በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የግንቦት 2015 ዓ.ም ርክበ ካህናት ምልዐተ ጉባኤውን ጀምሯል፡፡ ጉባኤው ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በጸሎት ሥነሥርዓት ተጀምሯል። ከዚያም በኋላ ባሉት ተከታታይ ቀናት ምልዓተ ጉባኤው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሣኔዎችን አሳልፏል፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም ከመጀመሪያው ዕለት አንስቶ የነበሩትን የጉባኤውን ውሎዎችና ውሣኔዎች እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 2 ቀን 2015 ዓ.ም በ2ኛ ቀን ውሎው የተከፋፈለ ሲኖዶስ እንደሌለ እና ከዚህ ሐሳብ ውጪ የሆነ አካል ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ውጪ ገልጽዋል፡፡ ጉባኤው በሁለተኛው ቀን በነበረው ውሎ በሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነበር የተወያየው። ቅዱስ ሲኖዶስ በቀዳሚነት በሀገር ሰላም ዙሪያ በተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ጉባኤው ብዙ ሲወያይ ከቆየ በኋላ በመጨረሻም ‹‹ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ማድረግ ትችላለች፣ ምእመናንም የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ድምጽ ይሰማሉ›› የሚለው ሐሳብ አሸንፎ ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስን ወክለው የሚሰሩ ሦስት ብፁዓን አባቶች ተመርጠው የሀገር ሰላምን በተመለከተ ረዥም ርቀት በመሔድና ከሚመለከተው አካል ጋር ሁሉ በመነጋገር በሀገር ሰላም ዙሪያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉና አሁን ካለንበት መከራ የምንወጣበትን መፍትሔ እንዲያመጡ ተመርጠዋል።
በቀጣይነት በወቅታዊ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ችግር አስመልክቶ በትግራይና በኦሮሚያ አህጉረ ስብከት የነበሩትን ችግሮች መነሻ በማድረግ፤
ሀ) በክልል ትግራይ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት የትግራይ አባቶችና አባላቱን በአካል የሚያነጋግሩ ብፁዓን አባቶች ተመርጠው ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል።
– በተጨማሪም ተቋርጦ የነበረው በጀት እንዲለቀቅ
– የማጽናኛ መርሐ ግብር እንዲካሄድና በተቻለ መጠን አስቸኳይ እርዳታ እንዲደረግ በጉባኤው ተወስኗል።
ለ) በጥር 14 ቀን 2015 ዓ.ም የተከሰተውን የቤተ ክርስቲያን ፈተና በተመለከተ ሰፊ ውይይት ከተደረገ እና ወደ መግባቢያ ሐሳቦች መደረሱን ገልጸው
በስድስት አህጉረ ስብከቶች ምንም ዓይነት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ የደረሰውን መረጃ መነሻ በማድረግ የማያዳግም የመፍትሔ ለመስጠት ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ከሦስቱ ብፁዓን አባቶች ጋር አራት ብፁዓን አባቶችን ተጨማሪ በማድረግ በቀጥታ የነበረው ችግር ሙሉ በሙሉ መቀረፉንና ከአንድ ሲኖዶስ ውጪ ሌላ አለመኖሩን ለመንግሥት አካላት በጋራ ሔደው የተደረሰበትን ስምምነት ተገቢውን መረጃ እንዲሰጡ፤
ብፁዕ አቡነ ኤርምያስን
ብፁዕ አቡነ ሩፋኤልን
ብፁዕ አቡነ ናትናኤልን
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስን
ብፁፅ አቡነ ሳዊሮስን
ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስን እና
ብፁዕ አቡነ ኤውስጣቴዎስን
በመመደብ እነዚህ ሰባት ብፁዓን አባቶች በአንድ ላይ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር ፍጹም በሆነ የመግባባት ስምምነት መፈጠሩን ገልጸው ከእንግዲህ በኋላ የተከፋፈለ ሲኖዶስ እንደሌለ እና ከዚህ ሐሳብ ውጪ የሆነ አካል ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት ውጪ የሆነ መሆኑን በአንድነት ለመንግሥት እንዲያሳውቁ ተወክለዋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በሦስተኛ ቀን ውሎው ደግሞ ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ እና ብፁዕ አቡነ ቶማስ ቀደም ሲል ሲያገለግሉባቸው በነበሩባቸው አህጉረ ስብከት አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ በዚህም መሠረት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የደቡብ ትግራይ ማይጨው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ቶማስ የአዊና መተከል ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቀደም ሲል ያገለግሉባቸው በነበሩባቸው አህጉረ ስብከት አገልግሎታቸውን እንዲቀጥሉ ጉባኤው ወስኗል። ጉባኤው በውሎው እንዲነጋገርበት ተይዞ የነበረው የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጉዳይ የጉባኤው የመጨረሻ አጀንዳ እንዲሆን የአጀንዳ ሽግሽግ አድርጓል። እንዲሁም የዋልድባ ዳልሻህ ኪዳነምሕረት ማኅበረ ደናግል ገዳምን በተመለከተ ፣ የያዘው አጀንዳ ላይ መወያየቱን እና ለውሳኔ በይደር አቆይቷል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በአራተኛ ቀን ውሎው በኦሮሚያ ክልል በኢሊአባቦራ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲቋቋም የቀረበውን ጥናት መርምሮ አጸድቋል፡፡ ባለፈው ጊዜ የቀረበው የኢሊአባቦራ ሀገረ ስብከት የመንፈሳዊ ኮሌጅ ማቋቋሚያ ሰነድ ተሻሽሎ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ተሻሽሎ በመቅረቡ የኮሌጁ መቋቋም በመርኅ ደረጃ በቅዱስ ሲኖዶስ ሊጸድቅ ችሏል። በተያያዘ ዜና በምዕራብ ኦሮሚያ ማዕከላዊ በሆነ ቦታ አንድ ኮሌጅ እንዲቋቋም እንዲሁም በደቡብ ጎንደር እና በሰሜን ሸዋ አህጉረ ስብከት መንፈሳዊ ኮሌጆች እንዲቋቋሙ በጠቅላይ ጽ/ቤት ተጠንቶ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ መሆኑም ተገልጿል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በአምስተኛ ዕለት ውሎው ውስብስብ የሆነውን የቤተ ክህነት ችግር እንደሚያቃልል ተስፋ የተጣለበትን መሪ ዕቅድ መርምሮ ማጽደቁ አስታውቋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በዕለቱ በሁለት አጀንዳዎች ላይ ነው ውሳኔ ያስተላለፈው። የመጀመሪያው ለረጅም ጊዜ የቤተ ክህነቱን ውስብስብ ችግሮች ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የመሪ ዕቅድን በተመለከተ ሲሆን በዚህ ውስጥ መንፈሳዊ ልማት ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና አስተዳደር ጉዳዮችን ተመልክቷል። በዚሁ አጀንዳ፤
ሀ) የመንፈሳዊ ልማት ዓላማ የቤተክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ጉዳይ በምድሪቱ ላይ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረሰብ መፍጠር ፣ መገንባት የሚያስችል ሆኖ መጽደቁን እና በዚሁ መሠረትም ወደ ሥራ እንደሚገባ ተገልጾዋል።
በዚሁ አጀንዳ
ለ) ቤተክርስቲያን በብዙ የልማት ሥራዎች ውስጥ የምትሳፍበት እድል መኖሩ የተመላከተ ሲሆን ይኸው ወደ ተግባር እንዲገባ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሳልፏል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ሁሉም ሰው በመሪ ዕቅዱ ትግበራ ላይ እንዲተባበር ጥሪ ቀርቧል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በስድስተኛ ቀን ውሎው በአራት አጀንዳዎች ላይ ውሳኔ አሳልፏል። በዚህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርቷን ለትውልዱ የታስተምርበት ተቋማት አንዱ መንፈሳዊ ኮሌጆች መሆነቸውን አውስቷል፡፡ እነዚህ ኮሌጆች ወጥ የሆነ ሕግ ሳይኖራቸው የቆየ ሲሆን፣ በቅርቡም በሐዋሳ እና በወልቂጤ የተቋቋሙት ኮሌጆች ባቀረቡት መተዳደሪያ ደንብ መሠረት፤ ቅዱስ ሲኖዶስ ውይይት አድርጎ ለሁሉም መንፈሳዊ ኮሌጆች የሚያገለግል ወጥ የሚሆን ሕግ አዘጋጅቶ አጽድቋል፡፡
በሌላ አጀንዳ በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በጀርመን ገዳም እንዲኖራት ያቀረበው በጥናት የተደገፈ ሰነድ ጸድቋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተጨማሪ ብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ አማካኝነት በሰሜን አሜሪካ በካሊፎርኒያ የተመሠረተው የኆኅተ ሰማይ ገዳምን በተመለከተ ጉባኤው የተወያየ ሲሆን፣ ገዳሙ የተመሠረተበትን ሰነድ ለጥቅምት ጉባኤ ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የሚያረክቡም ይኾናል፡፡ ጉባኤው የአእምሮ ንብረትን የተመለከተ ጉዳይም በስፋት ተወያይቷል። ይህ ኮሚቴ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ የነበረ መሆኑ ታውቆ አሁንም በተጠናከረ መንገድ እንዲሠራ በጀት እንዲያዝለት ተወስኗል፡፡ በሌላ አጀንዳ የምስጢራት መፈጸሚያ የሆነው የጸሎት መጽሐፍም እንዲታተም ተወስኗል፡፡ ጉባኤው የጡረተኞችን አበልን የተመለከተ ጉዳይም ላይ ተወያይቷል። የጡረተኞችን አበልን የተመለከተ ተጠንቶ እንዲቀርብ በታዘዘው መሠረት ጥናቱ ቀርቦ ውይይት ተካሂዶበታል፡፡ በዕድሜያቸው በቤተክርስቲያን ሲያገለግሉ ቆይተው በአነስተኛ ደመወዝ ጡረታ የወጡ ማስተካከያ የሚደረግበት ውሳኔም ተላልፏል፡፡
የዳልሻህ ኪዳነ ምሕረት ማኅበረ ደናግል አንድነት ገዳምን የተመለከተ ቅዱስ ሲኖዶስ የተወያየበት ጉዳይ ነው፡፡ ገዳሙ ከተመሠረተ ከአንድ ሺሕ ዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ በዚህ ገዳም ላይ ተነሥቶ የነበረው ችግር በተመለከተ ቅዱስ ተወያይቶበት የውሳኔ ሐሳብ አሳልፏል፡፡ ውሳኔውም እናቶች በጥንት ገዳሙ ሲተዳደርበት በነበረው አሠራር መሠረት እንዲቀጥል ገዳማውያን እናቶች በጥያቄያቸውም መሠረት አምልኮአቸውን እንዲፈጽሙ ውሳኔ ተወስኗል፡፡ ይህም ሰፊ ውይይት ተደርጎበት የእናቶች ገዳም አሠራር መሠረት እናቶች በቆየው ትውፊት፣ በጥያቄያቸው መሠረትም አምልኮታቸውንን እንዲፈጽሙ በመወሰን የዕለቱ ስብሰባ ተጠናቅቋል፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ በሰባተኛ ቀን ውሎው አዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ሢመት ጉዳይ ተወያይቷል፡፡ በዕለቱ ከአንድ ቀን በፊት ውሳኔ ያገኘው የዋልድባ ዳልሻህ ኪዳነ ምህረት ማኅበረ ደናግል ገዳም ጉዳይን በተመለከተ ምንም እንኳ አጀንዳው ውሳኔ ያገኘ ቢሆንም በገዳሙ የሚኖሩ አባቶች መጥተው በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ቀርበው እና ጸሎት ተደርጎ እንዲሁም በዕርቅና በስምምነት አጀንዳው ተዘግቷል። በዕለቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ከቀትር በኋላ በነበረው ውሎ የመጨረሻውን አጀንዳ የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳትን ሢመት ጉዳይ አስመልክቶ ውይይት ያደረገ ሲኾን የመጨረሻ ውሳኔ ሳይሰጥ በይደር አጀንዳው ለቀጣዩ ቀን ተላልፏል፡፡
ኾኖም በማግስቱ በስምነተኛው ቀን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሎ መግባባት ላይ ሳይደረስ በመቅረቱ ጉባኤው ለሰኞ ግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም ተላልፏል፡፡ በዕለቱ በነበረው ዘጠነኛ ቀን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሎ የግንቦት 2015 ዓ/ም የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በሰላም እና ደስ በሚል ሁኔታ መጠናቀቁም ተገልጽዋል። በዕለቱም በመጨረሻው አጀንዳ ላይ ብዙ ውይይት ተካሂዷል። በመጨረሻ ሁሉም አባቶች ተወያይተው ቤተክርስቲያንን የሚጠቅመው ምንድነው? የሚለው ላይ በመምከር ውሳኔ መተላለፉ ተነግሯል። በዚህም የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት እንዲካሄድ የተወሰነ ሲኾን፣ ይኽም በሁለት ዙር ተከፍሎ፣ የመጀመሪያው ‹‹ችግር ያለባቸው ሀገረ ስብከቶች›› በሚል 7 አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል፤ እነሱ በሚያቀርቡት ጥናት መሰረትም ሹመቱ የሚካሔድ መኾኑ ተገልጽዋል። የሹመቱ ቀን ወደፊት እንደሚገለፅና ዋናው ነገርም ለቤተክርስቲያን የሚጠቅመው የትኛው ነው? የሚለው መሆኑም ተብራርቷል፡፡ የጉባኤው አባላት በሙሉ ተስማምቶ፣ በአንድ ልብ፣ በአንድ ሃሳብ፣ በመነጋገር ውሳኔ እንዳሳለፈም ይፋ ተደርጓል፡፡
በማግሥቱ ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም ቅዱስ ሲኖዶስ ይፋ ባደረገው መረጃ ደግሞ የአዳዲስ ኤጲስ ቆጶሳት ምልመላና ምርጫ የሚያከናውን 7 ሊቃነ ጳጳሳት ያሉት አስመራጭ ኮሚቴ መምረጡን አስታውቋል፡፡ ችግር ባላባቸውና አስፈላጊ በሆነባቸው ዘጠኝ አህጉረ ስብከት ላይ በዚህ ዓመት 2015 ዓ/ም ዘጠኝ (9) አዳዲስ ኤጲስ ቆጳሳት እንዲሾሙና በጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያን እውነትና ቀኖናን እንዲሁም መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲሁ አባቶች በሚያስፈልጉባቸው አህጉረ ስብከት የአዳዲስ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ጉዳይን እንደሚመለከተው ውሳኔ አስተላልፏል። ስለሆነም በዚህ ዓመት በሚካሄደው ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት የሚሾሙ አባቶች የሚመደቡባቸው የዘጠኙ አህጉረ ስብከት ስም ዝርዝር
፩. ምዕራብ ወለጋ ሀገረ ስብከት
፪. ምሥራቅ ወለጋ ሀገረ ስብከት
፫. ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ሀገረ ስብከት
፬. የቡኖ በደሌ ሀገረ ስብከት
፭ ምዕረብ አርሲ ሻሸመኔ ሀገረ ስብከት
፮. ምሥራቅ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት
፯.ድሬዳዋ ሀገረ ስብከት
፰.ጌዴኦ ቡርጅና አማሮ ሀገረ ስብከት
፱.ዳውሮ ኮንታ ሀገረ ስብከት መሆናቸው ታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ምልዓተ ጉባኤው ይህን ጉዳይ በጥናትና በቤተ ክርስቲያናችን ቀኖና መሠረት የሚለይና የሚያከናውን 7 ሊቃነ ጳጳሳት የተካተቱበት አስመራጭ ኮሚቴ መምረጡም ተገልጿል።
የአስመራጭ ኮሚቴው አባላትም ስም ዝርዝርም
1) ብፁዕ አቡነ ሄኖክ
2) ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
3) ብፁዕ አቡነ ማርቆስ
4) ብፀዕ አቡነ ናትናኤል
5) ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
6) ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ
7) ብፁዕ አቡነ ሩፋኤል በመሆን ኮሚቴው ተዋቅሯል።
አስመራጭ ኮሚቴው ጥናቱንና ምልምላውን ከቋሚ ሲኖዶስ ጋር በመናበብ የቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት በማድረግ ለመጨረሻ ምርጫ ለምልዓተ ጉባኤ የሚያቀርብ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤው እንደሥርዓቱ በመምረጥ ዘጠኙን መነኮሳት የሚለይ ይሆናል። በምልዓተ ጉባኤው የተመረጡ ዘጠኙ መነኮሳት አባቶች ሥርዓተ ሢመት ሐምሌ 9/2015 ዓ/ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አንብሮተ ዕድ እንደሚፈጸም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
በመንፈስ ቅዱስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የርክበ ካህናት መደበኛ ስብሰባውን ከግንቦት 1 ቀን 2015ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡ ምልዓተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ ለሐዋርያዊ ተልእኮ መስፋፋት እና መንፈሳዊ ዕድገት ትኩረት በመስጠት ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
- ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የሰላም ጉልላት እንደመሆኗ ሰላም መሠረታዊ ተልእኮዋ ነው፡፡ ስለዚህ ወቅታዊውን ችግር ታሳቢ በማድረግ በመላው አገራችን ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመራ፤ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ካሉ ተቋማት ጋራ የሚሠራ፣ በሀገሪቱ መንግሥትም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የሚኖረው የሰላም ኮሚቴ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰይሟል፡፡
- በትግራይ ክልል በሚገኙት አህጉረ ስብከት ተቋርጦ የነበረው መንፈሳዊና አስተዳደራዊ ግንኙነትን በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ተሠይሞ በሥራ ላይ የሚገኘው ልዑክ የጀመረውን እንቅስቃሴ እንዲቀጥል የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትን በማነጋገር ተልዕኮውን እንዲፈጽም ምልዓተ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፡፡
- በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ክልል የሚገኙ ወገኖቻችን ያሉበትን ከፍተኛ ችግር ታሳቢ በማድረግ አስቸኳይ የሆነ ሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ ሃያ ሚሊየን ብር ድጋፍ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
- በወቅታዊ ችግር ምክንያት በመላው ሀገራችን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖቻችን ሁሉ በአጠቃላይ ችግሮቹን በጥናት በመለየት፣ ቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ልጆቿን በማስተባበር ሁለንተናዊ ሰብዓዊ ድጋፍ፣ የማጽናናትና የመጎብኘት መርሐ-ግብሮች እንዲደረጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
- መቀሌ የሚገኘው የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የሠራተኞችን ደመወዝና የሥራ ማስኬጃ በጀት እንዲለቀቅና በ2016 በጀት ዓመት ተማሪዎችን በመቀበል መደበኛ የሆነ የመማር ማስተማሩ የሥራ ሂደት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመጪው ዐሥር ዓመታት የመንፈሳዊ እና ዘላቂ ልማት ግብ መሪ ዕቅድ በማጽደቅ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅሮች ተግባራዊ እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፡፡
- የቤተ ክርስቲያናችን ቀደምት አበው በቅድስት ሀገረ ኢየሩሳሌም ገዳማት እንዲስፋፉ ሁሉ የነሱን አሰረ ፍኖት በመከተል በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ ካልፎርኒያ ግዛት የተቋቋመው ኆኅተ ሰማይ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ወቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም እንዲጠናከር፤ በተጨማሪም በጀርመንና አካባቢው ሀገረ ስብከት የአስተዳደር፣ የጽሙና፣ የትምህርትና የምርምር ማዕከል እንዲመሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ አስተላልፏል፡፡
- በኦሮምያ ክልል በሚገኙ አህጉረ ስብከት ተፈጥሮ በነበረው ወቅታዊ ችግር ምክንያት በአህጉረ ስብከትና በአብያተ ክርስቲያናት አገልግሎት ስለተቋረጠ፣ በርካታ ምእመናንና ካህናት በእስርና እንግልት ላይ ስለሚገኙ በዚሁ መነሻነት ችግሮች እንዲቀረፉና ወደ መደበኛው የአሠራር መዋቅር እንዲመለስ ሰባት ሊቃነ ጳጳሳትን በመሠየም ከፌዴራልና ከኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ጋር በመወያየት ችግሮች እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
- የመንፈሳዊ ኮሌጆች መከፈት እና የአብነት ትምህርት ቤቶችን ማጠናከር በተመለከተ በኢሉ አባቦራ የመቱ ፈለገ ሕይወት የነገረ መለኮት መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲከፈት የተፈቀደ ሲሆን በሌሎች አህጉረ ስብከት ሊከፈቱ የታሰቡ ኮሌጆችን እና የአብነት ት/ቤቶችን መሠረታዊ ጥናት ተደርጎ ለ2016 ዓ.ም. የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ እንዲቀርብ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
- ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተ ክፍት በሆኑና በተደራቢነት በተያዙ፣ ጉልህና አንገብጋቢ ችግር ባለባቸው በኦሮምያ ክልልና በደቡብ ክልል ባሉ አህጉረ ስብከት ላይ 9 ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ አስመራጭ ኮሚቴ ሰይሟል፡፡ ወደፊትም ተደርበው በተያዙና አስፈላጊ በሆኑ አህጉረ ስብከት እንደአስፈላጊነቱ በመንበረ ፓትርያርክ ተጠንቶ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም በሀገራችን በአንዳንድ ቦታዎች የሚታዩትን አላስፈላጊ ግጭቶች የዜጐች መፈናቀል፣ ስደት ተወግዶ ሁሉም ዜጋ በሀገሩ በእኩልነት፣ በሰላምና በፍቅር ተከባብሮ በአንድነት እንዲኖር፤ ለማድረግ ግጭቶችና አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡ እንዲሁም በመላው ዓለም ጦርነት ባለባቸው ሀገራት ሁሉ ሰላም እና ዕርቅ እንዲሰፍን በመመኘት እና በመጸለይ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ በጸሎት አጠናቋል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
