የአንዲትሕይወትከፍ…ፍታ

Date:

ሙኤል በለጠ(ባማ)

የሕይወት ታሪክ የግለሰብን ስሜቱን፣ እምነቱን፣ ወጣውረዱን በራስ ተነሳሽነት የመጻፍ ሂደት ነው። በእርግጥ የሕይወት ታሪክ በሌላም ሰው ሊጻፍ የተገባ ነው። እኛም ተደራሲያን ገጹን ስንገልጥ የባለታሪኩን ልጅነቱን፣ ዓላማውን፣ ማንነቱን፣ በግልጥ እናያለን፤ ሕይወቱ ምን ማንጸባረቅ እንደፈለገች ወደ ኋላ እና ወደ ፊት በንባብ እርምጃ እየተመላለስን ከአንዲት ሕይወት ፍሬ ያለው ትምህርት እንማራለን፤ የሁላችንም ነፍስ ዓላማን በማድረግና ባለማድረግ መኃል ያልፋል። ስለዚህ የሕይወት ታሪኮች ከግለሰቡ ለኛ የቀረቡ የታሪክ ድግሶች ብቻ ሳይሆኑ የራዕይ ፍርፋሪዎችም ናቸው። ሲያልፍም የሕይወት ታሪኮች የትላንት አገራዊ ታሪካችንን በአዲስ ዕይታ እንድናይ ይረዱናል።

የሕይወት ታሪክ መጻፍ የተጀመረው በጥንታዊው ዘመን ቢሆንም በጣም የተስፋፋውና የታወቀው ግን በመካከለኛው ዘመን ነው፡፡ የመጀመሪያዎቹ የሕይወት ታሪኮች ምናልባትም በቀብር ሥነ-ስርዓት ላይ የሚነበቡና በመቃብር ስፍራ የሚጻፉ አጫጭር የግለሰቦች ታሪኮች ሳይሆኑ አይቀሩም። በአገራችን ገድሎች ለሕይወት ታሪክ እንደፈርጅ ቀዳጅ ስራዎች ሊታዩ ይችላሉ፡፡

ወቅቱን ባልጠበቀ ሁኔታ እና ሳይታሰብባቸው የሚጻፉ የሕይወት ታሪኮች ለምን እንደሚጻፉ አላህ ይወቀው! ከሰሞኑ ግን መጻፍም፣ ማንበብም፣ መደነቅም፣ ምንም መሆን ከብዶኝ ነበር(አላጋነንሁም) ያው አንዳንዴ የመከራ ዲንጋ ሳንገፋ የገፋን ይመስለን የለ ወይ እንደ ሲሲፈስ እየገፋንም ይሆናል። በእጄ ባልገፋ በምናቤ እገፋ ይሆናል። ማን ያውቃል? ታዲያ አንድ የመጽሐፍ መደብር ገብቼ በሕይወት ታሪኮችን መፈለግ ጀመርኩ ቀልቤ ካዘዘ አዘዘ ነው! ብዙ ፈልጌ ካጣሁት መጽሐፍ ጋር ዐይን ለ ዐይን ተፋጠጥን ምጽሐፉ መስህብ እንዳለው አስቀድሜ አውቃለሁ።

“I Stand Alone” ብለው አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ የሕይወት ታሪካቸውን ጻፉት ተስፉ ረፌራ ጫላ “ብቻዬን ቆሚያለሁ” ብሎ ተርጉሞታል። ርዕሱ ተናጋሪ ነው። ጽንስ ብንሆንም ለእውነት መቆም መባረክ ነው። በሃሳብ ነበልባል ላይ ቆሞ እንደ ሕጻኑ ቂርቆስ እናትን ማበርታት መልካም ነገር ነው። ብቻውን የቆመ ሌላ ያቆማል። ለብቻ የቆመ ከአበባው ይልቅ አፈሩንና ውኃውን በቅጡ ይመረምራል። አበባውን ያቆመው ውኃና አፈሩ እንጂ ውበቱ አይደለም መቆም ኋላ በምንነክሰው የእውነት አፈር ላይ እንጂ ሰው በሚያስነክሰን የሃሰት አፈር ላይ አይደለም! ዐይኔን ሳላሽ ከፍዬ ወጣሁ መጽሐፉን ለማግኘት ብዙ ጥረት ከድርጌ ነበር ታሳካ “What dream may came” የሚለው ፈረንጅ ለካ ለዚህ ነው። አነበብሁት ዝምታ ወርቅ ነው ። ማለት ከበደኝ አፈር ዝምታ ወርቅ ነው ሲል አያምርበትም ይህችን ከተብሁ:-

አምባሳደር ብርሀሃኑ ድንቄ ስመጥር ሊቃውንት ካሉበት ከእንጦጦ ራጉኤል ብቅ አሉ ። አያ መንግስቱ ለማ ገና በልጅነታቸው የቤተ ክህነት ትምህርት ከዜማ እስከ ጾመ ድጓ እና የግዕዝ ቅኔን ጠንቅቀው “የልጅ ሊቅ” ተባሉ። አንባሳደር ብርሃኑም ገና በ12 ዓመታቸው ድጓን ጠንቅቀው ያውቁ ነበር። በእውቀታቸው በድምፀ መረዋነታቸው ብዙዎች ያደንቋቸው ነበር “ይህ ልጅ አዕምሮ ስልነቱ ብቻ አይደለም ሰዎችን የማያስደንቃቸው ድምዐ መረዋነቱም ጭምር እንጂ። በዚያ በለጋ ዕድሜያቸው በቤተ መቅደስ ተገኝቶ ሲዘምር በድምፁ የማይመሰጥ ሕዝበ ክርስቲያን አልነበረም ። የድምጹ መረዋነትም ከንጉሳውያን ቤተሰቦች እጅ ልዩ ሽልማት እንዲበረከትለት አስቻለው። ይህንን ሽልማት ያገኘው የቅዱስ ቂርቆሶ በዓል በሚከበርበት ዕለት ነው።” ገጽ 13 ይህ የአምባሳደር ብርሃኑ ታሪካዊ የልጅነት ገድል ነው። ገድሉ ወይን ነው። የራሱ የሆነ ጣዕም አለው፤ ። አንባቢውም ታሪኩን በምናቡ ካሰፋው ለራሱ ምሉዕ በኩለሄ የሆነ ታሪክ ማግኘቱ አይቀርም፤

የአምባሳደር ብርሃኑ የእሳቱ(የወጣትነት) ዘመናቸውም ስኬታማ ነበር የሚጽፉትም ጽሑፍ ጋዜጣ ላይ ይታተምላቸው ነበር “ይህ የፅሑፍ ሙከራ እንዲሁም ከሰዎች ዘንድ ያገኘው ሞገስ እና አድናቆት ለወጣቱ ብርሃኑ ድንቄ ለኋለኛ ሕይወቱ እንደ እርሾ ሊቆጠር ይችላል። ምክንያቱም የመጀመሪያ ስራውን ያገኘው በብርሃንና ሰላም ጋዜጣ ላይ ታትሞ በወጣው ጽሑፉ ሰበብ ነው።” ገጽ-14  አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ ባይተዋር ነበሩ በወቅቱ ስራ ማግኘትም አልቻሉም ነበር ፤ ታዲያ ይህ ነገር ያስቆዝማቸው ነበር ና እንጉርጉሯቸውን በቅኔ እንዲህ ገለጡት

“በኢትዮጵያ የብዙ ሰዎችን ደም የጠጣው ጦርነት አለቀ። ግን ረቂቅና ብርቱ የሆነ የሠላም ጊዜ ጦርነት ተክቷል ። በመሪያችን በንጉሱ እናምናለን። አድሏዊነትና ጉቦኘነቴን በሕግ ተቆጣጥሮ ፣ ድል አድራጊነቱን በሕግ እንዲያረጋግጥ። ይህ ቅኔ ሰበብ ጃንሆይ ፊት ሞገስ አስገኘላቸው የዕለት አንጀራ የሚበሉበትም ስራ አገኙበት ግን

አገርን ለፈሪ አይሰጡም አደራ፣

ዳር አድርጎት ያድራል የመኋሉን ስፍራ፤

እንዳለው ባለ ቅኔው በዕውቀቱ በንቅዘት ጭቃ፣ በብልሹ አሰራር ምሰሶ፣ በአላዋቂዎች ሃሳብ የተማገረው የመንግስት ቤት ውስጥ መስራት ለአንባሳደር ለብርሃኑ ፈተና ነበር  እርሳቸው ያለጫማ መሄድ፣ ያለ አልጋ መተኛት ይችላሉ። እውቀታቸው ሕይወታቸው ነው። እውነትን ማንንም ሳይፈሩ የሚያጋልጡም ናቸው። “የእኛ አገዛዝ ደግሞ ለአንባገነንነቱ ኋላም ፊትም የሌለው ነው። እንመራለን የሚሉትም በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብን ለርሃብና ለቸነፈር፣ ለጥማትና ችጋር አጋልጠው የሚላስ የሚቀመስ የሌለውን ለምስኪን ሕዝባቸው ጥቂት ከመስጠት ይልቅ ላሞሌ ጌቶቻቸው በጆሮ የሚበላ ከሕዝብ ላብ ቀለብ ይሰፈርላቸዋል።”

ቄሳርና አቢዎት በተሰኘው መጽመፋቸው አምባሳደር ብርሃኑ እንዲህ ይላሉ። “አንዳንድ ሹማምንቶች በንቅዘት ምክንያት ከስራ ሲባረሩ ደስ የሚለኝ የእነርሱ ሃዘን ወይም እኔ ከእነርሱ ጋር ታግዬ ማሸነፌ ሳይሆን ነገር ግን

ሀ). የእነርሱን እድል በማየት ሌሎች ይታረማሉ

ለ). በእነርሱ ምክንያት የተበደሉ፣ የተገፉ ሰዎች ነጻነት ይሰጣቸዋል።

ሐ). የፍትህ መተካከል ቀስ በቀስ እያለ በንጉስ ነገስቱ አስተዳደር ይዛመታል። የሚል ጠንካራ ተስፋ ነበረኝ የሆነው ሆኖ የግል ጠላት ከማፍራት በቀር ተስፋዬን የሚደግፍ አንዳችም ምልክት አይታይም ነበር። ” እንዲ ነው። አገርን በኅልውና ዳር መውደድ…

ቀጣዩ የአምባሳደር ብርሃኑ እጣፈንታ “ስደት” ነው። በ “ስደት” ዙሪያ ዮርዳኖስ አልማዝ ሠይፉ ሰፊ ጥናት አድርጎ ራሱም በተሞክሮው አልፎ ሁለት ቅጽ መጽሐፍ ጽፎልናል። ዮርዳኖስ ስደትን እንዲህ ተረድቶታል። “ስደት ያለና የነበረ ወደፊትም የማይቀር ከሰው ልጅ ተፈጥሯዊ ባህሪ ጋር የተቆራኘ ማኀበራዊ ኹነት ነው። በተለያዩ አዎንታዊና አሉታዊ ምክንያቶች የሰው ልጅ ተወልዶ ያደገበትን ቀዬ ወይም አገር ትቶ ሊሰደድ ይችላል። በዚህ መነጽር ሲታይ ብዙዎቻችን ስደተኞች ነን ወይም ነበርን። “ስደት” ወይም “ስደተኛ” የሚለው ቃል በአብዛኛው አሉታዊ ትርጉም ቢሰጠውም፣ ሙሉ ለሙሉ በመጥፎ ጎኑ ብቻ መታየት የለበትም። (መንገደኛ-ገጽ 323)

አምባሳደር ብርሃኑ ሁሉንም ጸበል ቀምሰዋል። በቀለማቸው ሰብብ ጸጉር አስተካካይ ፊት ነስቷቸዋል። ይህ የስደት አስከፊው ገጽታ ነው። “ልዕለ-ቃልን ከልተገበር ነው። ተዋርደን መዋረዳችን አይቀርም አይደል?” ባለቅኔው አያ ሙሌ እንዳለው እንደሰው እስኪያልፍለት እንደምንም አስታውሱት፣ እንግዲህ ልጄን አደራ ሌላው ቢቀር ፊት አትንሱት ፣ ሰው ሰውን ፊት ሲነሳ ሕመሙ ጥልቅ ነው። አምባሳደሩ ተሰደውም ልባጀው እረፍት አላገኘም ስለ አገራቸው አብዝተው ይጨነቁ ነበር ፤ ደብዳቤም ይሰዱ ነበር  “አዎ፣ ከአገሬ ተባርሪያለሁ፤ አዎ ንብረቴን ተወርሻለሁ ፤ አዎ፤ በየጊዜው የሚመጡ የግርማዊነትዎ አምባሳደሮች የዚህ አገር ሕዝብ እንዳይቀበለኝና እንዳይረዳኝ በእኔ ላይ ልዩ ልዩ የሐሰት ወሬ ያወራሉ። ግን ይኼ ሁሉ እኔን በብርቱ አላሳሰበኝም። እኔን በብርቱ የሚያሳስበኝ የአገራችን የውጪው እድል ነው። ምናልባትም ይህ የኔ አስተያየት በአሁኑ ጊዜ ለግርማዊነትዎ ግልጥ ሆኖ ሊታይ አይችልም። አሁን የምገኝበት አስቸጋሪ ሁኔታ አስጨንቆኝ እንድቀባጥር እንጂ ቁምነገር እንዳለበት አይቆጥሩትም። ግን ይህ ታላቅ ስህተት ነው ። “

የአምባሳደሩ ተጋድሎ ግን ድንቅ ነው። ቀጣይም ትውልድ ሊዘክረው ይገባል ። ተርጓሚውም ብዙ ለፍቷል። ሊመሰገን ይገባል።

ዜኖች አንድ ተረት አላቸው ሁሌ ሳነበውም ሳስበውም የሚያስደንቀኝ አራት የዜን መናኞች ለሁለት ሳምንታት ያህል ካላንዳች ንግግር በፍፁም ፀጥታ ሆነው በተመስጦ ለማሰላሰል ተስማሙ፡፡ በመጀመሪያው ቀን ምሽት ፣ በርቶ የነበረው ሻማ ተርገብግቦ ጠፋ፡፡

የመጀመሪያው መናኝ ተናገረ፡- “ኦ! ሻማው ጠፋ!”

ሁለተኛው መናኝ ፣ “እንዳናወራ ተነጋግረን አልነበረምን?” አለ፡፡

ሶስተኛው መናኝ ተበሳጭቶ እንዲህ አለ፡- “ለምንድነው ሁለታችሁ ፀጥታውን የምታደፈርሱት?”

አራተኛው መናኝ ከት ብሎ እየሳቀ፣ “ሃሃሃ! ሁላችሁም አውርታችኋል፡፡ እኔ ብቻ ነኝ ያላወራሁት አለ” ብዙ ጸጥታ በትንሽ ቃል እንደሚደፈርስ ሁሉ የአንድ ሰውም ንቃት በብዙዎች እንቅልፍ ይዋጣል። ለእኔ አምባሳደር ብርሃኑ ድንቄ የተግባር ሰው ናቸው። የተግባር ሰዎች ደግሞ በሕልመኞች የተጋገረን ዳቦ እንዳይበሉ አማልዕክቱ ተጠንቅቀው ይጠብቋቸዋል። ለእውነት ብቻቸውን ቆመው እስከ መጨረሻው ጠብታ ይታገላሉ ። ጥያቄ መሆን ያለበት እነደነዚህ ያሉትን የአገር ዋርካዎች ሲሞቱ ቀብራቸውን ከማድመቅ(እሱንም ከታደሉ) በቀር በሕይወት እያሉ ምን ያህል አከበርናቸው? ምን ያህል እውቀታቸውን ተጠቀምነው? የሚለው ነው። ‹‹ብቻዬን ቆሚያለሁ›› የተሰኘው መጽሐፍ ለእውነት ስለቆመ ሰው የሚተርክ ብቻ አይደለም  የአገርም ታሪክ ነው። አገሩን በሃቅ ያገለገለ የሐገራችንን ታላቅን ሰው ሕይወት ፍንትው አድርጎ ያሳያልና ለማንበብ ማቅማማት የለብንም!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...