“እቴጌ ጣይቱ እና ዳግማዊ ምኒልክ፡ ኢትዮጵያ ከ1883-1910 [እ.ኤ.አ]” የተሰኘ የትርጉም መጽሐፍ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተመረቀ።
መጽሐፉ የዓድዋን 130ኛ የድል በዓል እና 50ኛውን የዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን መታሰቢያ በማድረግ ነው ለንባብ የበቃው።
የምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ትናንት ቅዳሜ መጋቢት 5 ቀን 2018 ዓ.ም. የተከናወነ ሲሆን በመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ ምሁራንና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
መጽሐፉ የተጻፈው በክሪስ ፕራውቲ ሲሆን በዶክተር መሠረት መንግሥቱ አሳታሚነት እና ተርጓሚነት፤ እንዲሁም በህይወት ተፈራ እና በዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ተርጓሚነት ተዘጋጅቷል።
የታሪክ ድርሳኑ እቴጌ ጣይቱ ብጡል በሀገር አመራርና በዓድዋ ድል የነበራቸውን ዲፕሎማሲያዊና ስትራቴጂካዊ ሚና እንዲሁም ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊነት ለማሸጋገር ያከናወኗቸውን የተሃድሶ ሥራዎች በዝርዝር ይዳስሳል።
ከ1883 እስከ 1910 እ.ኤ.አ ባለው ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የጸናበት እና ዘመናዊ የመንግሥት መዋቅር የተዘረጋበት ወቅት እንደሆነ በመድረኩ ተገልጿል።
በጠቅላላው 457 ገጾች ያሉት መጽሐፉ በ1ሺህ ብር ዋጋ ለገበያ ቀርቧል።
