የአባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት ረድኤት እና ምልጃ አይለየን

Date:

ታኅሣሥ 24 ቀን 1212 ዓ.ም ከካህኑ አባታቸው ጸጋ ዘአብና ከእናታቸው ከቅድስት እግዚእ ኃረያ በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድና በሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል ብሥራት ተወለዱ፡፡ 

ወላጆቻቸውም ፍሥሐ ጽዮን ብለው ሰየሟቸው፡፡ በተወለዱ በሦስተኛው ቀን ከእናታቸው ዕቅፍ ወርደው “አሐዱ አብ ቅዱስ አሐዱ ወልድ ቅዱስ አሐዱ ውእቱ መንፈስ ቅዱስ” በማለት ሥላሴን አመስግነዋል፡፡

በተወለዱ በ15 ዓመታቸው መዓርገ ዲቊናን፣ በ22 ዓመታቸው ደግሞ መዓርገ ቅስናን ከግብጻዊው ጳጳስ አባ ቄርሎስ ተቀብለዋል፡፡ በአንድ ወቅት ሕፃኑ ፍሥሐ ጽዮን ወደ ጫካ ለአደን በሔዱበት ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጦ ጸጋ መንፈስ ቅዱን አሳደረባቸው፡፡ ለሐዋርያዊ አገልግሎት ወንጌል ወዳልተዳረሰበት ቦታ እንደሚልካቸውም አስረዳቸው፡፡ 

ቅዱስ ሚካኤልም ከአዳኝነት ሰውን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመመለስ እንደተመረጡ፣ ስማቸውም ተክለ ሃይማኖት እንደሚባል፣ ትርጓሜውም ተክለ አብ፣ ተክለ ወልድ፣ ተክለ መንፈስ ቅዱስ ማለት እንደሆነ አበሠራቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ያላቸውን ንብረት ዅሉ ለቤተ ክርስቲያንና ለነዳያን ሰጥተው “አቤቱ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! የመንግሥተ ሰማያትን በር ትከፍትልኝ ዘንድ እነሆ ቤቴን እንደ ተከፈተ ተውኹልህ” በማለት ቤታቸውን ትተው ወንጌልን ለማስተማር ፈጥነው ወጡ፡፡

በደብረ ዳሞ ገዳምም ለ12 ዓመታት ተቀምጠው ከዚያ ሲወርዱ ገመዱ ገመዱ ሲበጠስ ስድስት ክንፍ አውጥተው በረዋል፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምረው በመላው ኢትዮጵያ እየተዘዋወሩ ወንጌልን በመስበክና ተአምራትን በማድረግ በርካታ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር፤ ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መልሰዋል፡፡ አብያተ ክርስቲያናትንም አሳንጸዋል፡፡

ከዚህ በኋላ በደብረ ሊባኖስ ገዳመ አስቦ ዋሻ በመግባትም በዙሪያቸው ስምንት ጦሮችን ተክለው እጆቻቸውን በትእምርተ መስቀል በመዘርጋት የክርስቶስን ሕማም፣ ሞትና ነገረ መስቀል በማሰብ በተመስጦ ለ22 ሌሊትና ቀን ያለ ማቋረጥ በጾምና በጸሎት ተወስነው ሲጋደሉ፤ ከመቆም ብዛት የአንድ እግራቸው አገዳ ተሰብራል፡፡

ደቀ መዛሙርቱም የመንፈሳዊ አባታቸውን የዐፅም ስባሪ አክብረው አኑረውታል፡፡ እግራቸው ከተሰበረ በኋላም ለሰባት ዓመታት በአንድ እግራቸው ቆመው ሌሊትና ቀን ጸንተው ለሰው ዘር ሁሉ ድኅነትን ሲለምኑ ጥቂት ውኃ እንኳ የቀመሱት በአራተኛው ዓመት ብቻ እንደ ነበረ መጽሐፈ ገድላቸው ይናገራል፡፡

ጻድቁ አባታችን ምድራዊ ሕይወታቸውን በተጋድሎና በሐዋርያዊ አገልግሎት ከፈጸሙ በኋላ ከዚህ ዓለም ድካም የሚያርፉበት ቀን ሲቃረበ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከቅዱሳን መላእክት፣ ከወዳጆቹ ጋር መጣ፡፡

በስማቸው መታሰቢያ ለሚያደርጉ፣ ለነዳያን ለሚመጸዉቱ ቤተ ክርስቲያን ለሚያሠሩ የምሕረት ቃል ኪዳን ሰጥቷቸው፣ ስለ ተጋድሏቸው ጽናትም “በሰው እጅ የማይለካውን ይህንን የመንግሥት አዳራሽ ውሰድ” በማለት የጸጋ ልብስ አልብሷቸው፤ በመስቀል ምልክት ያጌጡ ሰባት የሕይወት አክሊላትንም አቀዳጅቷቸው በክብር በምስጋና ወደ ሰማይ ዐረገ፡፡

አቡነ ተክለ ሃይማኖትም የመንፈስ ልጆቻቸውን ጠርተው ጌታችን የነገራቸውን ዅሉ አስረድተው አባታዊ ምክርና ተግሣፅ ከሰጧቸው በኋላ ነሐሴ 24 ቀን በዘጠና ዘጠኝ ዓመታቸው ከዚህ ዓለም ድካም ዐርፈዋል፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውም በማኅሌት፣ በዝማሬና በምስጋና ቀብረዋቸዋል፡፡

ጌታችንም ነፍሳቸውንም በክብር ተቀብሏታል፡፡ የጻድቁን ቃል ኪዳን ያመኑ ገዳማውያን እንደሳቸው ዓለምን ንቀው በተጋድሎ ይኖራሉ፡፡ ገዳማቸውን እየደገፍን በዓታቸውን እያጸናን ከበረከታቸው እንካፈል፡፡
 

ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ  ማር  ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት  ገዳም

ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ 1000442598391 ወይም

አቢሲኒያ ባንክ 141029444

ለበለጠ መረጃ:- 09 38 64 44 44/0918077957
 

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አዲስ አበባ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ...

የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የ5 በመቶ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ክፍያን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና...

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ለኢራን ህዝብ – “እኛ ከእናንተ ጋር ነን”

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ፥ የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ...

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና...