሞ የማንነት መገለጫዎችና የታሪክ የመረጃ ምንጮች በመሆናቸው ለአንድ ሀገር ወይም ሕዝብ እጅግ በርካታ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችን እንደሚያስገኙ የገባቸው አይመስለኝም፡፡

ግዮን፡- ስለዚህ መፍትሔው ምንድ ነው ትላለህ?

አለባቸው፡- መንግሥት ከፖለቲካ አመለካከት ነጻ የሆኑ ሰዎችን መርጦ ተገቢውን ሙያተኛ በተገቢው ቦታ መመደብ አለበት፡፡ ቅርሶች ተሰብስበው በአግባቡ እንዲቀመጡ በርካታ ሙዚየሞችና የቅርስ ማበልፀጊያ ማኅበራትን በየክፍለ ከተማው ማቋቋምና ለሕብረተሰቡ የቅርስ አስፈላጊነት ትምህርት እንዲሰጥ መፍቀድ ይኖርበታል፡፡ ስለ ቅርስና ታሪክ በትምህርት ፖሊሲው ውስጥ መቀረፅ አለባቸው፡፡ ቅርሶች ለቀጣዩ ትውልድ የአእምሮ ብርሃን፣ የዕውቀት መሠረት በመኾናችው ትውልዱ የበለጠ ታሪክ እንዲሰራ ለማድረግ፣ ከሌሎች ሐገሮች ጋር የባህል ልውውጥ ለማድረግ  ቱሪዝምን ለማስፋፋት፣  ዋና ዋና ምክኒያቶች በመሆናቸው ሐገርንና ታሪኩን የሚወድና የሚያከብር ትክክለኛ ሰው በባሕል ሚኒስትር መመደብ አለበት፡፡

ግዮን፡- አሁንም ስለቅርስ መንግሥት ትኩረት አይሰጥም ነው የምትለው?

አለባቸው፡- እውነቱን ንገረኝ ካልክ ለሚዲያ ፍጆታ ካልሆነ በቀር ብዙም እንቅስቃሴ በቅርስና በታሪክ ሲሰራ አላየሁም፡፡ ምናልባት ከለውጡ በኋላ አገራዊ ኩራትን ለመፍጠር/ማንነትን ለማወቅ/፡- ቅርሶች የአንድ ሕዝብ የዘመናት የኑሮ እንቅስቃሴ፣ የሥራና የፈጠራ ክንውን መዘክር መሆን አለባቸው ብለው ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ ቤተመንግሥቱን በማደስ በግላቸው ጥረት አድርገዋል፡፡ ነገር ግን ሕብረተሰቡን ያላሳተፈ በመሆኑ ውጤቱ ከዚህ በዘለለ የትም ሊደርስ አይችልም፡፡

ግዮን፡- አቶ አለባቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጥረት አድንቀህ፣ ነገር ግን ሕብረተሰብን ያላሳተፈ ነው ስትል ምን ማለት ፈልገህ ነው?

አለባቸው፡- አየህ የቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥራ አይደለም፡፡ እሳቸው ያሳዩት እንደዚህ አድርጎ መሥራት ማስዋብ ይቻላል ብለው ነው፡፡ ነገር ግን የሳቸውን ፈለግ ተከትለው የሠሩ ባለሥልጣኖችን ወይንም የክልል መሪዎችን እስኪ ጥራልኝ፡፡ እሳቸው የሰሩትን ለመመረቅ ተሰብስበው ከማጨብጨብ ውጭ የጎንደርን ቤተ መንግሥት አሳድሳለሁ ብሎ የተነሳ፣ የወደቀውን የራስ መኮንን ሐውልት አቆመዋለሁ፤ ጉዳት የደረሰበትን የአክሱምን ሐውልት ክትትልና ጥገና አደርጋለሁ የሚል ባለሥልጣን ሰምተህ ታውቃለህ?  አንተኑ መልሼ ነው የምጠይቅህ? ቅርሶች የአንድ አገር ሕዝቦች ከሌላው ሕብረተሰብ የሚለዩበትን ነገር የሚያሳዩ የማንነት መገለጫዎች መኾናቸውን መዘንጋት የለብህም፡፡ የሰው ልጅ የተጓዘባቸውን የለውጥና የዕድገት ሂደት እንዲሁም ተፈጥሯዊና አካባቢያዊ ሁኔታ በማስረዳት አሁን ያለው ትውልድ ማንነቱን እንዲያውቅና በማንነቱ እንዲኮራ የትውልድ ቀረፅ ላይ ትልቅ ድርሻ ያላቸውን ዘመን ተሻጋሪ ቅርሶችን መጠበቅና መንከባከብ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡

ግዮን፡- ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምን ትጠብቃለህ?

አለባቸው፡- ኧረ እባክህ አታስቀኝ፡፡ አልሞትኩም ብዬ አልዋሽም ያሉት ማን ነበሩ፡፡ ለመሆኑ አለ እንዴ? ቢኖርስ በነፃነት ለመሥራት የሚችል ተቋም ነው ብየ እኔ አላምንም? ቅርስና ታሪክ ላይ ለመሥራት ሙሉ የሙያ ነፃነት ይጠይቃል፡፡ በዘር፣ ፖለቲካና በጥላቻ እርስ በእርስ በሚወንጃጀል ሕብረተሰብ እንዴት አድርገህ ትሰራለህ፡፡ ኢትዮጵያውያኖች ስለአገራቸው፣ ስለታሪካቸው፣ ስለባሕላቸው የበለጠ እንዲያውቁ፣ እንዲማሩ፣ ብሔራዊ ስሜታቸው፣ የአገር ፍቅራቸው እንዲጠነክርና ለአገራዊ ችግሮች በአንድነት እንዲቆሙ፣ የአብሮነት ስሜታቸው እንዲጎለብት የሚያነሳሱ በቅርስ ላይ፣ ሲምፖዚየሞች፣ ሴሚናሮች ልዩ ልዩ ኤግዚቪሽኖች መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ በተጨማሪም መንግሥትና የቅርስ ተቆርቋሪዎች በትብብር ቢሰሩ  አገራችን ትልቅ የቱሪስት ተጠቃሚና የአፍሪካ የቅርስ ግምጃ ቤት በሆነች ነበር፡፡ እኛ ግን የምንሰራው በተገላቢጦሽ ነው፡፡ በጎሳ ፖለቲካ ውስጥ ገብተን ትውልዱን በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲዳክር የዘመናት ግርዶሽ ጭነንበታል፡፡ ቅርሶቻችንን በአግባቡ ብንጠቀምባቸው ኑሮ ለትውልዱ የወደፊቱን ወርቃማ ዘመን አሻግሮ የሚመለከትባቸው አጉሊ መነፀሮቹ እናደርጋቸው ነበር፡፡ ካወቅንበት ቅርሶቻችን ችግሮቻችንን ለመፍታት የማኅበረሰብ ትስስርን፣ የመቻቻል ባሕልን የሚያሳድጉ ጠንካራ የአገር ሀብቶች በመሆናቸው ከተኛንበት እንድንነቃ የሚደርጉን ብሔራዊ ደወሎቻችን ናቸው፡፡

ግዮን፡- ቅርሶቻችን ጥበቃና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልጋቸው ደጋግመህ ገልፀህልናል፡፡ ምን ዐይነት ጥንቃቄ ነው መደረግ የሚገባው?

አለባቸው፡- ብዙ ዐይነት ሙያዊ ጥንቃቄ ያሰፈልጋቸዋል፡፡ ታሪካዊ ቅርሶች እድሜ ጠገብ በመሆናቸው ልዩ ጥበቃና ጥንቃቄ ማግኘት ይገባቸዋል፡፡ እንዳልባሌ ዕቃ የትም የምትጥላቸው ግድየለሽ ከሆንክ በቅርስ ዘራፊዎች እየተመነተፉ ባሕር አቋርጠው በውጪ ዓለም ለመቸብቸብ ይጋለጣሉ፡፡ እኔ የምኖርበትን እንግሊዝ ሐገር እንኳን ብንወስድ በየሙዚየሙ የምታያችው ቅርሶች በሙሉ ከቅኝ ግዛቶቻቸው ከነበሩት ከአፍሪካ የተዘረፉ ናቸው፡፡

ግዮን፡- ምን ያህል ቅርሶችን ሰብሰበክ? በገንዘብ ደረጃስ ለዚህ ዓላማ ምን ያህል አወጣህ?

አለባቸው፡- መጀመሪያ አካባቢ ቅርሶችን ሰብስቤ የምይዘው ዝም ብዬ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ነበር፡፡ በኋላ ግን ቅርስ የሚባሉት የትኞቹ እንደኾኑ መመራመርና ማንበብ ጀመርኩ፡፡ ቅርሶቹን ራሳቸው ማንነታቸውን ይናገራሉ፡፡ እኔ ደግሞ የቅርሶች ታሪክና ማንነት የማወቅ ግዴታ ንበረብኝ፡፡ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ የማይችሉ አሉ፡፡ አሠራራቸውም ልዩ ልዩ ነው፡፡ ከአልማዝ፣ ከወርቅ፣ ከብር፣ ከነሐስ፣ ከድንጋይ፣ ከእንጨት የሚሠሩ ማዕድናት አሉ፡፡ የእነዚህ ታሪክና ባሕል ለትውልድ ለማተላለፍ መመርመር ግዴታዬ ነበር፡፡ ስለዚህ ቅርሶቹ ለመታቢያነት ብቻ የሚያገልሉ አይደሉም፡፡ በታሪክ ሂደት ውስጥም ብዙ ታሪክ ፈጽመው ያለፉ ናቸው፡፡ ቅርሶቹን ለመፈለግ የተከፈለው መሥዋዕትነት፣ ቅርሶቹ የተሸከሙት ታሪክና መሰል ነገሮች የሚያስገኙት ጥቅም ከፍተኛ በመሆኑ የጠየቁኝን ሁሉ ዋጋ ከፍያለሁ፡፡

ፈረንጆች ቅርስን በአግባቡ በጥንቃቄ ነው የሚይዙት፡፡ እዚህ እንግሊዝ ሀገር ውስጥ ‹‹ኢምፔሪያል ዋር ሙዚየም›› የሚባል ተቋም አለ፡፡ በዚህ ተቋም ውስጥ ያየሁትን ታሪክ በአጭሩ አድርጌ ልንገርህ፡-

እንግሊዞች ጥቁሮችን እያሠሩ ወደ ባርነት የሚያመጡባቸው ሰንሰለቶች ተደርድረው ተሰቅለዋል፡፡ ካቴናዎች በጥንቅቄ የተሰቀሉ ናቸው፡፡ አንድ ቦታ ላይ ግን እጅግ የሚያስገርም ነገር አለ፡፡ አንድ የሰንሰለቶች ሁሉ ፊትአውራሪ የኾነ ሰንሰለት ጉብ ብሏል፡፡ ሰንሰለቱ ትልቅ ታሪክ የታቀፈ ሰንሰለት ነው፡፡ ዐፄ ቴዎድሮስ የአውሮፖን ዲፕሎማትና ሰባኪ ያሰሩበት ሰንሰለት ነው ፤ ያ ሰንሰለት፡፡ ዛሬ እንግሊዞሽ እየመረራቸውም ቢሆን ለታሪክ አስቀምጠው ያስጎበኙታል፡፡ አየህ ወዳጄ ይህንን ሰንሰለት ታሪኩን ካነበብኩ በኋላ ‹‹በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ›› ብዬ ነበር ያማተብኩት፡፡

ተመልከት ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል፡፡ በትውልድ መካከል አልፈው የመጡ ቅርሶች የአንድ ሀገር መሠረቶች ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ መጋደልና የእርስ በእርስ መበጣበጥ የመጣው ታሪካችንን ጠንቅቀን ባለማወቃችን ነው፡፡ የጋራ ሀገራዊ ቅርስ ያለን ባለታሪክ ሕዝቦች ነን፡፡ ሀገር ስንከፋፍል ታሪካችንን መከፋፈል አልቻልንም፡፡ ኤርትራ ለብቻዋ ስትሄድ ታሪኳን አልተካፈለችም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የሁሉም ብሔረሰቦች ታሪክ ነው፡፡ ማንም ተነስቶ የጥላቻ ፖለቲካ ሲያሞቀውና ሲያሰክረው የኔ ብቻ ነው እያለ ዘራፍ የሚልበት አይደለም፡፡ ሥራ መሥራታችንን ትተን በአፈታሪክ እየተጨቃጨቅን ተገዳድለን የምንበቃቀለውም ለዚህ ነው፡፡ የተዛባው ትርክት የብሔራዊ አንድነት ታሪክ ድሃ እንድንኾን አድርጎናል፡፡ የተዛባ ትርክት ብሔራዊ ኩራታችንን አጥፍቶታል፡፡ ይህን ችግር ለመቅረፍ ቅርሶቻችንን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እኔ በግሌ በርካታ ሰዎችን አናግሬያለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ቅርስ ላይ ትልልቅ እውቀት ያላቸውን ምሁራኖችም ሆነ የቀድሞ መንግሥት ፕሬዝዳንት መንግሥቱ ኃ/ማርያም ቅርሶቻችን ለምን እንዳልተጠበቁ ረጅም ሰዓት የወሰደ ቃለ ምልልስ አድርጌያለሁ፡፡ ቅርሶቹን ከሰበሰብኩ በኋላም ብዙ ለማወቅ ከፍተኛ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ የኛ ትውልድ የአሁኑን ትውልድ የዘር ኮሮጆ ውስጥ የገባ በመሆኑ ትውልዱ ቀጣይ ዘመኑን አሻግሮ የሚያይበት መሠረት ለማስቀመጥ ጠንክሮ መሥራት እንደሚኖርብኝም አምናለሁ፡፡ ያለፈው አልፏል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ግን ሁላችንም በዘመቻ የኢትዮጵያን ቅርሶች መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ የቅርስና ታሪክ ወራሪ የተፈፀመብን እንጠፋ ዘንድ አዋጅ የታወጀብን ሕዝቦች በመኾናችን ሳናጎበድድ የኢትዮጵያን ታሪክ መጠበቅ ይኖርብናል፡፡

እኔ በበኩሌ ታሪክ ነፃ ያወጣኛል፡፡ ላለፉት 28 ዓመታት ይህንን ቅርስ ስሰበስብ ቆይቻለሁ፡፡ ከዛሬ አራት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ብዙ ሙከራ አድርጌያለሁ፡፡ የዲያስፖራ ሙዚየም ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲቋቋም ለማድረግ ፕሮፖዛል አውጥቼ በወቅቱ ለባሕልና ቱሪዝም ሚኒስተር ለዶ/ር ሂሩት አቅርቤያለሁ፡፡ ይህን ካደረኩ አምስት ዓመት እየሞላው ነው፡፡ ለውጡ ከመጣ ጀምሮ ቅርሱን ለማስገባት እየጣርኩ ነው፡፡  ጉዳዩም እስከ ከፍተኛው የመንግስት ባለ ስልጣኖች ድረስ  ደርሷል፡፡ ነገር ግን ማንኛውም አካል ትኩረት ወስዶ ቀና የትብብር መልስ አልሰጡኝም፡፡ በመላው ዓለም ያለ ዲያስፖራ በየሀገሩ ተበትነው የሚገኙ የኢትዮጵያ ቅርሶች እንዲሰበስብ ለማድረግ የዲያፖራ ሙዚየም በማቋቋም አሻራውን እንዲያስቀምጥ በማሰብ ነበር ‹‹ዲያስፖራው ሙዚየም ይቋቋም›› እያልኩ ያሳስብኩት፡፡ በተለያየ ምክንያት በዘረፋ የወጡ ታሪካዊ ቅርሶችን በገንዘብና በስጦታ የምናገኛቸው በመኾናቸው ተመልሰው ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ ዲያፖራውን አስተባብሬ ነበር፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በኩል ሐሳቤ ተቀባይነት ባለማግኘቱ እስካሁን ድረስ እቅዱ ተፈፃሚ አልኾነም፡፡

ግዮን፡- መንግሥት ለምንድነው መልስ መስጠት የከበደው?

አለባቸው፡- የሙዚየም መሥሪያ ቦታ ጠይቀን አልተሳካም፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ዶ/ር ሂሩት የሰጠችን ምርጫ ሀገሪቱ ላይ የሚገኙ የቅርስ ቤቶችን አድሳችሁ ተጠቀሙ የሚል ነበር፡፡ እኛም ቤቶቹን ለማደስ ዝግጁ መኾናችንን አሳወቅን፡፡ ግን ማን ይወስንና ይስጠን? የመወሰን አቅም ያላቸውን ባለስልጣኖችን ለማግኘት ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ ግን በየት በኩል አልፈህ ታገኛቸዋለህ፡፡ በተለያዩ ለሀገራዊ ጉዳዮች ወደ ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ መጥቼ ነበር፡፡ ሙከራዎቼ በሙሉ አልሰሩም፡፡ ብዙ ቃለ ምልልሶች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በኩል ተላልፈዋል፡፡ ያንን አዳምጦ ሊረዳኝ የሞከረ ግን አላገኘሁም፡፡ ከእንግዲህ እኔ የምኖረው የአንድ ሰው እድሜ ነው፡፡ ይህን ሁሉ ዓመት ደክሜ የሰበሰብኳቸው ቅርሶች ወደሀገራቸው ሳይገቡ ቢቀሩ ምን ያህል ከባድ ሕመም ሊኾን እንደሚችል ማሰብ አያዳግትም፡፡ በተለይ አዲሱ ትውልድ ስላለፈው ትውልድ እንዲያውቅ ግልፅ በኾነበት መንገድ ማስረዳትና እንዲማርበት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቅርስን በመጠበቅ የሀገር ተቆርቋሪ ወጣቶችን ማፍራት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ እድል አሁን ላይ እየሰጠመ ነው፡፡

ግዮን፡- በለንደን ያሉ ኢትዮጵያውያን እነዚህን ቅርሶች ይጎበኟቸዋል?

አለባቸው፡- አዎ ይጎበኛሉ፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማስተዋወቅ በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የእንግሊዝ ኮሌጆች እየዞርኩ ኢትዮጵያን እንደ ታሪክ አምባሳደር ሁኜ አስተዋውቅ ነበር፡፡ እነጀኔራል ታመነ ደልነሳው፣ እነ ሊቀ መምህራን አበበ ይግዛው፣ እነ አቶ ሀብተ ገብርኤል ከተማ የሚባሉ ትልልቅ ሰዎች ይዤ ከለንደ ውጭ ድረስ  እየዞርን አስጎበኝተናል፡፡

ግዮን፡- አሁን መንግሥት እንዲተባበርህ የምትፈልገው ምንድ ነው?

አለባቸው፡- ቅርስ ቤቶች እንዲሰጠን የጠየቅነው ከአራት ዓመት በፊት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በሙሉ ማለት ትችላለህ ቅርሱ ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ብዙ ፕሮግራሞችን እየሰሩ መንግሥትና ሕዝብ እንዲያውቀው ብዙ  ጥረዋል፡፡ በተለይ ሸገር ሬዲዮ እነ ቴዲ ብዙ ጮኸዋል፤ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ እነ ማህሌት፣ የጀርመን ድምፅ ሬድዮ ባህል አዝግጇ አዜብ ታደሰ በጣም ጥረዋል፡፡ በቅርስ ጉዳይ ላይ በርካታ ፕሮግራሞች ሠርተዋል፡፡ የአሜሪካን ድምፅ ጋዜጠኞች እነ አሉላ ከበደ፣ ሰለሞን ክፍሌ፣ በጣም ብዙ ሙከራ አድርገዋል፡፡ ከፍ ሲል እንደጠቀስኩት ቅርሶች እንዴት ከሀገር እንደሚወጡና ማን እንዳስወጣቸውም መረጃው ሲደርሰኝ ለጋዜጠኞች እነግራቸዋለሁ አብረን እንጮሀለን፡፡ ይህን በተመለከተ በተለይም መንግሥቱ ኃ/ማርያም የኢትዮጵያን ቅርሶች መሸጥና መዝረፍ የጀመሩት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ወያኔዎች ናቸው፡፡ ለትጥቅ ትግል እያሉ በሱዳን በኩል እያወጡ እንዴት እንደሸጧቸው በደንብ ያስረዳኝና በበቂ ማስረጃ የነገሩኝ የኮ/ል መንግሥቱ ኃይለማርያም ናቸው፡፡ በኦነግ በኩልም እንዲሁ በኬኒያ የኢትዮጵያ ቅርሶች እየወጡ ተሸጠዋል፡፡ ይህ የተመቻቸላችው ነጋዴዎችም ባለስልጣኖችም አብረው ዘርፈው ወደ አውሮፓ እየወሰዱ ይሸጣል፡፡ በጅብቲ በኩል የሚውጡት ቅርሶቻችን ፈረንሳይ የቅርስ ደላላዎች እጅ ገብተው ተሽጠዋል፡፡ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ቅርሶች ከሀገር የሚወጡት በጅቡቲ፣ በኬኒያና በሱዳን ነው፡፡ ቅርስን ከሐገር አገር እያዘዋወሩ የሚሸጡ የቅርስ ጃርቶች ለዓለማችን ችግር ሆነዋል፡፡

ግዮን፡- እነዚህ የቅርስ ጃርቶች ብለህ የምትጠራቸውን ሌቦች እንዴት መቀነስ ይቻላል?

አለባቸው፡- እኔ እንደሚመስለኝ ቅርሶች በሚቀመጥባቸው ገዳማትና ደብሮች ሙዚየሞች ገዳማትና ደብሮች በመሳሰሉት ቦታዎች ሕጋዊ የቅርስ ምዝገባ ማድረግና ቁጥጥሩን ጠበቅ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ስለ ቅርስ ያለንን ግንዛቤ ለሕብረተሰቡ ማስጨበጥና ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ያላስተማርነውን ሰው ቅርስ ሲሸጥ ቢገኝ ብታስረው ብትቀጣው ምን ትርጉም ይኖረዋል? ነገር ግን ስለ ቅርስ ጠቀሜታውን ቢያውቅና ቢረዳ ኑሮ የቅርስ ተቆርቋሪና ጠባቂ የሚሆነው እራሱ ሕብረተሰቡ ነበር፡፡ የራስ መኮንንን ሐውልት አፍርሶ የጀነራል ሰዓረን ሐውልት ማቆሙ ምን ትርጉም አለው፡፡ ይህንን የምነግርህ ለምን ሐውልት ቆመላቸው ብየ መከራከሬ አይደለም፡፡ ለሐገራቸው የተዋደቁ ብዙ ጄኔራል መኮንኖች አሉ፡፡ ለነሱም ሁሉ ቢሰራላቸው ደስታውን አልችለውም፡፡

ቅርስ ትርጉም የሚኖረው የተወከለለትን ቁስ ወይም ሐውልት በሚይዘው ምሥጢር ልክ ነው፡፡ ሐውልቱ የቆመበት ዓላማ ነው ትርጉሙ፡፡ ቅርሶቻችንን እያጠፋን ትውልዱን እርስ በእርስ እያጫረስን ነው እየኖርን ያለነው፡፡ ቅርስ የምናጠፋበት ዋናው ምክንያት ትውልዱን ለማደናገር ነው፡፡ ቅርስ ከጠፋ ትውልዱ ኢትዮጵያዊ የሚሰኝ ማንነታዊ ምርኩዝ ተደግፎ መቆም እንዳይችል እያደርግነው ነው፡፡ ስለዚህ የቅርስ መጥፋትና መበተን ሊቆጨን ይገባል፡፡ የጋራ ታሪካችንን እያጠፋንና እያበላሸን መቀጠል የለብንም፡፡ አሁን እየታደሱ የሚገኙም እድሜ ጠገብ ቅርሶች በአግባቡ በትክክለኛ ባለሙያ ተጠንተው መጠገን አለባቸው፡፡

(ከአቶ አለባቸው ጋር የነበረን ቃለምልልስ በቀጣይ ዕትም ይቀጥላል…)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...