
የኢትዮጵያ መንግስት ለ2017 በጀት ዓመት የነበረውን ከፍተኛ የዕዳ ጫና በግልጽ አስቀምጧል። የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ እንደተናገሩት፣ ምቹ የዕዳ ማስተካከያ (ሽግሽግ) ባይኖር ኖሮ ሀገሪቱ በዚህ ዓመት ብቻ 2.8 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ከፍተኛ ዕዳ መክፈል በግድ ይላት ነበር።
ይሁን እንጂ መንግስት በ G20 የጋራ ማዕቀፍ ውስጥ ከአበዳሪ አገራት ኮሚቴዎች ጋር ባደረገው ውጤታማ ድርድር 1.9 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ለመክፈል ተችሏል። ይህም የዕዳ ሽግሽጉ በግምት 1 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን እፎይታ እንዳስገኘላቸው ሚኒስትሯ አመልክተዋል።
በተጨማሪም በ2016 በጀት ዓመት መገባደጃ ላይ የሀገሪቱ አጠቃላይ የውጭ ዕዳ ከሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት (GDP) ጋር ሲነፃፀር 13.7 በመቶ እንደነበር ፍፁም አሰፋ ( ዶ/ር) አብራርተዋል።
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ መንግስት ከአበዳሪ ኮሚቴዎች ጋር ባካሄደው ገንቢ ውይይት በመርህ ደረጃ 3.5 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን የዕዳ እፎይታ ስምምነት ላይ ደርሷል።
ይህ ስምምነት እንደተገለፀው በ2017 የ 1.5 ቢሊዮን ዶላር፣ በ2018 የ 400 ሚሊዮን ዶላር፣ በ2019 የ 500 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም በ2020 የ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ሽግሽግን ያካተተ ነው።