ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ የገቡት የእስራኤል ፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ፣ ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር እንዲሁም ከ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ጋር ፍሬያማ ውይይቶችን አድርገዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ፕሬዚዳንቱን ተቀብለው ባደረጉት ውይይት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በጥልቀት መርምረዋል። ውይይቱ በዋናነት በጋራ ፍላጎቶች ላይ ተመስርቶ የሁለቱን ሀገራት ትብብር ይበልጥ ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ያተኮረ እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
ፕሬዚዳንት ታዬ በበኩላቸው የእስራኤሉን ፕሬዚዳንት በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል። በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረገው ምክክር በኢትዮጵያና በእስራኤል መካከል ያለውን ጠንካራና የቆየ ታሪካዊ እንዲሁም ባህላዊ ትስስር ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር።
በአጠቃላይ የፕሬዚዳንት አይዛክ ሄርዞግ የዛሬው የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ወዳጅነት እና ዘርፈ ብዙ ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያለመ መሆኑ ተመልክቷል።
