የቅራኔዎች ጥናት – ለወጣቶች

Date:

ክፍል አንድ ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶክተር )

መግቢያ

ግዮን መጽሔት :- በእውቅም ይሁን በአጋጣሚ የአንድ ወገን ፍላጎት ከሌላኛው ወገን ፍላጎት ጋር ሳይጣጣም ሲቀር ቅራኔ ተፈጠረ ይባላል። የፍላጎቶች አለመጣጣም በግቦች አለመስማማት፤ በግቦች መስማማት ቢኖር እንኳን ግቦቹን በማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎችና ስልቶች አለመስማማት ሊያስከትሉና የተፈጠረውን ቅራኔ ሊያባብሱ ይችላሉ።

ቅራኔ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥም ክስተት ነው። የፍላጎቶች አለመጣጣም ቁሳዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ብቻ ሳይሆን ቁሳዊ ካልሆኑ ጉዳዮች ጋር ተያይዞም ሊነሳ ይችላል፤ ለምሳሌ “የሚገባኝን ክብር ተነፈገኝ” በሚል ቅሬታ (ቅራኔ) ሊነሳ ይችላል።

ንብረትን ከመሰለ ቁሳዊ ነገሮች በተጨማሪ ከሰብዓዊ ክብር፣ ከሀይማኖት፣ ከጎሳ፣ ከነገድ፣ ከብሔር፣ ከአገር ወይም ከርዮተ ዓለም ልዩነቶች ጋር ተያይዘው የሚነሱ አለመጣጣሞች ለቅራኔዎች ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ።

አንዳንድ የፍላጎት አለመጣጣሞች በቀላሉ የሚፈቱ ናቸው፤ ጥቂቶቹ ግን ወደ አለመግባባት፣ ከፍ ሲልም ወደ ግጭቶች ሊያድጉ እና ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።

እያንዳንዱ ቅራኔ ቢያንስ ሶስት ነገሮች ይይዛል – አለመጣጣም (incompatibility)፣ ተዋናዮች (actors) እና ተግባራት (actions)።  “አለመጣጣሞች” የተለያዩ ፍላጎቶችን በአንድ ጊዜ ለማሟሟት ባለመቻሉ ምክንያት የሚፈጠሩ እክሎች ናቸው።

አንዳንዶች አለመጣጣሞች የሚፈጠሩት በግብዓቶች (resources) ውስንነት ምክንያት ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የተዋናዮቹ ፍላጎቶች አብረው መሄድ የማይችሉ በመሆናቸው ነው። በእሴቶች (መርሆዎች፣ እምነት፣ ሀይማኖት፣ ርዕዮት፣ ባህል፣ ወግ)፣ በግዛት (ድንበር፣ ክልል) እና በአስተዳደር ጉዳዮች የሚነሱ አለመጣጣሞችን አቻችሎ ማስኬድ ይከብዳል፤ በዚህም ምክንያት ከእነዚህ ሰበብ የሚቀሰቀሱ ቅራኔዎች ወደ ከረረ ግጭት የማደጋቸው ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።

“ተዋኒያን” የሚባሉት በግጭቱ ውስጥ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች፣ ድርጅቶች፣ ቡድኖች፣ ማኅበረሰቦች፣ አገሮች … ወዘተ ናቸው። አንዳንድ ተዋንያን የቅራኔው (ወደ ግጭትም ካደገ የግጭቱ) ቀጥታ ተሳታፊዎች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግም ቀጥታ ያልሆነ ተሳትፎ ሊኖራቸው ይችላል።

ተዋናዮች የተለያዩ ናቸው፤ ከቅራኔው ሊያሳኩት በሚፈልጉት ግብ፣ ለቅራኔው በሚሰጡት ዋጋ (importance) እና የቅራኔውን ሂደት ለመወሰን ባላቸው አቅም (power) ይለያያሉ።

በዚህም ምክንያት የቅራኔ ወይም የግጭት የዋናዎችን ለያይቶ ማጥናት ስለቅራኔው ያለንን ግንዛቤ ከፍ ያደርግልናል፤ የመፍትሔ ሀሳቦችን ለማቅረብም ይረዳናል። 

“ተግባራት” ማለት ተዋንያን የተፈጠረውን አለመጣጣም በተመለከተ የሚያደርጓቸው ወይም ማድረግ ሲችሉ ያላደረጓቸው እንቅስቃሴዎችንና ውሳኔዎችን ይመለከታል። ቅራኔዎችን የሚያባብሱት (escalation)፣ የሚያረግቡት (de-escalation) ወይም ባለበት እንዲቆም (stagnation) የሚያደረጉት የተዋንያን ተግባራት ናቸው።

እርግጥ ነው ቅራኔዎች ሁሉ ጎጂዎች አይደሉም፤ ከቅራኔዎች የሚገኙ ጥቅሞች አሉ። የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ግን ጎጂ ስለሆኑ ቅራኔዎች ነው። በብልሃት ከተያዙ የጎጂ ቅራኔዎች የጉዳት መቀነስ ይቻላል፤ ከዚያም አልፎ አንዳንድ ጎጂ ቅራኔዎችን ገንቢ ወደሆኑ ቅራኔዎች መቀየር ይቻላል።

ይህንን ለማድረግ ግን የቅራኔዎቹን መነሻ ምክንያቶችን፣ የተዋናዮቹ ማንነትና ፍላጎቶቻቸውን  እና ተዋናዎች የፈፀሟቸውን ተግባራት ማጤን ያሻል።  ይህ በአግባቡ ከተፈፀሙ አለመጣጣሞች ሲፈጠሩ ወደ ከፋ ቅራኔ ሳያድጉ መፍትሄ ሊያገኙ ይችላሉ።

ተዳፍነው የቆዩ ቅራኔዎች እንዳይቀሰቀሱ፤ ከተቀሰቀሱም እንዳይባባሱ፤ ከተባባሱም ወደ ግጭት እንዳያመሩ በየደረጃው ሊወሰዱ የሚችሉ የመከላከያ መንገዶች አሉ። ይህ ሁሉ ሳይደረግ ወይም ተደርጎ ሳይሳካ ቆርቶ ግጭት ከተፈጠረና ጉዳት ከደረሰም በኋላም ግጭቱ ተራዝሞ የጉዳቱ መጠን ይበልጥ የከፋ እንዳይሆን እርቅ እንዲወርድ መደረግ የሚገባቸው ተግባራት አሉ።

ቅራኔ የሕይወታችን አንድ አካል ነው። አብዛኛውን ጊዜ ቅራኔ ውስጥ የምንገባው በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ቅርባችን ከነበረ ግለሰብ፣ ቡድን ወይም ማኅበረሰብ ጋር ነው። የሰውም ልጅ እጅግ ቅርቡ ከሆነ ከገዛ ራሱ ሕሊና ጋር ሳይቀር ቅራኔ ውስጥ ሊገባ ይችላል።

ቅራኔዎች ስሜት ቀስቃሽ ናቸው፤ ያናድዳሉ፣ ያበሳጫሉ፣ ያሳዝናሉ። በእንደዚህ ዓይነት ስሜት ውስጥ ሆነም የምንወስዳቸው ርምጃዎች ቅራኔዎቹን ይበልጥ የሚያባብሱ ሊሆኑ ስለሚችሉ በተለይ ወጣቶች በእንደዚህ ዓይነት ተግባራት እንዲታቀቡ ለማገዝ ነው ይህ ጽሁፍ የተዘጋጀው።

በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቶችን ችግር ፈጣሪዎች፣ ግጭት ጠማቂዎች ወይም ጠብ ፈላጊዎች አድርጎ የሚያየው አስተሳሰብ መቀየር ይገባል። የሀገራችን ወጣቶች ሰላም አውራጆችና አስታራቂዎች መሆን ይችላሉ።

የዘመናችን ወጣቶች ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ቁርሾ በእነሱ ዘመን እንዲያበቃ፤ በእነሱ ዘመን የተቀሰቀሱ ቅራኔዎች ደግሞ ወደሚቀጥለው ትውልድ እንዳይተላለፉ ማድረግ ይችላሉ።

ይህንን ለማድረግ ግን ወጣቶቻችን ስለቅራኔዎች እናግጭቶች ያላቸውን ግንዛቤ ማስፋት ይኖርባቸዋል። ወጣቶች በቅራኔዎች ውስጥ ራሳቸውን አስገብተው ተግባራዊ እርምጃዎችን ከመውሰዳቸው በፊት ስለቅራኔዎቹ ያላቸውን እውቀት ለማዳበር የሚረዷቸውና በቀላሉ ሊለምዷቸው የሚችሉ የቅራኔ መተንተኛ መሣሪያዎች (Conflict Analyses Tools) አሉ።

የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ቀለል ያሉ የቅራኔ መተንተኛ መሣሪያዎችን ለወጣቶች ማስተዋወቅ ነው፤ በዚህ ጽሁፍ ክፍል አንድ የቅራኔ ደረጃዎችን (Conflicts Stages) እንመለከታለን፤ በቀጣይ ክፍሎች ደግሞ የቅራኔዎች ካርታ (Conflict Mapping)፣ የቅራኔ ዛፍ (Conflict Tree)፣ የቅራኔ ሥርዓት ትንተና (Systems Conflict Analysis.) ይቀርባሉ። 

የቅራኔ መተንተኛዎቹን ለመግለጽ ኢትዮጵያን በምሳሌነት እንጠቀማለን። ኢትዮጵያን የተጠቀምነው ለምሳሌ ያህል ብቻ ነው። አንባቢ መሣሪዎቹን ተጠቅሞ ማንኛውንም (ትልቅም ይሁን ትንሽ) ቅራኔ መተንተን፤ የኢትዮጵያንም ሁኔታ ከተለየ አቅጣጫ መመልከት ይችላል (ትችላለች)።

የዚህ ፁሑፍ ቀጣይ “የቅራኔ ደረጃዎች” በሚል ርዕሰ ይዘን እንቀርባለን ።

ታደሰ ብሩ ኬርስሞ (ዶ/ር) በ ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቨሎፕመንት ፋውንዴሽን የሰላምና የግጭት ጥናቶች ባለሙያ ናቸው። በዚህ ጽሁፍ ላይ ያላችሁን አስተያየት ycdfoundationethiopia@gmail.com  ወይም tkersmo@yahoo.com መላክ ትችላላችሁ።

የዚህ ፁሑፍ እስፖንሰር :- ዩዝ ኤንድ ካልቸራል ዴቬሎፕመንት ፋውንዴሽን ሀገር በቀል የሲቨል ማህበረሰብ ድርጅት ሲሆን ከተመዘገበ 2006 ዓ.ም ጀምሮ በ አቅም ማጎልበት፤ ትምህርት፤ ጤና፤ አካባቢ እንክብካቤ፤ ማህበራዊ ሃላፊነት መወጣት፤ ድህነት ቅነሳና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት፤ እንዲሁም በሰላም እና ደህንነት፤ ዘርፎች ላይ በማተኮር አሳታፊ የሆኑና የተቀናጁ ፕሮጄክቶችን በመተግበር ላይ ይገኛል።

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 230 መጋቢት 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በ2026 የዓለም ዋንጫ ላይ ለተለያዩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚጫወቱ ወንድማማቾች

የ2026 የፊፋ የዓለም ዋንጫ ከመላው ዓለም የተውጣጡ ምርጥ ተጫዋቾችን...

ኢንፊኒቲ ለቤትና ለመኪና መግዣ ብድር እየሰጠ እንደሚገኝ አስታወቀ

ኢንፊኒቲ ኃላፊነቱ የተወሠነ መሠረታዊ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ...

የአዲሱ የወንጀል ህግ ስነ-ስርዓት የእርማት ስራዎች ሳይጠናቀቁ በሥራ ላይ እየዋለ ነው

የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላለፉት 64 ዓመታት...

ናይጄሪያው ዩናይትድ ካፒታል በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የውጭ ኢንቨስትመንት ባንክ ፈቃድ አገኘ

​የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን በሀገሪቱ የካፒታል ገበያ ታሪክ ለመጀመሪያ...