ለአርባ ዓመታት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ከፍተኛ መሥዋዕትነት ሲያስከፍል የቆየው የወልቃይት ፖለቲካ አሁን ላይ የድፍን ኢትዮጵያ ከፍ ሲልም የምሥራቅ አፍሪካ የፖለቲካ ግለት ማሳያ ኾኗል፡፡ እንደሚታወቀው አካባቢው በአማራና ትግራይ ክልል መንግሥታት የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ ጉዳዩ ይበልጥ እየጋመና እየጓነ መጥቷል፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከቅርቡ የሰሜኑ ጦርነት በኋላ አካባቢው በአማራ ክልል ሥር መኾኑ በትግራይ ክልል አመራሮች ዘንድ ያስከተለው ጥያቄ፣ የበጀት አመዳደብና የማንነት ጥያቄው ሕጋዊ ምላሽ የመሥጠቱ ጉዳይ መልስ የሚያሻው ኾኖ በመገኘቱ ነው፡፡ በተለይ ከማንነት ጋር ተያይዞ የሚነሳው ጥያቄ ከሁለት ዓመታት በፊት በኃይል የተመለሰ ቢመስልም ሕጋዊ እውቅናን መላበስ ግን አልቻለም፡፡ ይህን ሕጋዊ እውቅና ለማግኘትም የአካባቢው ሕዝብ በርካታ ጊዜያትን በሰላማዊ ሰልፍና በተለያዩ መንገዶች ጠይቋል፡፡
በጥያቄዎቹም በዋናነት ‹‹አማራ ነን አልን እንጂ አማራ እንሁን አላልንም ፤ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄ የፍትሕ ወዳድ ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ነዉ፤ የማይገባንን አልፈን አንጠይቅም ፤ የራሳችንንም አሳልፈን አንሰጥም ፤ በማንነታችን/በአማራነታችን በርስታችን አንደራደርም›› ወዘተ የሚሉ አንኳር መፈክሮችን አንስቷል፡፡ በተመሳሳይ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ እና የሰላም እና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱም ሰሞኑን ከቢቢሲ አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ የወልቃይት ሕዝብ የማንነት ጥያቄውን ለማስመለስ ጥረት ያደረገው ገና ህወሓት የትጥቅ ትግል በማካሄድ እያለ ጀምሮ መኾኑን አንስተው ‹‹እኛ የእናት ቋንቋችን አማርኛ ነው፣ ባሕላችን አማራ ነው፣ ሥነ ልቦናችን የጎንደር ማኅበረሰብ ነው። ስለዚህ ታሪካችን እና ማንነታችን ከጎንደር ጋር እንጂ ከትግራይ ጋር የተሳሰረ አይደለም›› በማለት ጥያቄው ማንነትን የማስመለስ ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደኾነ አስምረውበታል።
በአንጻሩ ከሳምንት በፊት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ ‹‹ወራሪዎች›› ሲሉ በጠሯቸው አካላት ሥር ይገኛሉ ያሏቸውን ‹‹የትግራይ ክልል ግዛቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመመለስ እየተረባረብን ነው›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱ በንግግራችው ሰፊዉ የትግራይ ግዛት አሁንም ‹‹ወራሪ›› ብለዉ በጠሯቸዉ በአማራ ኃይል ሥር መኾኑን አንስተው በአስቸኳይ ከትግራይ እንዲወጡ እና ሕገ-መንግሥታዊ የትግራይ ግዛት እንዲመለስ ጠንክረዉ እየሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል። በተመሳሳይ ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤልም ይኽንኑ ሐሳብ ደግመውታል፡፡ በአማራ ክልል ሥር የሚገኙ የወልቃይትና ራያ አካባቢዎች በአስቸኳይ ወደትግራይ እንዲመለሱ አሳስበዋል፡፡
ከሰሞኑን እየወጡ እንዳሉ መረጃዎች ከኾነ ደግሞ በፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ አሸማጋይነት በአማራና በትግራይ ከፍተኛ አመራሮች መካከል በተደረገው ንግግር እነአቶ ጌታቸው ረዳ ‹‹አካባቢው ወደ ቀድሞ ግዛታችን ተመልሶ እናስተዳድር›› የሚል ጥያቄ ሲያነሱ በእነዶ/ር ይልቃል ከፋለ በኩል ደግሞ ተፋናቃዮችን መልሶ ከማስፈር ውጭ የወልቃይትና የራያ ሕዝብ ዳግም በትግራይ አስተዳደር ውስጥ የሚካተትበት አንዳችም ምክንያት እንደሌለ መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ ይህን ተከትሎም የትግራይ ክልል አመራሮች ጉዳዩ በሚፈልጉት ዓይነት መልኩ የማይፈታ ከኾነ በኃይል ሊያስመልሱት እንደሚገደዱ መናገራቸውም ተጠቁሟል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የዩናይትድ ስቴትስ አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ ጉዳይ አስፈፃሚ ትሬስ አን-ጃኮብሰን በመቀሌ ተገኝተው ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በተወያዩበት ወቅት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ግዛቶቹ ወደትግራይ እንዲመለሱ ግፊት እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡ በተመሳሳይ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት የኾኑት ሌተናል ጀነራል ጻድቃን ገ/ተንሳይ ሰሞኑን ወደ አሜሪካ በማቅናት ከትግራይ የዲያስፖራ አባላትና ደጋፊዎቻቸው ጋር ‹‹የትግራይ ግዛት›› በተባሉትና መሰል ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ላይ ይገኛሉ፡፡
በሌላ በኩል አካባቢው ያለፉትን ሁለት ዓመታት በጀት ያልተለቀቀለት መኾኑ የፖለቲካ ግለቱ እንዲንር ተጨማሪ ሰበብ ኾኗል፡፡ ሰሞኑን የ2016 ዓ.ም አጠቃላይ ሀገራዊ በጀት ይፋ መኾኑን ተከትሎ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይም ወደፊት ሊመጣ ችሏል፡፡ ይኽን አስመልክቶ የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ መሠረት የወልቃይት ሕዝብ የበጀት ጥያቄ ተገቢነትን አስምረውበት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተፈጻሚ እንደሚኾን ገልጸዋል።
እንደእውነታው ግን ሕገ መንግሥቱ ይህን የበጀት ጥያቄ መመለስ የሚያስችልበት ደረጃ ላይ የሚገኝ አለመኾኑ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለዚህ ጉዳይ መልስ ቢኖረው ኖሮ ያለፉትን ሁለት ዓመታት አካባቢው ያለበጀት ባልሰነበተ ነበር፡፡ የኾኖ ኾኖ ዞኑ የግድ በጀት እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ላይ ዞኑን እያስተዳደረ የሚገኘው አማራ ክልልም ይሁን ፌደራል መንግሥቱ ለዞኑ ሕዝብ የሚገባውን በጀት የማድረስ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡ የፌደሬሽን ምክር ቤትም ዞኑን ታላሚ ያደረገ የበጀት ቀመርን በመሥራት ለተፈጻሚነቱ መትጋት ይጠበቅበታል፡፡
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱም በሰሞኑ ቃለ ምልልሳቸው የወልቃይት ጉዳይ ሕጋዊ ምላሽ እና ዕውቅና እንዲያገኝ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን እየጠበቁ ሲኾን፣ ለአካባቢው ተገቢው በጀት ተመድቦ ነዋሪው ተገቢውን ጥቅም እና አገልግሎት እንዲያገኝ የአማራ ክልልን እና የፌደራል መንግሥቱን መጠየቃቸውን ገልጸዋል። ‹‹አካባቢውን እያስተዳደርነው እስከኾነ ድረስ፣ መንግሥት የሚያጣራውን ጉዳይ እስኪያጣራ እንጠብቃለን። የማንነቱ ጉዳይ ያን ያክል የሚያስቸኩለን አይደለም። ማንነቱ ቢመለስም በጀቱ ግን እስካሁን አልተሰጠንም። በጀት እና ማንነት ደግሞ ተለያይተው መኖር አይችሉም›› ብለዋል።
በሌላ በኩል በቅርቡ የመብት ተከራካሪው ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት ላይ በዞኑ በርካታ የትግራይ ተወላጆች በግዳጅ መፈናቀላቸውን፣ ብዙዎችም በእስር ላይ እንደሚገኙ እና ግድያዎችም እንደሚፈጸሙ አመልክቷል። ኮ/ል ደመቀ በበኩላቸው አስተዳደሩ ከአካባቢው ያፈናቀለው የትግራይ ሰው አለመኖሩን አንስተው ‹‹ህወሓት ወልቃይትን ወደ ትግራይ አስተዳደር ያስገባው ነባሩን ማኅበረሰብ በማፈናቀል እና በመግደል የታጠቀ ኃይል አምጥቶ በማስፈር ነው። ይህ የታጠቀ ኃይል ደግሞ ለ27 ዓመታት ብዙ የአካባቢውን ነዋሪዎች ስላፈናቀለ እና ስለገደለ ጦርነቱ ሲጀመር ሸሽቶ ነው የሄደው›› በማለት አብራርተዋል፡፡ በእርሳቸው ላይ የተቃጣውን የሂዩማን ራይትስ ዎች ክስን አስመልክተውም ‹‹የወልቃይት ጠገዴ አማራ ሕዝብ ለዘመናት ከፍተኛ ግፍ ሲፈጸምበት አይተው እንዳላዩ ሲያልፉ ኖረው፣ አሁን የራሳቸው አጀንዳ ሲኾን ግን ግለሰብ እስከ መወንጀል መድረሳቸውን ስመለከት የህወሓት ቃል አቀባይ እንጂ የመብት ተሟጋች ኾነው አልመጡም›› በማለት የመብት ተቆርቋሪ ድርጅቱን በወገንተኝነት ወቅሰዋል።
በአጠቃላይ አሁን ላይ አካባቢው አፋጣኝ የኾነ አንዳች መፍትሔ እንደሚያስፈልገው በሁሉም ዘንድ የታመነበት እና ጊዜ የማይሰጥ ጉዳይ ኾኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ የይገባኛል ጥያቄውን አስመልክቶ ሦስት ዓይነት የአፈታት አተያዮች ይደመጣሉ፡፡ የመጀመሪያው፣ በህወሓት በኩል የሚነሳው ‹‹ሕገመንግሥቱን መሠረት አድርጎ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረው ትግራይ ክልል ይመለስ›› የሚለው ዐቋም ነው፡፡ ይህ ሐሳብ ድጋፍ ያለው በህወሓት ብቻ ሳይኾን ከአገር ውስጥ ብሔርተኞች አንስቶ እስከ አሜሪካና አውሮፓ ሕብረት ድረስ ነው፡፡ ሁለተኛው አተያይ ደግሞ ለማንነት ጥያቄው እውቅና በመስጠት በአካባቢው ላይ ሕዝበውሳኔ ተደርጎበት ዘላቂ መፍትሔ መስጠት የሚል ነው፡፡ የዚህ ሐሳብ ተቀባይነት ደግሞ በከፊል የአማራ ክልል አመራር ዘንድና የገዢው ፓርቲ የብልጽግና ይመስላል፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ያለው አተያይ ደግሞ ለዚህ የማንነት ትግል አርባ ዓመታትን ዋጋ ከፍሏል የሚባለው የወልቃይት ሕዝብ ያነሳዋል የሚባለው ጥያቄ ነው፡፡ ይኸውም ‹‹በጉልበት የተካለለው ማንነታችን በጉልበት ወደቦታው ተመልሷልና አሁን ባለበት ክልል እውቅና ይሰጠን›› የሚል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከ10 በላይ የሚኾኑ የአማራ ማንነት ማረጋገጫ ታሪካዊ መረጃዎችን ሰንዶ ይፋ እስከማድረግ ደርሰዋል፡፡ እነኚህ ሁሉ ግን አልበርድ ያለው ያለውን የወልቃይት ፖለቲካ ምን ያህል ያቀዘቅዙታል የሚለው ለብዙዎች እንቆቅልሽ ነው፡፡
