የአዳማ-አዋሽ የፈጣን መንገድ ሁለተኛ ክፍል ግንባታን አስመልክቶ በአፍሪካ ልማት ባንክ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር መካከል ሲካሄድ የነበረው የመጨረሻው የገንዘብ ድጋፍ ድርድር መጠናቀቁ ተገለፀ።
ይህ ድርድር ባንኩ ፕሮጀክቱን በቅርቡ ለቦርዱ አቅርቦ እንዲያፀድቅ የሚያስችል ሲሆን፣ ለፕሮጀክቱ ከታሰበው አጠቃላይ ወጪ ውስጥ 181.5 ሚሊዮን ዶላር በአፍሪካ ልማት ባንክ እንደሚሸፈን ይጠበቃል። የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ 34.2 ሚሊዮን ዶላር ለመሸፈን አቅዷል።
የፈጣን መንገዱ ግንባታ በሁለት ምዕራፎች የተከፈለ ነው። የመጀመሪያው 48 ኪሎ ሜትር በአፍሪካ ልማት ባንክ በሚሰጠው ብድር ሲገነባ፣ ቀሪው 19 ኪሎ ሜትር ደግሞ በኮሪያ ኤግዚም ባንክ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግለት ታውቋል።
ይህ መንገድ ኢትዮጵያን፣ ጅቡቲን እና ደቡብ ሱዳንን የሚያገናኝ ትልቅ ፕሮጀክት ሲሆን፣ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የትራንስፖርት ትስስር በማሻሻል ለንግድና ኢኮኖሚያዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የፋይናንስ ስምምነቱ በ2026 መጀመሪያ ላይ ተፈርሞ ግንባታው ወደ ትግበራ ይገባል ተብሎ ታቅዷል።
CapitalNews
