የብሔር ግጭት እሳት አቀጣጣዩ የከንቲባዋ ንግግር

Date:

አዳነ ጥላሁን ዳኜ(ወልድያ)

የሰሞኑ ያገራችን ፖለቲካ ቀውስ እየባሰበት እንጂ ሲያገግም አይታይም፡፡ በዚህም የተነሳ እጅግ በርካታ የተጠራቀመና የታመቀ ብሶት ተሸካሚ ሆነናል፡፡ በዚህ ላይ የኑሮ ውድነቱ እንደእግር እሳት እየለበለበን ነው፡፡ የዋጋ ንረቱ ከፍላጎታችን ጋር አልጣጣም ብሎ ሌላው ቀርቶ መሠረታዊ ፍላጎታችንን ማሟያ አቅም ካጣን ሰነባበትን፡፡ ባለፈው የልደት (የገና) በዓል ዕለት የአንዲት በግ ሥጋ ለ 4 የተካፈሉ የቤተሰብ አባወራዎች ‹‹በዚሁ ከቀጠልን ለበዓለ ፋሲካ ዶሮ ለ4 እንዳንቃረጥ እንሰጋለን›› ነበር ያሉት፡፡ ስለሥጋታቸው እውን መሆን አለመሆን ፋሲካ ሲደርስ እናየዋለን፡፡

ቁራሽ ዳቦ አጥቶ የሚንከራተት ወገናችንን ስናይ የነዚህ አራት አባወራዎች ምሬት የቅንጦት ሆኖብኝ ትኩረት አልሰጠሁትም፡፡ ግን 5 ቤተሰብ ያለው በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደር ዜጋ በመቶ ብርና ከዚያም በላይ በሆነ ዋጋ የገዛት ሞኮረኒ ለ1 ጊዜ ቁርስ ቤተሰቡን ማጥገብ አቅቷት ስናይ  የወደፊት አኗኗራችን ከብሩህነቱ ይልቅ ጨለማነቱ አመዝኖ ነው የሚታየው፡፡

በዚህ ላይ ልክ እንደኑሮ ውድነቱ ሁሉ ፖለቲካው ጤና አጥቶ እኛንም ጤና አሳጥቶናል፡፡ በየቦታው የቀጠለው የሕዝብ ጭፍጨፋ ተጠናክሮና አድማሱን አስፍቶ ቀጠለ እንጂ አልቆመም፡፡ መፈናቀሉ፣ በፀጥታ ኃይል መታፈኑ፣ መታሰሩም ሆነ መደብደቡ ብሎም መንገላታቱም እንዳለ አለ፡፡

በሕገወጥነት ሽፋን ቤት በማፍረስ በርካታ ቤተሰብ በመበተን የጎዳና ተዳዳሪ በማድረጉ ረገድ  ይመሩናል ብለን በመሪነት ወንበር ላይ እንዲቀመጡ ድምፅ የሰጠናቸው መሪዎቻችን የሥልጣን ማሳያ ሆኖ ዕለት በዕለት የምንሰማው በእንባ ጎርፍ የታጀበ የሕዝብ ለቅሶ ተው ባይ አላገኘም፡፡

ያገራችንን ውስብስብና ዘርፈብዙ ችግር በዚች አጭር መጣጥፍ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡ ባጭሩ ባገር ደረጃ ከዚህ ቀደም ያልታየና ያልተከሰተ ሀገራዊ የአደጋ ዳመና በሰማዩ ላይ መዓት ሊያዘንብ እያንዣበበና ሀገራዊ ሕልውናችን አጠያያቂ የሆነበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ምን ዓይነት የፖለቲካ ትርፍ እንደሚያገኙ ግልፅ ባይሆንልንም በተለይ ይኸ የታመቀ ብሶትና ምሬት ተሸካሚ ሕዝብ ወደጠብና ግጭት ያመራ ዘንድ የሚገፋፉትም ሆነ የሚተነኩሱትና በሰበባ ስበብ የሚያበሳጩት አሁን ላይ ጥርስ ያወጡ በመንግሥታችን ከፍተኛ እርከን ላይ የተሰገሰጉ መንደር ናፋቂ የጎሳ ፖለቲከኞች ናቸው፡፡

የእነዚህ ባለሥልጣናት እኩይ ድርጊት ይበልጥ አስከፊነቱ የጨመረውም ከጥቃቅኗ ጀምሮ ተሰራ የሚሉትን ስህተት በብሔር መነፀር እየተመለከቱና በጎሳ ሚዛን መዝነው እየመነዘሩ ብሔሮችን እየከፋፈሉ በእነርሱ ጥቁር መዝገብ ላይ መመዝገባቸው ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ ለም/ቤታቸው ያቀረቡት ሪፖርት ላይ የመንግሥት ግልበጣ ለማካሄድ ከክልሎች ወደ አዲስ አበባ የሚፈልስ ዘውድ ናፋቂ ቡድን እንዳለ የነገሩንም ከላይ የገለፅኩትን የብሔር ምንዘራ ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ ነው፡፡ ‹‹ፍልሰት›› በሚለው ዓ.ነገር ዙሪያ ትኩረት እንዳንሰጥ ያደረገን ሌላ የገዘፈ አሳሳቢ ጉዳይ ስላለ እንጂ የፍልሰት ጉዳይ ከተነሳ እርሰዎስ አንዷ ፈላሲ አይደሉም እንዴ! አዲስ አበባ እርሰዎን የጡት ልጅ አድርጋ ከአርሲ ሲመጡ እጇን ዘርግታ ከተቀበለች እኔን ከወልድያ ስመጣ ተራ ዜጋ ነኝና እንደእርሰዎ እጇን ዘርግታ ባትቀበለኝ እንኳ በእንጀራ ልጅነት ከማህፀኗ ገፍትራ ለምን ታባርረኛለች? እርስዎ ወደዚች ከተማ በነፃነትና ያለመሸማቀቅ በሰላም ገብተው መውጣት ከቻሉ እኔ እገባለሁ አልገባም በሚል ኬላ ላይ ከሚፈትሹ የፀጥታ አካላት ጋር አታካራ ውስጥ ለምን እገባለሁ ወይም በከተማዋ ውስጥ እንደሌባ ለምን በሥጋት እየተገላመጥኩ እጓዘዛለሁ? የሚል መከራከሪያ ይዤ ወደ ሙግት መግባት እችል ነበር፡፡ የከንቲባዋን አደጋ ጠሪና አደጋ ጋባዥ ንግግር በማዳመጥ ማብራሪያ እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ በእርሳቸው ምትክ መልስ የሰጡት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነሩ የመፈንቅለ መንግሥቱን ጥንስስ አረጋግጠው ወደዝርዝር አፈፃፀሙ ሲገቡ በምን ስሌት እንዳሰሉት ባይዘረዝሩትም ዙፋን ነጣቂውን  ቡድን በመቶኛ አስቀምጠው ነው መልስ የሰጡን፡፡

በኮሚሽነሩ ገለፃ መሠረት ዙፋን ናፋቂው ቡድን ከአማራ ክልል 64/100፣ ከደቡብ ክልል 21/100 እና ከኦሮሚያ ክልል እንደሚይዝ ገልፀው ቡድኑ ወደዙፋኑ መጠጋት የሚፈልገውም በዓላትን ተንተርሶ መሆኑን ሲናገሩ ትዝ ያለኝ በ127ኛው የአድዋ የድል በዓል ዕለት በምኒልክ አደባባይ ተገኝቶ …

“አንዱ በዱላ ሌላው በከስከስ እየረገጡን፣

ሰላም ነወ አሉን ሰላም ነው አሉን” እያሉ በፀጥታ ኃይሉ የሚደርስባቸው ወከባ፣ እንግልትና ድብደባ  ያስከተለባቸውን ምሬት በሆታ ሲገልፁ የነበሩ ወጣቶች ናቸው፡፡ የከንቲባዋ ንግግርም ሆነ የኮሚሽነሩ ገለፃ በከተማዋ አስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ሀላፊም በኩል ይሁንታ አግኝቷል፡፡ እንግዲህ በባለሥልጣናቱ ስሌት መሠረት በከፍተኛ ደረጃ በምኒልክ አልጋ ላይ ለመቀመጥ ፍላጎቱ የናረው የአማራ ክልሉ ዙፋን ነቅናቂው አካል ነው ማለት ነው፡፡

የሰሞኑን  የአማራ ክልል ዕጣ ፈንታ ኮከብ ስቆጥረው አሰድ እሳት የሚለው የኮከብ ዕጣ ነው የወጣው፡፡ የአሰድ እሳትን ምስጢር ዘርዛሪ መፅሐፍ ስገልጠው ደግሞ የአሰድ እሳት ዕጣ ፈንታ የወጣለት ሁሉ በዐመቱ ነገር ስለማያጣው ጥንቃቄ የሚያሻው መሆኑንና ለክፉም ለደጉም ጥንቃቄ  ማድረግ እንዳለበት ያትታል፡፡   

እና ክብርት ከንቲባዋ ከ2ቱ ቁልፍ ባለሥልጣናት ጋር ጥርስ የነከሱበትም ሆነ መወንጀልም ማስወንጀልም የፈለጉት የአማራን ሕዝብ ስለመሆኑ መጠርጠሩ አይከፋም፡፡ በተለይ ወንጀልን በብሔር መተመናቸው በራሱ አንዱን ብሔር ከሌላው የሚያጋጭ በሕዝቦች መካከል ጥርጣሬን የሚያሰፍን ለዜጎችም ለመንግሥትም ለሀገርም ጭምር የማይበጅ የፖለቲካ ነዲድ እሳት አቀጣጣይ ግጭት ጠሪ ንግግር መሆኑን እርሳቸውም ያውቁታል እኛም አልተሰወረብንም፡፡

በብሔር ደረጃ የሚነሳ የፖለቲካ እሳት ዜጎችን በተቃራኒ ጠላትነት አሰልፎ እርስ በርስ የሚያጨራርስ መዘዙም ብዙ ውጤቱም እጅግ አሰቃቂና ሰቅጣጭ ፀፀቱም መቸም ጊዜ ቢሆን ከአዕምሮ የማይጠፋ ልብ ሰባሪ ስለመሆኑ መናገሩ የሚጠበቅብኝ አይመስለኝም፡፡

በኔ እምነት ያገራችን ፖለቲካ በሰከንድ ፍጥነት እየተለዋወጠ ለዕውቀትም ለእውነትም ባስቸገረበት ሁኔታ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት ክብርት ከንቲባዋም ሆኑ ክቡር ኮሚሽነሩ ወንጀልን በብሔር ተምነው በግልፅ አደባባይ መግለፃቸው ተከባብሮ ተሳስቦና ተፋቅሮ ይኖር የነበረውን ሕዝብ ጎራ ለይቶ በፍልሚያ ሜዳ ለሻምላ ፍልሚያ መጋበዝ ነው፡፡

የብሔር ግጭት ከተነሳ ደግም ተያይዘን ከምናልቅ በስተቀር አሸናፊም ተሸናፊም ስለማይኖር  በዚህ ስበብ ከወዲያ ወዲህ ሲቅበዘበዙ በትዝብት የምናያቸው አክራሪ ብሔረተኞች ፍላጎት የሚሳካ  አለመሆኑን ክብርት ከንቲባዋም ሆኑ ኮሚሽነራቸው ይስቱታል ብየ አልገምትም፡፡

ስለብሔር ግጭት አሰቃቂነት ከሩዋንዳ የዘር ፍጅት ትምህርት ልንቀስም ይገባል፡፡ ሩዋንዳ አክራሪ የሁቱ አክራሪ ብሔርተኛ ባለሥልጣናት በለኮሱት የብሄር ግጭት ጠሪ እሳት ለ3 ወራት ያህል የምድር ሲዖል ሆና 1 ሚሊዮን ዜጎቿን ለሞት ገብራለች፡፡

የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ከመጀመሩ በፊት በአክራሪው የሁቱ ቡድን ሥር የሚተዳደረው ሬድዮ አሁን በኛ ሀገር የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ በአማራ ሕዝብ ዙሪያ እየፈፀመ ያለው የጥላቻ ቅስቀሳ ዓይነት ፕሮፓጋንዳ በቱትሲ ጎሳዎች ላይ ይቀሰቅስ ነበር፡፡ ያ ሬድዮ ጣቢያ በየዕለቱ በሚያስተላልፈው ቅስቀሳ… በቱትሲ ጎረቤቶቻችሁ ላይ ተነሱ! ፈፅመንም እናጥፋቸው!.. እያለ ሁቱዎችን ያነሳሳ ነበር፡፡ የሁቱ አክራሪ ብሔረተኛ የነበሩት ያገሪቱ ፕሬዚዳንት ሐበይሪማና ያቋቋሙት ኢንተረሀሞይ (በአንድነት ኾነው የሚያጠቁ/የሚያደባዩ/ የሚል ነው ትርጉሙ) የተባለ የወጣት ገዳይ ቡድን አደራጅተውና አስታጥቀው በሀገረ ሩዋንዳ ለመናገርም ለመስማትም የሚሰቀጥጥ ጭፍጨፋ እንዲፈፀም አመቻችተዋል፡፡

የሚገርመው የሩዋንዳ የዘር ፖለቲካ ጦሱ የተረፈው ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን ለፕሬዚዳንቱም ጭምር መሆኑ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሐበይሪማና ሆን ተብሎ በተቀነባበረ ሴራ ተገደሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ሩዋንዳ የደም ጎርፍ የሚንዠቀዠቅባት መሬት ሆነች፡፡

ዘር ተኮል ፖለቲካ በጥላቻ የታወረ ጓደኛን ከጓደኛ፣ ጎረቤትን ከጎረቤት የሚያጋድል የሰውን ልጅ ማሰቢያ አዕምሮ አዛብቶና ከክብሩ አውርዶ የአውሬነት ባህርይ የሚያላብስ መሆኑን ማወቅ ለሚፈልግ የሩዋንዳን ታሪክ እንዲያነብ ይመከራል፡፡ አሁን ላይ በየመንደሩ የጎበዝ አለቃው እንደአሸን ፈልቶ ያዙኝ ልቀቁኝ ባዩ ለበዛባት የሀገሬ ሕዝብ ትምህርት ይሆን ዘንድ የሩዋንዳን ዘር ተኮር የጅምላ ጭፍጨፋ ታሪክ ዘርዘር አድርጌ አቀርበው ዘንድ ፍቀዱልኝ፡፡

ኢማኩሊ ሊባጊዛ ከሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በተዐምር ተርፈው የጅምላ ግድያውን በዝርዝር ከትበው ለዓለም ካሳወቁ ፀሐፍት አንዷ ናት፡፡ ይቺ ከቱትሲ ቤተሰብ የተገኘች ውብ ቁመተ ሎጋ ሩዋንዳዊት የዩኒቨርስቲ ተማሪ ለ3 ወራት ያህል ከሌሎች 6 ሴቶች ጋር በአንድ የቤተክርስቲያን አገልጋይ ቄስ ሽንት ቤት ተቆላልፈው በመደበቅና ብዙውን ጊዜም በረሀብ እየተጠራሞቱ ቆይተው ከሞት ከተረፉት አንዷ ስትሆን ያን የጨፈገገ የ3 ወራት የገሀነም ወቅት በዝርዝር የከተበችበትን ዝርዝር መረጃ ይልማ ሀይሉ የተባለ ተርጓሚ ‹‹ለወሬ ነጋሪ›› በሚል ርዕስ ተርጉሞ ለንባብ ሲያበቃው መዝሙር ግርማ የተባለ ሌላው ተርጓሚ ደግሞ ይህንኑ መፅሐፍ ‹‹ሁቱ ቱትሲ›› በሚል ርዕስ ለገበያ አቅርቦታል፡፡ እኔ በዚህ መጣጥፍ ላይ በመረጃነት የተጠቀምኩት የአቶ ይልማ ሀይሉን ‹‹ለወሬ ነጋሪ›› መፅሐፍ ነው፡፡

ኢማኩሊ በዚያ አስከፊ የዘር ጭፍጨፋ ሴኔጋል በትምህርት ላይ ከነበረው ታላቅ ወንድሟ በስተቀር አባትና እናቷን ሁለቱን ወንድሞቿን በሞት ተነጥቃለች፡፡ በተለይ ሞትን ለማምለጥ መጠጊያ ፍለጋ ወደቄሱ ቤት ከእርሷ ጋር ሄደው የነበሩት ቫኒያ የተባለው ታናሽ ወንድሟና የረፍት ጊዜውን ከነኢማኩሊ ቤት ለማሳለፍ ከኪጋሊ መጥቶ የነበረው የወንድሟ ጓደኛ የአውግስቲን ማታባ አሟሟት ፀፀት እንኳን እርሷን መፅሐፏን ያነበበን  ሁሉ እንደእግር እሳት ይለበልባል፡፡

አውግስቲን ወደቄሱ ቤት በሚሮጡበትም ወቅት ዙሪያውን ቢለዋ፣ ገጀራ፣ ቆንጨራ፣ በያዙ አረመኔ ገዳዮች መከበባቸውን እንደተመለከተ ሰው ሆኖ መፈጠሩን ጠልቶ ‹‹ምነው በዚች ደቂቃ  ወፍ በሆንኩና ኪጋሊ ከቤተሰቦቸ ጋር በሄድኩ›› ነበር ያለው፡፡ ይኸን የአውግስቲን የጭንቅ ምኞት ላዳመጠቺው ኢማኩሊ በህይወት እስካለች ድረስ በፀፀት ልቧን ሲያደማ ይኖራል ብሎ መገመት አይከብድም፡፡

ቄሱ ሁለቱን ወጣቶች ከቤታቸው እንድታስወጣላቸው በሰጡት ቁርጥ ያለ ትዕዛዝ መሰረት በእንቅልፍ ላይ የነበረውን ወንድሟን ቀስቅሳ ጉዳዩን ስትነግረው ከእንቅልፉ ሙሉ በሙሉ ባልነቃ ልብ ዐይኑን እያሻሸ  ‹‹ወደየት እንሂድ ኢማኩሊ?›› የሚል ልብ አንሰፍስፍ ጥያቄ ነበር የጠየቃት፡፡

ኢማኩሊ በወንድሟ ጭንቅ አዘል ጥያቄ ልቧ በሀዘን ቢሰበርም ከማልቀስ ውጭ ሌላ የምታደርገው ስላልነበራት ወንድሟን ከነጓደኛው ከቄሱ ቤት በጨለማ አስወጣቻቸው፡፡ እነርሱም ብዙ ርቀው ሳይሄዱ በዘር ፖለቲካ በታወሩ በሰው ደም በሰከሩ አክራሪ የሁቱ ገዳዮች እጅ ወደቁና በቆንጨራ ከታትፈው ገደሏቸው፡፡

የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በመንግሥት ስልጣን ላይ በተቀመጡ ባለስልጣናትም የሚደገፍና የሚበረታታ ነበር፡፡ ኢማኩሊ በተደበቀችበት ሽንት ቤት ሆና ቄሱ የከፈቱትን ሬድዮ ስታዳምጥ ካገሪቱ ሚኒስተሮች አንዱ ገዳይ ሁቱዎች አንድነታቸውን ይበልጥ አጠናክረው ቱትሲዎችን በሙሉ ህፃናትን ጭምር እንዲጨፈጭፉ ሲያበረታታና በተጨማሪም የቱትሲዎችን ግድያ ሊያስቆም በውጊያ ላይ የነበረው በፖል ካጋሚ የሚመራው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር የማሸነፍ ዕድል ቢገጥመው ተዋጊዎቹ የቤተሰቦቻቸውን ሬሳ እንዲረከቡ እንጂ በህይዎት የሚተርፍ ዘመድ  እንዳያገኙ ጭፍጨፋው ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ገዳዮችን አደራ ሲል ሰምታለች  (ገፅ 104)

የጭፍጨፋውን ዘግናኝነት በተመለከተም የቄሱ ሴት ልጅ ከደቡብ ሩዋንዳ ደብቃ ወደአባቷ ቤት አምጥታ ከነኢማኩሊ ጋር በመደባለቅ በዚያች ሽንት ቤት ታጭቀው በመደበቅ ሕይወታቸውን ያተረፉ ሁለት ሴቶች ነግረዋታል፡፡ መንገዳቸው ሙሉ በሙሉ በቱትሲዎች ሬሳ ተሞልቶ ጉዟቸውን ቀርፋፋ አድርጎት እንደነበርና ከተገዳዮች ብዛት የተነሳም የሬሳው ክምር እንደተራራ መቆለሉን የአገዳደሉ ዓይነትም በቆንጨራ በመከታተፍ እንደነበር ገልፀው በሬሳው ላይ የሰፈረው ዝንብ ድምፅ የመኪናቸውን ድምፅ እንደዋጠው በዝርዝር ገልፀውላታል፡፡

ደማስከስ የተባለው ሌላኛው ወንድሟ አገዳደል ደግሞ አሰቃቂነቱ ከሁሉ የከፋ ነበር ‹‹ማስትሬት ድግሪ ያለው ሰው ጭንቅላት ምን እንደሚመስል ማየት እፈልጋለሁ›› ብሎ የተናገረ አንድ ገዳይ ነበር በያዘው ቆንጨራ አናቱን ለሁለት ሰንጥቆ ጭንቅላቱን ለማየት የሞከረው፡፡ የኢማኩሊ ወንድም ከመገደሉ በፊት እርሷ የት እንደተደበቀች እንዲነግራቸው እጅግ ዘግናኝ ድብደባ ቢፈፅሙበትም ምራቁን ተፍቶባቸው የክብር ሞት ሞተ እንጂ ምንም ፍንጭ አልሰጣቸውም፡፡ በዚህ ወጣት ግድያ ላይ ኪራራ የተባለ የፕሮቴስታንት ቄስ የይሁንታ ቡራኬ መስጠቱና ገዳዮቹ ጊዜ ሳያጠፉ እንዲገድሉት ማበረታታቱ የሚያሳየን የዘር ፖለቲካ በሽታ ከዓለማውያን አልፎ መንፈሳውያን ነን የሚሉትን ጭምር ጠልፎ ከእግዚአብሔር መንገድ አስወጥቷቸው እንደነበረ ነው፡፡

በ3ወራት ውስጥ በሩዋንዳ የተፈፀመውን እልቂት ያየ ወይም ታሪኩን ያነበበ ሰው ለተወሰኑ ጊዜያት የሰላም እንቅልፍ ስለመተኛቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ያበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም ነው ነገሩ፡፡ ከዚህ ውጭ በመረጃ እጥረት እንጂ በኛም ሀገር ከሩዋንዳ ያልተናነሰ እልቂት ማስተናገዳችንን አልዘነጋሁትም፡፡

የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋን አስከፊነት ለማሳየት ይኸን ያህል የማሰንኩት የሰሞኑ ያገራችን ሁኔታ አሳስቦኝ እንደሆነ እንደምትረዱኝ አስባለሁ፡፡ ያ ጭፍጨፋ ከሞት በተረፉ ሩዋንዳውያን ላይ ጥሎት ያለፈ የፀፀት ጠባሳም ነበረ፡፡ የዚህ የፀፀት ጠባሳ ማሳያም ያቺው ከላይ የጠቀስኳት ወጣት ናት፡፡ ከዚያ ሁሉ መከራና ጭንቅ ከተረፈች በኋላ በመፅሐፏ ላይ ‹‹መች ይሆን እንባችን የሚቆመው›› ብላ ትጠይቅና ‹‹የጎሳ ፖለቲካ ውጤቱ ይኸ ነው፡፡ ይኸ ሰይጣናዊ የዘር ፍልስፍና ሥዕል በዓለማችን ዳግም አይምጣ!›› የሚል መልዕክቷን ለዓለም በማስተላለፍ ወደግፍ ድርጊቱ በማምራት ‹‹ይኸ ዓይነቱ ግፍ እንደነሒትለር በጎሳ የታወሩ በዘር አስተሳሰብ የሰከሩ አረመኔዎች ውጤት ነው፡፡ የዓለም ሕዝብ ከዚህ ዓይነቱ ሰቆቃ እጅግ ሊማር ይገባል፡፡ በምንም ዓይነት ጎሰኝነትን የሰው ፍጥረት ሊደግፍ ወደቤተሰቡ ወደመንደሩ ወደአገሩ ሊያስገባ አይገባም፡፡ የዘር ፖለቲካ እርጉም ነው ከኛ ተማሩ›› ትለናለች (ገፅ 159)፡፡

ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላና በመጠለያ በነበረችበት ወቅት ጭምር ኢማኩሊን ልቧን የሚያደማ ቅስሟን የሚሰብር ክስተት አለተለያትም፡፡ ብዙ ጊዜ በፀፀት የምታነሳቸው የ4 እና የ3 ዓመት ወንድማማች ህፃናት አንድ ቀን ወደመጠለያው ሰፈር እንደመጡና ታናሹ ታላቁን ለስላሳና ድንች እንዲሰጠው ሲያስቸግረው ታላቁ ህፃን በታላቅ ትህትናና ትዕግስት ከቤታቸው ስላልሆኑ እንዳያስቸግር ሲመክረው ማየቷን ገልፃ የነዚያ ህፃናት የወደፊት ሕይወት በሀዘንና በጥላቻ የተሟላ እንደሚሆን አብራርታ ጉስቁልና፣ መራራነትና ጥላቻ በነዚህ ልጆች ሥር ሰደው ሕይወታቸውም ምንም ተስፋ የሌለው እንዳይሆን ስጋቷን ታጋራናለች (ገፅ 169)፡፡

ኢማኩሊ እንዳለችውም ቅንነቱ ካለ ከሩዋንዳ ጭፍጨፋ ብዙ ትምህርት የምንቀስምበት ወቅት አሁን ነው፡፡ ያ የማይሆን ከሆነ በአሁኑ አያያዝ ኢትዮጵያ የሩዋንዳ ዕጣ ፈንታ ሊያጋጥማት ቢችልም እልቂቱ ግን ልክ እንደሩዋንዳ አንዱ አባራሪ ሌላው ተባራሪ፣ አንዱ ገዳይ ሌላው ተገዳይ ሆኖ የመንደር ናፋቂው የጎሳ ቡድን በሚፈልገው መልክ እንደማይጠናቀቅ አስረግጦ መናገር ይቻላል፡፡ ከዚያ ይልቅ የእርስ በርስ መተላለቅ ውስጥ ነው የምንገባው፡፡ እዚያም ቤት እሳት አለ የሚባለው ዓይነት ማለቴ ነው፡፡ ነገሩን ይበልጥ ግልፅ ለማድረግ ፈጣሪ አያድርገው እንጂ የብሔር  ግጭት እኛ ሀገር ቢከሰት መሣሪያ አንጋቢው የሁቱ አክራሪ ዘረኛ ቡድን መሣሪያ የለሹንና   ከሞት ለማምለጥ የሚባዝነውን የቱትሲ ተወላጅ ተዝናንቶ የሚጨፈጭፍበት ሁኔታ ይፈጠራል ማለት ዘበት ነው፡፡ ቱትሲዎች በግፍ ተጨፍጭፈው ያለቁት ያለመሣሪያ ባዶ እጃቸውን ስለነበሩ ነው፡፡ እኛ ጋር ግን…. 

በሩዋንዳ ተከስቶ የነበረው የዘር ፖለቲካ ጦስ በሕዝቡ ላይ ያሳደረውን የምሬት ጠባሳ በመጠኑ ከላይ አሳይቻለሁ፡፡ አሁን ላይ ካለው ወቅታዊና ተጨባጭ ያገራችን ሁኔታ ጋር ስናስተያየው ምቾት የሚሰጥ አይደለም፡፡ በዚህ ሁኔታም ጠ/ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ የሚዘምሩላት ኢትዮጵያ የት እንደምትገኝ ማወቅ ተስኖኛል፡፡ እርሳቸው ከሚዘምሩላት ኢትዮጵያ ይልቅ ገደል አፋፍ ላይ የቆመችና የኦሮሚያ የጦር አበጋዞች ሊውጧት ሊሰለቅጧት ወቅት የሚጠብቁላት ኢትዮጵያ ናት የምትታየኝ፡፡

ክብርት ከንቲባዋም ሆኑ ክቡር ከሚሽነሩ የአስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊዋ ጭምር መጋቢት 5 ቀን 2015 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ም/ቤት የመንግሥት ግልበጣን ወንጀል በብሔር ተምነው ያቀረቡልንም ለዚሁ የመዋጥ የመሰልቀጥ ፕሮጀክት በእርሾነት እንዲያገለግል ነው፡፡ በንግግር የተነኮሱት ብሔሮች በተለይም አማራው ለምን ተወነጀልን በሚል ቁጭት ወደግጭት እንዲገባ ለመገፋፋት በስሌት የተቀመረ የፖለቲካ ሴራ ነው የሚል ጥርጣሬ አለኝ፡፡ አትጠርጥር አልባልምና አዎን ጠርጥሬአለሁ፡፡ ስለዚህ በስልጣን ወንበሩና በስልጣኑ አካባቢ የምትገኙ መንደር ናፋቂ የጎሳ ፖለቲከኞች በብሄሮች መካከል ያለው የአንድነት የመተሳሰብና የፍቅር ገመድ ተበጥሶ ቡጢ ወደመሰናዘሩ ከተገባ መዘዙ ከሩዋንዳ የባሰ ነውና እባካችሁ ግጭት ጠሪ የጦርነት አዋጅ ነጋሪ ለሆነው አንደበታችሁ ልጓም አብጁለት፡፡

ለዛሬው እዚህ ላይ አበቃሁ፡፡ እስከሳምንት ቸር እንሰንብት!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይጠብቃት ይታደጋትም!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫ በሚያካሂድባቸው ቦታዎች ሁሉ እሳተፋለሁ

በዘንድሮው ሀገራዊ ምርጫ እንደሚሳተፍ ያስታወቀው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትህ...

በሲዳማ ክልል ከ62% በመቶ በላይ የሚታረሰው መሬት በአሲዳማነት የተጎዳ ነዉ

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ የሚታየው የምርታማነት ማነቆ በዋናነት የመሬት አሲዳማነት...

የኢትዮጵያ እዳ እና ሃብት አስተዳደር ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች ስብሰባ ሳይገኙ ቀሩ

የመንግስት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እዳ እና...

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት

የኢትዮጵያ እና ሕንድ የቆየ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት የአፍሪካ-ሕንድ...