የኢትዮጵያ መሪዎች በታዛቢዎች አንደበት!

Date:

አዳነ ጥላሁን ዳኜ (ወልድያ)

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ፣ በኢትዮጵያዊነትና በኢትዮጵያ መሪዎች ዙሪያ እጅግ አወዛጋቢ እንጂ ወጥ የሆነ አቋም የለንም፡፡ ለዛሬው ትንሽ ማለት የፈለግሁት በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ምንነት ትርጉም ላይ ሳይሆን በኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥት ላይ በፈራጅ ቀዳጅነት ባጭሩ በመሪነቱ መድረክ ብቅ ብለው በነበሩትና አሁንም ባሉት መሪዎቻችን ዙሪያ ከታዛቢዎች አንደበት የሚደመጠውን ትዝብት ላካፍላችሁ፡፡

አጀንዳው መማማሪያ ይሆንም ዘንድ ነገሩን ከስሩ ነውና ከዐፄ ቴዎድሮስ እስከ ዶ/ር ዐቢይ ያለውን አገዛዝ እጂግ በጣም አጭር በሆነ አቀራረብና አንባቢን በማያሰለች መልክ በሁለት ክፍል ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡

ከዘመነ መሣፍንት አገዛዝ አላቅቀው በኢትዮጵያ የተማከለ አገዛዝ የመሠረቱትን ዐፄ ቴዎድሮስን በርካቶቻችን የዘመናዊት ኢትዮጵያ ታሪክ ፈርቀዳጅ አድርገን እናያቸዋለን፡፡ ከኛ በተቃራኒ የሚመለከቷቸው ታዛቢዎች ደግሞ ንጉሡን ከተራ የሽፍትነት ዘመናቸው ጀምሮ በጨካኝነታቸው የሚታወቁ እጅግ የከፉ ንጉሥ እንደነበሩ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ አብዱልጀሊል ዐሊ ደግሞ ንጉሥ ቴዎድሮስ ታሪካቸው የተጋነነ እንጂ ከቁም ነገር መቆጠር የማይገባቸው ንጉሥ እንደነበሩ ከመናገር አልፎ  ‹‹ኪነት ያገነነው ዐፄ›› በሚል ርዕስ ባቀረበው መፅሐፍ ንጉሡ የነአርቲስት ቴዎድሮስ ካሣሁን (ቴዲ አፍሮ) የኪነት ሥሪት አድርጎ ሊያሳየን ይሞክራል፡፡

በዐፄ ዮሐንስ አገዛዝ ዙሪያም ታዛቢዎች ሁለት ዓይነት አመለካከት ነው ያላቸው፡፡ ባንድ በኩል ዐፄ ቴዎድሮስን ለመውጋት በጀኔራል ናፒየር እየተመራ ከሕንድ የመጣውን የእንግሊዝ ወራሪ ጦር በክብር ተቀብለው አስተናግደውና ስንቅና መንገድ መሪ ጨምረው ወደመሀል ኢትዮጵያ በመሸኘታቸው ሀገር የከዱ ባንዳ ነበሩ፡፡ በዘመነ አገዛዛቸውም የወሎን ሙስሊም ያለፍላጎቱ ወደክርስትና በመመለሱ ረገድ ጭካኔ የተሞላበት እርምጃ ወስደዋል፡፡ ወደሥልጣናቸው ማብቂያ ዘመንም ጎጃምን ያለርህራሄ ዘርፈዋልና ሌላም ሌላም እያነሱ የሚወቅሷቸው ታዛቢዎች እንዳሉ ሁሉ በዘመነ አገዛዛቸው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ ለሁለት ጊዜያት ያህል የግብፅን ተስፋፊ ጦር ለአንድ ጊዜም ከሱዳን የተነሳውን የድርቡሽ ጦር እንደገናም ከምፅዋ ተነስቶ ወደአሥመራ ሊገባ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ሙሉ በሙሉ በመደምሰስ በመጨረሻም ጦር ሰብቆ ለ2ኛ ጊዜ የተንቀሳቀሰውን የሱዳን ወራሪ ለማጥፋት ግንባር ቀደም ተዋጊና አዋጊ በነበሩበት ወቅት ‹‹በጦር ሜዳ የወደቁ ጀግና ናቸው›› የሚሏቸው ታዛቢዎችም አሉ፡፡ ‹‹ወሬሣው ካሣ ከ1825 -1881›› የሚል መፅሐፍ ፅፈው ለንባብ ያበቁት አቶ ይትባረክ ግደይ በበኩላቸው እንዳውም ንጉሡ በታሪክ መድረክ የሚገባቸውን ቦታ አላገኙም በማለት በፀፀት ይናገራሉ፡፡

በዐፄ ምኒልክ ዙሪያም ቢሆን ወጥ አመለካከት የለም፡፡ እንዳውም ዛሬ በ21ኛው ክፍለዘመን ዓለም በሥልጣኔ ማማ ላይ ለመድረስ በምትጣደፍበት ወቅት እኛ በታሪክ ዙሪያ ከምንነታረክባቸው አንዱና ዋናው ዐፄ ምኒልከ ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ከነገሡት ነገሥታት መካከል እንደዐፄ ምኒልክ ብልህና ዲፕሎማት መሪ የለም፡፡  የታሪክ አጋጣሚ ተገጣጥሞ ምኒልክ ወደዙፋኑ የመጡት የአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች አፍሪካን ተከፋፍለው ለመግዛት ጀርመን በርሊን ላይ ተስማምተው ወደተግባራዊ እንቅስቃሴ በገቡበት ወቅት ሲሆን ኢትዮጵያ በእንግሊዝም ሆነ ፈረንሳይ ቅኝ አገዛዝ ሥር ካልወደቀችባቸው ምክንያቶች አንዱ የዐፄ ምኒልክ ብልህነት የተሞላበት ዲፕሎማሲያዊ አመራር ሲሆን በጉልበት ገፍቶ የመጣውን የኢጣሊያ ሠራዊትም በጉልበት መክተውና ዐድዋ ላይ አሳፋሪ ሽንፈት አከናንበው የኢትዮጵያን ኃያልነት በማስመስከር የዓለም ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት አርዓያ ሲሆኑ በሰላም ጊዜም ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ሥልጣኔ ጋር እኩል ትራመድ ዘንድ ሁሉንም ዓይነት የአውሮፓ ቴክኒዮሎጂ ያስተዋወቁ መሪ መሆናቸውንና በሀገር አመራር ብልሀታቸው ተወዳጅነት የተነሳ ከህዝብ. ‹‹እምየ ምኒልክ›› የሚል የፍቅር ስም ጭምር እንደተሰጣቸው የሚናገሩ እንዳሉ ሁሉ ንጉሡ ‹‹ጨካኝ፣ አረመኔ፣ የሌሎችን መብት ገፋፈ፣ ሀገር ወራሪና ዘራፊ›› ብሎም ‹‹በጦርነት ወቅት ጡት እስከመቁረጥ የደረሰ የጭካኔ ተግባር የፈፀሙ ግፈኛ መሪ ነበሩ›› ሲሉ በተለይም ጎሳ አቀንቃኝ ፖለቲከኞች አምርረው ይኮንኗቸዋል፡፡ ሕዝቅኤል ጋቢሳ የተባለው የኦሮሞ ተወላጅ የታሪክ ባለሙያ ለምኒልክ ካለው ሥር የሰደደ ጥላቻ የተነሳ ምኒልክ የሚባል መሪ እንደማያውቅ የነገረን በግልፅ አደባባይ ነው፡፡

አንዳንድ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆችም የዓለም ጥቁር ሕዝቦች መመኪያ የሆነውን የዐድዋ ድል ለማድበስበስ ሲሯሯጡ በትዝብት ያየናቸው ለዐፄ ምኒልክ ካላቸው ጥላቻ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

የዐፄ ምኒልክን ዙፋን የወረሱት ወጣቱ ልዑል ልጅ ኢያሱ በበኩላቸው በታሪክ ፊት እጅግ አወዛጋቢ መሪ ሆነው አልፈዋል ፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን የ1923 ዓ.ም ሕገ መንግሥት በማዘጋጀቱ ረገድ አሻራቸውን ያስቀመጡልን ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም ‹‹የሕይወቴ ታሪክ›› በሚል ርዕስ ባቀረቡት ግለታሪካቸውን የሚገልፀው መፅሐፋቸው ላይ ልጅ ኢያሱን ሁለመናቸው ያልበሰለ፣ ችኩልና ቅብጥብጥ፤ ለዋዛ ለፈዛዛ እንጂ ለቁም ነገር ያልተፈጠሩ፣ ለኢትዮጵያ የማይመጥኑ መሪ አድርገው ሲያቀርቧቸው ‹‹አንፋሮ›› በሚል ርዕስ በፃፈው መፅሐፍ የልጅ እያሱን ማንነት የሚያስተዋውቀን አቶ ሀብታሙ አለባቸው ደግሞ ወጣቱ ልዑል ሴት ለማሽኮርመም ብቻ የተፈጠሩ ሴት አጫዋች ዝሙተኛ አድርጎ አቅርቧቸዋል፡፡

በሌላ በኩል ‹‹የአቤቶ እያሱ አነሳስና አወዳደቅ›› የሚል መፅሐፍ የፃፉልን አጥናፍሰገድ ይልማ፣ ‹‹እያሱ አባጤና›› የሚል መፅሐፍ ለገበያ ያበቁት ደራሲ ጎበዜ ጣፈጠና ‹‹የቀድሞው ጦር ከ1927-1983›› የሚል መፅሐፍ ለንባብ ያበቁት ገስጥ ተጫኔ ‹‹ወጣቱ ንጉሥ ሩቅ ዓላሚ የሀገር ተቆርቋሪ፣ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መጠበቅ አበክረው የሚጥሩ፣ የኤርትራ በኢጣሊያ ቅኝ አገዛዝ ስር መውደቅ የሚፀፅታቸውና ነፃ ለማውጣት ብርቱ ፍላጎት የነበራቸው ወጣት መሪ›› እንደነበሩ ይገልፃሉ፡፡ ወጣቱ ልዑል እንደቀደምት አባቶቻቸው ‹‹ዐፄ›› በሚለው የማዕረግ ስም ለምን እንደማይጠሩ ለጠየቋቸው ባለሟሎቻቸው ‹‹ፈረሴ ከቀይ ባሕር ውሃ ካልጠጣ ዐፄ አልባልም›› የሚል መልስ እንደሰጡ ደራሲ አጥናፍሰገድ ይልማ ሲነግሩን፣ ደራሲ ገስጥ ተጫኔ ደግሞ ወጣቱ ንጉሥ ሰማኒያ ሺ ወታደር በዘመናዊ ወታደራዊ ስልጠና አሰልጥነው የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ለማስከበር ብርቱ ፍላጎት ስለነበራቸውና ለዚሁ ፕሮጀክታቸው ስኬታማነት በግልፅም ሆነ በስውር ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛትነት ለመያዝ ብርቱ ፍላጎት ከነበራቸው እንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኢጣሊያ ይልቅ የገለልተኛ አቋም ያራምዳሉ ብለው ያሰቧቸው የቱርክና የጀርመን መንግሥት ጋር የቀረበ ግንኙነት መመሥረታቸው ሥጋት ያሳደረባቸው የእንግሊዝ፣ ፈረንሳይና ኢጣሊያ መንግሥታት በሀገር ውስጥ ካሉ ተቃዋሚዎቻቸው ጋር ተባብረው በምስጢር በሸረቡት ሴራ ተጠልፈው ወደአያታቸው ዙፋን ዳግም ላይመለሱ መባረራቸውን ከላይ ርዕሱን በጠቀስኩት መፅሐፋቸው ላይ  በዝርዝር አስነብበውናል፡፡ (ገፅ 18)

በልጅ ኢያሱ አስተዳደር ዙሪያ ሚዛናዊ ታሪክ ያስነበቡን ልዑል ራስ እምሩ ኃ/ሥላሴ ናቸው፡፡ ልዑሉ ‹‹ካየሁትና ከማስታውሰው›› በሚለው መፅሐፋቸው እንደሚሉት ወጣቱ ልዑል ፍፁም ነፃነት የሚወዱ፣ እንደልባቸውና ፈቃዳቸው መሆን የሚያበዙ፣ የሾሟቸው ባለስልጣናትም ፍፁም ነፃ እንዲሆኑ የሚፈቅዱ፣ ግን እነዚሁ ሹመኞች ካጠፉ ያለርህራሄ የሚቀጡ ንጉሥ እንደነበሩ ይናገራሉ፡፡ (ገፅ 40)

ታዛቢዎች ልጅ ኢያሱ እንደተመኙት ኤርትራን ነፃ አላወጡም፡፡ ፈረሳቸውም ከቀይ ባሕር ውሃ አልጠጣም፡፡ በራስ ተፈሪ መኮነን ፊታውራሪነት፣ በእንግሊዝና ፈረንሳይ ቆንስላዎች መካሪነት፣ በሸዋ መሣፍንትና መኳንንት ተባባሪነት በተሸረበባቸው ሴራ ተጠልፈው ከዙፋናቸው ወረዱ ይላሉ፡፡

ልጅ እያሱን የተኩት የዐፄ ምኒልክ ሴት ልጅ ዘውዲቱ ምኒልክ ናቸው፡፡ ንግሥቷ ከ1909 ዓ.ም ወርሃ መስከረም እስከ መጋቢት 21 ቀን 1921 ዓ.ም በዙፋኑ ላይ ቢቆዩም ቤተክርስቲያን ከማሰራት ውጭ በሀገር ውስጡም ሆነ በዓለም አቀፉ ፖለቲካ ዙሪያ ያከናወኑት ለታሪክ የሚሆን አበርክቶ ስለሌላቸው በታዛቢዎች ዐይን ውስጥ አልገቡም፡፡

(ይቀጥላል)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር ተፈጸመ

የአርቲስት ነጻነት ወርቅነህ ስርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት...

በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም ዓይናቸው በጽኑ መታመሙን ጠበቃቸው ገለጹ

ከሁለት ዓመት በላይ በእስር ላይ የሚገኙት መምህርት መስከረም አበራ...

ንግድ ባንክ “ስታርፔይ” የተሰኘ አዲስ መተግበሪያ ይፋ አደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንክ ሥርዓቱን ይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ...

በኢትዮጵያ በካንሰር ከሚያዙ ሕፃናት መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት ህክምና አያገኙም

በኢትዮጵያ በየዓመቱ በካንሰር ከሚጠቁ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ...