በኤስድሶስ ኮንስትራክሽን ንግድና ኢንዱስትሪ ማህበር ስር የሚገኘው የአቡነ ጎርጎርዮስ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ ዓመታዊ የትምህርት አውደ ርዕይ እና የኪነ-ጥበባዊ ተግባራት ማካሄድ መጀመሩን አስታውቋል።
ተቋሙ በመሪ ቅርንጫፍ ትምህርት ቤቱ እያከናወነ የሚገኘውን ይህንን መርሃ ግብር አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ አውደ ርዕዩ ከመጋቢት 25 እስከ መጋቢት 26 ቀን 2018 ዓ.ም. ድረስ ለሁለት ተከታታይ ቀናት እንደሚቆይ ተገልጾአል።
የትምህርት ቤቱ ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ አለሙ ወልዴ ትምህርት ቤቱ በመንግስት የተቀመጠውን የትምህርት ብቃት መስፈርት በከፍተኛ ደረጃ አሟልቶ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት በሁሉም ቅርንጫፎቹ ከ25 ሺህ በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ እያስተማረ ይገኛል ብለዋል፡፡
ከ2 ሺህ ለሚበልጡ መምህራን የሥራ ዕድል የፈጠረው የአቡነ ጎርጎርዮስ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው የቀሰሙትን የንድፈ ሀሳብ ትምህርት ከሀገር በቀል ዕውቀት ጋር በማጣመር፣ የማኅበረሰቡን ችግር ፈቺ የሆኑ የፈጠራ ሥራዎችን እንዲያቀርቡ ዕድል እንደፈጠረ አቶ ዓለሙ ገልጸዋል።
በዚህም መሠረት 16 ተማሪዎች በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በሥነ-ስዕል እና በቅርጻ ቅርጽ ዘርፎች ያዘጋጇቸውን የፈጠራ ሥራዎች ለአውደ ርዕዩ አቅርበዋል። ተቋሙ የመማር ማስተማር ሂደቱን ይበልጥ ለማሳለጥ ዘመኑ የሚጠይቀውን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ የቤተ-ሙከራ እና የቤተ-መጻሕፍት ቁሳቁሶችን ማሟላቱን አስታውቋል።
ትምህርት ቤቱን ከሌሎች ተቋማት ለየት የሚያደርገው የግዕዝ ቋንቋ እና የሥነ-ምግባር ትምህርትን በጥራት መስጠቱ መሆኑን ምክትል ሥራ አስፈፃሚው አብራርተዋል። በዚህም ተማሪዎቻቸው በሥነ-ምግባር የታነጹና የግዕዝ ቋንቋን የማዳመጥ፣ የመናገር፣ የማንበብ እንዲሁም የመጻፍ ክህሎት እንዲያዳብሩ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
