‹‹በትግራይ ሽሬ ከከተማው ወጣ ብሎ የሚገኝ አንድ የወርቅ ገበያ አለ›› ሲል ዘኮንትኔንት መፅሄት ዘገባውን ጀምሯል፡፡ ይህ ገበያ እስከምሽቱ 3 ሰአት ድረስ እንደሚቆይና መደበኛ ባልሆነ መልክ ለገበያ የሚቀርበው ወርቅ ግብይት ቀኑን ሙሉ ሲፈፀም እንደሚውል አስረድቷል፡፡
ዘገባው ሲቀጥልም ‹‹እዚህ ቦታ በጥሬ ገንዘብ ወይንም በቼክ መክፈል ይቻላል፡፡ ዋናው በዋጋው ላይ መስማማት ብቻ ነው›› ብሏል፡፡ እንደዘገባው በወርቁ ዋጋ ላይ የተስማማ ገዢ የሚከፍለው ቀብድ ብቻ ነው፡፡ ቀሪውን ገንዘብ ወርቁ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር ከወጣ በኋላ የሚከፍል ይሆናል፡፡ ባለፈው ሚያዝያ ወር ወደዚህ የገበያ ቦታ መሄዱን የመፅሄቱ ዘጋቢ ገልጿል፡፡
በወቅቱ በሽሬው የወርቅ ገበያ አንድ ግራም ወርቅ 14 ሺህ ብር ወይንም 106 ዶላር ሲያወጣ ማየቱንም አስረድቷል፡፡ ይህ ዋጋ ደግሞ መንግስት ካስቀመጠው የወርቅ ዋጋ ተመን በ25 ፐርሰንት እንደሚበልጥ አስታውቋል፡፡
በወቅቱ በአለም ላይ የአንድ ግራም ወርቅ ዋጋ ከ100 እስከ 110 ዶላር እንደነበር የጠቀሰው ዘገባው የሽሬ የወርቅ ዋጋም በዚህ ላይ ተመስርቶ እንደሚወሰን አስታውቋል፡፡
በፊት ወታደር የነበረውና አሁን ማእድን በማውጣት ላይ የተሰማራው ከሊል የተባለው ወጣት ለመፅሄቱ እንደገለፀው የሽሬ የወርቅ ዋጋ በተለይ በዱባይ ገበያ ላይ ተመስርቶ የሚተመን ነው፡፡
‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ግለሰቦች ወይንም ድርጅቶች ፈቃድ አውጥተው በአገር ውስጥ የወርቅ ገበያ ላይ መሳተፍ ይችላሉ›› ያለው ዘገባው በውጭ የወርቅ ንግድ ላይ የመሰማራት ህጋዊ ስልጣን የተሰጠው ለብሄራዊ ባንክ ብቻ መሆኑን ጠቅሷል፡፡
በተባበሩት አረብ ኤመሬቶች ግን አሰራሩ የተለየ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ አንድ ሰው መጠኑ ከ60 ሺህ ድርሀም ወይንም 16 ሺህ ዶላር ያልበዛ ወርቅ ተሸክሞ መግባት እንደሚችልም አስታውቋል፡፡ ይህ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው የአሰራር ክፍተት በህገ ወጥ መንገድ የወርቅ ግብይቱ እንዲከናወን ማድረጉንም ገልጿል፡፡
በሽሬ ቀብድ የተከፈለበት ወርቅ ከኢትዮጵያ ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ወጥቶ የመጨረሻ መዳረሻው ዱባይ የሆነውም በዚህ የተነሳ እንደሆነ አስረድቷል፡፡ የአባት ስሙ እንዳይጠቀስ የገለፀው ከሊል ለመፅሄቱ እንደተናገረው ለ3 አመታት ከፌዴራል መንግስቱ ጋር በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ከተሳተፉት በሺህ የሚቆጠሩ የትግራይ መከላከያ ሀይል(ቲዲኤፍ) አባላት አንዱ ነው፡፡
ሲናገርም ‹‹ጦርነቱ ትግራይን ብቻም ሳይሆን የቀድሞ ኑሯችንንም አውድሟል፡፡ ወታደራዊ አመራሩም ለከፈልነው መስዋእትነት የሚሰጠን ምንም ነገር አልነበረም›› ካለ በኋላ የቀድሞ ተዋጊዎች 25 ሆነው በመደራጀት ወርቅ እንዲያወጡ እንደተፈቀደላቸው አስረድቷል፡፡ በባህላዊ መንገድ የሚያወጡትን ወርቅ በሽሬው ገበያ ላይ ለሽያጭ እንደሚያቀርቡትም አስረድቷል፡፡
ይህንን ስራ ስደተኞች፣ ተፈናቃዮችና የአካባቢው ወጣቶች ጭምር የተቀላቀሉት መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው ባለፈው አመት በተደረገ አንድ ጥናት በትግራይ ክልል ከ100 ሺ በላይ ባህላዊ ወርቅ አውጪዎች መኖራቸውን አስታውቋል፡፡ ካሊል ለመፅሄቱ እንዳስታወቀው አብዛኛውን የወርቅ ማውጫ የሚያስተዳድሩት የትግራይ ጄኔራሎች ናቸው፡፡
ከጦርነቱ በፊት የፌዴራል መንግስት በትግራይ ክልል ማእድን ለሚያወጡ ከ90 በላይ ለሚሆኑ ድርጅቶች ፈቃድ ሰጥቶ ነበር፡፡ የዛሬ ሁለት አመት ገደማ ከእነዚህ ውስጥ 27ቱ ስራ መጀመር ባለመቻላቸው ማእድን ሚኒስቴር ፈቃዳቸውን እንዲሰርዝ የክልሉ አስተዳደር መጠየቁን ዘገባው አውስቷል፡፡
ይሁንና በዚህ ወቅት አብዛኛውን የወርቅ ማውጫ የትግራይ ጄኔራሎችና የቀድሞ የቲዲኤፍ ታጣቂዎች ተቆጣጥረው እየሰሩበት እንደነበር አስረድቷል፡፡ የቲዲኤፍ ታጣቂ የነበረው ቴዎድሮስ ካህሳይ ለመፅሄቱ ሲናገር ‹‹ጄኔራሎቹ ትልልቅ የወርቅ ክምችት ያለባቸውን ቦታዎች ለራሳቸው ወስደው የተቀረውን ለበታች ወታደሮች ሰጥተዋል›› ብሏል፡፡
ቴዎድሮስ የአንድ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ጥበቃ ሰራተኛ በመሆኑ ወደእነዚህ ትልልቅ የወርቅ ማውጫዎች የመግባት ፈቃድ ያለው ነው፡፡ የመፅሄቱ ጋዜጠኞች በራህዋ፣ ሂፃትስ፣ ሜሊና ማቶ ቡላ ወደሚገኙት የወርቅ ማውጫዎች ለመግባት የጠየቁት ፈቃድ ውድቅ እንደተደረገባቸው ገልፀዋል፡፡
እነዚህ ትልልቅ ወርቅ ማውጫዎች በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰውም ወደአካባቢው መጠጋት ህይወትን ለአደጋ እንደሚዳርግ አስረድተዋል፡፡ ከእነዚህ የወርቅ ማወጫ ስፍራዎች አንዱ ባለቤትነቱ የካናዳው ኢስት አፍሪካ ሚኒራልስ ነበር፡፡
የድርጅቱ ሀላፊ እንዳስታወቁት የወርቅ ማውጫ ንግድ ፈቃዱን ያወጡት 70 ሚሊዮን ዶላር ትርፍ ለማግኘት አቅደው የነበረ ቢሆንም አሁን ወደስፍራው ከደረሱ አመታት ተቆጥረዋል፡፡ የተሰጣቸው ቦታም በህገ ወጥ መንገድ የወርቅ ማውጣት ስራው እየተከናወነበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የትግራይ ክልል ማእድን ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ፍስሀ መረሳ ሲናገሩ ደግሞ ‹‹ይህ በስፋት የሚታወቅ እውነት ነው፡፡ እንደኤክስካቫተር የመሳሰሉ ትልልቅ ማሽኖችን አስገብተው የወርቅ ማውጣቱን ቀጥለውበታል›› ብለዋል፡፡
የህወሀት ጄኔራሎች በዚህ መንገድ እያወጡት ያለውን ወርቅ በሽሬ ገበያ በኩል ለሽያጭ ካቀረቡ በኋላ ተመልሰው ሌላ ወርቅ የማውጣት ስራቸውን ይቀጥላሉ፡፡
ከሽሬ የተገዛው ወርቅ ደግሞ መዳረሻው ዩናይትድ አረብ ኤመሬትስ መሆኑን የጠቀሰው መፅሄቱ እንዲህ አይነት ድርጊት በበርካታ የአፍሪካ አገራትም እንደሚከናወን አስረድቷል፡፡ የወርቅ ገበያው የጣማቸው እነዚህ ጄኔራሎች ይዞታቸውን እያስፋፉ ነዋሪዎችን እስከማፈናቀል መድረሳቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡ የ37 አመቷ እናት ፅዮን ይህን በተመለከተ ምስክርቷን ሰጥታለች፡፡
በአስገደ ወረዳ ሂፃትስ ነዋሪ የሆነችው ይህች እናት ባለፈው አመት ታጣቂዎች መጥተው በውርስ የያዘችውን መሬት እንድትለቅ እንደነገሯት ገልፃለች፡፡ ስትናገርም ‹‹መሬቱን ማእድን ለማውጣት ስለምንፈልገው ለቀሽ ሂጂ አሉን፡፡
እኔም ፈቃደኛ አለመሆኔን ስገልፅላቸው እንድታሰር አደረጉ›› ብላለች፡፡ ከአንድ ሳምንት እስር በኋላ ስትፈታ መኖሪያ ቤቷና የእርሻ መሬቷ ፈርሶ ማእድን የማውጣት ስራ ሲከናወንበት ማግኘቷንም ለመፅሄቱ ገልፃለች፡፡ መፅሄቱ ዘገባውን የቋጨው የትግራይን ወርቅ ‹‹ሀቢቢ፣ ካም ቱ ዱባይ›› (Habibi, come to Dubai) በሚል ንኡስ አንቀፅ ነው፡፡
ሽሬ፣ ኢትዮጵያ። (ዘ-ሐበሻ ዜና)
