በአመት ከ1 ሚሊየን በላይ የቤት ፍላጎትና 300 ሺህ የቤት አቅርቦት ብቻ ባለባት ኢትዮጵያ የቤት ችግር አሳሳቢ ሆኖ ቀጥሏል።
በደመወዝ የሚኖረው ሰውም ቤት መግዛት ይቅርና ለኪራይ የሚከፍለውንም እያጣ ነው።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፈው አመት መጨረሻ ላይ ቤት የሌላቸውን የቤት ባለቤት ለማድረግ ከንግድ ስራ ውጪ የሆነ ብድር ለመስጠት ውሳኔ አሳልፏል።
በቅርቡም ባንኩ የቤትና የመኪና ብድር ጠያቂዎችንን የሚያስተናግደበትን መመሪያ አውጥቷል።
በመመሪያው ቤት ለመስራት ወይም ለመግዛት እንደዚሁም ያለውን ለማደሰና ለማስፋፋት ብድር እንደሚሰጥ ተቀምጧል።
በመመሪያው የተካተቱ ነገሮች መካከል ፦
➡️ ለሚገነባው ቤት ከሚጠየቀው ብድር በ200% ዋጋ የሚያወጣ መሰረተ ልማት ያለበት አካባቢ ያለ ቤት በማስያዣ መቅረብ አለበት።
➡️ ለብድር ከሚጠየቀው ገንዘብ 50% ያህሉ ቀድሞ በባንኩ መቆጠብ አለበት።
➡️ ለቤት የተሰጠው ብድር በ10 አመት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ መመለስ ይገባዋል።
➡️ ከ3-6 ወር የእፎይታ ጊዜ ጭምር 14% ወለድ ተበዳሪው መክፈል አለበት።
➡️ ወለዱ በየጊዜው ሊስተካከል እንደሚችልና በዛ መሰረት እንደሚከፈል ተቀምጧል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ መምህሩ ካሳሁን ወልዴ (ዶ/ር) ለሸገር ኤፍ ኤም ሬድዮ በሰጡት ቃል ፤ ” ቅድመ ሁኔታው ከፍ ማለቱ ብዙሃኑን ያገለለ ነው ‘ ብለዋል።
መምህሩ ” የቆጠበው 50% ሲደመር ደሞዙ በነዚህ 10 አመታት ውስጥ ደመወዙ ማክሲመም ሊከፍል የሚችለው ታሳቢ ተደርጓል፤ ባለትዳሮች ሁለቱም ሊሆኑ ይችላሉ ወይም አንደኛው ወገን ከሆነ የነሱ ታሳቢ ተደርጎ ቤቱን በወቅቱ ባለው ግምት 100% መሸፈን የሚችል ሲሆን ነው ፕሮሰስ የሚደረገው ለዚህ ነው እንደ ኮላተራል 200% የተባለው ” በማለት ብድሩ የብዙሃኑን ጥያቄ የሚመልስ አይደለም ብለዋል።
የፋይናንስ መምህሩ አክለውም ” ሚድል ኢንካም ታርጌት የሚል ተቀመጠ እንጂ እነሱ አፎርድ የሚያደርጉት አይደለም ” ብለዋል።
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለቤት ብድር መውሰድ የሚፈልግ ሰው ባንኩ ባስገመተው መሰረት ከሚበደረው ብድር 200% ግምት ያለው ማስያዣ ማቅረብ እንደሚጠበቅበት መመሪያው ሲያስቀምጥ ” ማስያዣው all season road access ያለባቸው ከተሞች፣ የመብራትና ውሃ ያለበትን ከተሞችን ታርጌት ያደረገ ነው ” ያሉት ካሳሁን (ዶ/ር) ይህም ለሽያጭ አመቺ እንደሚሆንና ” ከአበዳሪ አንፃር ሪስክ ለመቀነስ የተወሰደ ” ስለመሆኑ ገልፀዋል።
የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ባለሙያው መርዕድ ፍቅረዮሃንስ ” ኢኮኖሚው አብዛኛው የሚፈቅድለት አይደለም የሰው ቁጠባ መንምኗል የትኛው የመንግስት ሰራተኛ ወይም የግል ሰራተኛ ነው የሚችለው ” በማለት ባንኮች ብድር ቢያመቻቹም ሰፊውን ማህበረሰብ ያማከሉ እንዳልሆኑ ይገልፃሉ።
ደሞዝተኛው በኢትዮጵያ ከፍተኛ የታክስ ጫና አለበት ያሉት ባለሙያው ” በኢትዮጵያ በወር 90 ዶላር ሲገባ መንግስት 30% ታክስ የሚወስደው፤በኬንያ አንድ ሰው 800,000 ብር ሲያገኝ ወይም በነሱ የውጪ ምንዛሬ 6000 ዶላር ሲያገኝ ነው የኬንያ መንግስት ከዛ የመንግስትም የግልም ሰራተኛ ቅጥረኛ ሊሆን ይችላል 30% የሚወሰደው ” በማለት ተቀጣሪው ከፍተኛ ጫና እንዳለበት ተናግረዋል።
በሌላ ሃገሮች በብድር የሚገዛው ቤት ወይም የሚገዛው መኪና እንደ ማስያዣ ሲውል ለነዚህ ዘርፎች የሚሰጠው ብድርም ከፍ ያለ ነው።
አጠቃላይ የብደር ክምችቱ 3 ትሪሊየን ከሆነበት ሃገር ውስጥ 64 ቢሊየኑ ብቻ ለቤት አቅርቦት ይውላል ያሉት ባለሙያው ለባንኮቹ ለማደግም ለመስራትም ትልቅ እድል ነው ብለዋል።
የሰው አቅም፣ የመሬት አቅርቦት እና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት ለዘርፉ ፈተና ሆነው ሲቀጥሉ በሌሎች ሃገራት በብድር የተገዛው ንብረት እንደማስያዣ አድርገው ሲበደሩ የወጣው አዲሱ የንግድ ባንክ መመሪያ ግን ቅድመ ሁኔታውን ከፍ አድርጎ ብድሩን ለብዙሃኑ ከባድ አድርጎታል ተብሏል።
ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ሬድዮ
