‹‹የአባቴ ታሪክ እንደታሪክ እንዳይወጣ የተደረገው በመንግሥት ነው›› አታመንታ ጽጌ ዲቡ

Date:

‹‹እስከ 1980 አባቴ ከሠራቸው ተቋማት ውጪ ተቋም አልተመሠረተም››

‹‹የኾነውን ሁሉ በጸጋ ተቀበሉ እየተባልን ነው ያደግነው››

‹‹በሀገራችን ተጠያቂነት እና ይቅርታ የለም››

የመጽሔታችን የዛሬ እንግዳ አታመንታ ጽጌ ዲቡ ይባላሉ፡፡ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የፖሊስ ሰራዊት አዛዥ የነበሩት የብርጋዴር ጀነራል ጽጌ ዲቡ ልጅ ናቸው፡፡ በቅርቡም ከ27 ዓመታት በላይ የለፉበትን እና ለረዥም ዓመታት ተዳፍኖ እንዲቀር ተደርጎ የነበረውን የአባታቸውን ታሪክ የሚያወሳ መጽሐፍ ‹‹የጠዋቱ ጤዛ›› በሚል ርዕስ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ አባታቸው ጀነራል ጽጌ ድኅረ ፋሽስት ኢጣሊያ እንደ አዲስ ዳግም በቆመችው ኢትዮጵያ ተቋማትን ከማደራጀት አንስቶ እስከማዘመን ድረስ የነበራቸው ሚና ገዝፎ የሚነሳ ቢኾንም፣ በተለምዶ ‹‹የታኅሣሱ ግርግር›› ተብሎ በሚታወቀው የ1953 ሥዒረ መንግሥት ሙከራ በነበራቸው ተሳትፎ ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ ይኽንን ተከትሎም ሥራዎቻቸውና ታሪካቸው ተዳፍኖ እንዲቀር በወቅቱ በነበረው መንግሥት ብዙ እመቃ ስለተፈጸመባቸው ከዚያ በኋላ በመጡት ተከታታይ ትውልዶች ዘንድ ከ17 ዓመት ዕድሜያው አንስቶ ለሀገራቸው እና ለወገናቸው የፈጸሟቸው ተጋድሎዎች እና እንደ ፀሐይ የሚያበሩ ሥራዎቻቸው በሚገባው መጠን ሳይታወቁ ቀርተዋል፡፡ እንግዳችን ልጃቸው አታመንታ ጽጌም በዚህ ቁጭት ለረዥም ዓመታት ወጥተውና ወርደው ይኽንን የአባታቸውን ብቻ ሳይኾን የኢትዮጵያንም ታሪክ ‹‹ያሳያል›› ያሉትን መጽሐፍ ለንባብ አብቅተዋል፡፡ የግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅተመወርቅም በአባታቸው እና በቤተሰባዊ ታሪካቸው፣ ብሎም በመጽሐፋቸው ዙርያ የሚከተለውን ሰፋ ያለ ቆይታ ከእርሳቸው ጋር አድርጓል፡፡ እነኾ!    

ግዮን፡- የመጽሔታችን እንግዳ በመኾንዎ እያመሰገንን ራስዎንና የጀነራል ጽጌ ዲቡ ቤተሰቦችን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?

አታመንታ፡- አታመንታ ጽጌ እባላለሁ፡፡ እኛ የጄነራል ጽጌ ዲቡ ቤተሰቦች ብዛታችን ስድስት ሲኾን አሁን በሕይወት የቀረንው አራት ነን፡፡ እናታችን ወ/ሮ ከበቡሽ ተስፋዬ፣ ትልቁ ወንድማችን ቴዎድሮስ ጽጌና ተከታይዋ እህታችን ወ/ት ባዩሽ ጽጌ አርፈዋል፡፡ እቴነሽ ጽጌ፣ ራሔል ጽጌ፣ እኔና ትንሿ እህታችን ሶፊያ ጽጌ በሕይወት አለን፡፡ እኔ አሜሪካን ሀገር ነው የምኖረው፡፡ በታኅሣሱ ግርግር ጊዜ በጣም ትንሽ ልጅ ነበርኩ፡፡ በወቅቱ እድሜዬ ሁለት ወይ ሦስት ቢኾን ነው፡፡ ግርግሩ በተፈጸመበት ወቅት እህቶቼ ተማሪዎች ሲኾኑ እኔና ትንሿ እህቴ ደግሞ ሕጻናት ነበርን፡፡ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ቤተሰባችን ላይ ያልተጠበቀ ትልቅና አስከፊ አደጋ ተደቀነ፡፡ ያም ካለፈ በኋላ እኔም ከዓመት በኋላ ናዝሬት ትምህርት ቤት ገባሁ፡፡ በወቅቱ ከእርሱ ውጪ የተሻለ ትምህርት ቤት አልነበረም፡፡ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤትም ከሁለተኛ ክፍል ነበር የሚጀመረው፡፡ እኔ ግን ሁለተኛ ክፍል ከመድረሴ በፊት ትንሽ የልጅ ኃይለኛ ስለሆንኩ ያለጊዜዬ ወደ ቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት እንድዛወር ተደረገ፡፡ እዚያ ገብቼም ቤተሰባችን ላይ በደረሰው ችግር ምክንያት በተለያዩ ነገሮች ዙሪያ የነበረዉ ሁኔታ አስቸጋሪ ነበር፡፡  

በዚህም ምክንያት በትምህርት ቤቱ በተለይ በልጅነቴ የነበረኝ ቆይታ ጥሩ የሚባል አልነበረም፡፡ የኾኖ ኾኖ እኔና እንዲሁም ትንሽዋ እህታችን 12ኛ ክፍል ጨርሰን በፈረንጆች 1977 ዓ.ም ተመረቅን፡፡ ይህ ከመኾኑ በፊት ግን እኔ ለትንሽ ጊዜ የ‹‹እድገት በሕብረት›› ዘመቻ አዲግራት ሄጄ ነበር፡፡ ትንሿ እህቴ ባለመዝመቷ ሁለታችንም በተመሳሳይ ዓመት ልንመረቅ ችለናል፡፡ ይህ ከኾነ በኋላ ደግሞ እኔና እህቴ ሶፊያ ጽጌ ወንድማችን ለሥራ ሲመደብ ከእሱ ጋር ወደ ግሪክ አቀናን፡፡ እዚያም ለአንድ ዓመት ከሰባት ወር ተቀመጥን፡፡ ምክንያቱም የትምህርት ማመልከቻውን እና መሟላት የነበረባቸዉ መሥፈርቶቹ አስቸጋሪዎች ነበሩ፡፡ እህቶቼ ግን ቀደም ብለው አሜሪካን ሀገር መጥተው ስለነበር እነርሱ ብዙ ሂደቶችን ጨራርሰውልን በተማሪ ቪዛ ከግሪክ ወደ አሜሪካን ሀገር ገባን፡፡ ከዚያም ቨርጂኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ገባን፡፡ እህቴም እዚያው ተመረቀች፤ እኔም እንደእርሷ እዚያው ዩኒቨርሲቲ ነበርኩ፡፡ ሥራዬም እዚያው ነበር፡፡ በኋላ ግን ከዚያ ወጥቼ አሌክሳንድሪያ አካባቢ መኖር ጀመርኩኝ፡፡ የተለያዩ ኮርሶችንም እከታተል ነበር፡፡ በወቅቱ ትልቅ ችግር የነበረው የኑሮ ፈቃድ አለማግኘታችን ነበር፡፡ አብዛኛው ሰው ከሄደ በኋላ የሚያደርገው ሥራ አግኝቶና ጥገኝነት አመልክቶ መኖር ነው፡፡ እኛ ግን ጥገኝነት ባለመጠየቃችን መኖሪያ ፈቃድ አልነበረንም ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ያለምንም መኖሪያ ፍቃድ ለ15 ዓመታት ሁሉን ችለን ኖረናል፡፡ እኔም ከነበርኩበት በመውጣት ወደ አገልግሎት ክፍል እና ድርጅቶች ገባሁ፡፡ አሁንም ድረስ የምሠራው በሱፐር ቫይዘርነት ነው፡፡

ግዮን፡- የት ስቴት ነበር የሚኖሩት?

አታመንታ፡- የምኖረው አሁንም ድረስ አሌክሳንድሪያ ቨርጂኒያ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜ ከዚህ ቦታ ውጭ የትም ኖሬ አላውቅም፡፡ ይህ የምኖርበት ስቴት የዋሽንግተን ዲሲ አጎራባችና የተያያዙ በመኾናቸው ሁለቱ ከተሞች ሜሪላንድን ጨምሮ ‹‹ዲሲ ሜትሮፖሊታን ሲቲ›› ይባላሉ፡፡ 

ግዮን፡-  አሜሪካን ከገቡ በኋላ ትዳር ያዙ? በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነበር የሚኖሩት?

አታመንታ፡- በፈረንጆቹ 2006 ላይ ከባለቤቴ ከወ/ሮ ቅድስት ሱራፌል ጋር ትዳር መሠረትን፡፡ ከተጋባን ጀምሮ ኑሯችን እዚሁ አካባቢ ነው፡፡ የጋብቻ ሂደታችን ላይም ከፍ ያለ ችግር በእርግዝናዋ ላይ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ችግሩን አብዛኛው ሰው ያውቀዋል፡፡ እርሷም ከሞት ነበር የተረፈችው፡፡ ችግሩ የተፈጠረው በሰርጉ ማግስት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም ልጅ አልወለድንም፡፡

ግዮን፡- አሜሪካን ሀገር ከሚኖሩ የዲያስፖራ ማኅበራት ጋር በምን ዙሪያ ይሳተፋሉ? ያለዎት ማኅበራዊ ግንኙነትስ ምን ይመስላል?

አታመንታ፡- ብዙ ነገሮች ውስጥ ተሳተፌአለሁ ብዬ እገምታለሁ፡፡ በጊዜዉ በኢትዮጵያ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ማናቸውም ጉዳዮች ላይ ከፖለቲካው ቡድን መሪዎች ዉጭ በአብዛኛዉ ከራስ ዉጭ ሕዝቡ የጠለቀ የመረዳት እድል የለውም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በተለይ በዚያ ሀገር የተወለዱና የሚኖሩ ሰዎች አብዛኛውን ግዜ ግለኝነትና ራስን ማስቀደም ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ይህን ሳይ እኔ ደግሞ ከኖርኩበትና ከማውቀው ሀገሬ ጋር በማስተያየት በጣም አዘንኩኝ፡፡ በዚህም ዝም ብየ ሳልቀመጥ የማውቃቸውንና በዙሪያዬ ያሉትን አሰባሰብኩ፡፡ ወደፊት ለመጻፍ ያሰብኩትን ለመጽሐፌ የማሰባስበውን መረጃም አሳየኋቸው፡፡ አንዳንድ ነገሮችንም ጋበዝኳቸው፡፡ ጎን ለጎንም ታሪካቸውንና ሀገራቸውን እንዲያውቁ ለማድረግ ሞከርኩ፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ አየር ጥሩ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በወቅቱ ኢትዮጵያ ላይ የፖለቲካ ትግሉ ተጧጡፎ ነበር፡፡ የኤርትራ፣ የትግራይ፣ የሶማሌና መሰል ነጻ አውጪዎች ከወዲያ ወዲሀ የሚራወጡበት ወቅት ነበር፡፡ በወቅቱ ጥሩ ነገር ለማድረግ ሰዎችን ማሰባሰብ የተለየ ፖለቲካዊ ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ይህ በመኾኑም ተልዕኮ ያላቸው ሰዎች ብዙዎች እንዳይሰባሰቡና እንዳይደራጁ ያደርጋሉ፡፡ ኾኖም የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ መሰባሰብ ጀመርን፡፡ የተሰባሰቡትን መሠረት በማድረግም ‹‹ካልቸራል ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ›› የሚባል ድርጅት አቋቋምኩ፡፡ በዚህ ዙሪያ እየሠራሁም አንድ ወቅት አዲስ አበባ መጣሁ፡፡

እዚህ ከመጣሁ በኋላም ከወንድሜ ጋር እየተዟዟርን የተለያዩ ገዳማትንና ታሪካዊ ቦታዎችን አየሁ፡፡ በተለይ አንድ ገዳም ገብቼ ያየሁት ነገር በጣም ያሳዛናል፡፡ ገዳማውያን ምንም ነገር ሳይኖራቸው 24 ሰዓት ለአምላካቸውና ለኢትዮጲያ ይጸልያሉ፡፡ የሚኖሩት በልመና ነው፡፡ የሚበሉት ምንም የላቸዉም ማለት ይቻላል። ከርሃቡና ብርዱ የተነሳ እነዚህ ደካሞች ተኝተዉ በነጋታዉ በሕይወት ሊነሱ እንደማይችሉ በመገመት እርስ በእርሳቸዉ ‹‹እባክዎ ጠዋት ከተነሱ የጎጆዬን በር ይቆርቁሩ›› ተባባለዉ ነበር ወደ መኝታ የሚሄዱት። ይህን ሳይ ያለውን እውነት ለቤተሰቦቼ ነገርኳቸው፡፡  በዚህ መነሻም ከቤተሰቦቼ ጋር በግሸን ማርያም ትልቅ ፕሮጀክት ሠራን፣ ጥቂት ጓደኞቼና ዘመዶቼ በመጠኑም ቢኾን ረድተዉኛል። ከጅማሮ እሳካሁን የተሰሩት በሙሉ በቪዲዮ ተቀርጸዉ ተቀምጠዋል። በጊዜዉም ቅንጥቡን በፌስ ቡክ ላይ አስቀምጨዉ ነበር።

ግዮን፡- ፕሮጀክቱ ምን ነበር?

አታመንታ፡- የኤሌክትሪክ ማምንጫ ኃይልና መሥመር ዝርጋታ ነበር፡፡ በወቅቱ ይህን በራስ አነሳሽነት መሥራት በጣም አስቸጋሪ ነበር፡፡ የመጓጓዣዉ መንገድም ጥሩ አልነበረም፡፡ ሥራዉን ስንጀመር ከሁለት ጊዜ በላይም ለኢትዮጵያ አየር ኃይል ከፍለን ከአየር ኃይሉ ትልቁን ሄሊኮፕተር በመከራየት ጄነሬተርና ቁሳቁሶችን አጓጉዘናል፡፡ በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ ግሸን ማርያም ደብረ ከርቤ ገዳም መብራት አስገባን፡፡ በፈረንጆች 2001 ነው ይህ የኾነው፡፡ በዚህ ሥራም ከጅማሮዉ ቤተ ክርስቲያኖቹ እና ከ800 በላይ ነዋሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የመብራት ተጠቃሚ መኾን ችለዋል፣ የደብሩ መንገዶቹም እንዲሁ፡፡ አሁን ከእዛ በእጥፍ በላይ ነዉ። አሁን ገና በቅርቡ ከደሴ የመብራት ኃይል ጋር መስመሩ ተገናኝቷል፣ ጄኔረተሩም ተጠባባቂ ኃያል ማመንጫ ኾኗል።  እስካሁንም ይህ ብቻ ሳይኾን በየዓመቱ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሥራዎችን ሠርተናል፣ አሁንም እየሰራን ነዉ፡፡ ሁሉም ተግባር ዶክመንት የተደረገና በቪዲዮ ተኾጾ ተቀምጧል፡፡ በወቅቱ በአካባቢው ይማሩ የነበሩ የቆሎ ተማሪዎች አካባቢው ችግረኛ ስለነበረ ለምነው ለመብላት ይቸገሩ ነበር፡፡ ስለዚህ ያ ሁሉ ቅርስ ያለጠባቂ ሊቀር ኾነ፡፡ ያ እንዳይኾን የቻልነውን ያህል ታግለናል፡፡ ይሄ ደግሞ ሌላ ታሪክ በመኾኑ አሁን አልጀምረውም፡፡ 

በጥቅሉ ግን ይህን ሁሉ ነገር ለማድረግ ስንነሳ ብዙ እንቅፋቶች ነበሩብን፡፡ አሜሪካን ሀገር በአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ዓመታት ላይ ወደ 4ሺህ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያኖች ነበሩ፡፡ በ80ዎቹ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ቁጥር በጣም ሊበዛ ችሏል፡፡ እዚያ ከሄድን በኋላ ደግሞ ወጣቱ እኛ ልጆቻችንን ማስተማር እና ሕይወታችንንም መምራት የምንፈልገው በሀገራችን ባሕልና ማንነት ሳይኾን በአሜሪካውያኑ ማንነት በማነጽ ኾነ፡፡ በዚህ ምክንያት የባሕል ግጭት አጋጥሞናል፡፡ አሜሪካ ላይ ብዙ ሰው በዚህ ችግር ውስጥ እየኖረ ነው፡፡ በቅርቡ በተደረገ ጥናት በእያንዳንዱ ቪርጂኒያ ስቴት ወረዳ ባሉት እሥር ቤቶች ውስጥ 2 በመቶ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንደሚገኙ ይፋ ኾኗል፡፡ የዚህ መነሻው በአብዛኛዉ ከፍ ብሎ እንዳልኩት ጠለቅ ያል የባሕል ግጭት መኖሩም ጭምር ነው፡፡ ይህን ለማስተካከል እኛ ብዙ ሞክረን ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙዎቹ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ስለመሰላቸው መፍትሔ ማበጀት አልቻልንም፡፡ 

ግዮን፡- በምን መልኩ ነበር መፍትሔ ለማበጀት ጥረት ያደረጋችሁት?

አታመንታ፡- ልናደርግ የነበረው ችግሩን ‹‹የካልቸራል ሶሳይቲ›› ውስጥ በማስገባት የልጆቹን ችግር ከማኅበረሰቡ አስተያየት ጋር አቀናጅተን ለማስተካከል ነበር፡፡ በዚህ ዙሪያ ብዙ መንገድ ከአገልግሎት ሰጪው ተቋማት ጋር ለማገናኘት ነበር፡፡ 

በሌላ በኩል አዲስ አበባ በመጣሁበት ጊዜ ፌስቱላ ሆስፒታል ቆይቼ ነበር፤ በጣም የሚያሳዝን ታሪክ ነው ያየሁት፡፡ ልጆች ያለእድሜያቸው በማግባታቸው ምክንያት ለፌስቱላ ችግር ተጋልጠዋል፡፡ በሆስፒታሉ ሰፊ ጉብኝት አድርጌያለሁ፡፡ እዚያም ከሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጇና መሥራቿ  ከዶክተር ሃምሊን ጋር ወደ ኋላ ቅርርብ ነበረን፡፡ በዚህም ዶክተሯ ይህን መሰል ሆስፒታል ሐረር ከተማ መሥራት ትፈልግ ነበር፡፡ በሥራው ደግሞ የሚረዷት ያስፈልጋት ነበር፡፡ እኔም አሜሪካ ጓደኞቼን ሰብስቤ ከ20ሺ በላይ በማስታወቂያ ፍላየር አዘጋጅተን በመበተን ለሴትየዋ ገንዘቡን ለማስገባት ሥራ ጀመርን፡፡ ቅድመ ዝግጅቱ ጥሩ ሄዶ ሄዶ ግን የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራው ፖለቲካዊ ትርጉም ተሰጥቶት ግጭት ተፈጠረ፡፡ ልናሰባስብ የነበረዉን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ ለመላክ በነበረን ዕቀድ በእነሱ ነባር ተወካይ ወገን ካለው ሰው ጋር አለመግባባት ተፈጠረ፡፡ ምክንያቱም ግለሰቡ በዚህ ሥራ ሂደት ውስጥ ለራሱ ሕጉ በሚፈቅድለት መጠን የሚቆርጣቸው ገንዘቦች ነበሩ፡፡ ይህን ሕጉ የፈቀደለትን በመቃወም ሳይሆን እኛ በኩል ከሚሰበሰበዉ ገንዘብ ሳንቲም ወጭ ሳይደረግ ለዚሁ ግንባታ እንዲደርስ ለማድረግ ነበር ምኞቴ (dollar for dollar) እንደሚባለዉ፣ ይህን ቁርሾ መነሻ በማድረግ በተለይ እኔን ማጥቃት ጀመረ፡፡ በዚህም በግል ተካሰስን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዳይደርስና ተጠቃሚ ጉዳተኞቹ ሕጻናትና ሴቶች ወገኖቻችንን እንዳይጎዱ በምክር ትተነዋል፡፡ ከትንሽ ጊዜም በኋላ እኔም ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ራሳቸዉ ዶክተሯን አግኝቻቸዉ ወደ ማኅበራዊ ኑሮ መመለስ የማይችሉት ሕጻናት የሚቀመጡበትን ግሩም የሆነ መንደር እና ሆስፒታሉን ደጋግመዉ አስጎብኝተዉኛል፡፡ ተመልሼ አሜሪካ ስሄድ ዉሳኔያቸዉን እንደማዉቅ ነገሩኝ፡፡ እኔም ወደዚህ እንደመጣሁ ችግር ፈጣሪው አካል ከነበረዉ ኃላፊነት ተነሳ፡፡ ከዚያ በኋላ የተሰበሰበው ገንዘብም ለታለመው ነገር ሙሉ በሙሉ እየደረሰ ነዉ እላላሁ፡፡ በኛዉ ሕብረተሰብ አንዳንድ የዚሁ አካል ጓዶች ከነበሩ በሰዉየዉ ተጽዕኖ እኛ ገንዘቡን እንዳናሰባስብ የተለያዩ አሉባልታዎች ተቃጥተዉብንና ተደንቅረውብን ስለነበር እኔም አዝማሚያው ስላላማረኝ ገንዘብ ማሰባሰብ አልፈለኩም ነበር፡፡ ምክንያቱም ባካሄዱት ማሰናከያ እንቅፋቶች ምክንያት ከብዙ ሰው አነስተኛ ገንዘብ ሰብስቤ ባስረክብ ከዚህ ሁሉ ሰው እንዴት ይቺን ብቻ የሚል ጥያቄ ያመጣብኛል በማለት አልሰበሰብኩም፡፡ ጉዳዩም እኔን ለመወንጀል ነበርና፡፡ ዶክተር ሃምሊን ያሠራችው ዓለም የሚባል ሲኒማ ነበር፡፡ እሱን ሰጥታኝ ለሕዝቡ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዘ ዲስትሪክት ኦፍ ኮሎምቢያ (University of the District of Colombia) ዉስጥ አሳየሁ፡፡ የሚያሳዝነው ግን ከዚያ ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነዋሪ 70% የሚኾነው የአሜሪካ ተወላጅና አሜሪካኖች ነበሩ የመጡት፡፡ ይህንን በማድረግ ግንዛቤ ፈጠርን፤ በዚህ ወቅት በቤታችን ሐዘን ተከስቶ ነበር፡፡ ይህ በመኾኑም ዶክተሯ ካዘጋጀቻቸው ሰዎች ጋር በቀጣይነት መሥራት አልቻልንም፡፡ በዚህም እናንተ ቀጥሉ አልኳቸው፡፡ በግለሰብ ደረጃ የጀመርኩት የማሰባሰብ ሥራው ስጀምረዉ በፈለግሁት ሰፋት እና ደረጃ ባይሆንም በሌሎች ኢትዮጵያዉያን በጥሩ ሁኔታ ተከናወነ፡፡

ሌላው በጣም የሚያሳዝነዉ ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሲሞት/ስትሞት በየሱቁ እና ሐዘን ቤቶች የተለያየ ሳጥኖችን በማስቀመጥ ገንዘብ ማሰባሰቡ የተለመደ ነበር፡፡ ይህን በቅርቡ ካለፉት ከአቶ ያዕቆብ አስፋዉ፣ ከኮማንደር ጣሰው፣ አቶ ቴዎድሮስ ነብዩ ልዑል እና ሌሎች ጋር በመኾን እድር ለማቋቋም ሞከርን፡፡ ሁለት ዓመት ሙሉ እድሩን ለማቆም መመሪያዉን ከሠራን በኋላ ዌብሳይት ሠርታችሁ አሳውቁ አሉን፡፡ ዌብሳይት ማውጣታችን እንደጥሩ አጋጣሚ ኾኖ ያንን መሠረት በማድረግ እድር በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች መቋቋም ተቻለ፡፡ 

ግዮን፡- አሁን በእናንተ ከተማ እድር አለ ማለት ነው?

አታመንታ፡- አዎ በየስቴቱ እድር አለ፡፡ አሁን ላይ ሁሉም ሀገር የሚገኝ ኢትዮጵያዊ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ እኛ ስንጀምርና ስናቋቁም የሄድንበት መንገድ ሳይቀር በዶክመንት የተቀመጠ ነው፡፡ 

ግዮን፡- የሥሞትን ሥያሜ የወጣት ምክንያት ምንድነው? ‹‹አታመንታ›› እንዴት ሊባሉ ቻሉ?

አታመንታ፡- ሥሜን በተመለከተ ብዙ ሰው የሚለው የ1953ቱን ግርግር ተመሥርቶ የወጣ ነው፡፡ በወታደሩም ዘንድ አባቴ ይህን ሥም መፈንቅለ መንግሥቱን መሠረት አድርገዉ እንዳወጡት ይነገር ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም በየጊዜዉ የተለያዩ የሠራዊቱ አባላት ሥሜን ስነግራቸው እንደሚያስታውሱ ይነግሩኛል፡፡ ነገር ግን በእዉነቱ ሥሜ የወጣው የአባቴ አጎቶች የአንዱ ስም ‹‹አታመንታ›› በመኾኑ የእርሳቸውን ሥም ለማስታወስ ተብሎ ይመስለኛል፡፡ እኚህ አጎቴና ወንድሞቻቸዉ ኃይለኛ አርበኞች ነበሩ፡፡ ወንድሞቻቸውም ‹‹ወዲያው-ምታ››፣ ‹‹ደባይ ምታ›› ይባሉ ነበሩ፡፡ ስለዚህ አባቴ በግልጽ ባይናገሩም ሥሜ የወጣው ከዚያ አንፃር የወጣ ይመስለኛል፡፡  የአክስታችን አባት ሥም ‹‹አታመንታ›› ነበር፡፡  

ግዮን፡- ከአያቶቻችሁ ጀምሮ የመጣው የአርበኝነት መንፈስ እናንተ ቤተሰብ ላይ ሲደርስ የተቋረጠ ይመስላል፡፡ ይህ ለምን ኾነ?

አታመንታ፡- አልተቋረጠም። ሀገርን መታደግ ወይም ማገልገል በፖለቲካ እና በድርጅት ጠብመንጃ ይዞ በትጥቅ ትግል መሳተፍ ብቻ አይደለም። ሁሉም ስልት ወቅታዊ እና ጥርት ያለ ጥሪ እና መምሪያ ሲኖር ብቻ ነዉ። የምታምንበት እና ሕይወትህን የምትሰጠዉ ድርጅት ቢቋቋም ጥሩ ተስፋ ይሆናል። በሀገራችን ግን ብዙ የኋላ አጀንዳ በያዙ ግለሰቦች የተተበተቡ ድርጅቶች ወደዚሁ መድረክ ቀርበዉ ብዙ ደም ፈሶ ግማሹ ዓላማዉን ሲያሳካ ቀሪዉም እንዲሁ ትበትኖ ቀርቷል። ስለዚህ ሌላዉ አማራጭ እና እንዲህ ዐይነቱ ትግል እስኪመጣ ባለን ውስን የሕይወት ዘመን እና አቅም ሳንሳተፍና ምንም ቋሚ ነገር ሳንሰራ፣ ሳናቋቁም ልንጨርሰዉ ነዉ ማለት ነዉ። ስለኾነም እኔና እና ቤተሰቦቼ  እኩል ወይም በበላይ የሚያስፈልገዉን ለወገን እና ለሀገር ተደራሽነትን በተለያዩ የልማትና እርዳታ መስኮች ላይ ብዙ ሰርተናል። ሁለቱም ሂደቶች ግባቸዉ አንድ ስለሆነ። ለሀገር መቆም እንደ ጊዜዉ እና ሁኔታው ይቀያየራል። በተሰጠ ጊዜ ብዙዉ ስላበደ ሁሉም አብሮ ማበድ የለበትም። አብዛኛዎቹ የፖለቲካ ስብስቦች እንደ አጀማመራቸዉ ሀገራዊ ፖለቲካ ዕሳቤ እንደነበራቸዉ ቀጥለዉበት ቢሆን ኖሮ መልካም ነበር፣ ወደ በኋላዉ ላይ ከሀገሪቱ እዉነታ ጋር ፈጽሞ የማይጣጣም የፖለቲካ ዕሳቤ ይዘዉ ከነጎዱ ጋር አሁንም ቢደገም የማናደገርዉ ነዉ። ኮሚኒዝም በሁሉም የምሥራቅ ሀገሮች እየተተወ በነበረበት ወቅት የሚልሰዉ የሚቀምሰዉ ያልነበረዉ ለአብዛኛዉ ሕዝብ ከሶቪየት እና ከቻይና በላይ ኮሚኒስት ሆነናል ይሉ የነበሩት የሃገራችን የፖለቲካ መሪዎቻችን ቀድሞ ሀገሪቱን በባዶ ሆዱ ከጠላት ጋር ተዋድቆ ካተረፋት ‹‹መሃይሙ›› የሃገራችን ሕዝብ ላይ በምኑም መስፈርት አይደርሱም።

አርበኞቻችን ሽንጣቸዉን አስረዉ ለዓመታት በየበረሃዉ የተንከራቱት እና የተዋደቁት ለአንድ ኢትዮጵያ ሲሆን በ60ዎቹ ጀምሮ የተካደው በተለይ የተማሪዉ ትግል ደግሞ ‹‹የራስን መብት በራስ መወሰን እስከመገንጠል›› የሚል ሀገርን አስገነጣይ ቅንቅን ይዞ ነበር። ይኸዉ ምሁር ተብዬዉ ዛሬ ሀገሪቱ ተከፋፍላ ተገነጣጥላ ያለ ባሕር ወደብ ራቁቷን አስቀርቷታል። ይኽ አርበኝነት አይደለም ልዩነቱም ይኸዉ ነዉ። ማስረጃም አያስፈልገዉም። መወቀሰም መገምገምም ይሻዋል። ቤተሰባችንም ይህን ለዉድድር ለማስቀመጥ ሳይሆን ከዚህ በተለየ ብዙዎች ያልሞከሩትን ያላደረጉትን እኛ ሰርተንናል ብል ስህተት አይሆንብኝም። የሚያዉቁን ሁሉ ያውቁታል። አሁንም ለሀገርና ለወገን ተደራሽነትን አላቋረጥንም። ካለማወቅ ወይም ለመምሰል እና ለማስመሰል ከመሞከር እና ሀገርን ከማጥፋት መቆጠብና ክቡር የሰዉን ሕይወት መታገድ ቀዳሚ ነዉና። ከ1953 ዓ.ም በኋላ እኛ በሔድንበት ፈር ብዙ ትግሎች ተካሂደዋል፡፡ ከቤተሰቤ መሃል ስለ እኔ ብጠቅስ ተማሪ እያለሁ የኾነ ነገር ቢፈጠር ጥቃት ሊደርስብን እንደሚችል ይነገረኝ ነበር ምክንያቱም ትምህርት ቤት ስመላለስ ጥበቃ የነበረኝ ተማሪ ነኝ፡፡ በዐይነ ቁራኛ የሚከታተሉኝ ሰዎች ነበሩ፤ በወቅቱ የቤተሰባችን ሁሉም ነገር ስለተወረሰ ወደቤት የሚያደርሰኝ አካል ይታሰርና ይጠለፍ ነበር፡፡ ተጠልፎም ተደብድቦና በአጠቃላይ ስለእኛ መረጃ እንዲሰጥ ተመርምሮ ይለቀቃል፡፡ ይሄ ነገር ለንጉሡ አራት ጊዜ ቀርቧል፡፡ እርሳቸው ማንኛውም አካል ቤተሰባችንን እንዳይጉላላ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል፡፡ ነገር ግን የታችኞቹ ሹመኞች እኛ ላይ ተጽዕኖ ይፈጥሩብን ነበር፡፡ ይሄ ሁልጊዜ ይነገረኝ ነበር፡፡ አንድ ችግር ሲከሰት ከአካባቢው ቶሎ መሰወር እንደሚገባኝ ብዙ ጊዜ ተነግሮኛል፡፡

አጎታችን አባተ ተፈሪም የደህንነት ሰው ስለነበር ቤታችን እየመጣ ይነግረን ነበር፡፡ እኔ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ፎቶግራፍ የሚያነሱኝ ሰዎች ነበሩ፡፡ 24 ሰዓት በቀን በዐይነ ቁራኛ እየተጠበቅን፣ እኔም እንዲህ ዐይነት ሥም ይዤ አንድ ነገር ቢፈጠር አንድ እርምጃ በእኔም ሆንኩ ቤተሰቡ ላይ ሩቅ ሳልሄድና ሳንሄድ እንደሚወሰድብን የታወቀ ነበር፣ በዉስጥም ተነግሮናል። ይህንን ጊዜዉ አልፎ እና እንደ ቀላል ዛሬ ቢወሰድም በጊዜው ባለሥልጣናቱ ታማኝነትን ለማሳየት፣ እኛም በጊዜዉ ሆነ በቀጣዩም መንግሥት አነሳሳሽ አካል እንዳንሆን ክትትል ነበረብን። ይኽ በብዙዎች ዘንድ ይታወቅ ነበር። ያለአንዳች እርዳታ ያሳለፍነዉ ሰቆቃ አንሶ እንደገና ቤተሰቤን ያዉም ጭራሹን በማላምንበት የርዕዮተ ዓለም ፍልስፍና ዕሳቤ ለመምሰል፣ ለማስመሰል እና ለመካፈል ቢሆንም ፍጹም የማላደርገዉ ነበር። እንኳንስ ያኔ አሁን ድረስ እንኳን የገባዉ ያለ አይመስለኝም። በቅርቡ በአንድ የቴሊቭዝን ስርጭት ላይ ያካሄድኩትን ቃለመጠይቅ የአዘጋጁን ዓላማ በቅጡ ማየቱ ጠቃሚ ነዉ። የምትጀምረዉን መጨረስ፣ ማወቅና ማድረግ እና በግብታዊነት ጀምሮ የፈረሰዉ ይፍረስና በበኋላዉ ይገነባል ተጻራሪ ሐሳቦችን በተመለከት ሁሌ መመሪያዬ የመጀመሪያዉ ሲሆን በጊዜው የፖለቲካ ቡድኖች ዕሳቤዉ መመሪያ ግን ባብዛኛዉ ሁለተኛዉ ነበር ፤ አሁንም ነዉ። የዴሞክራሲ ትግሉም ሆነ ተግባሩ ገደብ ሲኖረዉ ብቻ ነው እዉን ስኬታማነቱ የሚረጋገጠዉ፣ ይኽ መሰፈርት ከጎደለዉ ሽብርተኝነት የትግሉ ቋሚ ባሕሪ ይሆናል። የቃለ መጠይቁ አዘጋጅ የዚህ ታሪካዊ ግድፈት አቀንቃኝ ነዉ? ወይስ ጭራሹኑ አሁን ድረስ አልገባዉም? ለረገፉት ሕጻናት መልስም ጸጸትም የለዉም፣ እዚያዉ 40 ዓመት በፊት የነበረዉ ጊዜው እና ሰዓት ላይ የቆመ ይመስላል። ሁሉ አልፎ አክራሪ የፖለቲካ መሪዎች የትግሉን ሜዳዉን ትተዉ ብዙ በሚባል ደረጃ ዉጭ ሃገር ይኖራሉ ፤ ቤተሰብም ሃብትም መሥርተዋል፣ ድሃዉ ወገናችን አልቋል፣ ቀሪ ቤተሰቡን ዞር ብሎ ያየዉ የለም።

ስለሆነም መጀመሪያ ላይ ትንሽ ተሳትፎ ቢኖረኝም ወዲያዉኑ ‹‹ራስን በራስ ማስተዳደር እስከ መገንጠል›› የሚለዉን አቋም ስሰማ ወዲያዉኑ ተገልያለሁ። ያዉ አሁን እንደታየዉ ተማሪዉ የተሰዋዉ ለተገጣይ ቡድኖች ዓላማ ስኬት እግረኛ ወታደር ሆነዉ አለቁ። ይህን የምለዉ ደርግ በወደቀ ማግስት የተገንጣይ ጉዶቹ ዓላማቸዉ ስለተሳካ ወደ ቀጣዩ ክፍል ተራምደዉ ሃገራዊ ትግሉን እርግፍ አድርገዉ ትተዉ በዘር እና ቋንቋ የተዋቀረ አስተዳደርና አልፎም ነጻነትን አወጁ። ቀሪዉ ኢትዮጵያዊዉ ግን ባሕር ላይ የንፋስ ሸራዉ እንደተሰበረ መርከብ ያለ መሪ ሲዋልል ሰንብቶ በሐዘን ተዉጦ ቀረ። ብዙዎች የተማሪዉ መሪዎች ደርግ ሲወድቅ መመሪያቸዉን ይፋ አድርገዉ ወደ ቀጣዩ ዓላማቸው ስኬት ሲቀጥሉ የተቀረዉ ሕዝብ እና ጀሌዉ ተማሪ አሉኝ የሚላቸዉ የነበሩት መሪዎቹ በዚያዉ ሲጠቃለሉ የቀሩት በአነስተኛ ደረጃ የነበሩት ጥቂት መሪዎች ብቻ ነበሩ። ቀድመዉ ያለፉት መሪዎቹ እድሜ ስላነሳቸዉ እንጂ ደርግ ከወደቀ በኋላ እነሱም ከተገነጠሉትና በዘር እና ቋንቋ ከተቋቋሙት ጋር ይወግኑ እንደነበር ምንም ጥያቄ የለዉም። ከዚያ ወዲያ መሪዎቹ የት ደረሱ ብሎ መጠየቅ አግባባ ያለዉ ይመስለኛል። ይህ እስኪሳካ ድረስ ዴሞክራሲ ለጭቁኑ እያሉ ሲለፍፉ ነበር። ለዚህ ነበር ወይ የኢትዮጵያ ድሃ ልጆች ያለቁት? እስከዛሬ ድረስ በይፋ መልስ የሰጠ አላዉቅም ፤ አልሰማሁምም።

በሃገራችን ላይ አዉቀንም ኾነ ሳናዉቅ ለዚህ እኩይ ተግባር እኔም ቤተሰቦቼም ተባባሪ ባለመኾናችን በጣም ደስተኛ ቀና ብለን መሄድ እንችላላን። እህቶቼም አሜሪካ በተቋቋመዉ የተማሪዎች ማኅበር ሙሉ ተሳታፊ ነበሩ። ትልቅ እህታችን የትምህርት ጥናቷ ያደረገችዉ በምሥራቁ ዓለማትና ርዕዮት ዓለም ላይ ነበር። በጊዜዉ የሚሰበከዉ ግን ምንም ከምሥራቁ የፖለቲካ እሳቤ እጅጉን የራቀ፣ መመሪያ ሕጎቹንም የጣሰና የማይከተል እንደሆን ቀደማ ተረድታዉ ነበር። እነሱም የኢዙና አንድ አካል ለሁለት ሲከፈል እና አንዱ ጎልብቶ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች የራስን እድል በራስ መወሰን እስከ መገንጠል››ን ሲያዉጅ ጉዳዩን እና ይዘቱን በቅድሚያ በመገምገም ከድርጅቱን ገለል አሉ። ለሕዝብ መቆም ማለት በብዙ መንገድ ለሕዝብ መቆም ማለት ነዉ። እኛም በኑሯችን ትንሽ ከተቆናጠጥን በኋላ ብዙ ነገሮችን በሃገራችን ለሃገራችን አድርገናል አበርክተናል። ከፊሉን ከላይ እንደገለጽኩት ነው። የእወቁልኝ ጉዳይ አይደለም። ይህንንም ለአርዓያነትና ወጣቱን ለማነቃቂያ ይጠቅማል ስላልከኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ ተናግሬአለሁ። ቤተሰቦቼ መናግሬ ላይስማማቸዉ ይችላል ስለማዉቀዉ። ለሀገር፣ ለወገን ከዚያም ተርፎ ለሕሊናህ የምትፈጽመዉን ለግል እውቅና ማግኛ ካደረከዉ ትርጉም የለዉም፣ ትግላችን እና ተደራሽነታችን በተጨበጡ ሥራዎች በሌላዉ መልኩ ከአጥጋቢ በላይ በሚባል ደርጃ ቀጥሏል።

ግዮን፡-  ከሀገር ከወጡ በኋላ ይህ የልጅነት የኋላ ታሪክ ተጽዕኖ ፈጠረብዎ?

አታመንታ፡- አዎ፡፡ ገና ተማሪዉ ንቅናቄ ውስጥ ሲገባ ይከታተሉኝ ጀመር፡፡ አዲግራት በነበርኩበት ጊዜ እንደሚከታተሉኝ አውቅ ነበር፡ከሀገር ከወጣን በኋላ ወንድማችን ከእናታችን ጋር እቤት ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ በውጪም ይሁን በሀገር ውስጥ የነበረዉ የፖለቲካ እሳቤ ከባድ ነበር፡፡ በወቅቱ ፖለቲካ ውስጥ የተሳተፉት አብዛኞቹ የወንድሜና እህቶቼ ወደ በኋላዉም የኔ ጓደኞች ነበሩ፡፡ እኛ በልጅነታችን ብዙ መጻሕፍትን አንብበናል፡፡ በዚህም ወንድሜ ወጣቶችን ይመክራቸው ነበር፡፡ ወንድሜ በጣም ነበር የሚያነበው፡፡ ቤት ውስጥም ከሺህ በላይ መጻሕፍቶች ነበሩ፡፡ አብዛኛዉ በርዕዮተ ዓለም ዙሪያ ያተኮሩና አሉ የተባሉ ነበሩ።

በተማሪው ትግል ውስጥ ልዩ ልዩ ውይይቶች ነበሩ፡፡ እኔም ቁጭ ብዬ አዳምጥ ነበር፡፡ የነበረው የፖለቲካ እሳቤ ሀገሪቱ ከነበረችበት ተጨባጭ ሁኔታ እና ከምትሸከመው ዉጪ እንደነበር እንረዳ ነበር፣ ምክንያቱም ያ ሥርዓት ፊውዳላዊ ሥርዓቱን ለማፍረስ ቢመጣም የመረጠው መንገድ ግን የእብደት ጉዞን ነበር፡፡ በሁሉም ፓርቲዎች መካከል ያለው ነገር ደስ አይልም ነበር፡፡ በአክራሪነት የማይኾን ነገር ውስጥ ገቡ፡፡ ሰው ተጋድሎ ጓደኞቻችን ዘመዶቻችን አለቁ፡፡ እኔ እራሴ አንዱ የመከራው ተካፋይ ነኝ፡፡ በሁለቱም ወገን ተጎድቻለሁ፡፡ በወቅቱ ወደ ፖለቲካ ከተገባ ወደ መንግሥት ተቃውሞ ጎራ ያበደ ኮሚኒስት መኾን አልያም የመንግሥት አባል ኾኖ የኮሚኒስት ሀገራትን ዓላማ አስቀጣይ መኾን ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሁለቱንም መንገድ አላመንኩበትም፡፡ በወቅቱ ሲጀመር ኢትዮጵያ የሚለው ነገር ጠፍቶ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ ክርስትና፣ ሌላም ሃይማኖቶች የመሳሰሉት ነገሮች ቦታ አልነበራቸውም፡፡

በሌላው ወገን ደግሞ ፍልስፍና እና ተራማጅነት የተጣመሩበት ማርክሲዝም ሌኒንዝም የገነነበት ነበር፡፡ ይወራ የነበረውን ዞሮ ላስተዋለ 90 በመቶ በደም የተጨማለቀ ሰው ሆዱ ሳይሞላ ስለማይጨበጥ ነገር ነው የሚያወራው፡፡ ለሚወሰደዉ እርምጃ በሁሉም ወገን የሕሊና ጣሪያ ገደብ አልነበረም። ስለዚህ ያለምንም ጸጸት መግደል እና መጋደል የሂደት ጉዳይ ሆኖ ተወስዷል። ቤት ተወርሶ ንብረት ሄዶ ሰው ባዶውን ቀርቶ ድጋፍ እንዴት ይኖራል? የእኛ ቤተሰብ ግን ቀድሞ አልፎታል፡፡ ነገር ግን ያለፍንበትን ድጋሚ ዓይናችን እያየ እዚያ ውስጥ አንገባበትም፡፡ እኛ እዚህ ሀገር ከመጣን በኋላ የምናየው የተከፋፈለ ቡድን ነበር፡፡ ብዙ ስብሰባዎች ላይ እንሳተፍ ነበር፤ እዚያ የማያቸው የፖለቲካዉ ተዋንያን ያለፈውን አስቀጣዮች እንጂ አዲስ ነገር ይዘው የመጡ አልነበሩም፡፡ ይኽ ነዉ የማይባል ገንዘብ ተስብስቦ የት እንደደረሰም አይታወቅም። በዚህ ዐይነት ፖለቲካ ውስጥ መሳተፍ ለገጽታ ግንባታና ለይስሙላ ካልኾነ በቀር አስፈላጊ አይደለም፡፡ በተለያየ መንገድ መደራጀት፣ ገንዘብ አሰባስቦ ለተቸገሩ ወገኖች ተቋማት ለማቆም መጣር ተደራጅቶ ከሕዝብ ተጠያቂነት ዉጭ የሚሰራን መንግሥት በቆራጥነት ተጠያቂ ማድረግ ቀዳሚ ሲሆን ከመጣው መንግሥት ጋር ሁሉ ወዲያዉኑ ለጦርነት መዘጋጀት አያሻም፤ እኔም ያደረኩት ያንን ነው፡፡ ይኽ ከተከናወነ ከግማሽ በላይ አሸናፊነት ነዉ። አሁንም ያለው ፖለቲካችን ከቀድሞው የተለየ አይደለም፡፡ ብዙ ነገሮች የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ ከጀርባ ያሉ ጠላቶቻችንንም አናውቃቸውም፡፡ እኛ የምናውቀው የእርስ በእርስ ግጭታችንን ብቻ ነው፡፡ አንድ ነገር ለማድረግ ወይም ለመወያይት ስነሳ በቤተሰቤ ታሪክ አብዛኛዉ ወደ ፖለቲካዊ ግምጋሜ ይወስድብኛል። ስለዚህ በነፃ ሐሳቤን እንዳላካፍል እንዳላንሸራሽር ያለብኝ የብዙዉ አመለከካት ይቸግረኛል፣ ተጽኖም ፈጥሯል ለቤተሰቦቼም ጭምር።

ግዮን፡- ስለ አባትዎ የጻፉት መጽሐፍ ከእርሳቸው ሕልፈት 60 ያህል ዓመታትን ዘግይቷል፡፡ ይህን ያህል ዓመት እንዴት ሊቆይ ቻለ?

አታመንታ፡- ለመቆየቱ ትልቁ ችግር አባቴ ጀነራል ጽጌ የሠሯቸው ሥራዎች ናቸው፡፡ ከ14 ዓመት ዕድሜያቸው የአርበኝነት ዘመናቸው ጀምሮ እስከ ሕልፈታቸው ያለው ዘመን በጣም ረጅም ነው፡፡ ከአርበኝነት በኋላ ሀገር አረጋግተው ወደ ነገሌ ሄደዋል፡፡ በወቅቱ ከጅማ እስከ ነገሌ ጦሩን እየመሩ በእግር ነው የሄዱት፤ ነገሌ ከገቡ በኋላ የነገሌን ጦር አደራጅተው ወደ ሐረር በመሄድ ሦስተኛ ክፍለ ጦርን ገንብተዋል፡፡ ይህ ሁሉ የኾነው በንጉሠ ነገሥቱ ድጋፍ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ጀነራል ጽጌ የሚያደርጉት ሥራ ያውቃሉ፡፡ ንጉሡ ነገሌ ድረስ ሄደው የተሰራዉን አይተዋል፡፡ ወንድሜ ቴዎድሮስ ወደ እቴጌ መነን ት/ቤት ሄዶ እንዲማር ያደረጉት እርሳቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ ንጉሡና አባቴ በጣም ቅርብ ነበሩ፡፡ 

አባቴ በታኅሣሱ ግርግር ሕይወታቸው ሲያልፍ ወዲያውኑ የአባቴ ታሪክ በመንግሥት ደረጃ እንደታሪክነት እንዳይወጣ ተደረገ፡፡ ምክንያቱም የአባቴ የጀነራል ጽጌ ታሪክ የታኅሣሱ ንቅናቄ ብቻ ሳይሆን ለሌላው በራስ አነሳሸነት ያቋቋሟቸው ተቋማት ዐይን ገላጭ ስለኾኑ ያ እንዳይኾን የተቻለው ጥረት ሁሉ ተደረገ፡፡ በኢትዮጵያ እስከ 1980ዎቹ ድረስ አባቴ ከሠራቸው ተቋማት ውጪ ተቋም አልተመሠረተም ማለት ይቻላል፡፡ ይኽንን ብዙዎች ብለዉታል በተለያዩ ጋዜጦችም ተጽፈዋል። ከአባቴ ተቋም ውጪ ያሉ ተቋሞች ከውጪ ሀገር ተቋማት ጋር ተለጣፊ ኾነው የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ተቋም በአንድ ግለሰብ ብቻ የተቋቋመው በጀነራል ጽጌ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ በጊዜዉ አቶ መኮንን ሀብተወልድ ሀገር ፍቅርን አቋቁመዋል፡፡ የጀነራል ጽጌ ተቋማትን በተመለከተ ግን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡ እርሳቸው ካረፉ በኋላ የመንግሥት ባለሥልጣናት የእርሳቸውን ዶክመንት ነቅሰው አወጡት፡፡ ይህ የኾነው ደግሞ በሁለት ምክንያት ነው፤ አንድም ጀነራል ጽጌ ለሥራቸው እንቅፋት ከኾኑ ማናቸውም አካላት ጋር ይጋጩ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ክስ ሲመጣባቸው ንጉሡ ‹‹ጀነራል ጽጌ የሚጣላው ከማያሠሩት ሠዎች ጋር ነው፡፡›› በማለት ክሳቸውን ይጥሉባቸው ነበር፡፡ በዚህ ያቄሙ የሥራ አጋሮቻቸው ከአባታችን ሕልፈት በኋላ በአባታችን ታሪክና በእኛ ላይ በቀል ጀመሩ፡፡ እኛን ለመበቀል አባታችን ካረፉ በኋላ ሁለት ቀንም አልፈጀባቸው፡፡ ማንኛውንም የቤተሰብ ሰነድ አጠፉ፡፡ ይሄ በፖሊስ አዛዡ እና አስፈፃሚነት ጭምር የተተገበረ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአባቴ ጸሐፊ የነበረ መቶ አለቃ ለገሰ የሚባል የፖሊስ ሠራዊት አባል የነበረ እቤት ድረስ እያለቀሰ መጥቶ ሥራውን እንዳያስፈፅም መታዘዙን ለእናቴ ተናግሯል፡፡ ማንኛዉንም ጄኔራል ጽጌ ዲቡን የሚመለከቱ ዶክመንቶችን ማቃጠል። ሌላዉ በጊዜዉ በሥልጣን ላይ የነበሩት በዚያ ደረጃ ምን ሰርተዉ ነበር የሚለዉ ጥያቄ እንዳይነሳ አባታችን ያቋቋሟቸውን ተቋማትና ድርጅቶች በሙሉ በእሳቸዉ ሥር ለነበሩት ዝቅትኛ መኮንኖች ዕውቅናዉ እንደ ሎተሪ ታድሎ  ነበር። ያም ካላስኬደ እሳቸዉ እንደሰሩት እንዳይታወቅ ደብዛዉ እንዲጠፋ ወይም ጥያቄዉ እንዳይነሳ ይደረግ ነበር። አባታችን የሰሯቸዉን ከፊል ዝርዝሩን መጸሐፉ ላይ መመልከት ይቻላል።

ግዮን፡- የሚቃጠሉት ሰነዶች ከቤት ነው የሚወጡት ወይስ ከየት ነው?

አታመንታ፡- የቤታችንማ ሰነዶች ንቅናቄዉ በከሸፈ ማግስት እንዳለ ተዘርፏል፡፡ አባታችን እንዳረፉ ቤታችን ተከበበ፡፡ በወቅቱ የቤታችን ጥበቃ ፖሊሶችም ተማረኩ፡፡ ከሦስት መቶ በላይ የጦር ሠራዊት ነው መጥቶ ቤታችንን የከበበው፡፡ ከከበቡት በኋላም ቤታችንን ሰባብረው በመግባት ቤተሰቡን አንድ ሰርቢስ ቤት ውስጥ እስረኛ አድርገው አጎሩን፡፡ ቤት ውስጥ የሚገኝ የአባታችንን ማንኛውንም ነገር ልቅምቅም አድርገው ወሰዱት፡፡ ይህን ሲያደርጉ እናቴ ቤተሰቡ ከታሰርንበት በመስኮት እያዩ ነበር፤ እናታችን ሁሉንም ታውቃቸዋለች፡፡ ይህ ዘረፋ በዚያን ዕለት ብቻ የተገታ ሳይኾን በተከታታይ ቀናትም ቀጥሎ የተደረገ ነው፡፡ ዘረፋው በከፍተኛ የጦር ሠራዊት መኮንኖች በዘለለ ቀስ በቀስ በተዋረድ በሠራዊቱ አባሎች ቀጥሎ በመጨረሻም በሰፈርተኛዉ ወደ ቤት ውስጥ ቁሳቁሶች እና ንብረቶችም ተሸጋገረ፡፡ እኛ በዚህ መሐል ከሞት አምልጠን ለመውጣት በቃን፡፡ 

ግዮን፡- እናንተ በዚህ ሰዓት ቤቱን ትታችሁ ወጣችሁ?

አታመንታ፡- አዎ፡፡ እኛ እንድንገደል ትዕዛዝ ወጥቶ ስለነበር ወጥተን አመለጥን፡፡ 

ግዮን፡- ትዕዛዙ የተሰጠው ከማን ነው?

አታመንታ፡- ከአዛዦቹ በስልክ የተላለፈ መልዕክት ነው፡፡ 

ግዮን፡- ቤተሰባችሁ የታሰረው ለምን ያህል ጊዜ ነው?

አታመንታ፡- ቅዳሜ ጠዋት እኛው ግቢ አንድ ከፍል ውስጥ ነው ያገቱን፡፡ በዚህ እገታ ላይ እያለን እናታችን የተለያዩ መረጃዎችን ትሰማ ጀመር፡፡ በዚህ መሐል አባታችን በሕይወት እያሉ ሁሌ የሚሏትን የባንክ አካውንትና የቤተ ዘመድ መረጃ ለመያዝ እንደምንም ብላ የላይኛው ቤት ትሄዳለች፡፡ ስትደርስ በክፍሉ የሚገኙ ሦስት ስልኮች እየጠሩ ታገኛለች፡፡ ያው ቤታችን በሠራዊቱ ቁጥጥር ሥር ስለነበር የጦር መኮንኖች እርስ በእርስ የሚያደርጉት ንግግር ነበር፡፡ እናቴም የስልኩን ማዳመጫ አንስታ ስታዳምጥ እንድንረሸን ወታደራዊ ትዕዛዝ ሲተላለፍ ትሰማለች፡፡ እናቴም ይህን ስትሰማ በድንጋጤ የሄደችበትን ጉዳይ ትታ በርራ እኛ ጋር በመምጣት የአጎቶቼን ልጆች እኛ ጋር ስለነበሩ እነርሱን በመሸኘት እኛም ጎረቤት ሄደን ምግብ እንድበላ ፈቃድ ተጠየቀ፡፡ የአጎቶቼ ልጆች እንደወጡ ሦስቱ እህቶቼ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተከታትለዉ መዉጣት ቻሉ። ኾኖም በዚህ አጋጣሚ አንድ የደነበረ በሬ ወደእኛ ቤት በመምጣቱ ሠራዊቱም በሬው ላይ በመተኮስና በማረድ ላይ ሳለ እናቴ፣ እኔ እና አራስ እህታችንን ይዛ ሾልከን አምልጠን ወጣን፡፡ ስንወጣ ከሕዝብ ተደባልቀዉ ዉጭ የነበሩት አክስቶቻችንና በርካታ ዘመዶቻችን ይዘውን ሮጡ፡፡ አምልጠንም ካሳችንስ አረፍን፡፡ እዚያ ደርሰን ወደ ሌላ ቦታ እንደንሄድ ወታደሮች እኛን ፍለጋ አክስታችን ቤት ደረሱ፡፡ እኛን ሲያጡ አክስታችንን ደብድበው እቃዋን በታትነዉ ፍራሽ ሳይቀር በሳንጃ ቀዳደዉ ሄዱ፡፡

እኛ እየሄድን እያለ እናታችን ከእኛ እኩል መሄድ ተስኗት መንገድ ላይ ትወድቃለች፡፡ በኋላ ላይ እንደምንም ነቅታ ስትሄድ ፖሊሶች አደናቸውን አጠናክረው ቀጠሉ፡፡ እኛም ወደ ዮሐንስ ሠፈር ሄደን ከአንድ ወር በላይ ተደበቅን ተቀመጥን፡፡ በኋላ አቶ አክሊሉ የሚባል አጎታችን አራት ኪሎ ወስዶ ደበቀን፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳያችን ለከፍተኛ ባለሥልጣናት ደርሶ ያለንበት ሁኔታ ታወቀ፡፡ ከዚያ ይቅረቡ ተብለን ተይዘን ቤተመንግሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘንድ ቀረብን፡፡ ጉዳያችን ተነበበና ‹‹እርሱ ባደረገው ነገር እናንተ የሚያገባችሁ ነገር የለም›› ተባልን፡፡ እናቴም የት መሔድ እንደምትፈልግ ስትጠየቅ የትም የመሔድ ዓላማ እንደሌላትና ልጇቿ ያሉበት ትምህርት ቤት እንዲመልሱ  ብቻ ጠየቀች፡፡ ይህን ስትጠይቅ ንጉሡም ጀነራል ጽጌ በላቡ ያፈራው ይሰጠው በማለት ወሰኑ፤ በውሳኔው መሠረት ወደ 80ሺህ ብር ተገኘ ተባለ፡፡ እርሱን ለማግኘት ስንሄድ ‹‹የሚደርሳቹ 40 ሺህ ብር ነው፤ ቀሪው አርባ ሺህ ብር ቅጣት ነው›› በማለት ቆርጠው አስቀሩት፡፡ እኛም የተሰጠንን ገንዘብ ይዘን ሕይወታችንን ገፋን፡፡ 

ግዮን፡- የመጽሐፉ ሕትመት ለምን ዘገየ የሚለውን ጥያቄ ቢመልሱልኝ?

አታመንታ፡- መጽሐፉ የዘገየው የአባቴ መረጃዎች በሙሉ በመቃጠላቸውና በመጥፋታቸው በመረጃ እጥረት ነው፡፡ ወንድሜ አሜሪካ  መጥቶ አንዳንድ መረጃዎችን እንዲያጠናክር ስነግረው የአባታችን ታሪክ በሙሉ መጥፋቱን ነገረኝ፡፡ አንድ ‹‹ኢትዮፒክስ›› የሚል በፍራንሲስ ፎልሴቶ የተፃፈ ጽሑፍ አንብቤ ነበር፡፡ ግለሰቡ ስለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት ታሪክ የሠራ ነዉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ስለፖሊስ ኦኬስትራ ጽፎ መሥራቹ ጀነራል ጽጌ መኾናቸዉን ይነግረናል፡፡ እኔ ያንን ሳነብ በጣም ተገርሜ ነበር፡፡ ይህ የኾነው በነጮቹ 1980ዎቹ መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ወንድሜ ግን የመፃፍ ዓላማዬን እንድቀጥል ሞክር አለኝ፡፡ እኔም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የመጽሐፉን ግብዐቶች ማጠናቀር ጀመርኩ፡፡ ሥራውን ስጀምር ብዙ ሰዎች ስለአባቴ ማውራት የምፈልግ መስሏቸው ነበር፡፡ የኔ ጉዳይ ግን ይኽ አልነበረም፡፡ የሚያውቁትን እንዲነግሩኝ የሚያውቋቸዉንም እንዲጠቁሙኝ በሩን እንዲከፍቱልኝ ነበር።

የብዙዎቹን ባለሥልጣን ልጆችን አውቅ ስለነበር የሚያውቁትን እንዲነግሩኝ ብዙ ጥሬያለሁ፡፡ ብዙም ተሳካልኝ፡፡ ‹‹ላይብረሪ ኦፍ ኮንፍረንግረስ›› እንድሄድም ጥቆማ ደረሰኝ፤ እዚያ አቶ ፋንታሁን ጥሩነህ የሚባል በጣም ጥሩ ሰው አገኘሁ፡፡ ይህ ሰው በስብስቡ ጅማሮ ላይ በብዙ ነገሮች ረዳኝ፡፡ በእርሱ አማካኝነት ብዙ ፋይሎችን ሰበሰብኩ፤ አዲስ አበባ እየመጣሁ የተለያዩ ፎቶዎችን ሰበሰብኩኝ፡፡ በተለይም የድሮ መጻሕፍት መሸጫ እንደ ኮሜርስ ጀርባ ያሉ አካባቢዎች ላይ ብዙ ነገሮችን አገኘሁ፡፡ በመቀጠል የተለያዩ ሰዎችን ቃለመጠይቅ ሠራሁ፡፡ የጠየኳቸው ሰዎች በሙሉ ለሰዓታት ቀረፃ ተባበሩኝ፤ እነ ጄኔራል ወልደሥላሴ፣ ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ሥላሴ፣ እነ አቶ አምዴ ወንዳፍራሽ፣ እነ ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ፣ እነ ሻለቃ ያሬድ ቢተው፣ እነሻለቃ ለማ ገብረ እግዚአብሔር፣ እነሻለቃ ገድሉ ኃይሉ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ብርሃኔ ጭምር የመሳሰሉትን ሰዎች ከ70 ሰዓት በላይ ቃለ መጠይቅ ቀድቻቸዋለሁ፡፡ ይህን ሁሉ ዶክመንት አዘጋጅቼ መጽሐፍ ለማድረግ 27 ዓመታት ፈጀብኝ፡፡ ሥራውን ከመጀመሬ በፊት ከፎቶ አንፃር እንኳን እቤት የነበረው ፎቶ ሁለት ብቻ ነበር፡፡ ለእናቴ ከግድግዳ ላይ ሰዎች ልጠው የሰጧትና አንድ ወዳጅ ያመጣው ፎቶ ብቻ ነበር የነበረው፡፡ ከዚያ ውጪ ያለውን ነገር በሙሉ የምናውቀው በአፈ ታሪክ ነው፡፡ አንድ ጊዜ በሚገርም ሁኔታ ከአባታችን ጋር የሰሩ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ሚስተር ራልፍ ብራውን የሚባሉ በዋሺንግተን ዲሲ መንገድ ላይ በአጋጣሚ ተገናኝተን በመጽሐፉ ዉስጥ የተካተቱትን እና ሌሎችም ብዙ ፎቶዎችና ዶሴዎች ሰጥተዉኛል። ትልቅ ባለዉለታችን ናቸዉ።

ግዮን፡-  ይህን ትልቅ የሀገር ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ስታዘጋጁ እንደተቋም ያገዛችሁ አካል አለ?

አታመንታ፡- የለም። በፍፁም የተባበረኝ ተቋም የለም፡፡ እንኳን በተቋም በግለሰብ ደረጃ እንኳን የምለውን ማድመጥ የሚችለው በጣም ጥቂት ሰው ነበር፡፡ ስለዚህ የትኛውም አካል አልረዳኝም፡፡ ሙሉ በሙሉ በጥረቴ የተሠራ ነው፡፡ ወጪው ራሱ ቀላል አልነበረም፡፡ ለምሳሌ ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ መጀመሪያ ላይ ለ‹‹ሪሰርች›› የምከፍለው በሰዓት 75 ዶላር ነበር፡፡ በዚያ ላይ የመጓጓዣና የምግብ ለብቻው ነበር የምከፍለው፡፡ አንድ ግለሰብ ለሚሠራው ሥራ ይህን ያህል መክፈል ቀላል አልነበረም፡፡ ከብዙ ነገሮች ተቆጥቤ ነበር የምከፍለዉ። በወቅቱ ደሞዛችንም ይህን ያህል ብዙ አልነበረም። አዲስ አበባ አንድ ወቅት ፖሊስ ኮሚሽን መሥሪያ ቤት ሄደን ነበር፡፡ ምንም የረዱን ነገር የለም፡፡ ወመዘክርም ስንሄድ ምንም ዓይነት ነገር አላገኘንም፤ እንደውም አንዳንድ ሰው ስጠይቅ ‹‹ምን ያደርግላችኋል? ያለፈ ነገር ነው›› እያሉ ያጣጥሉብን ነበር፡፡ አሁን ወደኋላ ስመለከት አንዳንዶቹም በምናገኘዉ መረጃዎች ስሜታችን እንዳይጎዳ በማሰብም ጭምር ነበር እላለሁ።

ግዮን፡-  ይህን ያህል የመረጃ እጥረት እያለ መጽሐፉን ለማዘጋጀት ምን አነሳሳዎት?

አታመንታ፡- ለመፃፍ ያነሳሳኝ ዋናው ነገር የነገሮች ተገላቢጦሽ መኾን ነው፡፡ እኛ ስናድግ አባታችን በሀገራችን ለውጥ ለማምጣት ሲሉ መሰዋታቸውን እየሰማን ነው፡፡ የኾነውን ሁሉ ለሀገር ስልሆነ በጸጋ ተቀበሉ እየተባልን ነው ያደግነው፡፡ የእኛም ጥያቄ የነበረው አባታችን ለሀገር ከተሰዉ ይህ ሁሉ ሰቆቃ በእኛ ቤተሰቦች ላይ ለምን ይደርሳል የሚል ነበር፡፡ ይሄ አንድ ምክንያት ነው፤ ከውጪ ያለውን ሁኔታ ስናየው ደግሞ ሌላ መልክ አለው፡፡ ሕዝብ እንደቅጠል ይረግፋል፡፡ ፖለቲከኞች በየቦታው ተበጣጥሰው እርስ በእርሳቸው ጥቅም አልባ ፍልሚያ ያደርጋሉ፡፡ ለምሳሌ አባታችን የተሰውት ለሀገር ከኾነ ሀገር እንዴት ማንነታቸውን ክዳ ሰነድ ታቃጥላለች? ስለዚህ ይህ በመኾኑ ታሪኩ መታወቅ አለበት በሚል መነሻ መፃፍ ግድ እንደኾነ ተሰማኝ፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእኛ ላይ የኾነው ሁሉ በሌሎች ላይ እንዳይኾን ስል መጽሐፉን ለማዘጋጀት ተነሳሁ፡፡ እናታችን ያ ሁሉ መከራና ስቃይ ሲደርስባት እኛን ለማጥፋት ያ ሁሉ ርብርብ ሲደረግ ቤተሰብ እንዴት እንደሚጎዳ ትውልድ ማወቅ አለበት፡፡

አባታችን በአርባ ሁለት ዓመት ዕድሜያቸዉ ሙሉ ያመኑበትን ነገር ሠርተው አልፈዋል፡፡ ቤተሰባቸው ግን በእርሳቸው ሥራ መጠየቅ  የለበትም፡፡ በሀገራችን ተጠያቂነት የለም፡፡ ይቅርታ የለም፡፡ ሰው ገንዘብ ሲኖረው ይከብራል፤ ሳይኖረው ግን ማንም ዞሮ አያየውም፡፡ ሌላው ሀገር ግን አንድ ጡረታ የወጣ ወታደር ሲሞት እንኳን በወታደራዊ ክብር ነው የሚቀበረው፡፡ እኛ ጋር ግን ሬሳውን መጎተት መስቀልና በመሳሰለው ነው የምንታወቀው፡፡ ስለዚህ ተጠያቂነት አለመኖሩ መጽሐፉን ለማዘጋጀት አነሳስቶኛል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የጀነራል ጽጌ ታሪክ የሀገር ታሪክ በመኾኑ ትውልዱ የሀገሩን ታሪክ እንዲያውቀው በማለትም መጽሐፉን አዘጋጅቼዋለሁ፡፡ ጀነራል ጽጌ ያልነበሩ ተቋማትን ከዜሮ ጀምረው በመሥራት ትልቅ ደረጃ ያደረሱ የሀገር ባለውለታ ናቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ዛሬ ድረስ ስማቸው የጎላ ተግባራቸው የጠነከረ ነው፡፡ ስለዚህ ይኽ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ መሠረታቸው ጀነራል ጽጌ ዲቡ መኾናቸውን ለትውልዱ ማስታወቅ ያስፈልጋል፡፡ 

ግዮን፡- በመጽሐፉ የገለጹት ቢኾንም ለአንባቢያን መረዳት፣ ጀነራል ጽጌ ዲቡ ማናቸው?

አታመንታ፡- አባታችን ጀነራል ጽጌ ዲቡ የተወለዱት በ1911 ዓ.ም ሲኾን በ1953 ዓ.ም በ42 ዓመታቸው አርፈዋል፡፡ የተወለዱት ሐረር ነው፡፡ የአባታችን አባት ባሻ ዲቡ የራስ መኮንን የፈረስ ቤት ኃላፊ ነበሩ፡፡ ወደ ሐረር የሄዱት ከራስ መኮንን ጋር ሀገር ለማቅናት ነው፡፡ ባለቤታቸው ባዩሽ ይባላሉ፤ መጀመሪያ ጋራ ሙለታ ነበሩ፡፡ ከዚያም ወደ ጉርሱም ተዛወሩ፡፡ 

ግዮን፡-  ከእናታቹ በኩል ስለአባታቹ ሥራና ሕይወት ያገኛችሁት መረጃ አለ?

አታመንታ፡- አይ እናታችን በዚህ ዙሪያ የጠለቀ ነገር የላትም፡፡ እርሷ ሁሉ ጊዜ ዝምታ ነው ምርጫዋ፡፡ የመጽሐፍ ዝግጅቱንም ገና አጋማሽ ላይ እያለሁ በሰማኒያዎቹ መጨረሻ ላይ ነው ሕይወቷ ያለፈው፡፡ መጽሐፍ እየጻፍኩ መኾኑን ብቻ ነው የምታውቀው፤ እንጂ በእሷ በኩል ያገኘሁት መረጃ የለም፡፡ እንኳን እሷ አክስት አጎቶቻችንም የተለየ መረጃ አልሰጡንም፡፡ 

ግዮን፡- ጀነራል ጽጌ ዲቡ በ1953 የመጨረሻ ከቤት ሲወጡ ለእናታችሁ ያሏቸው ነገር አለ?

አታመንታ፡- ምንም ዓይነት መልዕክት የለም፡፡ ንጉሡ፤ ለጉብኝት ብራዚል ሲሄዱ፤ አጎታችን ለእሳቸዉ አቀባበል ሌጎስ ቀድሞ እንዲደርስ ማክሰኞ ነው የሄደው፡፡ ሌጎስ አዲስ በተከፈተዉ ኤምባሲ በተሾሙት በአምባሳደር ከበደ በኩል ያልፋሉ ተብሎ ሲጠብቁ አጎታችን አቶ ታምራት ተስፋዬ ለአምባሰደሩ ጸሐፊ ኾነው ለቅበላዉ ዝግጅት ለመድረስ ወደዚያ ሄዱ፡፡ ለመሸኘት እኔም እህቶቼም የእሱም ልጆች አየር መንገድ ተገኝተን ነበር፡፡ ጀነራል መንግሥቱ ነዋይ እና የእኛ አባትም ነበሩ፡፡ አጎታችን ሸኝተን ስንመለስ እኛን ወደ ቤት ያመጣን ሹፌር የጀነራል መንግሥቱ ነዋይ ሹፌር ነው፡፡ አባታችንና ጀነራል መንግሥቱ ነዋይ ግን ወደ ፖሊስ መምሪያ ነበር የሄዱት፡፡ ሹፌሩ በድጋሚ ወደ አባታችንን ፖሊስ መምሪያ ሄዶ ጀኔራል መንግሥቱ ንዋይን ይዞ ወደ ክቡር ዘበኛ ይሄዳል፡፡ በዚያ ሰዓት ግርማሜ ንዋይ ወደ ኦጋዴን ይሄዳል ተብሎ እራት አብረን እንበላለን የሚል ቀጠሮ ከአባታችን ጋር ነበራቸው፡፡ እኛ የምናውቀው ምንም ነገር የለም፡፡ ከዚያ ጀነራል መንግሥቱ አባታችንን በስልክ ሲያጡ እዚያው ድረስ መጥተው ተያይዘዉ የጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ መኖሪያ ወደ ነበረዉ ወደ ክብር ዘበኛ መምሪያ ሄዱ እንጂ ሌላ ምናውቀው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ እንግዲህ ማክሰኞ ወደ ከሰዓት በኋላ አጎታችንን ከሸኘን በኋላ አባቴና ጀነራል መንግሥቱ ነዋይ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ወደ ክቡር ዘበኛ መምሪያ ሄዱ፡፡ ይመጣሉ ብለን ከመጠበቅ ውጪ ይህ እንደሚፈጠር አላወቅንም፡፡ 

——————–

ማስታወሻ፡- ውድ አንባቢያን ከአቶ አታመንታ ጽጌ ዲቡ ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ የአባታቸውን የመጨረሻ አሟሟት ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ያደረግነውን ቆይታ በሚቀጥለው ዕትም ይዘንላችሁ የምንመለስ ይኾናል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን የመከላከያ ስምምነቶችና የፖለቲካዊ ድጋፎች

በመካከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ስጋት ተከትሎ፣ ጣሊያን ለባህረ...

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ ”ንዋይ” የተሰኘ መተግበሪያን ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች...

የነዳጅ እጥረት አሽከርካሪዎችን ለከፋ እንግልት እየዳረገ ነው

በአዲስ አበባ እና በልዩ ልዩ የክልል ከተሞች የሚስተዋለው የነዳጅ...

ሼክ ኢብራሂም ቱፋ በኢራን ኤምባሲ በመገኘት ሀዘናቸውን ገለጹ

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼክ ኢብራሂም...