የኢትዮጵ ብሄራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ ቀጣይነት ባለው የፈጠራ ስራዎች እና ትብብር፣ የካፒታል ገበያውን ስነ ምህዳር እና ደጋፊ መሰረተ ልማቶች፣ የሃገሪቱን የረጅም ጊዜ የፋይናንስ ብልፅግና በሚደግፍ መልኩ ለማሳደግ ባንኩ ቁርጠኛ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶችን እና ሌሎች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን የማገበያየት ሂደት በይፋ ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ፣ የመንግስት የግምጃ ቤት ሰነዶችን እና ሌሎች የሰነደ ሙዓለ ንዋዮችን የማገበያየት ሒደት በይፋ ያስጀመረበት ክንውን “ለኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ታሪካዊ ሂደት ነው” ተብሏል።
የመንግሥት የግምጃ ቤት ሰነዶችን ለህዝብ ይፋዊ ሽያጭ በማስጀመሩ ሒደት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ማዕከላዊ ግምጃ ቤት እና የኢትዮጵያ ሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ በጋራ ተሳትፈዋል።
ክንውኑ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ አዲስ ምዕራፍ መጀ’መሩን ያመላክታል የተባለ ሲሆን፣ በግልጽነት፣ በገበያ ላይ የተመሰረተ የፋይናንስ አቅርቦትን እና የተሻለ ኢንቨስትመንት አማራጮች ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስቸል እንደሆነም ተጠቅሷል።
ይህም የአገር ውስጥ ካፒታልን ለማሳደግ፣ የፋይናንስ ዘርፍ አካታችነትን ለማስፋፋት እና የረጅም ጊዜ የኢኮኖሚ እድገትን ለመደገፍ የታለመ የዓመታት ስትራቴጂካዊ የሆኑ የምጣኔ ሃብት ሪፎርሞች ውጤት ነው ተብሏል።
