በክቡር ገና
ከ1970ዎቹ ወዲህ ባለውና ዛሬ ድረስ በምናየው እያንዳንዱ የሀገራት ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ውስጥ የማኑፋክቸሪንጉ ዘርፍ ከ18-20% በላይ የሚኾነውን ድርሻን ይወስዳል። በዚህም ሳቢያ፣ የበርካታ ሀገራት መንግሥታት በልማት እቅዳቸው ውስጥ የማኑፋክቸሪንጉን ዘርፍ የትኩረት ነጥባቸው አድርገውታል። በጥር 2023 የተካሄደው 17ኛው የኢንደስትሪያላይዜሽን እና የኢኮኖሚ ብዝኃነት የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤም፣ የአፍሪካን ኢንዱስትሪያላይዜሽን እና የአህጉሪቱን የኢኮኖሚ ብዝኃነት አስፈላጊነት ዳግም ያረጋገጠ ነበር።
ለዚህ ማሳያ ይኾነን ዘንድ ኢትዮጵያ ብናነሳ፣ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርቷ የማኑፋክቸሪንጉን ድርሻ በ17.2 በመቶ ለማሳደግ አቅዳ እናገኛታለን። እቅዱ ከግብርና እና ከሌሎች ንዑስ ሴክተሮች ጋር ተዳምሮ የሥራ እድልን ጨምሮ ተጨማሪ የሰው ኃይልን ለመሳብ እና በክልሎችም ውስጥ የከተማ መስፋፋትን ለማምጣት የሚረዳ እንደኾነ ተገልጾዋል [የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር – 2020]። በተመሳሳይ የጋና መንግሥትም ዘርፉ በኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣውን ጉልህ ለውጥ እና ወሳኝነት ተገንዝቧል። በዚህም ምክንያት በዘርፉ መልከ ብዙ የምርት ውጤት ይታይ ዘንድ አሠራሩ እየተስፋፋ እና እየተበረታታ በመሔድ ላይ ይገኛል [የጋና ኢንቨስትመንት ማስፋፊያ ማዕከል – 2021]፡፡ ይኽም የጋና የተፈጥሮ ሀብቶችን አቀነባብሮ ወደ ውጭ የመላክ እንቅስቃሴን እንደሚያግዝ ጭምር ታምኖበታል። አልጄሪያም እንዲሁ በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ፍላጎት ያላት ሌላኛዋ ሀገር ስትኾን፣ በዚህም እንደ አነስተኛ የሰው ኃይል እና የኢነርጂ ወጪዎች፣ ለአውሮፓ ገበያዎች ቅርብ መኾን ብሎም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እየወደቀ የመጣውን የአልጄሪያ ዲናር ምንዛሬ ለማሻሻል እና የመሳሰሉትን ዋና ዋና ጥቅሞች ለማግኘት ትፈልጋለች፡፡ [ኦክስፎርድ ቢዝነስ ግሩፕ – አልጄሪያ 2018]
ከፍ ብሎ የተገለጸው እንዳለ ኾኖ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ኢኮኖሚው ከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ምርትን እና የሥራ ሥምሪትን ለማስቀጠል ብሎም የደመወዝ እና የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል አስቸጋሪ ኾኗል የሚል ግንዛቤ እየጨመረ መጥቷል (ሮድሪክ 2009)። ለዚህ ችግር ቢያንስ ሁለት መላምቶች ይቀመጣሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ዓለም አቀፋዊ መኾን እና የዓለም አቀፍ የገበያ ውድድሩም መጨመርን ተከትሎ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ያለውን የደሞዝ ማሻሻያ እና ሌሎች ነገሮችን እኩል የማድረጉን ሒደት ይበልጥ አሳሳቢ እያደረገው መኾኑ ነው፡፡ (Hasan, Mitra, and Ramaswamy 2007; Rodrik 1997)
ሁለተኛው ደግሞ፣ ዓለም የደረሰበት ቴክኖሎጂ የሚያመጣቸው ለውጦች በዘርፉ የተሰማሩ እና የሥራ አቅማቸው አነስተኛ በኾኑ ሰራተኞች ላይ ጫና እያሳደረ መምጣቱ ነው [Berman, Bound, and Griliches 1994 Berman, Bound, and Machin 1998; Goldin and Katz 2009]፡፡ በዚህም ሳቢያ ቴክኖሎጂያዊ ለውጦች በዓለም የምርት ሒደት እያስገኙ ያለው የላቀ ውጤት የሰው ኃይልን እያፈናቀለ ነው የሚለው ሥጋት እያደገ እንዲመጣ ምክንያት ኾኗል [Cowen 2013; Brynjolfsson and McAfee 2014]፡፡ ይኽንን አስመልክቶም ሮድሪክ ‹‹ቴክኖሎጂያዊ ለውጦች ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የበለጠ ካፒታል እና የማምረት ብቃትን እያጎናፀፉ በመምጣታቸው፣ ኢንዱስትሪላይዜሽንን ሲፈጥረው የነበረውን የሥራ ስምሪት መጠን እና የምርት አቅም ቀንሷል፡፡ በዚህም የተነሳ ዘርፉ ከገጠር የሚመጡ እና ያለትምህርት ወደ ዘርፍ የሚሰማሩ ሰዎችን የመሳብ አቅሙ እየቀነሰ ነው [2013b, p. 52]›› በማለት ሐሳቡን አጠናክሯል፡፡
እነዚህ ሁለት መላምቶች ስንደምራቸው በኮሪያ ሪፐብሊክ፣ በሲንጋፖር ወይም በታይፔ፣ በቻይና የተመዘገቡት ፈጣን በማኑፋክቸሪንግ ላይ የተመሠረቱ ዕድገቶች በሌሎች ቦታዎች እውን ሊኾኑ ይችላሉ ወይ ብለን እንድንጠራጠር ያደርገናል።
ድንበር ዘለል ምርቶችን አስመልክቶ እንደሚሰጡ ትንተናዎች ከኾነ፣ በማኑፋክቸሪንግ የሥራ ስምሪት እና በልማት ደረጃዎች መካከል ያለው ትስስር፣ በኢኮኖሚ ትብብር እና ልማት ድርጅት (OECD) ሀገራት ብቻ የተገደበ ነው። ይህም በብዙ ታዳጊ ሀገራት መንግሥታት ዘንድ የማኑፋክቸሪንግ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት በያዟቸው ትላልቅ ፕሮግራሞች ውስጥ ቀጥሎ ይመጣል ብለው በሚያስቡት የሥራ ዕድል እና ከፍተኛ ገቢ ዙርያ ተጽዕኖ የሚፈጥር ይኾናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቀጥሉት ዐሥር ዓመታት ከ10 ሚሊየን በላይ ለሚኾኑ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ያግዛሉ የተባሉት እንደ ማስተርካርድ ፋውንዴሽን ያሉ ታላቅ የሥራ ዘርፎች ይፋ ተደርገዋል። እንዲህ ያሉ ዘርፎች በሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቀድላቸው በተለምዶ እንደ ኮሪያ እና ታይዋን ያሉ ቀደምት የኢንዱስትሪ አራማጆችን ተሞክሮ ዋቢ በማድረግ ነው። እነዚህን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ለማሳለጥ ያመችም ዘንድ የመንግሥት በጀት፣ የመሬትና የሠራተኛ ሕግ፣ የትምህርት ፖሊሲ ሳይቀር እየተሻሻለ ይገኛል። በእርግጥም መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከ1970 ወዲህ ዛሬ ላይ ሀብታም ሆነው የምናያቸው ሀገራት በየትኛውም ምክንያታዊ መመዘኛ ቢጤን ከ18-20% በላይ የሚኾነው ዕድገታቸው ድርሻን የሚወስደው የማኑፋክቸሪንጉ ዘርፍ ነው። ኾኖም ከ2000 ጀምሮ በተለመደው ኢኮኖሚ የሚጠበቀው የዘርፉ ድርሻ ከ13% – 15% ተሸቆልቁሏል፡፡ በዚህም ሳቢያ በየጊዜው በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የሥራ ሥምሪትን እና ገቢን እያሳደጉ የመቀጠሉ ሒደት አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል፡፡
ሀገራት አሁንም የኢንደስትሪ ልማትን በማካሔድ ላይ ናቸው፡፡ ወደ ብልጽግና በደረሱ ቁጥር ግን ከኢንዱስትሪው ዘርፍ ራሳቸውን ያርቃሉ። ኾኖም እንደ ቻይና፣ ሕንድ እና ባንግላዲሽ ላሉ ዘግይተው የኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍን በተቀላቀሉ ሀገሮች ሳይቀር ዘርፉ በሥራ ሥምሪት ረገድ ያለው ድርሻ ከ16% በታች ነው፡፡ ወደፊትም አሁን ካለበት ደረጃ ብዙ ፈቅ የሚል አይመስልም፡፡ በተጨማሪም፣ አነስተኛ የኢንዱስትሪ መጠን በነበረበት 1970 የነበረው 34,000 ዶላር የነፍስ ወከፍ ገቢ በ2010 ወደ 9,000 ዶላር አሽቆልቁሏል።
እዚህ ጋር ልብ ማለት የሚያስፈልገው የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ በድሃ ሀገራት ውስጥ በገቢ ደረጃ እያደገ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ በበለጸጉ (ኢንዱስትሪ አልባ በኾኑ) ሀገራት ግን በገቢ እና ደመወዝ ደረጃ እያነሰ መሔዱን ነው። ለዚህ ሰራተኛ መር የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ፈታኝ እየኾነ መምጣት ምክንያት ናቸው ብለን የምንጠቅሳቸው ጉዳዮች ሁለት ናቸው፡፡
- የሰራተኛ ምርታማነት ከሰፊው ኢኮኖሚ ይልቅ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በፍጥነት ጨምሯል። ከፍተኛ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች አሁን ላይ ከዝቅተኛ የአምራችነት ደረጃዎች ጋር ተወዳዳሪ ናቸው።
- የሠራተኛ ወጪ እየጨመረ በመምጣቱ የማኑፋክቸሪንግ እንቅስቃሴ አሁን ወደ ሌሎች አገሮች ለመሄድ በጣም ምቹ ነው፡፡ ስለዚህ፣ የኢንዱስትሪው ዘርፍ አለመኖር ዝቅተኛ ከሚባል ገቢ ለመጀመር ያመቻል፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ የኢንዱስትሪው ዘርፍ አለመኖር ከሌላው ይልቅ በሥራ ሥምሪት ዘርፉ ላይ ተጽዕኖው በግልጽ ይታያል። ሰራተኞችን በማሽነሪዎች እየተካ መምጣቱ ለዚህ ጉልህ አብነት ነው፡፡
እነዚህ ውጤቶች፣ የኢንዱስትሪ ልማትን አስመልክቶ ሚዛናዊ መንገድ መከተልን ግድ መኾኑን ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ አገላለጽ የኢንዱስትሪ ልማቶች የሥራ ዕድሎችን ከማምጣት ጋር መያያዝ እንዳለባቸው ያረጋግጣሉ፡፡ ኾኖም ይኽ የመኾን ዕድሉ አነስተኛ መኾኑንም እግረ መንገድ ግልጽ ያደርጋሉ፡፡ ይኽም ኾኖ መንግሥታት የቱንም ያህል እንደ ቀድሞ ሊተማመኑበት ባይችሉ እንኳ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ችላ ማለት አይኖርባቸውም፡፡
