‹‹የንግዱን ማኅበረሰብ ተግዳሮቶች ለመንግሥት ማሳየት እንፈልጋለን›› ሃይማኖት ጥበቡ

Date:

ሃይማኖት ጥበቡ ይባላሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር መድረክ የፓን አፍሪካ የንግድ ኢንዱስትሪ ም/ቤት አስተባባሪ ናቸው፡፡ በቅርቡ የሚካሔደው የመንግሥት እና የንግዱ ዘርፍ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ምን ይዘት ይኖረዋል? በዚህ ፕሮግራም የሚጋበዙ አካላትስ በየትኛው ዘርፍ የተሠማሩ ናቸው? ስንል የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ እነኾ!

በፕሮግራሙ ላይ ያለዎትን ኃላፊነት ቢገልጹልን?

ሃይማኖት፡- የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሀገራዊ ምክክር መድረክ ፕሮጀክት የፓን አፍሪካ የንግድ ኢንዱስትሪ ም/ቤትን በመወከል አስተባባሪ ነኝ፡፡ ፓን አፍሪካ ከመጀመሪያ ጀምሮ ይህ ፕሮግራም እንዲካሄድ ሲሠራ ነበር፡፡ በተለይ የግሉ ዘርፍን ለማገዝ ከኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር በመኾን እያንዳንዱን የፋይናስና ቴክኒክ ድጋፍ ያደርጋል፡ ስለዚህ በየቀኑ የምንሠራው ሥራ የኢትዮጵያን ንግድና ዘርፍ ማኅበራትን ማገዝ ነው፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ ሐምሌ 18 እና 19 ቀን 2023 የሚካሄደው ፕሮግራም ምንድነው?

ሃይማኖት፡- በዕለቱ የሚካሄደው የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ሀገራዊ የምክክር መድረክ ነው፡፡ የምክክር መድረኩ የሚካሄደው በንግዱ ማኅበረሰብና በመንግሥት በኩል ነው፡፡ የሚካሄደበት ቦታም ስካይ ላይት ሆቴል ነው፡፡ በመድረኩ ላይ ከመንግሥት በኩል ይሳተፋሉ ተብሎ የሚገመቱት በርካታ አካላት ናቸው፡፡ በተለይ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ በቱሪዝም ዘርፍና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ይገኛሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ በእነዚህ በሦስቱ ፖሊሲ አውጪዎችና አስፈፃሚዎች ዙሪያ ያሉ የመንግሥት አካላት ይሳተፋሉ፡፡ በንግድ ማኅበረሰቡ በኩል ደግሞ በዘርፉ ተሠማርተው እየሠሩ ያሉ አካላትን ያካትታል፡፡ በተጨማሪም በዚህ ሙያ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎችም ጭምር እንዲገኙ ይደረጋል፡፡

ይህ ፕሮግራም ለስንተኛ ጊዜ የተዘጋጀ ነው?

ሃይማኖት፡- ይህኛው ፕሮግራም ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት እንዳገኘነው መረጃ ለ4ተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡

ከዚህ በኋላ በቋሚነት ለማዘጋጀት የወጡ ፕሮግራሞች አሉ?

ሃይማኖት፡- አዎ አሉ፡፡ በእኛ በኩል ይህ የምክክር መድረክ በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ለማሻሻል መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተቀራርቦ ለመሥራት የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው፡ በመኾኑም በቋሚነት መንግሥትም በእቅዱ ውስጥ አስገብቶ እንዲሠራበት በየዓመቱ እንዲካሄድ ታስቦ እየተሠራ ነው፡፡

በዚህ ፕሮግራም የሚጋበዙ አካላት በየትኛው ዘርፍ የተሠማሩ ናቸው?

ሃይማኖት፡- የመድረኩ ታዳሚዎች ተብለው የተለዩ በቱሪዝም፣ በአግሮ ኢንዱስትሪ፣ በሆቴልና ቱሪዝም ላይ የተሠማሩት ናቸው፡፡ ምክንያቱም እነዚህን አካላት በፕሮግራሙ አሳትፎ የፖሊሲ ወይም የአሠራር ችግር ካለ ሊጠቁሙ ይችላሉ፡፡ የመንግሥትን ፖሊሲ አጠቃላይ ተግዳሮት ሂደቱም የሚያሳዩት እነርሱ ናቸው፡፡

እነዚህ ሦስት ዘርፎች ተጋባዥ የኾኑበት ዋና ምክንያት ምንድነው?

ሃይማኖት፡- በመጀመሪያ እነዚህን ዘርፎች ለመምረጥ ጥቅምት ወር ላይ የምክክር መድረክ አካሂደናል፡፡ እያንዳንዱን ቻምበር ክልሎችንም ጨምሮ በዚህ ዓመት የሚካሄደው የምክክር መድረክ በየትኞቹ ዘርፎች ላይ የበለጠ ቅድሚያ መስጠት ይገባል በሚለው ላይ አንድ የምክክር መድረክ አካሂደናል፡፡ ስለዚህ ከየክልሉ የመጡ የቻምበር ኃላፊዎች በየክልላቸው ያለውን ችግር ለማቅረብ ሞክረዋል፡፡ እነዚህ ነገሮች ካደረግን በኋላ ብዙ ነገሮች ተዘርዝረው ወስነናል፡፡ በተመሳሳይ ሌላው እነርሱን ለመምረጥ ምክንያታችን በመንግሥት ትኩረት ከተሠጣቸው እና ለኢኮኖሚው እድገት ካላቸው ሚና እንዲሁም ከኤክስፖርት አንጻር ያላቸውን አስተዋጽኦ ምክንያት በማድረግ ውይይት አድርገን ልንመርጣቸው ችለናል፡፡ በመንግሥት በኩልም የትኩረት አቅጣጫ መኾናቸውን ስላወቅን እነዚህ ሦስቱን መርጠናቸዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ውጨም ያሉ ተቋማትን ጋብዛችኋል?

ሃይማኖት፡- አዎ፡፡ አብዛኞቹ መቀመጫቸው አዲስ አበባ ቢኾንም ለምሳሌ ጎጃም ቡሬ ካለው ከቲላቫ የዘይት ፋብሪካ ጋር ተነጋግረናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከሌሎች አግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ጋርም ተወያተናል፡፡

ይህን ጥናታዊ ጽሑፍ ለማዘጋጀት ምን ያህል ጊዜ ፈጀ?

ሃይማኖት፡- አራት ወራትን ጨርሷል፡፡

ጥናቱ የዳሰሰው የግል ሴክተሩን ብቻ ነው?

ሃይማኖት፡- ጥናቱ ትኩረት ያደረገው የግል ሴክተር ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ዋናው ዓላማ በግሉ ዘርፍ በኩል ያሉ ተግዳሮቶች ምንድናቸው የሚለውን መለየት ነው፡፡ የጥናቱ ውጤትም ሁለት ሦስት ግዜ ተገምግሟል፡፡ ይሄ ቢጨመር ይሄ ቢቀነስ ተብሎ አስተያየት ተሰጥቶበት ነው ወደ ሥራ የተገባው፡፡

ለውይይት በቀረቡ ሐሳቦች ላይ የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲደረግባቸው የእናንተ ጥረት እስከምን ድረስ ነው?

ሃይማኖት፡- የመጀመሪያው ነገር የንግዱን ማኅበረሰብ ተግዳሮቶች ለመንግሥት ማሳየት እንፈልጋለን፡፡ ይሄ ማለት መንግሥት ችግሩን አያውቀውም ማለት ሳይኾን ትኩረት እንዲሠጠው ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ጉዞ የምክክር መድረኩን አዘጋጅቶ መሄድ ብቻ አይደለም፡፡ የስብሰባው መጨረሻ ቀን ከመንግሥት የሚሰጡ አቅጣጫዎች ይኖራሉ፡፡ ይህን ተከትሎም የጋራ ኮሜቴ ይቋቋማል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህን በየጊዜው እየተከታተልን ከመንግሥትና ከግል ሴክተሩ የተዋጣ አስፈፃሚ ኮሜቴውን እናያለን፡፡ ችግሮችን በየደረጃው እየለየን እንሄዳለን፡፡ አንዳንዶቹ ችግሮች ከገቢዎች ጋር የተያያዙ ከኾኑ ወደ ገቢዎች ሚኒስቴር መሄድ ይችላል፡፡ ሌሎች ችግሮችን ደግሞ ከታችኛው አስፈፃሚ አካል ከኾን እዚያው ይታያሉ፡፡ ስለዚህ እንደ የችግሮቹ ደረጃ እንዲታዩ በጋራ ኾነን በየሦስት ሁለት ወሩ እናያቸዋለን፡፡ የጋራ ኮሚቴ ኖሮ ሁሉንም ጉዳይ ይከታተላል፡፡

የአሁኑ የምክክር መድረክ ውጤታማነት በምን ያህል ጊዜ ታይቶ ሪፖርት ይደረጋል?

ሃይማኖት፡- አንዳንድ ችግሮች የዚያኑ ዕለት ሊፈቱ ይችላሉ፡፡ የበላይ አመራሮች ከሚያስቀምጧቸው አቅጣጫዎች ጋር ተያይዞ የሚፈቱ ይኾናል፡፡ ሌሎች ደግሞ በሦስትና ሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የሚሻሻሉ ሊኖሩ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ አምስት ዓመት ሦስት ዓመት ሊወስዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ በአጭር በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ችግሮቹን ለመፍታት ይጣራል ብለን እናምናለን፡፡

አንዳንዴ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ውይይት ከተደረገ በኋላ ተድበስብሰው የመቅረት ነገር ያታያል፤ እናንተ ለማስጨረስ እስከዳር ድረስ ትሄዳላቹ?

ሃይማኖት፡- የግሉ ዘርፍ ተወካይ የኾነው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንደሚታወቀው የተለያዩ ጉዳዮችን ይዞ ከመንግሥት ጋር ያሠራል፡፡ ከዚህ አካል ጋር እኛም እንደ ፓንአፍሪካ ቻምበር የሚያስፈልጉ ቴክኒካዊ ጉዳዮች እየረዳን እስከመጨረሻው ለመሄድ እንሞክራለን፡፡ ከዚህ በፊትም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን የመጨረስ ልምድ ስላለን እንገፋበታለን፡፡ ተማክሮ ለማለፍም የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር ይሞክራል ፤ በእነርሱ በኩልም ከፕሬዝዳንቱ ጀምሮ ሁሉም አካል ሥራውን ከጀመርን አንስቶ የተቻላቸውን ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ ከመስከረም ጀምሮ እስካሁን ድረስ የተለያዩ መድኮችን አዘጋጅተናል፡፡ ብዙ ለውጦችም አምጥተናል አሁንም አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡ በመንግሥት በኩልም ይኼ የሚደገፍ ነው፡፡

እንዲህ ዐይነት መድረኮችን በክልል ከተሞች ደረጃ ለማዘጋጀት የታቀደ ነገር አለ?

ሃይማኖት፡-  የአሁኑ የሀገር አቀፍ መድረክ ነው፡፡ ከአሁን በፊት የተደረገውም አዲስ አበባ ነው፡፡ ክልሎችም በክልል ደረጃ የሚደረጉ የምክክር መድረኮች ይካሄዳሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አማራ ክልል የነጋዴ ሴቶች የምክክር መድረክ ተካሄዷል፡፡ በተለይ በቱሪዝም ላይ ሲኾን ዘርፉን ለማነቃቃት ከከተማ ወጣ ተብሎ እንዲደረግ ታስቧል፡፡ የተለያዩ የቱሪዝም መዳረሻዎችንም ለማስፋፋት መድረኩ ከአዲስ አበባ ውጪ መደረጉ እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡

ይህ ፕሮግራማችሁ ተደራሽ እንዲኾን ከሚዲያ አጠቃቀም አንፃር ምን ለመሥራት አስባችኋል?

ሃይማኖት፡- የምክክር መድረኩ ከመካሄዱ አንድ ሳምንት ቀድሞ ጋዜጣዊ መግለጫ ይሰጣል፡፡ በዚህም የግልም የመንግሥትም የሀገር ውስጥ ሚዲያዎች ይጋበዛሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ለሚዲያ ክፍት መድረኮች ይዘጋጃሉ፡፡

ማስተላለፍ የምትፈልጊው መልዕክት ካለ?

ሃይማኖት፡- ዋናው መልዕክቴ በተለይ የግሉ ዘርፍ እንዲህ ዐይነት አጋጣሚዎችን አሟጦ መጠቀም ይኖርበታል የሚል ነው፡፡ መንግሥት በመድረኩ የተነሱ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ትኩረት በመሥጠት መፍትሔ ያበጅላቸው ዘንድ እንጠይቃለን፡፡   

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...