የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የሁለተኛ ቀን ውሎ በተለያዩ አጀንዳዎች ውሳኔ አሳለፈ

Date:


የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ በሁለተኛ ቀን ውሎው በአጃንዳ ቁጥር ፭ እና ፮ ላይ በሁለት አጀንዳዎች ውይይት በማድረግ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ አጀንዳ ቁጥር ፭ የነበረው ውይይት ከተለያዩ የቤተክርስቲያኒቷ አህጉረ ስብከቶች ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እንዲመደብላቸው ጥያቄ የቀረቡትን የተመለከተ ነበር፡፡

ይህንንም ጥያቄ መልስ ለመስጠትና ውሳኔ ለማሳለፍ አስቀድሞ ምልዓተ ጉባኤው አምስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ለኮሚቴነት በመሰየም የቀረቡትን ጥያቄዎች በማየት የውሳኔ ሐሳብ ለምልዓተ ጉባኤው እንዲያቀርቡ  በማድረግ አምስት  አባቶችን ሰይሟል፡፡

የተሰየሙት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትም ከምልዓተ ጉባኤው ጎን ለጎን  የቀረቡትን ሦስት ጥያቄዎች  በኮሚቴው በማየት የምክረ ሐሳብና የውሳኔ ሐሳብ  ለምልዓተ ጉባኤው አቅርበዋል፡፡

ብፁዓን አባቶችም ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብም ምክንያት  ምልዓተ ጉባኤውም ሰፊ ውይይት በማድረግ  አሳልፏል።

በዚህም መሠረት፡-

፩ኛ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ያቀረበውን አባት  ይመደብልን የሚል ጥያቄ  በተመለከተ ብፁዕ አቡነ ቶማስ የአዊና የመተከል አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከትን ደርበው የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከትን እንዲመሩና እንዲይዙ ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡

በ፪ኛ ደረጃ ደግሞ ከደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት ብፁዕ አቡነ አትናቴዎስ ያቀረቡት  እንዲሁ አባት እንዲመደብ ጥያቄ ነው፡፡

ብፁዕነታቸው በሚመሩአቸው የደቡብ ወሎ ሀገረ ስብከት  የከሚሴ የደቡብ ወሎ ልዩ ዞን  ሁለቱን ሀገረ ስብከቶች አባት እንዲመደብላቸው  ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የብፁነታቸውን ጥያቄ ተቀብሎ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ መሠረት  ለአግልግሎትም እንዲመች በአቅራቢያ የሚገኙትን የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ደርበው እንዲመሩ ምልዓተ ጉባኤው  ወስኗል፡፡

በ፫ኛ ደረጃ ከምሥራቅ ወለጋ፣ ከምዕራብ ወለጋ ከሆሮ ጉድሩ ወለጋ አባት እንዲመደብ የቀረቡ ጥያቄዎችን በአጀንዳ ቀርጾ በብፁዓን አባቶች በቀረበው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት የምሥራቅ ወለጋንና የሆሮ ጉድሩን ብፁዕ አቡነ ኒቆዲሞስ የምሥራቅ ሐረርጌ ጳጳስ ሀገረ ስብከታቸውን እንደያዙ  ደርበው እንዲመሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡

የምዕራብ ወለጋን በተመለከተ ደግሞ ብፁዕ አቡነ ኤውስጣቴዎስ የኢሊባቡር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  የምዕራብ ወለጋን ደርበው እንዲመሩ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ወስኗል፡፡ 

በ፮ኛ ተራ ቁጥር የነበረው አጀንዳ የኢትዮጵያ ገዳማት ኅብረት ያቀረበውን ጥያቄ በተመለከተ ውይይት የተደረገበት አጀንዳ ነው፡፡

በዚህ አጀንዳ ላይ የገዳማቱ የሥራ አስፈጻሚ አባላት የሆኑት  አባቶች ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ቀርበው ጥያቄአቸውን በንባብ አሰምተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ገዳማት ከ፳፻፲ ዓ.ም ጀምሮ  ያደረጋቸውን ሥራዎች የሚገልጽ በዚያም በየደረጃው በገዳማት መምሪያና በቋሚ ሲኖዶስ  በተሰጡአቸው የመተዳደሪያ ደንቦች ሥራቸውን እያካሄዱ እንደሆነ ከዚያም ደግሞ የገዳማቱ አባቶች ለተልዕኮና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ጊዜ ማረፊያ ስለሚያስፈልጋቸው ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት መሠረት ይህን የመሰለውን አጀንዳዎቻቸውን ለቅዱስ ሲኖዶስ በንባብ አሰምተዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስም የአባቶችን  ጥያቄ በመስማት  ውይይት በማድረግ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

በዚሁ መሠረት በአንደኛ ደረጃ የገዳማቱ ኅበረት ያቀረቡት ከገዳም ለአገልግሎትና ለተለያየ ተልእኮ  ወደ  አዲስ አበባ ሲመጡ የሚያርፉበት ቦታ ያለውን አስፈላጊነት  ምልዓተ ጉባኤው በመገንዘብ  በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ተመቻችቶ  በዚያ መልስ እንዲሰጣቸው ወስኗል።

በሁለተኛ ደረጃ የታየው የገዳማት ኅብረቱ  ለገዳማት ዘላቂ ልማትና ራስን ለመቻል  በልማት ለሚያካሂዷቸው እንቅስቃሴዎች  ጥያቄዎችን የተመለከተ ነው፡፡

ይህንንም ጥያቄ ምልዓተ ጉባኤው በሰፊው በመወያየት ጉዳዩ ጥናት የሚያስፈልገው፣ የሕግ አስተያየት የሚያስፈልገው በመሆኑ ጥያቄው ለመንበረ ፓትርየርክ ጠቅላይ ቤተክህነት  በቋሚ ሲኖዶስ ክትትል ወደፊት ውሳኔ  ይሰጠዋል በማለት ምልዓተ ጉባኤው ወስኗል፡፡ 

በሁለተኛዉ ቀን በአጀንዳ ቁጥር ፭ እና ፮  ቅዱስ ሲኖዶስ  ያደረገው ውይይት ይህን ይመስላል፡፡

በቀጣይ በቀሪዎቹ አጀንዳዎች ላይ ምልዓተ ጉባኤው ውይይቱን የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ዋናው ማእከል:

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...