ጎሹ ሞገስ ( 1928-2018)
ግንቦት 28/ 2018 ዓ.ም ህይወታቸው ያለፈው አቶ ጎሹ ሞገስ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት የማይዘነጋ አሻራ ያኖሩ ናቸው። የእርሳቸውን ታሪክ ዕዝራ እጅጉ እንደሚከተለው ሰንዶታል።
የነፃ ፕሬሱ ታጋይ የአቶ ጎሹ ሞገስ አጭር የሕይወት ታሪክ
የጦቢያ መፅሔት መሥራች የነበሩት አቶ ጎሹ ሞገስ ከአባታቸው አቶ ሞገስ በለጠ ፣ ከእናታቸው ወ/ሮ ፈጠነች ምሕረቴ በ1928 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ ተወለዱ።
ዕድሜያቸው ለትምህርት እንደ ደረሰ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት ት/ቤት እስከ 12 ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሚማሩበት በዚህ ወቅት በቀለም ትምህርታቸውና በስፖርት ተሳትፏቸው ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤትና ትጋት ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ እጅ የወርቅ ተሸላሚ ለመሆን በቅተዋል።
አቶ ጎሹ በወጣትነት ዕድሜያቸው ከስፖርት በዘለለ ለቴአትር ልዩ ፍቅር በማሳደራቸው ቴአትር ይፅፉ ነበር። ከመፃፍ ባሻገርም የመተወን ልዩ ክህሎት እንደነበራቸው የ10 ዓመት ታናሽ ወንድማቸው አቶ ክብረ ሞገስ ይናገራሉ።
ያኔ ቴአትር ሲደርሱ ይህ ቴአትር አንተ የፃፍከው አይደለም። ሌላ ሰው የፃፈልህ ነው ይባሉም እንደነበር ወንድማቸው አቶ ክብረ ሞገስ ይናገራሉ።
አቶ ጎሹ ሞገስ በዚያ የወጣትነት ዕድሜያቸው ለፓርላማ ይወዳደር ለነበረ ለአንድ መምህር የምረጡት ዘመቻ ያደርጉ እንደነበር ታናሽ ወንድማቸው አቶ ክብረ ነግረውናል።
በ1947 ዓ.ም በደብረ ብርሃን መምህራን ኮሌጅ በዲፕሎማ ለመመረቅ የበቁት አቶ ጎሹ ሞገስ በሞዴል ት/ቤት በአስተማሪነትና በርዕሰ- መምህርነት ከማገልገላቸውም ባሻገር በ1953 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በዲግሪ ኘሮግራም ለመመረቅ በቅተዋል።
አቶ ጎሹ ሞገስ፣ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን በሚከታተሉበት በዚህ ወቅት የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ፕሬዝዳንት በመሆን የተመሰገና አገልግሎት አበርክተዋል።
ከዚህ በመቀጠል ከ1964 – 1967 ዓ.ም በወንጂ ስኳር ፋብሪካ ሥር በሚተዳደረው በወንጂ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት በአስተማሪነትና በርዕሰ መምህርነት ካገለገሉ በኋላ በ1968 ዓ.ም በማስታወቂያ ሚኒስቴር በሳንሱር ክፍልና በፕሬስ መምሪያ የሥራ ክፍሎች በኃላፊነት ሲሠሩ ቆይተዋል።
ከ1980 – 1983 በአገር ውስጥ ንግድ ሚኒስቴር በንግድ መምሪያ የሥራ ክፍል የኃላፊነት መደብም ሠርተዋል።
በተጨማሪም ከ1984 – 1996 ዓ.ም የጦቢያ ጋዜጣ አዘጋጅ ፤
ከ1996 – 1998 ዓ.ም የልሳነ ሕዝብ ‘ ጋዜጣና መፅሔት አዘጋጅ በመሆን አገልግለዋል።
አቶ ጎሹ ሞገሱ ነፃ ፕሬስ በአገራችን ከተፈቀደበት ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ጦቢያ ጋዜጣን የመሠረቱ ሲሆን ድርጅቱም እድገት እንዲያሳይ በህትመቶች ላይ በመፃፍ ጭምር የራሳቸውን ትልቅ አሻራ ማኖር ችለዋል።
በጊዜው በጦቢያ መፅሔት እና ጋዜጣ ላይ ከመንግሥት የሚደርስባቸውን ጫና በመቋቋም ህትመቶቹ እስከተቋረጡበት እስከ 1998 ድረስ ሰርተዋል። በመፅሔቷ ላይ የነበሩትንም’ አፍ ለአፍ’ እንዲሁም’ ‘ሙሻ ዘር’ የተሰኙ አምዶችን በማዘጋጀት ሙያዊ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል።
የሚድያ ባለሙያ አቶ ጎሹ ሞገስ ለነፃነት፣ ለፍትህ ፣ እንዲሁም ለዲሞክራሲ መስፈን የታገሉና ዋጋም የከፈሉ ታላቅ ባለውለታ ነበሩ። ከ5 ጊዜ በላይ በህወሓት የአገዛዝ ዘመን የታሠሩ ሲሆን እውነት በመናገር የሚያምኑ ታላቅ የነፃ ፕሬስ ታጋይ ነበሩ።
በቅርበት የሚያውቋቸው የህግ ባለሙያ አቶ ደርበው ተመስገን ስለ አቶ ጎሹ ሞገስ በሰጡት ምስክርነት እንዲህ ይላሉ”….. ጎሹን ሳንሱር ክፍል ከነበረበት ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ አውቀዋለሁ። ሥራውን ጥንቅቅ አድርጎ የሚሠራ ባለሙያ ነበር።
ላለፉት 50 ዓመታት ጎሹ ሞገስን ሳውቀው የሰዎችን መበደል የሚቃወም ፣አጥብቆም የሚታገል ወንድማችን ነበር። ልሳነ ህዝብ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል መኖሪያ ቤቱ ውስጥ ነበር። እናም ያኔም ቢሆን ለእስር ሲዳረግ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ነበር።” በማለት አቶ ደርበው ተመስገን ምስክርነት ሰጥተዋል።
አቶ ጎሹ ሞገስ የሰላ ብዕር የነበራቸው ባለሙያ የነበሩ ሲሆን ” ኦሪዮን “በሚል የብዕር ስማቸው ጦቢያ ጋዜጣ ላይ በሳል እና ሂሳዊ ፅሑፎችን ይፅፉ ነበር። ይህንን ልዩ የፅሑፍ ችሎታቸውንም ሁሉም ባልደረቦች በሙሉ አንደበት የሚመሠክሩት ጉዳይ ነው።
ታናሽ ወንድማቸው አቶ ክብረ ሲናገሩ ወንድሜ አገሩን በጣም የሚወድ ፣ ለአገሩ መሥራት እንዳለበትም ፅኑ እምነት ያሳደረ ባለሙያ ነው ሲሉ በሚያውቁት ልክ ምስክርነት ሰጥተዋል።
ልጃቸው አደይ ጎሹ ሞገስ ደግሞ የሀዘን ስሜቷን እንደምንም ተቋቁማ አባቷ ለአገሩ እና ለቤተሰቡ የሚኖር ሕይወትን በምክር ሳይሆን በተግባር በመኖር ያሳየ ሰው ነው ስትል ትገልፃቸዋለች።
“…አባቴ ለሁላችንም ቀና ሆኖ ትዳሩን አክብሮ፣ ሙያውን ከልብ ወዶ ፣ በመንፈሳዊ ሕይወቱም ጠንክሮ የኖረ መልካም አባት ነበር ” ስትል ትዝታዋን አውግታለች።
አቶ ጎሹ ሞገስ፣ በ1999 ዓ.ም ከሥራ ዓለም በጡረታ እስከተገለሉበት ጊዜ ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ አገራቸውንና ሕዝባቸውን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገላቸው በቅርበት በሚያውቋቸው ሰዎች ዘንድም የተመሰከረ ጉዳይ ነው።
አቶ ጎሹ ሞገስ የሁለት ወንዶችና የሁለት ሴት ልጆች አባት ነበሩ። የአቶ ጎሹ ሞገስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ግንቦት 28 2018 ዓ.ም በሳህሊተ ምህረት ቤተ ክርስቲያን ተፈፅሟል።
ይህ ዜና በተወዳጅ ሚድያ እና ኮምዩኒኬሽን የተዘጋጀ ነው። ድርጅቱ የሚድያ ባለሙያዎችን የሙያና የሕይወት ታሪክ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል። እስከዛሬ የ400 ሰዎችን ታሪክ ሰንዶ ያስቀመጠ ሲሆን ወደፊትም የስነዳው ተግባር ተጠናክሮ ይቀጥላል።
